ቅንጅት 109 ወንበር በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ኃይሎች (ህብረት) 52 ወንበሮችን በማሸነፍ፣ በጥቅሉ 161 የፓርላማ ወንበር አግኝተው ነበር። ትብብር ለአንድነት ያገኘው የፓርላማ ወንበር ሁለት ብቻ ነው። ቅንጅት የሕዝብ ጎርፍ አብሮት ነበር። ደጋፉ እንደ ዛሬው የማህበራዊ ሚዲያ ጩኸትና መናጆ ያፈጠረው አልነበረም። ትብብር ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወስዶ አደባባይ ሲወጣ የተከራያቸውና አበል የከፈላቸው ጥቂት አባላቱ ካልሆነ በቀር የሚታይ ነገር አልነበረም …..ይህንን ድጋፍና አቅም ይዞ ነው መንግስት ላይ ጫና አደርጋለሁ የሚል ከበሮ እየመታ ያለው፤ ጫናው ለምን ከውጭ በዚህ ደረጃ አራዳቸው?
በአዲስ አበባ፦ ቅንጅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ከተወዳደረባቸው 138 ወንበሮች ውስጥ 137ቱን በማሸነፍ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሰፊ ድል ተቀዳጅቶ ነበር። በተመሳሳይ ለአገር አቀፍ ፓርላማ ከአዲስ አበባ የተመደቡትን 23 ወንበሮች በሙሉ አሸንፎ ነበር።
አዲስ ሪፖርተር ዜና አዲስ አበባ | በኢትዮጵያ ምድር በ1997 ዓ.ም የተደረገው ምርጫ በኢህአዴግ አልሸነፍም ባይነት፣ በቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራሮች ስንፍና መጨረሻው ሞትና እስር ሆኖ ተመዘገበ። የዚህ ምርጫ አጠቃላይ ሂደት ፍጹም ገለልተኛ በሆነ መንገድ ቢጠና፤ የወቅቱን የሚዲያ አሰላለፍ፣ ከመንግስትም ሆነ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ታዋቂ በሚባሉ ሰዎች ምን እንደተፈጸመ መጪው ትውልድ ሊማርበት የሚችል ሰነድ ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ቢሰጥም ዛሬ ድረስ ሰሚ አልተገኘም።
በተለይም በወቅቱ የነበሩ ሚዲያዎች የምርጫው ሂደት ሰባራ እንዲሆን፣ “ወደ ፓርላማ እንዳትገቡ፣ አዲስ አበባን እንዳትረከቡ፤ ወዮላችሁ!” በሚል በቀን ሁለቴ ሳይቀር ጋዜጣ እያተሙ ይቸበችቡ ነበር። በወቅቱ “ምርጫ ትገቡና ዋ!” ሲል የነበረው የሦስት ሕትመት ሚዲያዎች ባለቤት እስክንድር ነጋ ዛሬ ፋኖ ሆኗል።
ለቅንጅት በቅጥርና ለቅንጅት መሪዎች በሎሌነት ሲሰሩ የነበሩ፣ ለኦሮሞ ድርጅቶች ብቻ ልሳን የነበሩ፣ ለደቡብ የሚናገሩ ተቧድነው ሲለቁት የነበረው “የፓርላማ አትግቡ” ዘመቻ ባለቀበት መንገድ ከተጠናቀቀ በኋላ፤ በውጭ አገር ሆነው የለውጥ መሪዎች፣ አጀንዳ ቀራጮች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ክተት የሚያውጁ ወዘተ በዚያን ዘመን “መንግስትን ሸሽተው” በውጭ አገር ጥገኝነት የጠየቁ ናቸው። እነሱኑ አይተው በድፍረት ማታ ማታ እየተቀባቡ በዩቲዩብ ንግድ ላይ የተሰማሩትን ጨምሮ!
ይህን አስተያየት የሚሰጡ የተለያዩ አካላት ዛሬ ላይ “ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት” በሚል አምስት ፓርቲዎች ያነሱትን “ፓርላማ አንገባም” ወሬ “ልክን አለማወቅ” ይሉታል።
ቅንጅት በወቅቱ “ሱናሚ” በሚል ስያሜ ከምርጫው አንድ ሳምንት በፊት ሕዝብ አደባባይ ፈሶ “የንብ ቆዳ ያለው” በማለት አዚሞ፣ በምርጫው ዕለት በሰጠው ድምፅ ራሱ ኢህአዴግ ባመነው 109 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) ወንበር አሸንፎ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ምርጫን 137 ወንበሮች (ከ138 ወንበሮች ውስጥ 136ቱን በቀጥታ፣ 1 ወንበር ደግሞ በድጋሚ ምርጫ በማሸነፍ) ምክር ቤቱን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት ነበር። በተጨማሪም የአማራ ክልል ምክር ቤት 106 ወንበሮች፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት 19 ወንበሮች፣ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት 12 ወንበሮች ወዘተ አሸንፎ ነበር። ሆኖም “የተሰረቀው ድምፄ ሲታከል መንግሥት እሆናለሁ” በሚል ምርጫ እንደማይገባ አስታውቆ ጨዋታው ወደ ጥይት የተቀየረው።
ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የሚባለው የአምስት ፓርቲዎች ጥምረት በስም ደረጃ “ቅንጅት” መሆኑ ነው። በተግባርም ከምርጫ በኋላ “በተመረጥኩበት ስፍራ ሁሉ አልወከልም፣ ቅድመ ሁኔታ አለኝ፣ እሱ ካልተሟላ ውርድ ከራሴ” እያለ ነው። ሕብረቱ ያገኘው ሁለት የፓርላማ፣ እና አምስት የክልልና የከተማ አስተዳደር ወንበሮችን ብቻ ነው።
አዲስ ሪፖርተር ያናገራቸው ሁለት የትብብሩ አባላት የሆኑ ተመራጮች “ውሳኔው የራሳችን ነው” በሚል በሕብረቱ ስም የወጣውን መግለጫ “ወግ ነው ሲዳሩ ማለቀስ” እንዲሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ለጊዜው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ሁለቱ ሰዎች፣ እነሱ ባላቸው መረጃ ሕብረቱ ወደ ምርጫ የገባው “በምርጫ ጀምረን በምርጫ እንጨርሳለን” በሚል ስምምነት ነው። ከዚህ የተለየ ስምምነት ካለ ይፋ እንዲሆንላቸው ይህንን ለሚያነቡና መግለጫውን ለሚያወጡ አካላት ጥያቄ አቅርበዋል።
የትብብሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ “ውሳኔው የሕብረቱ ነው። ውሳኔውን የማያከብር ካለ የዲሲፕሊን ቅጣት ይጣልበታል። ከፓርቲም ይባረራል” በማለት በአዲስ ሪፖርተር በኩል መልስ ሰጥተዋል።
የትብብሩ የምርጫ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምርጫው ስንሻው እንደሚሉት ደግሞ በትብብሩ ስም የሚወጡ መግለጫዎች በሙሉ ሕጋዊ አይደሉም። ምርጫ ቦርድ የገባው የመተዳደሪያ ደንብ ይህን አይፈቅድም። አንዱ አባራሪ፣ ሌላው ተባባሪ የሚሆንበት አግባብም የለም።
ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ እስረኞች እንዲፈቱ፣ ጦርነት እንዲቆም፣ መንግሥት ወደ ድርድር እንዲመጣና ከተቃዋሚዎች ጋር ተቀራርቦ እንዲወያይ የሚሉ ሐሳቦችን በጋራ ያራምዱ እንደነበር ያመለከቱት አቶ ምርጫው፤ “ወደ ምርጫ ስንገባ ያስቀመጥነው አንድም ቅድመ ሁኔታ የለም። ካለ በሰነድ ተደግፎ ይቅረብ” ሲሉ ለአቶ ጌትነት ጥያቄ አቅርበውላቸዋል።
ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ወደ ምርጫ የገባበትን ምክንያት ወደፊት ይፋ ለማድረግ ቀጠሮ ይዞ፣ ለጊዜው ያገኛቸውን ድምፆች እንደማይቀበል ይፋ ያደረገው ትብብር ለአንድነት፤ በግለሰቦች ፍላጎት ከሚያሰራጨው መግለጫ ውጭ በጋራ የተያዘ ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለ ሌሎች የትብብሩ አካላትም ይናገራሉ። “ቀጠሮ አያስፈልግም፤ በሰነድ የተደገፈ የተያዘ ቅድመ ሁኔታና ምርጫ የተገባበት ምስጢር ካለ ይፋ ይሁን። እኛ እስከምናውቀው በድምፅ ብልጫ የተወሰነ ነው። የኢህአፓ አመራር ይህንኑ በውጭ አገር ባሉ የዩቲዩብ አውዶች መስክረውታል” በማለት ይሞግታሉ።
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ከውስጥና ከውጭ የቀረበው ገንዘብ የፈጠረው ጫና ልዩነት እንዳስነሳ የሚሰማው ዜና ጎልቶ የሚወጣው። ትብብሩን “ይነዱታል” የሚባሉት ውስን አመራሮች ከውጭ አገር ገንዘብ ሲላክላቸው በጓሮ የተስማሙት “ምርጫውን ማደናቀፍና ብልጽግና ዕውቅና እንዳያገኝ በመናበብ መሥራት” የሚለውን አጀንዳ ለማራመድ ነበር።
ከምርጫ ቦርድ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ከተረከቡ በኋላ ወደ ምርጫ ሲገቡ “ከሃዲ፣ ሌቦች፣ ተንበርካኪ፣ ባንዳ፣ ፀረ-ሕዝብ ወዘተ” በሚል ወቀሳ የዘነበባቸው የትብብሩ የፊት ሰዎች “ለማስተባበል ሲወጡ” የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጡ።
አርበኛ በሳይ መኮንን “አንከር” በሚባለው ሚዲያው እያራከሰ እና ለመስማት በሚከብድ ፍረጃ እያጣደፈ ምርጫ ለመግባት መወሰናቸውን እያንኳሰሰ ሲጠይቃቸው፤ የኢህአፓው መሪና የብሉይ ሊቁ አቶ አብርሃም፦ “ሰባት የሚያህሉ የማዕከላዊና የሥራ አስፈጻሚ አባላት (ሚስጥረስላሴን ጨምሮ) በምርጫው መቀጠል የለብንም የሚሉ ነበሩ። ሦስት ድምፀ ተዓቅቦ፤ በልዩ ሁኔታ ለምሳሌ ምርጫው ሁለት ቀን ሲቀረው እንውጣ የሚሉ ደግሞ ሁለት ነበሩ። በአጠቃላይ አሥራ ሁለት ሰዎች ተመሳሳይ የሚባል አቋም ያዙ። የተቀሩት ደግሞ ‘መቀጠል አለብን፤ ለሚቀጥለው መራራ ትግል መዘጋጀት አለብን’ የሚሉ በሌላ ቡድን ሆኑ። አብላጫው በምርጫው እንቀጥል የሚል ሆነና ተወሰነ” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሳይሸሽጉ “ራስን መከላከል” በሚለው ስሌት ይፋ አደረጉ።
የኢህአፓው መሪ መጋቢ ብሉይ አብርሃም “ሚያዝያ ሃያ አራት ቀን የወጣው የፓርቲው በምርጫ መቀጠል ውሳኔ እነ ክርስቲያን ታደለንም ጭምር አማክረን ያደረግነው ነበር” ይላሉ። አክለውም “እነሱም ያሉን ድርጅታችሁን ጠብቁ፣ ለአብላጫው ውሳኔ ተገዙ ነው ያሉን” ብለዋል። ይህን ሲሉ በአብን ስም ፓርላማ የገቡት ክርስቲያን ታደለ በምን አግባብ የኢህአፓ አማካሪ እንደሆኑ አቶ አብርሃም አልተናገሩም፤ ጠያቂውም አላነሳላቸውም።
አቶ ጌትነት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ከዚህ ቀደም ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ ከተሟሉ ያሸነፋቸውን ወንበሮች የመረከብን ጉዳይ ሊያጤነው እንደሚችል ለአዲስ ሪፖርተር ሲያስታውቁ፤ ከላይ የኢህአፓው መሪና የሕብረቱ የፊት ሰው ስለመሰከሩበት ጉዳይ ያሉት ነገር የለም።
ሕብረቱ ያሸነፈውን ድምፅ መያዣ አድርጎ መንግሥት ላይ ጫና የማሳደርና ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ አቅሙን አስመልክቶ “ወግ ወጉ ተይዟል” የሚሉት የሕብረቱ አባላት፤ ዘግይተው እንደሰሙት ከሆነ ከውጭ የተላከውን ገንዘብ ከወሰዱ በኋላ በውላቸው አለመገኘታቸው አመራሮቹን በሥጋት የከተተ በመሆኑ፣ ይህ አጉል መላላጥና የሚዲያ ጩኸት ማነሳሻ ካልሆነ በስተቀር የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።
ዶክተር ጫኔ ብቻቸውን በፓርላማ ሲያደርጉ የነበረውን ተቃውሞ እንደምሳሌ በማንሳት ሕብረቱ ካገኘው ድምፅ አንጻር ጫናው ቀላል ሊባል እንደማይችል አቶ ጌትነት ያስረዳሉ። “ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ፓርላማ ገብተው ነው፤ እናንተ ያገኛችሁትን ሁለት ወንበር ተቀብሎ ፓርላማ ለመግባት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣችኋል፣ ቅድመ ሁኔታ ለማስቀመጥ ደግሞ አቅም ያስፈልጋል። የእናንተ አቅም ምን ድረስ ነው?” በሚል በድጋሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ “በተለያዩ መንገዶች፣ በኤምባሲዎች በኩል እየሠራን ነው” ብለዋል።
ከወራት በፊት አሜሪካ አገር ከተደራጀው የዓመፅ አደራጅ ግብረ ኃይል ምርጫውን በተመለከተ ለኢህአፓና ትብብር ውስጥ ላሉ አካላት የተሰጠው የፕሮጀክት አካሄድ መመሪያ፦ “እንወዳደራለን ብላችሁ ግቡ፤ ለምርጫው ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርቡ፤ አስቻይ ሁኔታዎች እንደሌሉ አስቀድማችሁ በተደጋጋሚ ተናገሩ፤ የተወሰነ እንቅስቃሴ አድርጉ፤ ምርጫው ሲቃረብ ለቃችሁ ውጡ፤ ይህንንም በማድረግ በመንግሥት ላይ የፖለቲካ ጫና ብቻ ሳይሆን ምርጫውን ሕገ-ወጥ ወይም ዲሌጂቲማይዝ (delegitimize) የማድረግ ሥራ ትሠራላችሁ” የሚል ሲሆን፤ በጀትና አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አዲስ ሪፖርተር መረጃ አግኝቶ መዘገቡ አይዘነጋም።
የሻዕቢያ ወኪልና የኤርትራን ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆኑ በግልጽ በተለያዩ ስብሰባዎች የሚናገሩት አቶ ነዓምን ዘለቀ፤ ከወራት በፊት በተካሄደ የዙምና የዋትስአፕ (WhatsApp) ስብሰባ የተለያዩ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችን ሰብስበው ምርጫውን ሕገ-ወጥ ወይም ዲሌጂቲማይዝ ስለማድረግ በግልጽ ሲናገሩ መደመጣቸውም አይዘነጋም። የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግተን ዲሲ ተባባሪ ባሰባሰበው መረጃ የትብብሩ አባላት ሆነው ከላይ ከተገለጹት አካላት ጋር ሲሠሩ የነበሩት ምርጫ እንደማይገቡ እንዲወስኑ የተደረጉት በጫና ነው። ይህንን ካላደረጉ ይኸው ግብረ ኃይል ባለው የሚዲያ ፕላትፎርምና የማኅበራዊ ሚዲያዎች በሚስጥር የተደረጉ ውይይቶችንና የገንዘብ ልውውጦችን ይፋ እንደሚያደርግላቸው ዝቷል።
አቶ ጌትነት እንዲህ ያለውን አባባል “ተራ ፈጠራ፣ ራሳቸውን የሚሸጡ ሰዎች የሚያናፍሱት ገለባ ወሬ” ሲሉ ያጣጥሉታል። አክለውም ትብብሩ በመርህ የሚመራ እንደሆነ አስታውቀዋል። አሁን ለጊዜው ያልዘረዘሯቸው አካሄዶች ውጤት ካመጡ ነገሮች ሊቀየሩ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
በ1997 ዓ.ም ምርጫ ቅንጅት የነበረው ድጋፍ እንደ ሱናሚ ማዕበል ነበር። ሕዝብ በሙሉ ልቡ አምኖና ፈቅዶ ድጋፉን የሰጠው ፓርቲ ነበር። ዓመፅ ሲጠራ የሚሰማ፣ ተሰለፉ ሲል ሕዝብ የሚጎርፍለት፣ እቤት ተቀመጡ ሲል የሚታዘዝ…. የምሁራንና አዋቂዎች ስብስብ የነበረውን ቅንጅትን ሚዲያ መራውና ፍጻሜው እነሱንም ኢትዮጵያንም ወደ ኋላ ጎተተ። ዛሬ ትብብር የጎዳና ስብሰባ ሲያደርግ ብቻውን፣ በዚህ የዲጂታል ዘመን የአንድ ጎረምሳ ያህል እንኳ ተከታይ የሌለው መሆኑ እየታወቀ፣ በቀጥታ ሥርጭት (Live) መግለጫ ሲሰጡ የሚከታተላቸውን ሰው ቁጥር እያዩ “ጫና እናሳድራለን” ማለታቸው “ጫና የፈጠረው መላላጥ ነው” የሚሉት የራሱ የሕብረቱ አባላት ናቸው።
አቶ አበባ አካሉ “አስቀድሞ ነበር እንጂ” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። አስቀድሞ ምርጫ ባይገባ ጥሩ ነበር። ከተገባ በኋላ ምርጫው አልቆ ይህን ማለት አግባብ አይደለም። ትብብሩ ያለው የፓርላማ ወንበር ሁለት ብቻ እንደሆነ አመልክተው አሸናፊዎቹ ካልገቡ ወነበሩ ባዶ ሆኖ እንደሚቀጥል አመልክተዋል። አክለውም፣ “በትብብሩ ውስጥ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ የሚያመላክቱ በርካታ መረጃዎች አሉ። ይልቁኑ ቁጭ ብለው ልዩነታቸውን ሊፈቱ በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ቢሰጡ ይሻላል። እዚህ ላይ ትኩርት ይሁን”
አቶ ምርጫው “ብዙ ጉዳዮች አሉ። ሁሉን ይፋ ብናደርግ ፣ ብንናገር ህዝብ ይጎዳል። ያው ልማዳቸው ነው። አይገባቡም በማለት ያዝናል ብለን ትተነው ነው” በማለት ብዙም ጠልቀው መናገር እንደማይፍለጉ ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል።
ትብብሩ ምርጫ እንደሚወዳደር ቃል ገብቶ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወስዷል። ምርጫውን እንደማይወዳደር ማሳወቅ ከሚገባው ጊዜ በፊት ሳያሳውቅ ቆይቶ አሁን ሰባትም ብትሆን እሷኑ እንደማይቀበል አስታውቋል። ምርጫ ቦርድ ሂሳቤን ይል ይሆን?
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






