የአሜሪካ ሴኔት በሱዳን ቀውስ ላይ አዲስ ማዕቀብ ጣለ፤ የሕወሓት/ትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) እና «አርሚ 70» በሽብርተኝነት ሊፈረጁ እንደሚችሉ ተመልክቷል። ቀደም ባሉ ሪፖርቶች የድርጅቱ የገንዘብ ምንጭና ዝውውር እየተጠና እንደነበር፣ በዚሁ መረጃ መሰረት በርካታ ንክኪ ያላቸው አካላት ስጋት ላይ መውደቃቸውን ጠቅሰን በዝርዝር ሪፖርት ማድረጋችን አይዘነጋም።
አዲስ ሪፖርተር ዋሽንግተን ዲ.ሲ. — የአሜሪካ ሴኔት በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚንቀሳቀሱና ለሱዳን ግጭት መባባስ ምክንያት የሆኑ የውጭ ታጣቂ ኃይሎችን ኢላማ ያደረገ አዲስና ጠንካራ የሕግ ረቂቅ አጽድቋል። «S. 4726» የተሰኘውና «የሱዳን የሰላም ሕግ» (PEACE in Sudan Act of 2026) ተብሎ የተሰየመው ይህ ባለሁለት ፓርቲ (Bipartisan) የሕግ ረቂቅ፣ በሱዳንና በጎረቤት አገራት ድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን በቀጥታ ተጠያቂ ለማድረግ ያለመ ነው።
በዚህ አዲስ የሕግ ረቂቅ ውስጥ በዋናነት የአሜሪካን ጥብቅ ክትትልና ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ከተለዩት የውጭ ኃይሎች መካከል፣ የትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) እና «አርሚ 70» (Army 70) የተባለው ታጣቂ ቡድን በዋናነት ተጠቅሰዋል።
በሽብርተኝነት የመፈረጅ ትዕዛዝ
በሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ጂም ሪሽ እና በሌሎች ታዋቂ ሴናተሮች ክሪስ ኩንስ፣ ጆን ኮርኒን እና ጂን ሻሂን የቀረበው ይህ የሕግ ረቂቅ፣ በኮሚቴው ደረጃ ታይቶ በአብላጫ ድምፅ አልፏል።
የዚህ ሕግ ዋነኛ ዓላማ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) እና አስፈጻሚው አካል በሱዳን ቀውስ ውስጥ እጃቸው ያለበትን ታጣቂ ቡድኖች መርምሮ፣ «በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈረጁ የሽብር ቡድኖች» (Specially Designated Global Terrorists – SDGT) በሚለው የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ነው።
ከአሜሪካ ኮንግረስ (Congress.gov) የተገኘው ሰነድ እንደሚያሳየው፣ በሕጉ አንቀጽ 4 ሥር በሱዳን ውስጥ የሚፈጸሙ ግጭቶችና ግፎች ውስጥ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ፣ የሚያመቻቹ ወይም ድጋፍ የሚሰጡ መንግስታዊ ያልሆኑ ታጣቂ ቡድኖችን በሚመለከት ዝርዝር የምርመራ ሪፖርት ለአሜሪካ መንግስት እንዲቀርብ ያዛል።
በትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) እና በአርሚ 70 ላይ የተጣለው ትኩረት
የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት በሱዳን መደበኛ ጦር (SAF) እና በፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይል (RSF) መካከል ባለው ጦርነት ላይ ብቻ ቢያተኩርም፣ የአሜሪካ ሴኔት ግን የሱዳን ቀውስ ወደ ጎረቤት አገራት የመስፋፋቱንና የድንበር ተሻጋሪ ታጣቂዎችን ሚና በከፍተኛ ስጋት እየተከታተለ መሆኑን ይህ ሰነድ ያረጋግጣል።
በሕጉ ረቂቅ ገጽ 10 ላይ፣ በሽብርተኝነት ማዕቀፍና በውጭ ጣልቃ ገብነት ምርመራ ሥር እንዲወድቁ በስም ከተዘረዘሩት ቡድኖች መካከል፣ የትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) በንዑስ አንቀጽ Q ሥር እና አርሚ 70 (Army 70) በንዑስ አንቀጽ P ሥር ተመድበዋል።
እነዚህ ቡድኖች በሽብርተኝነት ሊያስፈርጅ በሚችል የአሜሪካ የሕግ ረቂቅ ውስጥ መካተታቸው፣ ዋሽንግተን በአፍሪካ ቀንድ ደኅንነት ላይ የያዘችውን አቋም በከፍተኛ ደረጃ መለወጧን ያሳያል። አሜሪካ እነዚህን ቀጣናዊ ኃይሎች በሱዳን ቀውስ ውስጥ እንደ ሕገ-ወጥና ግጭት አባባሽ ተዋናዮች አድርጋ በይፋ ለመፈረጅ እንቅስቃሴ መጀመሯን፣ የገንዘብ ዝውውራቸውን አስመልክተን ቀደም ሲል ባዘጋጀነው ሪፖርት ማስታወቃችን አይዘነጋም።
ቀጣዩ እርምጃ ምን ይሆናል?
ይህ የሕግ ረቂቅ ጸድቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ፣ ትህነግ በሽብርተኝነት (SDGT) መፈረጁ እጅግ ከባድ የሆኑ ዓለም አቀፍ መዘዞችን ሊያስከትልበት ይችላል። ይህም የአሜሪካ መንግስት የእነዚህን ቡድኖች በቁጥጥሩ ሥር ያሉ የፋይናንስና የንብረት ይዞታዎችን በቅጽበት እንዲያግድ፣ ዓለም አቀፍ የባንክ ዝውውራቸውን እንዲዘጋ፣ እንዲሁም ለእነዚህ ቡድኖች ቁሳዊም ሆነ ሎጂስቲክሳዊ ድጋፍ ለሚያደርጉ ማናቸውም የውጭ አካላት፣ አገራት ወይም ግለሰቦች ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጣል ሙሉ የሕግ ሥልጣን ይሰጠዋል።
የኮሚቴው ሰብሳቢ ሴናተር ጂም ሪሽ የሕግ ረቂቁን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ “ሱዳን ወደ ከፋ ትርምስ እንድትገባ፣ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የስደተኞች ፍልሰትና ሰብአዊ ቀውስ እንዲቀጥል፣ እንዲሁም አካባቢው የሽብርተኞች መሸሸጊያ እንዳይሆን አንፈቅድም” ብለዋል።
ሕጉ በአሁኑ ወቅት በሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ወደ ዋናው የሴኔት ምክር ቤት ለሙሉ ውይይትና ድምፅ አሰጣጥ እንዲቀርብ ተመርቷል። የቀጣናው የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ትህነግ እና ተያያዥ የድንበር ታጣቂ ቡድኖች በአሜሪካ የፀረ-ሽብርተኝነት ማዕቀፍ ውስጥ መካተታቸው በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በሱዳን መካከል ያለውን የጂኦፖለቲካ ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ሊቀይረው እንደሚችል ይገልጻሉ።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






