“የሟች ቤት እስኪ ውሰደኝ” አልኩት። “ለምን?” ሲል ጠየቀኝ። “ለቅሶ ደርሼ፣ ከፊቷ አባቷ የተገደለባትን የስድስት ዓመት ህጻን አይቼ፣ እናቷን ስለ ሁኔታው ለማነጋገር እና…” የቡሬው ነዋሪ አላስጨረሰኝም። “ወሬ ሳታበዛ በመጣህበት መንገድ ቶሎ ውጣ። እናትየው ልጆቿን ታሳድግበት” አለኝ። ይህንን ሲለኝ ፊቱ ላይ የሚታየው አለመረጋጋትና ዓይኑ ውስጥ አካባቢውን ለመቆጣጠር የሚታየው መቅለብለብ አስፈራኝ። ቡሬ!! ነገም ሌላ ቀን ነው። ለቡሬና ለመላው አማራ፣ በተለይም ሰላማዊ ነዋሪዎች ለሚሰቃዩባቸው አካባቢዎች መልካም ከመመኘት ውጭ አማራጭ አልነበረኝም።
ከላይ እንደ መግቢያ የቀረበውን የተናገረው የ‘አዲስ ሪፖርተር’ ተባባሪ ነው። ይህን ያለው በርካታ የሚጻፉና የማይጻፉ ጉዳዮችን በዓይኑ ካየ እና ከሰማ በኋላ ነው። በተለይም ለዚህ ሪፖርት መነሻ የሆነው የስድስት ዓመቷ ታዳጊ የወደፊት ዕጣ ፈንታ፣ በዓይኗ ያየችውን በደል ማን? እንዴት እና መቼ ከልቦናዋና ከአዕምሮዋ ሊያጸዳላት ይችላል? የሚለውን በማሰብም ጭምር ነው።
በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያም፣ በትግራይም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ህጻናት ዓይናቸው እያየ፣ ቤተሰቦቻቸው ላይ እረፍት የሚነሱ፣ እስከወዲያኛው የማይረሱ እና እንደ ትኩስ ወንጀል ዕለት ዕለት ልብንና ሕሊናን የሚጠብሱ ወንጀሎች ተፈጽመዋል።
የዚያች ምሽት ዘግናኝ ድርጊት
በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት ግድም የግቢው የውጭ በር ተንኳኳ። አምስት የፋኖ ታጣቂዎች ነበሩ። ቀኑ የተቆረጠለት አቶ አላዬ መከተ “ማን ነው?” አለ። በድጋሚ እንዲከፍት ጠየቁት። ከፈተ። ከአምስቱ አንደኛው ወደ ውስጥ ዘልቆ ገባና ክላሹን አንስቶ ምላጭ ሲስብ አቶ አላዬ ዞረ። ምላጩን የሳበው ታጣቂ ጀርባውን መታው።
አቶ አላዬ ጀርባውን እንደተመታ፣ ተከትላው የወጣችውን የአምስት ዓመት ሴት ልጁን ወደ ቤት ለማስገባት ሲጠጋ፣ ሌላ ታጣቂ ገብቶ ደጋግሞ በጥይት ደበደበው። እዚያው በሚስቱና በሕፃን ሴት ልጁ ፊት ተዘረረ። ሚስት ብትጮህ፣ ልጅ “አባቴ” ብትል የሚደርስ ጠፋ። በቡሬ አይቶ እንዳላዩ፣ ሰምቶ እንዳልሰሙ መኖር ከሆነ ከራርሟል።
በፍርሃት ምክንያት ድጋፍ የሚሰጥ አካል ባለመገኘቱ፣ እስኪነጋ ድረስ ሚስት የወደቀ ባሏን ነፍስ ለማትረፍ የምትችለውን ሁሉ ስታደርግ ቆየች። ሊነጋጋ ሲል በአስራ አንድ ሰዓት አካባቢ፣ አጋዥ አግኝታ ኮሶ በር ሆስፒታል ብትወስደውም ደሙ ፈሶ በማለቁ ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም።
ሰኔ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ተወልዶ ባደገባት ቡሬ ከተማ በጥይት ተደብድቦ የሞተው አቶ አላዬ የሂሳብ ባለሙያ ሲሆን፣ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ነበር። በዩኒቨርሲቲ ቆይታው የተዋወቃትን ጓደኛውን አግብቶ፣ በዚያው በተወለደበት ከተማ በፋይናንስ አስተዳደር ውስጥ ይሰራ ነበር።
ይህን ሪፖርት ያዘጋጀው የ‘አዲስ ሪፖርተር’ ተባባሪ ምስክሮችን ጠቅሶ እንዳለው፣ ሟች አቶ አላዬ በማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የማይሳተፍ፣ ስፖርት የሚወድና ሥራውን ሰርቶ የሚኖር ገለልተኛ ሰው ነበር።
በስጋት የተከበበው ኑሮ
ቡሬ መስጊዱ ጀርባ ቀበሌ 01 ነዋሪ የነበረው አቶ አላዬ በጥይት ተደብድቦ ሕይወቱ ሲያልፍ በዓይኗ ያየችው ሴት ልጁ እጅግ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መሆኗን የሚያውቁ ነዋሪዎች፣ “ብዙ ጉድ አለ፣ መናገር ግን አይቻልም” በማለት በስጋት እንደሚኖሩ አመልክተዋል።
ቤተሰቦቹን ማናገርም ሆነ “ነፍስ ይማር” ለማለት የፈሩ ነዋሪዎች ለ‘አዲስ ሪፖርተር’ እንዳሉት፦ “ቡሬ ማታ ማታ ሰላም የላትም። መከላከያ ወደ ካምፑ ሲገባ ጥበቃ የሚያደርጉት የሚሊሻ ኃይሎች ምንም ቢፈጠር እርዳታ አያደርጉም። እንዲያውም ከመካከላቸው ተባባሪ የሚመስሉ አሉ” ብለዋል።
“ማንን እንመን?” ሲል የሚጀምረው የቡሬ ነዋሪ፣ በሚኖርባት ከተማ የሚታየው ድራማ ራሱን እንዲጠራጠር አድርጎታል። በቡሬ የአገር መከላከያ፣ የአካባቢ ሚሊሻና የፋኖ ታጣቂዎች አሉ። ከሁሉም ይልቅ ሕዝቡ የሚያምነው የመከላከያ ሠራዊትን ብቻ ነው። ሚሊሻ የሚባሉት ከፋኖ ጋር ሸሪክ እንጂ የተለያዩ አካላት አይመስሉም። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ በከተማዋ መዋቅር ውስጥ መረጃ የሚያሾልኩም አሉ። ችግሩ “የት? ለማን? እንዴት አቤት ይባላል?” የሚለው ነው።
ከአስተዳደር መዋቅሩም ሆነ ከሚሊሻ ውስጥ ሥራቸውን በታማኝነት የሚሰሩ ቢኖሩም፣ መዋቅሩ ሙሉ በሙሉ የጸዳ ባለመሆኑ ሕዝቡ እምነት አጥቷል። በተዘዋዋሪ መንገድ መረጃ ያሰባሰበው ተባባሪ እንደሚለው፣ ሞት ተለምዷል። ገዳይን ማወቅ ባይከብድም ሕግ ፊት ማቅረብ አይታሰብም። ጊዜውን ተንተርሰው ቂም የሚወጣጡም አሉ።
የጥቅም ትስስር እና የፍትህ መናፈቅ
“አሻጥር አለ” የሚል ሌላ ነዋሪ፣ “ቡሬ የቢዝነስ ማዕከል ሆናለች። ፋኖ ከአካባቢው ከተወገደ አበልና ጥቅማ ጥቅም የሚቀርባቸው እና ወደ መደበኛ ደሞዛቸው የሚመለሱ አካላት ሰላሙን አይወዱትም” በማለት ችግሩ በሰው ልጆች ስቃይ ኪስን የመሙላት በሽታም እንደሆነ ያስረዳል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ሰላምን በሚፈለገው ደረጃ ማረጋገጥ አስቸጋሪ ሆኗል።
በቡሬ ትንሽ ፍራንክ ያለው ሰው ለሚሊሻ ከሰጠ የፈለገውን ሰው ያስቀጠቅጣል፣ ያስወነጅላል፣ ያሻውንም ያስደርጋል። በቡሬ “ያለው” አዛዥ ናዛዥ ነው። እናም ዝምታ “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ” ሆናለች። መተንፈስ መዘዙ የከፋ በመሆኑ አለመናገር ተመራጭ ሆኗል። አቶ አላዬን ጨምሮ ሌሎች የተገደሉት በልዩ ምስጢር ሳይሆን በገሃድ ነው። መናገር ግን ዋጋ ስለሚያስከፍል ምስጢር ያልሆነ ምስጢር ሆኗል።
ከቦቴዎች፣ ከሕዝብ ማመላለሻ መኪኖች፣ ከከባድና ቀላል ተሽከርካሪዎች ቀረጥ የሚሰበስቡ የፋኖ ታጣቂዎች፣ መከላከያ ሲንቀሳቀስ መረጃ ወዲያው ስለሚደርሳቸው እንደሚሰወሩ የሚያመለክቱት የከተማው ነዋሪዎች፣ “ሥራ የማይወዱ፣ ቀላል የገቢ ምንጭ ያደረጉት ፋኖ መባልን ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
በቡሬ በሚታወቁ የንግድ ባንክ አካውንቶች “ገንዘብ አስገቡ” በሚል ማዘዝ፣ በሚላከው የባንክ አካውንት ገንዘብ ማስገባት፣ ያስገቡበትን ደረሰኝ ታቅፎ “ፍትህ የት ነች?” ብሎ በሐሳብ መባተትና “ፍትህ ትመጣ ይሆን?” ብሎ በቀን ማለም የቡሬ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ገጽታ ሆኗል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






