አዲስ ሪፖርተር – በትግራይ ክልል እየተከናወነ ያለው የአስገዳጅ አፈሳ እና የእገታ ድርጊት በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እየገጠመው ነው። ከትግራይ የሚወጡ የቪዲዮ ማስረጃዎች፣ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ይህንኑ አፈሳ እያወገዙ ይገኛሉ። በተለይም ህወሃትን በመደገፍ የሚታወቁ የሚዲያ ስዎች “ህወሃት ከህዝብ ተለይቷል። አንክትሞለታል” እያሉ ነው። በውጭ አገር እና በአገር ውስጥ የሚገኙ የሚዲያ ደጋፊዎቹ ሳይቀር ህወሃት መፈራረሱን፣ ሕዝብን ለሌብነት ምሽግ ማድረጉን እያጋለጡ ነው።
በኃይል ሰዎችን ወደ ማሰልጠኛዎች የማስገባትና የሕዝብ ማመላለሻዎችን ጭምር አስቆሞ ወጣቶችን የማፈስ ተግባር፣ ቡድኑ በሕዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማጣቱን የሚያሳይ መሆኑ በሰፊው እየተነገረ ነው። ቀደም ሲል የህወሃት ደጋፊ የነበሩ፣ በአባልነት አብረው ሲሰሩ የቆዩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እንደሚሉት፣ ድርጊቱ ከክልሉ የተፈጥሮ ማዕድናትና ወርቅ ንግድ ጋር የተያያዙ የግል ጥቅሞችን ለማስከበር ሲባል ተፈናቃዮችን የመመለስ ሰብዓዊ ምክንያት እንደ ሽፋን በመጠቀም የሚከናወን ተግባር እንደሆነም እያመለከቱ ነው።
ይህ በክልሉ እየታየ ያለው የግዳጅ ምልመላና የእገታ ሪፖርት ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ክትትልና ስጋት ውጪ አይደለም። ሂውማን ራይትስ ዎች እና መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ቀደም ሲል በነበሩት የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭቶች ወቅትም ሆነ ከስምምነቱ በኋላ ባሉት ጊዜያት በሁሉም ወገኖች የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን፣ ህገ-ወጥ እስራቶችንና አስገዳጅ ምልመላዎችን ሲያወግዙ ቆይተዋል።
ተቋማቱ መሰረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና ሲቪሎች ከማንኛውም ዓይነት የኃይል ጫና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ በተደጋጋሚ የሚያሳስቡ ሲሆን፣ አሁን ላይ የሚወጡት ሪፖርቶችም ህወሃት ከትግራይ አልፎ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ መሆኑን የሚያመላክቱ ሆነዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት ለመከታተልና ለማስፈጸም በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ መፍታትና ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለስ (DDR) ዋነኛው ምሰሶ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲያሳስብ ቆይቷል። ኅብረቱ በክልሉ የሚስተዋሉ ማናቸውም ዓይነት አዳዲስ ወታደራዊ ንቅናቄዎች፣ የኃይል ምልመላዎችና የጸጥታ መቃወሶች የሰላም ሂደቱን ወደኋላ የሚመልሱ በመሆናቸው፣ ሁሉም ወገኖች ከስምምነቱ ድንጋጌዎች መስመር እንዳይወጡና ወደ አዲስ ግጭት የሚያመሩ ቅስቀሳዎችን እንዲያስወግዱ የጸጥታና ሰላም ምክር ቤቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ከዩናይትድ ስቴትስ የዲፕሎማሲ አቋም አንጻር ሲታይ፣ ዋሽንግተን የፕሪቶሪያው ስምምነት መፈረምን ተከትሎ ሕወሃትን ቀደም ሲል ከነበረበት የሽብርተኝነት መዝገብ ወይም ተያያዥ ማዕቀቦች ማውጣቱ የሚታወስ ቢሆንም፣ በቀጣናው የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የዲሞክራሲያዊ ምህዳር መጥበብ አንጻርና ቀጠናውን ከማተራመስ አኳያ አቋም መቀየር ግድ ሆኗል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ የተጠያቂነት መረጋገጥና የሲቪሎች መብት መከበር ላይ ያተኮረ ጥብቅ ክትትል የሚያደርግ ሲሆን፣ በትግራይ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት እንቅስቃሴዎችና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች የአሜሪካና የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ወደ ቀደመው ጠንካራ ይዞታው ለመመለስ በሚደረገው ሂደት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሆነዋል። ስለዚህም አሜሪካ የከረረውን መንገድ መርጣለች። በሽብርተኛነት የሚያስፈርጅ ቢል እስከማዘጋጀት የተኬደውም በዚሁ መነሻ ነው።
እስከ ሱዳን የተዘረጋውና የትግራይን ወጣቶች ለሱዳን አሳልፎ የመስጠት፣ ወይም በተቃዋሚዎች ገለጻ “መሸጥ” ዓለም አቀፍ ወነጀል ሆኖ እየተመዘገበ ነው። በተለይም እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ታዳጊዎችን ለጦርነት በመመልመል ማረጋገጫ የተገኘበት ህወሃት በዓለም አቀፍ ወንጀል እንደሚከሰስ እየተጠቆመ ነው።
ይህንን አስመልክቶ የቀድሞ የህወሃት ደጋፊ የነበሩ የሚዲያ ሰዎች ሳይቀር / አዲስ ሪፖርተር በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኛ በማለት የምትገልጻቸው ባለመኖራቸው አቶ ወይም ወይዘሮ ወይም በስም እንጠራቸዋለን/ አሁን ላይ ህወሃት ከትራይ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንዲነሳ እይወተወቱ ይገኛሉ። ለአዲስ ዘመን አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ዳዊት ከበደ የአውራምባ ታይምስ ባለቤት፣ ሄርሞን ፍቃዱ እና አብረሃም ፅጌ የሚባሉት የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስተያየት ከስር ቀርቧል።
ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉ አካላት ከወርቅ እና ማዕድን ንግድ ጋር የተያያዙ በርካታ የግል ጥቅሞች አሏቸው። እነዚህን ጥቅሞች ለማስጠበቅ ሲባል “ተፈናቃዮችን ለማስመለስ” የሚሉ ምክንያቶችን እንደ ሽፋን ወይም ማስተባበያ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ አቶ ዳዊት ከበደ ተናግረዋል።
“ድርጊቱን የሚፈጽሙት አካላት ለሰከንድም ቢሆን ስለሕዝቡ ይጨነቃሉ ብዬ አላስብም፤ አሁን የሚያደርጉት እንቅስቃሴም በማኅበረሰቡ ዘንድ ውድቅ ተደርጓል” በማለት የአውራ አምባ ባለቤት አስተያየቱን አመልክቷል።
አቶ ዳዊት አክሎም “ሕዝባዊ ተቀባይነት በማጣታቸው ምክንያት ወጣቶችን በኃይል ወደ ማሰልጠኛዎች ማስገባትና አስገዳጅ አፈሳዎችን ማካሄድ ጀምረዋል። አሁን ላይ ድርጊቱ ተባብሶ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ጭምር በማስቆም ወጣቶችን የማፈስ እጅግ የሚያሳዝን ተግባር እየተከናወነ ይገኛል” በማለት የሚያውቀውን መስክሯል።
ሄርሞን ፍቃዱ በበኩሏ የሕወሃት አመራሮችና የጥፋት ኃይሎች እየፈጸሙ ያሉትን ድርጊት በጽኑ አውግዛለች። በአሁኑ ዘመን የፕሮፓጋንዳ ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል ሰዎችን በግድ ማገትና ማፈስ የማይጠበቅና እጅግ የወረደ ድርጊት መሆኑን አመልክታለች።
አቶ አብረሃም ፅጌ የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነው። እሱም እንደሌሎቹ ሁሉ ድርጊቱን እየፈጸመ ያለው ቡድን ከቀደመው ስህተቱ መማር እንዳልቻለ ያመለክታል።
የክልሉ ሕዝብ አሁን ላይ “ያለፈው ይበቃናል፤ ከዚህ በኋላ ዳግም ስህተት ውስጥ አንገባም” በማለቱ የቡድኑ ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ ማክተሙን አስታውቋል።
ህወሃት አሁን ከሕዝብ የነበረውን ተቀባይነት ሙሉ በሙሉ በማጣቱ ምክንያት አስገዳጅ ሁኔታዎችን በመፍጠር ህዝቡን እያሰቃዩ መሆኑን ያለመከተው የትንሳኤ ሰብዓ እንደርታ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፤ ድርጊታቸው ሕዝቡ እንዳልተቀበላቸው ምስክር እንደሆነ ተናግሯል።
ቡድኑ በትግራይ ሕዝብ ዘንድ የነበረውን ተቀባይነት ካጣ መቆየቱን ጠቅሶ፣ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ማጣታቸው እንዳጡ በማመልከት በትግራይ ለውጥ በድጅ ላይ እንደሆነ አስታውቋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






