[መጥረቢያና እጀታ] በጋራ የተቃውሞ መግለጫ አወጡ፤ “በሱዳን ተዋጊ ኃይል የለንም፤ ኤርትራ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት አትፈቅድም”

Date:

አዲስ ሪፖርተር – በመጥረቢያው ብረትና በእንጨቱ እጀታ የተሳሉት ሻዕቢያና ትህነግ በጋራ መንግስትን ተቃወሙ። የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር በተለመደው አንድ የመተንፈሻ አውዳቸው አማካይነት ኤርትራ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ እንደማትፈቅድ ገልጸው ተቃውሟቸውን ገልጹ። “የሚያሳዝነው የሁለቱን ድርጅቶች ቅራቅንቦ በመልቀም ስማቸውን በመጥቀስ ‘እንዲህ አሉ’ በማለት በሰበር እያጀቡ በውጭ አገርና በየስርቻው ሆነው የሚይቀባበሉት ሚዲያና የማህበራዊ ገጽ አምደኞች ናቸው” ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ። ሚዲያዎች የሰሙትን ብቻ ሳይሆን እውነታውን በመከተል ሲዋሽ ማጋለጥ እንጂ ማንም የረጨውን መረጃ እየለቃቀሙ ህዝብ መጋት እንደሌለባቸውን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ይፋዊ ንግግር፣ ትህነግ፣ ኤርትራና ሱዳን በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ ላይ አዲስ ስልታዊና ወታደራዊ ጥምረት ፈጥረዋል በማለት ያቀረቡትን ክስ ትህነግና የኤርትራ መንግሥት በተከታታይ ባወጧቸው መግለጫዎች ሲያስተባብሉ በገሃድ መዋሸታቸው ጎን ለጎን ተመልክቷል።

በሱዳን ጦርነት ትህነግ እንዳልተሳተፈ የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም አስታውቀዋል። እሳቸው ይህን ቢሉም፣ በሱዳን ጦርነት እየተሳተፉ ያሉ የሳምሪ (አርሚ ሰባ) አባላት በቪዲዮ በግልጽ በሱዳን ጦርነት ሲሳተፉ የቀረጹትን ምስል ማሰራጨታቸውን ተንተርሶ ያሉት ነገር የለም፤ በመግለጫቸውም ላይ አልተጠየቁም። የአርሚ ሰባ ምርኮኞች በገሃድ በቪዲዮ ቀርበው የመሰከሩትን ሃቅ አልስተባበሉም።

በመጥረቢያ እጀታና በዛቢያ አስመስለው ሻዕቢያን፣ ትህነግን እና ላኪውን ግብጽን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመጥረቢያው “እጀታ” ያሉት ሻዕቢያ ታዛዥ የሆነውን ትህነግን እንዴት እንደሚነዳው በፓርላማ የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓት ላይ አንስተው ነበር።

በንግግራቸው “ትህነግና ድል ሊገናኙ አይችሉም” በማለት፣ እጀታው ካላዘዘው ዛቢያው ምንም ማድረግ ስለማይችል የኢትዮጵያ ዝግጅት ዛቢያው ላይ እንደሆነ አመልክተው ነበር። አልፎም “የትግራይ ሕዝብ ሙሉ በሙሉ ካልጠፋ” በሚል ሻዕቢያን ያስኮረፈውን የፕሪቶሪያ ስምምነት በማንሳት፣ “የአሸናፊና ተሸናፊ” ስምምነት እንደሆነም ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት በነበራቸው ቆይታ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተደረገውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በማስታወስ፣ ትህነግ ስምምነቱን የፈረመው ስለተሸነፈና መፈናፈኛ ስላጣ ነው ማለታቸው ልክ እንዳልሆነ የትህነግ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

አቶ ሚካኤል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ትህነግ በጦር ሜዳ ተሸንፏል” ላሉት ምላሽ ሲሰጡ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት የአንድ ወገን እጅ መስጠትን የሚያሳይ ሳይሆን፣ የሁለቱንም ወገን መሠረታዊ ጥቅም ያስከበረና የሕዝብን እልቂት ለማስቆም የተደረገ የጋራ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን በማመልከት ተቃውመዋል።

ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ የትህነግ “አልተሸነፍንም፣ ስምምነቱ የጋራ ስምምነት ነው” የሚለው መግለጫ የድርጅቱን የፖለቲካ ሕልውና፣ በታሪክ ያለውን ስም እና የተከታዮቹን ሞራል ለመጠበቅ የሚደረግ ስልታዊና የተለመደ ቅጥፈት እንደሆነ አመልክተዋል።

ዋናው ተደራዳሪና የወቅቱ የትህነግ ቃል አቀባይ የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ዶክተር ደብረጽዮን “እንደፈለጋችሁ አድርጋችሁ ካልፈረማችሁ ወደ በረኃ ልንጓዝ ነው እያለ ይጨቀጭቀኝ ነበር” በማለት ከድርድሩ ማግስት መናገራቸው አይዘነጋም።

የትህነግ ቃል አቀባይ አቶ ሚካኤል አስገዶም፣ ድርጅታቸው ከየትኛውም የውጭ ኃይል ወታደራዊ ድጋፍ እንደማይፈልግና በራሱ ውስጣዊ ጥንካሬና በትግራይ ሕዝብ ላይ ብቻ እንደሚተማመን ያስታወቁት ከሻዕቢያና ከአንዳንድ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ፈጥረውታል የተባለውን ጥምረት ሲያስተባብሉ ነው። አክለውም የፌደራል መንግሥቱ ራሱ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የኤርትራን ጦር ጨምሮ የውጭ ኃይሎችን ወደ ሀገር ውስጥ መጋበዙንና ማሳተፉን ቃል አቀባዩ አስታውሰዋል።

ዛሬ ከትህነግ ጋር አብሮ እየሠራ ያለውን ሻዕቢያን አንስተው ትግራይን እንደወጋ ያስታወቁት ቃል አቀባዩ፣ በዚህ ደረጃ በወንጀል የሚከሱት ሻዕቢያ አሁን ላይ እንዴት ከትህነግ ጋር ለመሥራት እንደተስማማ ግን አላብራሩም።

ጥምረቱ ሲመሠረት ስለ ሻዕቢያ፣ በተለይም በአስገድዶ መድፈር፣ በጦርነቱ ስለጨፈጨፋቸው ንጹሐን እና ስላካሄደው መጠነ-ሰፊ ዝርፊያ ትህነግም ሆነ የትህነግ ደጋፊ ሚዲያዎች ምንም እንዳያነሱ ቅድመ-ሁኔታ ተቀምጦ እንደነበር ርዕዮት ሚዲያ በተደጋጋሚ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር በይፋዊ የማኅበራዊ ገጻቸው በረዥሙ የኮነኑ ሲሆን፣ ገዥው የብልጽግና ፓርቲ ለቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ግዴለሽ የሆኑ ፖሊሲዎችን እያራመደ ነው ሲሉ ከሰዋል። ክሳቸው ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳታገኝ ሻዕቢያ ከሚልኳት ሀገራት ጋር የሚያራምደውን አቋም ያረጋገጠ ነው።

ሚኒስትሩ “በአፍሪካ ቀንድ በአሁኑ ወቅት ለተፈጠረው ከፍተኛ ውጥረት ዋነኛ መንስኤው የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ፍላጎቱን ተከትሎ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ነው” ሲሉ ኤርትራን የማይመለከት መከራከሪያ አቅርበዋል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሱዳን ፈጣን ደጋፊ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) ድብቅ ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰዋል።

ይህንን ሲሉ፣ ሀገራቸው በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ታጣቂ ማደራጀቷን፣ ከለላ መስጠቷን፣ ማስታጠቋን፣ እንዲሁም በውክልና በምታገኘው ገንዘብ የፋይናንስ ድጋፍ ስለማድረጓ ለሚቀርበው ክስ እና በገሃድ ለሚታዩት ማስረጃዎች ማስተባበያ ስለሌላቸው ክሱን “ተራ ቀልድ” ብለውታል።

ሚዲያ ፊት የማይቀርቡት የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ ዘወትር በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ሻዕቢያን ለመከላከል ይትጉ እንጂ፣ ማናቸውንም ጉዳዮች እንደሚያሰራጩ ያመለከቱ አስተያየት ሰጪዎች “የሚያሳዝነው የእኚህን ሰው የፈጠራ ወሬ ‘የማነ እንዲህ አሉ’ በማለት የሚያሰራጩ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ናቸው። ቢያንስ የማነን ‘ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ የባህር በር ብትከራይ ምን አገባዎት? ሻዕቢያ አይሆንም ካለ ኢትዮጵያ አማራጯን እንዳታይ እርስዎና ድርጅትዎ ምን ያገባችኋል?’ አለማለታቸው አሳዛኝ ድንቁርና መሆኑን አመልክቷል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ለሱዳኑ አንደኛ ወገን ድጋፍ ይሰጣል የሚለውን ክስ ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ምላሽ ሰጥተውበታል። ይልቁኑ ሱዳንን የምታተራምሰው ኤርትራ፣ እንደለመደችው የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማደናቀፍና ትግራይን መልሳ ለማወክ እየሠራች መሆኑ ቢታወቅም፣ አሁንም የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር ይህንን ሐቅ አይቀበሉም፤ የሚጠይቃቸውም የለም።

ሻዕቢያና ወያኔ በጋራ ኢትዮጵያ ለሱዳን ፈጣን ደጋፊ ኃይሎች በድብቅ እርዳታ እንደምታደርግ ስለሚያነሱት ክስ “ትህነግ በግልጽ ወታደር አሰልፎ በሱዳን እየተዋጋ፣ ሻዕቢያና ግብጽ በግልጽ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነውን የሱዳን ኃይል እየደገፉ በምን ሞራላቸው ኢትዮጵያን እንደሚከሱ ሊገባን አይችልም” የሚሉ ወገኖች፣ በተደጋጋሚ እንደሚሉት “እኛ ተደራጅተን ስናፈራርስ እናንተ አርፋችሁ ቁጭ በሉ፣ እኛ ተደራጅተን ያሻንን ስናደርግ ልክ ነን፣ ኢትዮጵያ ምንም ነገር ብታደርግና ራሷን ለመከላከል ብትሞክር ኃጢአት ነው የሚሉ የድንጋይ ስብስቦች ናቸው” ሲሉ አጣጥለዋቸዋል። ይህንኑ “የቅራቅንቦ ወሬ” የሚሉትን የነዚሁ ቡድኖች መግለጫና የፌስቡክ ጽሑፍ እየተቀበሉ የሚያስተጋቡትን ደግሞ “ለሚዲያ ሥራ ያልበቁ፣ ብሔራዊ ስሜትና ብሔራዊ አጀንዳ የሌላቸው” ሲሉ ስም ጠቅሰው ይተቻሉ።

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካና የደኅንነት ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ በይፋዊ መግለጫዎች የሚነገሩ መረጃዎችን፣ መሬት ላይ ካሉ ተጨባጭ ኩነቶች ጋር እርስ በእርስ በሚጋጭ መልኩ መቃወሚያ ሲቀርብ ዝም ብሎ ማግበስበስ ስህተት መሆኑን አመልክተዋል። “የዚህ ዋንኛ ችግር ከህንጻው በስተቀር መኖሩና አለመኖሩ በግልጽ የማይታወቀው፣ መረጃ ከማሰራጨት ይልቅ በሪባን ቆረጣ፣ በደመቁ ስብሰባዎች ላይ በመሳተፍና በማዘጋጀት የሚታወቀው የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጭምር ነው” ሲሉ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አደባባይ ብቅ ካላሉ በስተቀር አዳዲስ መረጃ ማቀበል የተሳናቸው የኮሙኒኬሽን ሰዎች፣ በግልም ሆነ በተቋም ደረጃ መረጃ የማያሰራጩ፣ መረጃ ሲጠየቁ የማይተባበሩና ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታቸውን የማይወጡ በመሆናቸው የሐሰተኛ ዘገባዎች ሊበራከቱ መቻላቸውን እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ። አክለውም በዚህ ተቋም መፍዘዝ የተነሳ ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ቁጭ ብለው ሰበር ዜናን ከውጭ ለመስማት እንደሚገደዱ ጠቁመዋል።

በኮሙኒኬሽን ቢሮው አማካይነት በተደጋጋሚ አጀንዳ ቢተከል፣ እንደ ኤርትራ ያለ ምንም ልማትም ሆነ ሥራ የሌለበት፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ ቋንቋ “የመንግሥት ቅርጽ አለባ” የሆነች ሀገር የማስታወቂያ ሚኒስትር ቀን በቀን ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ ሊሹለከለክ እንደማይችል እነዚሁ አካላት ይናገራሉ። ይህን ሲሉ ከቆመ ሀገር የማስታወቂያ ሚኒስትር ወይም እንደ ትህነግ ዓይነት ያረጀ ድርጅት ጋር እሰጥ አገባ ይግቡ ማለት ሳይሆን፣ ልክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚደርጉት አጀንዳ መስጠት፣ ሕዝብን ማንቃትና በመረጃ ማብቃት የተቋሙ ዋና ሥራ መሆን እንዳለበት ለመጠቆም ነው።

ለሥራው ቅርብ ስለሆኑ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት አስተያየት ሰጪ፣ ሻዕቢያ በአደባባይ “ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄዋን ከየትኛውም ሀገር ጋር ማድረግ አትችልም። ይህን ካደረገች አተራማሽ ናት” ማለት ከጀመረ መክረሙን ገልጸዋል። እሳቸው እስከሚያውቁት በዚህ ጉዳይ በግልም ይሁን በድርጅት አንድም የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይም ባለሙያ ዕለት በዕለት ሲሠራ አይተው አያውቁም። “በቅርቡ በአርሲ በተፈጸመው ግድያ ሰላሳና ሃምሳ ሰው አለቀ እየተባለ ሐሰት ሲረጭ ወጥቶ እውነቱን ለሕዝብ ለማሳወቅ የሞከረ አካል አላየሁም። ይህ ከተቋሙ ዓላማ አንጻር ሲታይ ያሳፍራል” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ተቋም ለምን ዝም እንደሚሉ እንደማይገባቸውም አመልክተዋል።

እነዚህ ወገኖች ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት የነበረውን ተጨባጭ ወታደራዊ እውነታ ወደኋላ መለስ ብሎ ማየት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።

በጥምር ኃይሉ አማካኝነት መቐለ ሙሉ በሙሉ ተከባ በነበረበት ሁኔታ፣ ትህነግ ከባድ መሣሪያዎቹን በይፋ ያስረከበበት ሂደት፣ ቀደም ሲል ያካሄደውን ክልላዊ ምርጫ ሕገ-ወጥ መሆኑን አምኖ መቀበሉ እና በክልሉ የፌደራል መንግሥቱ ዕውቅና የሰጠው የጊዜያዊ መስተዳድር መዋቅር መዘርጋቱ የኃይል ሚዛኑ ወዴት አጋድሎ እንደነበር በተጨባጭ ቢያሳይም፣ ትህነግ ለብቻው አይቀበለውም።

ስምምነቱ የተደረገው ድርጅቱ ከፍተኛ ወታደራዊ፣ ቁሳዊና ሰብአዊ ኪሳራ ደርሶበት፣ ጦርነቱን በተመሳሳይ አቅም የመቀጠል ዕድሉ በጠበበበት ወቅት መሆኑ የማይታበል የመሬት እውነታ እንደነበር የትህነግ ተደራዳሪዎች ራሳቸው መስክረዋል።

ምንም እንኳን ትህነግ፣ ኤርትራና ሱዳን ጥምረቱን “የለም” ብለው ቢያስተባብሉም፣ በአፍሪካ ቀንድ የተፈጠሩ አዳዲስ የስልታዊ ጥቅም አሰላለፎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ክስ መነሻ መሆናቸውን ተንታኞች ያመለክታሉ። በሱዳን የተደረገው ተደጋጋሚ ስብሰባ የዚሁ ምስክር ሲሆን፣ ይህንኑ ተከትሎ “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ባንዳዎች” ያሏቸው አካላት በሀርጌሳ፣ ቱርክ፣ ግብጽና ሱዳን መካከል እንደሚሯሯጡ ይናገራሉ። አስፈላጊ ከሆነም በስም ሊገልጿቸው እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

“በእነዚሁ ባንዳዎች ሩጫና አጫፋሪነት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ የቀጠናውን ዲፕሎማሲያዊ ቅርጽ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል” በሚል የሚራገበውን የሻዕቢያ ወሬ፣ የ”ተዘግታችሁ ኑሩ” ፖለቲካን በመቀበል በሚዲያቸው የሚያሰራጩ አስመሳዮችን ማራከስ የእያንዳንዱ ዜጋ ድርሻ እንደሆነም ያመልክታሉ።

የአስመራው ቡድን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከትህነግ፣ ከሱዳን ጦር ኃይል እና ሞቃዲሾ አሰልጥኖ ከላካቸው ኃይሎች ጋር በተደጋጋሚ የጋራ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶችን እንደሚያደርግ በግልጽ የሚታወቅ እንደሆነ የሚጠቁሙት እነዚህ ወገኖች፣ ሀገር ወዳድ ዜጎች በግል የማኅበራዊ ገጻቸው፣ እንዲሁም አንዳንድ ሚዲያዎች ይህንን እየተከታተሉ ማጋለጣቸው ሊበረታታ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related