” …የኤርትራ መንግስት አጋጣሚውን ይጠቀማል ብለው አብይ አሕመድ መክረውንናል”

Date:

ኢዲስ ሪፖርተር – ጥንቆላ የወደፊት እንጂ ያለፈ እንዳልሆን በማውሳት የትህነግ አመራሮች አሁናዊ ቁመና ሲያሳዩ “ያለፈውን እንደ ወደፊት ግብ አድርገው የሚጠነቁሉ” ይሏቸዋል። ያለፈውን፣ የወደፊት ራዕይና ግብ አድርገው የሚያስቡ የዞረባቸው እንደሆኑ ዝርዝር ጉዳዮችን በማንሳት ያሳያሉ። የዚህ ቡድን አመራሮች የሚያስቡትን ለመመርመር መሞከር ህመም ላይ እንደሚጥል በበርካቶች ዘንዳ የሚሰጠውን አስተያየት በማጠንከር አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው።

አቶ ጌታቸው ረዳ የትህነግ አፈ ቀላጤ ሆነው ወደ ተንቤን በረሃ በሚሸሹበት ወቅት “ጓዶቻቸው” የሚያስቡትንና ይናገሩ የነበረውን እይጣቀሱ፣ ያነበቡትን በማጣቀስ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ፍጹም እንግዳ የሆነ ጉዳይ ይፋ አድርገዋል። “በኢትዮጵያ በስፋት የተሰራጨውን የፈጠራ ትርክት ገለጡት” ሲሉ ብዙዎች የተገረሙበት ይህ እውነት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የተመለከተ ነው።

“አብይ ከአምስትና ስድስት ዓመት በሁዋላ ነጻ ወጡ” በማለት የአቶ ጌታቸው ረዳን ቃለ ምልልስ የተቀባበሉ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚረባ የሕዝብ ግንኙነት እንደሌላቸው በማጉላት ነው። መረጃ ለመስጠት የመረጃ ጠያቂውን ሪፖርቶች፣ የሪፖርቶች ይዘትና ዝንባሌ መገምገምን ቅድመ ሁኔታ አድርጎ የሚሰራ የኮሙኒኬሽን ቢሮና ኃላፊዎች ይህን አቶ ጌታቸው ያጋለጡትን ትልቅ ሃቅ “እንደ ወይዘሮ ስርጉት ወይ ጉድ ብሎ ስምቶ ዝም አለ” በማለት የተቹ ጥቂት አይደሉም።

ሰብለ ወንጌል ስሟ የተቀየረ የሶስተኛ ዓመት የጋዜጠኛነት ተማሪ ናት። ለአዲስ ሪፖርተር እንዳለችው ከሆነ የመንግስት ኮሙንኬሽንን ቢሮና የመንግስት የሕዝብ ግንኙነት ሰራተኞች አቶ ጌታቸው የገለጡትን እውነት ደጋግመው ለሕዝብ ማቅረብና ቀደም ሲል የተረጨውን ሃሰተኛ ትርክት ማጠብ በተገባቸው ነበር።
“የትህነግ የሳይበር ሰራዊት ‘ዲጂታል ወያኔ’ ትግራይ ከሄደበት ቀን ጀምሮ፣ ጦርነት ጠማቂ፣ ጦርነትን አከፋፋይ፣ ጸረ ሰላም፣ አምባገነን፣ እርቅን የማይወድ፣ የትግራይን ሕዝብ ለማስጨረስ ከሻዕቢያ ጋር ያበረ…ወዘተ በማለት ለይተው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ላይ ያለማቋረጥ የማቆሸሸ ዘመቻ በመክፈት ለውጡን ተከትሎ ከተቀበላቸው ሕዝብ ለመለያት ሰፊ ስራ ሰርተው ነበር። ይህንን ትርክትም በርካቶች ገዝተውት እንደነበር ይታወሳል” ያለችው ሰብለ “በራሱ የትህነግ ከፍተኛ አመራር ትርክቱ ውሸት መሆኑ ሲገለጽ እንደ ተራ ሰው ተመልክተው ዝምታን የመረጡ የፕሮፓጋንዳ ሰራተኞች አስገራሚ መሆናቸውን አስታውቃለች።

አቶ ጌታቸው ረዳ ከኤንቢሲ ጋር ባደረጉት ክፍል አንድ ቃለ ምልልስ “አብይ አሕመድ አቶ ሬድዋንን ትግራይ ድረስ በመላክ መክረዋል” በማለት የሰጡት አስደንጋጭ መረጃ ለሰብለ አስተያየት መነሻ ነው። አቶ ጌታቸው ” ሬድዋን ሁሴን ትግራይ መጥቶ ሁላችንንም አግኝቶናል” ካሉ በሁዋላ የዛሬው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የተላኩበትን ጉዳይ ይፋ አድርገዋል።

ትህነግ ለጦርነት በሚሟሟቅበትና የማጠልሸት ዘመቻውን ባጠናከረበት ወቅት “የኤርትራ መንግስት አቋሙ ግልጽ ነው። ግጭት ውስጥ ከገባን አድቫንቴጅ ይወሳዳል። ስለዚህ ያለንን ልዩነት አቻችለን አብረን እንስራ። የሚጠቅመውም ይሄ ነው” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአቶ ሬድዋን በኩል መማጸናቸውን አቶ ጌታቸው አምነው መስክረዋል። እንደ ሰብለ አባባል የመንግስት የፕሮፓጋንዳ ተቋማት የተኙት እዚህ ላይ ነው። ወይም “ትህነግ በጦርነቱ ወቅት አብይ አሕመድ ሻኧቢያን ጋብዘው የትግራይ ህዝብን አስወገተዋል” በማለት የፈጠራ ትርክት ሰርቶ የፈጸመውን ጥፋት አላዩም።

አቶ ሬድዋን አስር ቀን ትግራይ አብረዋቸው እንደቆዩ ያመለከቱት አቶ ጌታቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ግምገማ ትክክል እንደሆነ ካስታወቁ በኋላ ” ኢሳያስ ከትህነግ ውጪ ሌላ ጠላት አለ ብሎ አያስብም፤ ፉክክሩ ትግራይም ኤርትራም እኩል ቢወድቁ ኤርትራ አንድ ኢንች ከፍ ብላ ከወደቀች ስኬታቸው ነው” ሲሉ እሳቸውም ሆኑ ድርጅታቸው ስለገፉት እርቅና የሰላም ተማጽኖ ያዩትን፣ የሰሙትንና የነበሩበትን ሃቅ መስክረዋል።

እውነታው ይህ ከሆነ “አብይ አሕመድ ሻዕቢያን ወደ ትግራይ ምድር ጋብዞ የትግራይን ሕዝብ አስወጋ” የሚለው ትርክት ከየት እንደተነሳ አስረዱ” ያልተባሉት አቶ ጌታቸው፣ ትህነግ ሻዕቢያ ትግራይን ለማጥፋት ዕቅድ እንዳለው እንደሚያውቅ አመልክተዋል። በዚሁ መነሻ ቀድሞ አስመራን መያዝ የሚል አሳብም ተነስቶ እንደነበር አስታውቀዋል። “ብልጽግና ከኋላ ይወጋናል” በሚል ስሌት ቅድሚያ በሶስት ሳምንት አዲስ አበባ የመግባቱ ዕቅድ በጭፍን መመረጡን ገልጸዋል። ግጭት ቢፈጠር ሻዕቢያ አድቫንቴጅ እንደሚወስድ የመከረ መንግስት እንዴትና ለምን ከኋላ እንደሚወጋ ግልጽ ሊሆንላቸው እንደማይችልም ተናግረዋል።

ከያዙት አንድ ሺህ ገጽ በላይ የዕለታዊ መመዝገቢያ ሰነዳቸው እያዋዙና ካነበቧቸው መጽሐፍት ጋር እያገናኙ የትህነግን ገበና የገለጡት አቶ ጌታቸው፣ የሻዕቢያ ጭፍራ ትግራይን ወሮ የተሰማነውና የታየውን ዘግናኝ ጉድ ሁሉ 75 በመቶ በላይ መፈጸሙን መስክረዋል። ጥናቱ እጃቸው ላይ እንዳለና የተጠናውም በጥልቅና በጥንቃቄ መሆኑን በጥናቱ የተሳተፉትን ወገኖች ዘርዝረው አመልክተዋል።

“ሰሜን ዕዝ ትግራይ ድንበር ላይ ከሃያ ዓመት በላይ የተቀመጠው ለምንድን ነበር? ይህን ጥያቄ ሁሉም የሚመለሱት ቢሆኑም የትህነግ አብዛኛ አመራሮች ግን እንኳን ሊመልሱት የጥያቄውን መነሳት አይወዱም። ለምን? መልሱ የሻዕቢያ ጭፍራ ትግራይን ወሮ የሰማነውን ሁሉ ግፍ፣ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ የምላ ጭፍጨፋ፣ ነብረትና አገር ማውደም ብሎም ጄኖሳይድ እንዲፈጽም የፈቀደው ማን እንደሆነ ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳይና የትግራይ ሕዝብ በሃሰት ትርክት መጭበርበሩን እንደ ዛሬው ዘግይቶም ቢሆን ሃቁን እንዳይረዳ ነው” ሲሉ ያስታወቁ እንዳሉት፤ አቶ ጌታቸው በቅጣይ ቃለ ምልልሳቸው በርካታ ጉዳዮችን ይፋ እንደሚያደርጉ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

“ስምህን ቀይር አሁን መንግስት ነህ?” ሲባል ጀርባውን እየሰጠ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በሚለው ስሙ ሃያ ሰባት ዓመታት አገር ሲመራ የነበረው ትህነግ ሽምግልና፣ ልመና፣ ተማጽኖ፣ የእናቶች ለቅሶ፣ የኃይማኖት አባቶች ተግሳጽ፣ ሁሉም ዓይነት የሰላም አማራጮችን ‘አልቀበልም’ ብሎ በእብለት ያጣጣለው፣ ይህንንም ሲያደርግ ያለ አንዳች ሃፍረት የልቡናውን መደደር በቲቪ ቀርቦ ሲያሳይ ኩራት ሲሰማው የነበረው ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ የተዘጋጀበትን አጀንዳ ስለሚያውቀው ነው” በማለት እናቶች ትግራይ ሄደው አልቅሰው ሲመለሱ የተበሳጩ መናገራቸው ይታወሳል።

አቶ ጌታቸው ጦርነቱ ከተጀመረም በኋላ፣ በጅቡቲ ከአንዴም ሁለቴ በሲሸልስ ተደጋጋሚ የድርድር ስብሰባዎች ተካሂደው እንደነበር፣ ንግግሮቹ ጦርነትን ማስቆም የሚችሉ ደረጃ ደርሰው እንደነበር፣ ይሁንና የትህነግ አመራር “አራት ኪሎ እንገባለን” በሚለው ስሌታቸው ላይ በመቸከላቸው ሳይሳካ እንደቀረ አስታውቀዋል።

“ትህነግ የሰሜን ዕዝ ላይ የክህደት ጥቃት ወስዶ፣ የወስደውን የክህደት ጥቃት እንደ ጀብድ በመቁጠር መግለጫ አውጥቶ፣ በሶስት ሳምንት አዲስ አበባን እንደሚቆጣጠር አምኖና አሳምኖ ወደ ጦርነት ሲገባ የሰራዊት ምጥጥኑ አምስት ለአንድ በመሆኑ ዳግም ቤተመንግስት እንደሚገባ አይጠራጠርም ነበር። አቶ ጌታቸውን ጨምሮ አክቲቪስቶቻቸው በኩራት ስልጣን እስከመመዳደብ ደርሰው ይዘምሩም ነበር። እነ ጃዋር መሐመድ የተካተቱበት የእስር ቤት የሽግግር መንግስት ተዘጋጅቶ አራት ኪሎን በምናብ ተከፋፍለው እንደነበር አውቃለሁ” ሲሉ የኦፌኮ አመራር ቀደም ሲል ለአዲስ ሪፖርተር መናገራቸው ይታወሳል። አቶ ጌታቸው የሽግግር መንግስት ሰነድ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።

አብይ ቀጥቅጦ ነው ያሸነፈን፣ የትግራይን ጀኖሳይድ የፈፀመው ፋኖ እና ሻቢያ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ይህ አባባላቸው “ጦርነት ባህላዊ ቸዋታችን ነው፣ ተራራውን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” ወዘተ በማለት ራሳቸውን በማግዘፍ ወጣቱን ቀስቀሰው ሲማግዱ ለነበሩ ሁሉ ህመም እንደሚሆን ቃለ ምልልሱን የተከታተሉ ገልጸዋል። “ካሰቡና ከተጸጸቱ በማይሆን ትርክት ቀስቅሰው የትግራይን ምስኪን ያስጨረሱ ሁሉ ንስሃ ሊገቡ ይገባቸዋል” ያሉ “አብይ አሕመድ ነጻ ወጡ” ብለዋል።

ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related