አዲስ ሪፖርተር ዜና – የዚህ ሪፖርት አቅራቢ ወደ ሬስቶራንቱ ሲገባ አስተናጋጆች እንደወትሮው ከወዲህ ወዲያ ይራወጣሉ። ሪፖርት አቅራቢው የተጠራበት ጉዳይ ፈጽሞ በሬስቶራንቱ ውስጥ አይስተዋልም። ቤቱ ሰላም አለው። ከቤቱ ሰላም ውስጥ አስደንጋጭ “ሽብር” መኖሩን ለሰማው ሪፖርተር ነገሩ ሁሉ ሐሜት፣ ወይም ሌላ ስውር ዓላማ ያለው ስለሚመስል የተፈጠረውን ለመስማት መቻኮል ግድ ነበር። እናም “የፍትህ ያለህ” የሚሉትን ለመስማት ጓጓሁ።
ደሞዝ ከተከለከሉ ሁለት ሳምንት ማገባደጃ ላይ የሚገኙትን ሰራተኞች ያቀፈው ካፌቴሪያ በዓመት 300 ሚሊዮን ገቢ ለማግኘት የሚሰራ በወር 2.5 ሚሊዮን ብር ደሞዝ የሚከፍል፣ ከሃምሳ ሚሊዮን ብር በላይ ግብር የሚያስገባ ከመሆኑ አንጻር እንዴት “አሰርቶ ደሞዝ መክፈል ተሳነው?” የሚለውን መሰረታዊ ጉዳይ ለመረዳት ከሰው ኃይል ኃላፊዋ እጅጋየሁ አየለ ፊት ቁጭ አልኩ።
የምስጋና እና ብሌን ኃላፊነቱ የተወሰነ የንግድ ማህበር ስር ካሉት አንዱ የሆነው SAVOR የተሰኘው ባለ ኮከብ ሬስቶራንት የሰው ኃይል ኃላፊ፣ የኦፕሬሽን ማናጀር ልዩ ሽመልስ፣ ዋና ካሸር ሃና ማሪያም ያዛቸው፣ በድርጅቱ አስር ዓመት ያገለገሉት ዕቃ ግዢ ገነት ተፈሪን ይዘው ቅራኔውን እያማሰሉ፣ አጠገባቸው ባሉ ባልደረቦቻቸው እየታገዙ የሆነውን ማስረዳት ጀመረች።
በወቅቱ ቤቱ ከውጭ በመጡ እንግዶች መሞላቱ፣ በሰራተኞች ላይ ያለው የስራ መንፈስ፣ በጥቅሉ የቤቱ ድባብ ከሰራተኞቹ የሚወጣውን ምስክርነት ለማመን ይከብዳል። ፍጹም ችግር አለ ብሎ ማመን አይቻልም። በዚህ ደረጃ ገቢና ገበያ የገጠሙለት ሬስቶራንት ገንዘቡን ማነቃነቅ እንዳይችል ሆኗል። በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የንግድ ማህበሩ ሸሪክ በድንገት ሁለተኛ ፈራሚ እንዲሆኑ በመሰየማቸው፣ እሳቸው ደግሞ በሚቀርብላቸው ሰነዶች ላይ “አልፈርምም” በማለታቸው ድርጅቱም受፣ ሰራተኞቹም አንድ ላይ ታንቀዋል። በእነሱ ቋንቋ “ተሸብረዋል”፤ ጉዳያቸውንም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሰራተኛና ክህሎት ቢሮ አቅርበው፣ ቢሮው ለግልግል ያመቻቸው ስብሰባ ውሳኔ በተሳካ መልኩ እንዲጠናቀቅ እየተመኙ ነው።
“እኛ በሁለቱ አካላት መካከል ያለ የፍርድ ቤት ጉዳይ አይመለከተንም። አያገባንም። ሰላሳ ቀን ሰርተናል። በገባነው ውልና የሀገሪቱ የአሰሪና ሰራተኛ ህግ በሚያዘው መሰረት ደሞዛችን መቆሙ አስደንግጦናል። ውሳኔውን ተከትሎ አንደኛ ወገን በያዙት አቋም እኛን ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻችንን ጭምር ለችግር ተጋልጧል። መንግስት፣ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት፣ አካላት፣ ፍትህ ወዳዶች፣ ለፍትህ የቆሙ ሁሉ ሽብርና ችግር መካከል እንዳለን ተረድተው ይድረሱልን። ውሳኔ የሰጡ አካላትም በዛሬ የኑሮ ውድነት ያለ ደሞዝ ሁለት ሳምንት መቆየት ምን ያህል የከፋ መሆኑን በማጤን፣ ህጻናትን እና መላ ቤተሰብን ከግንዛቤ ውስጥ በመክተት ውሳኔያቸውን እኛን በማይመለከትና ለከፋ ችግር በማያጋልጥ አግባብ እንዲያደርጉ ያገባናል የምትሉ ሁሉ አቤቱታችንን ስሙልን” በማለት ሰራተኞቹ ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል።
በሬስቶራንቱ በሾፌርነት የሚያገለግል ሰራተኛ “ጨነቀኝ ምን ልሆን ነው? ነገሩ እንዴት ነው? ሚስቴ ልትወልድ ተቃርባለች። የቤት ኪራይ አልተከፈለም። ሚስቴ እየተጠበቀች ነው። የዘጠና ዓመት እናቴ እና ሁለት ልጆቼን እንዴት ልምራ? ምን ጉድ ነው? የት ልሂድ? ማን ጋር ልግባ …” ለመጻፍ የማይመቹ ጉዳዮችን እያነሳ የህሊና እረፍት እንደነሳት ገነት ተፈሪ ታስረዳለች። “ከነገ ጀምሮ ስራ ለመምጣት አልችልም፤ በቤት ኪራይ ተወጥሬያለሁ” እያሉ ሰራተኞች እንደሚጨቀጭቋት የሰው ኃይል ኃላፊዋ ታስረዳለች።
“መልካም ከምሳ በኋላ አቶ ምስጋና” ይላል ለዋና ስራ አስኪያጁ የተላከ የስልክ መልዕክት፣ “እንዴት ነዎት? በዚህ ሰዓት እርስዎን ማስቸገሩ በጣም የማይመች ቢሆንም ምንም ዓይነት መፍትሄ ማግኘት ስላልቻልኩ ነው መልዕክት የምልክልዎት። አቶ ምስጋና፣ እንዴት ብዬ እንደምነግርዎት አላውቅም፤ ነገር ግን የቤት ኪራይ ክፍያ ለ10 ቀናት ያህል በመዘግየቱ ምክንያት ከተከራየሁበት ቤት እንድወጣ ተደርጌያለሁ። አዲስ የሚከራይ ቤት ባገኝም እንኳ በአሁኑ ወቅት ባለው የደመወዝ ችግር ምክንያት ለቤቱ የሚሆን የቅድመ ክፍያ (የማስያዣ) መክፈል አልቻልኩም…። ስለዚህ ከድርጅቱ የተወሰነ ገንዘብ ለቤቱ መክፈያ የሚሆን ተበድሬ成፣ ደመወዝ ሲለቀቅ መልሼ የምከፍልበት መንገድ ይኖር ይሆን? ወይም ደግሞ ሌላ ማንኛውም አማራጭ ካለ እባክዎትን ያግዙኝ፤ ይህንን የምጠይቅዎት ሌላ ምንም ዓይነት መውጫ መንገድ ስለሌለኝ ነው… በጣም አመሰግናለሁ…”
ለዚህ ጥያቄ ምን መልስ እንደተሰጠ የሰው ኃይል ኃላፊዋ “ለዚህ ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ሰራተኞች የሚነሱ ችግሮችን በተደጋጋሚ ለዋና ስራ አስኪያጁ ለአቶ ምስጋና አቅርቤያለሁ፤ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ነግረውኛል” የሚል መልስ ሰጥታለች። ዋና ስራ አስኪያጁም በበኩላቸው የሚደረገውን ማድረጋቸውን፣ የሰራተኞች ሮሮ እረፍት እንደነሳቸው፣ ያለ አንዳች ችግር ክፍያና ማናቸውም የድርጅቱ ወጪዎች በአግባቡ ይስተናገዱ እንደነበር፣ በዚህ ወር ሽርካቸው ሁለተኛ ፈራሚ እንዲሆኑ እነሱ ሳይጠየቁ በተሰጠ የፍርድ ትዕዛዝ ሳቢያ ይህ ችግር መከሰቱን ከመናገር ውጭ ሌላ አስተያየት ለመስጠት ዝግጁ አለመሆናቸውን አመልክተዋል። አክለውም በጠበቃቸው አማካይነት ውሳኔው እንዲሻር ዳኝነት መጠየቃቸውን አስታውቀዋል።
ወ/ሮ ብሌን ቀደም ሲል ከሁለተኛ ፈራሚነት የተነሱበትን አግባብ አሳግደው በሁለተኛ ፈራሚነት እንደተሰየሙ “አስገዳጅ መመሪያ” ሲሉ በቀን ሐምሌ 06 ቀን 2018 ዓ.ም “ከብሌን ዓይኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ” በሚል ለድርጅቱ፣ ማለትም ለሬስቶራንቱ የፋይናንስና ሂሳብ ክፍል (Company Finance & Accounts Department) ደብዳቤ ጻፉ።
ጉዳዩን “የሠራተኞች ደሞዝ ዝግጅትና ክፍያን በተመለከተ የተሰጠ አስገዳጅ መመሪያ” በሚል ርዕስ የተጻፈው ደብዳቤ ሙሉ ሃሳብ እንዳለ ተቀምጧል።
“በድርጅታችን ምስጋና እና ብሌን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ውስጥ የፋይናንስ ቁጥጥርን ሥርዓት ባለው መንገድ ለመምራት እና የፍርድ ቤት የጋራ ፊርማ ትዕዛዝን በአግባቡ ለማስፈጸም፣ የፋይናንስ ክፍል ይህ መመሪያ እንደደረሰው የሚከተሉትን አስገዳጅ እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወስድና የደሞዝ ክፍያ ሰነዱን (Payroll) በዚሁ መሠረት እንዲያስተካክል ታዟል” ይላሉ።
የመደበኛ ሠራተኞች ክፍያን በልዩ ሁኔታ ለይቶ ማጽደቅ (Selection of Regular Payroll)
ከዚህ በታች በዝርዝር ከተጠቀሱት 16 (አሥራ ስድስት) ሠራተኞች ውጭ ያሉት፣ የድርጅቱ መደበኛና ተራ ሠራተኞች ወርሃዊ የደሞዝ ክፍያ ያለምንም መስተጓጎል በአስቸኳይ እንዲፈጸም ተፈቅዷል። የፋይናንስ ክፍል የእነዚህን መደበኛ ሠራተኞች የደሞዝ ሰነድ (Payroll) ብቻ ለይቶ በማዘጋጀት ለፊርማ እንዲያቀርብ ታዟል።
የእነዚህ 16 ሠራተኞች ክፍያ ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ ስለማድረግ (Withholding of Specific Salaries)
እኔ ከድርጅቱ የባንክ ክፍያ ፊርማ ከተገለልኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ ከገበያ ዋጋ ፍጹም ውጭ የሆነ በጣም የተጋነነ የደሞዝ ጭማሪ ተደርጎላቸዋል የተባሉትን የሚከተሉትን 16 ሠራተኞች የፋይናንስ ክፍሉ ከዋናው የደሞዝ ዝርዝር (Payroll) ላይ ለይቶ እንዲያወጣና ክፍያቸውን እንዲያግድ ታዟል።
ጌታሁን አሰፋ፣ ልዩ ሽመኬት፣ አንተነህ ጌታቸው፣ ቶማስ አባዱ፣ አይናለም ደገፋ፣ ጣሰው ግርማ፣ በዛወርቅ መንገሻ፣ ባምላክ አበበየሁ፣ እጽገነት [የአባት ስም]፣ የትምወርቅ ግዛው፣ ገነት ተፈሪ፣ ተሾመ ብርሃኑ፣ ሰለሞን አስራት ቢሪ፣ ኤልያስ ወጥንጎ፣ ዳዊት ተሾመ፣ ሳምራዊት ሽፈራው
ለፋይናንስ ክፍሉ የተሰጠ የሰነድ ማቅረቢያ ትዕዛዝ (Required Evidence & Explanation)
የፋይናንስ ክፍል ከላይ ለተጠቀሱት 16 ሠራተኞች የተደረገውን ያልተገባ የደሞዝ ጭማሪ በተመለከተ፦
- የተደረገበትን ሕጋዊ መነሻ ምክንያት ዝርዝር ማብራሪያ (Detailed Explanation)፣
- እያንዳንዱ ሠራተኛ የነበረውን የቀድሞ ደሞዝ እና አሁን የተደረገውን ጭማሪ የሚያሳይ የቅጥር ውል/የደሞዝ ማሻሻያ ሰነድ (Evidence of Increment)፣በጽሑፍ አደራጅቶ በአስቸኳይ ለምክትል ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት እንዲያቀርብ በጥብቅ ታዟል።ለእነዚህ ግለሰቦች ክፍያ የሚፈጸመው የቀረቡት ሰነዶች ተመርምረው ሕጋዊነታቸው ሲረጋገጥ ብቻ ይሆናል።ማሳሰቢያ፦ የፋይናንስ ክፍሉ ይህንን የአመራር መመሪያ ተግባራዊ ሳያደርግና የደሞዝ ሰነዱን ሳይቀንስ (ሳይለያይ) በዕውር ድንብር የሚያቀርበውን ማንኛውንም የባንክ ክፍያ ሰነድ የማልፈርም መሆኑን በጥብቅ አሳስባለሁ።ከሰላምታ ጋር ብሌን ዓይኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ (Deputy Manager) እና 50% ባለድርሻ ምስጋና እና ብሌን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር
ይህንን ትዕዛዝ አስመልክቶ የድርጅቱ የሰው ኃይል እጅጋየሁ አየለ ስትናገር በደብዳቤው ወ/ሮ ብሌን እንዲጣራ ባዘዙት መሰረት የተፈጸመ አንዳችም አዲስ የደሞዝ ጭማሪ እንደሌለ ገልጻለች። እንዲጣራ ከተፈለገም ሰራተኞች የሰሩበትን ህጋዊ ደሞዝ በማገድ ሊሆን እንደማይገባ አመልክተዋል። የተጋነነም ይሁን ሌላ ዓይነት ሰነድ ካላቸውና ወ/ሮ ብሌን ብቻ የሚያውቁት ከሆነ ማጣራቱ የእሳቸው ፈንታ እንደሆነም አመልክታለች። ሌሎች ሰራተኞችም በተመሳሳይ ምላሽ በመስጠት “የወ/ሮ ብሌን ደብዳቤ አያስማማንም። ይልቁኑም ከህግ በላይ ነኝ የሚል መልዕክት ያዘለ፣ ሽብር የሚፈጥር ነው” በማለት አመልክተዋል። ማገድና ማረም ከተፈለገ የአገሪቱን ህግ ከምንም ባለመቁጠር የተፈጸመ፣ መንግስት ለራሱ ህግ፣ ለሰራተኞች መብትና ማህበራዊ ደህንነት ሲል ሊያርቀው የሚገባ አካሄድ ነው። በዚህ ደረጃ አዋጅ የሚመስል ደብዳቤ መላክ ከምን የመነጨ እንደሆነ አንባቢም መንግስትም ይፍረድ” ብለዋል።
አቶ ምስጋና እና ወ/ሮ ብሌን፣ ጋብቻቸውን ካፈረሱ በኋላ አምስት ዓመት ያህል ንብረት ሳይካፈሉ ከቆዩ በኋላ፣ ወ/ሮ ብሌን የንብረት ክፍፍል ክስ መሰረቱ። አያይዘውም ምስጋና እና ብሌን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር ስራ አስኪያጁ አቶ ምስጋና ስልጣን ሳይኖራቸው ብቻቸውን ሂሳብ እያንቀሳቀሱ በመሆኑ ሁለተኛ ፈራሚ እንዲሆኑ ባቀረቡት መሰረት አቶ ምስጋና ሳይጠየቁ ውሳኔ ተሰጠላቸው።
አቶ ምስጋና መጋቢት 20 ቀን 2016 የተሻሻለውን እና ወ/ሮ ብሌን የፈረሙበትን ቃለ ጉባኤ አያይዘው አቤቱታቸውን አቀረቡ። አያይዘውም ስራው ሬስቶራንት በመሆኑ፣ ወ/ሮ ብሌን ሌላ ቦታ በመሆናቸው፣ ተወዳዳሪ ስራ ስላላቸው እና ስራው መበደል እንደማይገባው በመዘረዘር ባቀረቡት መከራከሪያ፣ እንዲሁም የተሻሻለው የንግድ ማህበሩ ህግ፣ እንዲሁም ከባንክ በቀረበ ምክረ ሃሳብ መሰረት ከረዥም ክርክር በኋላ ወ/ሮ ብሌን ከሁለተኛ ፈራሚነት እንዲነሱ ተወሰነ።
ከላይ እና ከታች በዝርዝር በሚቀርበው የህግ አካሄድ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ሶስቱን ጉዳዮች ዘርዝረው ዳኝነት በጠየቁት መሰረት ድጋሚ ሁለተኛ ፈራሚ ሆነው መሰየማቸውን ተከትሎ የሰኔ ወር የሰራተኞች ደሞዝ ፔሮል ላይ ከላይ የተጻፈውን ደብዳቤ በመጻፍ እንደማይፈርሙ አስታወቁ። ይህንኑ ውሳኔያቸውን ተከትሎ አቤቱታ የደረሰው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሰራተኛና ክህሎት ጥበቃ ቢሮ ከሰባ የሚልቁ ሰራተኞች የፈረሙበትን ማመልከቻ ካጤነ በኋላ የሚከተለውን ደብዳቤ ለሁለቱም ወገኖች ላከ።
ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ጽ/ቤት በቁጥር፦ ቂ/ክ/ከ/ስ/ክ/ጽ/ቤት/001/18 በቀን፦ 03 / 11 / 2018 ዓ.ም “ለ ምስጋና እና ብሌን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር” በሚል ርዕስ “ጉዳዩ፦ ለውይይት እንድትገኙልን ስለመጠየቅ” ሲል እንዲህ ይላል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሥራ እና ክህሎት ፅ/ቤት የኢንዱስትሪ ሰላም፣ የሙያ ደህንነትና ጤንነት ቡድን በአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ተግባራትን እያስፈፀመ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በአሰሪዎችና በሰራተኞች መካከል ያለውን የስራ ግንኙነት በማጠናከር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢንዱስትሪ ሰላምን ማረጋገጥ ብሎም ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር የተቋሙ ተግባር ነው፤ በአሰሪና ሰራተኞች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በሁለቱም በኩል ያለውን ውጣ ውረድ ለመቀነስ ጉዳዩን በሶስትዮሽ አሰራር ቅሬታዎችን በማስማማት መፍታት፣ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በማወያየት ምቹ የስራ ሁኔታ በመፍጠር አሰሪና ሰራተኞች ፍፁም ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲኖራቸው እየሰራ ይገኛል፡፡
በመሆኑም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀፅ 141 እና 142 በሚያዘው መሰረት በድርጅቱ እና በድርጅቱ ሰራተኞች መካከል የደመወዝ መዘግየት ምክንያት የተፈጠረውን መጉላላት በጋራ ለመፍታት ሐምሌ 06/2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 እሰከ ሊባኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር 2ኛ ፎቅ ሥራ እና ክህሎት ፅ/ቤት አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ቢሮ በላይ በተገለፀው ቀን እና ሰዓት እንድትገኙልን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
የሚለው የጥሪ ደብዳቤ በአቶ ተሾመ መንግስቱ ሁነኛው የኢንዱስትሪ ሰላም፣ የሙያ ደህንነት ጤንነት ቡድን መሪ የተፈረመ ነው። ሰራተኞቹ ቢሮው ለሰጣቸው ፈጣን ምላሽ አመስግነው የንግድ ማህበሩ ባለድርሻዎች ጉዳያቸውን ከሰራተኞች በመነጠል ለድርጅቱ ሰላምና ለሰራተኞች ደህንነት ቅድሚያ ሰጥተው ውይይታቸውን በሰላም እንዲቋጩ ከወዲሁ ተማጽነዋል።
ጉዳዩን የያዘው የሰበር ሰሚው ፍርድ ቤት የተለያዩ ፍሬ ሃሳብ ያላቸውን ጉዳዮች አንድ ላይ እንዲጣመሩ የተሰጠውን ትዕዛዝና ከላይ ይገባኝ ባይ ወ/ሮ ብሌን ያቀረቡትን የዳኝነት ጥያቄ ያስተናገደበትን አግባብ ነቅሶ ባቀረበው የመልስ መከራከሪያ ላይ ቀጠሮ ለመስጠት ለመጪው ዓርብ ቀጥሯል።
ደሞዛቸው የተያዘባቸውና ድርጅቱ በገንዘብ እጥረት እንዳይጎዳ ለዴሊቨሪ ማድረሻ ሳይቀር እየተበዳደሩ በመስራት ላይ የሚገኙት ሰራተኞች “ቅጥርም፣ ማባረርም ህግና ደንብ ስላለው ሁሉም አካል ይህንን ህገመንግስታዊ መብታቸው፣ በአዋጅ የተደነገጉ የዘርፉን ህጎች በማክበር ማከናወን እንደሚገባው ጠቅሰው ለነገ የማይባለው የመኖር ዋስትናቸው የቅድሚያ ቅድሚያ እንዲሰጠው የፍትህ ያለህ እንላለን” ሲሉ ለሚሰሙ ሁሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የጉዳዩ ፍሬ ነገር
ባለ ኮከቡ SAVOR ሬስቶራንት ወ/ሮ ብሌን ዓይኑ አብዱ እና አቶ ምስጋና ከበደ ቦጋለ በመሰረቱት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተቋቋመና ከአስር ዓመት በላይ ያስቆጠረ ድርጅት ነው። መስራቾቹ ጋብቻቸውን ከሰባት ዓመታት በፊት በህግ አፍርሰው ተለያይተዋል። በተለያዩ ዘርፎች የተለያዩ አካላት የሚያዩት የፍርድ ቤት ጉዳያቸው ግን አላለቀም። በዚህ መካከል ወ/ሮ ብሌን ዓይኑ አብዱ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ሁለቱም ጉዳዮች ተጣምረው እንዲታዩ የሚያስችል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ፍ/ብሔር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ይላሉ።
ወ/ሮ ብሌን የጋብቻቸውን መፍረስ ተከትሎ ያላቸው የባልና ሚስት የንብረት ክፍፍል ጉዳይ በከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 236419 እና በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ንግድና ኢንቨስትመንት ችሎት በመዝገብ ቁጥር 19726 ያለው ክርክር እየታየ ያለው ክርክር፣ “በተናጥል የሚነሱት የህግ እና የፍሬ ነገር ጭብጦች አንድ ዓይነት በመሆናቸው በተመሳሳይ ጉዳይ የሚጋጭ ውሳኔ እንዳይሰጥ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 11(2) መሰረት መዛግብቱ ተጣምረው ይታይልኝ” በማለት ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።
በዚሁ መሰረት ወ/ሮ ብሌን የባልና ሚስት ንብረት ጥያቄ እና የንግድ ኩባንያው ክርክር ይጣመርልኝ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ችሎት ያለው መዝገብ በፍ.ቁ 332 መሰረት ይታገድልኝ፣ በተጠቀሰው ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር ስር ባለው የንግድ ድርጅት ሁለተኛ ፈራሚ ሆኜ ልሰየም በሚል ይግባኝ ባይ በሁለት የተለያዩ የክርክር ፍሬ ነገሮች በተለያዩ ችሎቶች እየተካሄዱ ያሉትን የክስ ሙግቶች ተጣምረው አንድ ላይ እንዲታይላቸው ዳኝነት ጠይቀው ባቀረቡት ማመልከቻ መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል። መልስ ሰጪ ውሳኔው የደረሳቸው አስተያየት ሳይጠየቁ እንደሆነ አመልክተዋል።
መልስ ሰጪ አቶ ምስጋና ይህንኑ ትዕዛዝ ተከትሎ የቀረበው ጥያቄ የአመክንዮ፣ የህግ ድጋፍ የሌለው፣ እንዲያውም “የስር ፍ/ቤት የያዘውን የክስ ሂደት ከወዲሁ ማሰናከል፣ ህገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ነው” በማለት ህግ፣ ደንብና መመሪያ አጣቅሶ ይግባኙ ውድቅ እንዲሆን ይግባኝ ባይ ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ላቀረቡት ክስ ከመልስ ሰጭ ወገን ሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. የተጻፈው የመልስ ማመልከቻ ያስረዳል።
በምላሹ “…ሁለቱም የክርክር መዛግብት በራሳቸው በይግባኝ ባይ የቀረቡና በየቀረቡበት ልዩ ሆኖ በተደራጁ ችሎቶች እልባት ሊያገኙ የሚችሉ፣ የተለያዩ የህግ እና የፍሬ ነገር ጭብጦች የሚነሱባቸው እንደሆኑ በመሰረታዊነት ለመገንዘብ አዳጋች አይደለም። በመሆኑም ያቀረቡት ይግባኝ በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 320 (3) መሰረት በሕግ ፊት ሊሰማ የማይችል (incompetent appeal) በመሆኑ ወደ ፍሬ ነገሩ መግባት ሳያስፈልግ ውድቅ ሊሆን ይገባል” ሲሉ ምላሽ የሰጡት መልስ ሰጪ፣ በማመልከቻቸው ክሶቹ ተጣምረው ሊታዩ የማይችሉበትን አግባብም ዘርዝረዋል።
በፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 11 መሰረት ክሶች የሚጣመሩት የሚከተሉት ሁኔታዎች ተሟልተው የተገኙ እንደሆነ ብቻ ነው፦ ተከራካሪ ወገኖቹ ተመሳሳይ ከሆኑ፣ የሚነሱት የፍሬ ነገር እና የህግ ጥያቄዎች አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ከሆኑ፣ ጉዳዮቹ ተነጣጥለው ሊታዩ እና ሊወሰኑ የማይቻሉ ዓይነት በመሆናቸው፣ ጉዳዮቹን አጣምሮ ማየት የተሳለጠ የሙግት አካሄድን እውን በማድረግ ፍትህን በተገቢው ጊዜ እና በተጣራ ሁኔታ ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነ ብቻ መሆኑን የጠቀሰው ማመልከቻ፣ ይህን ካለ በኋላ “…በከፍተኛ ፍ/ቤት የቀረበው ጉዳይ በጋብቻ ጊዜ የተፈራን ንብረት ክፍፍል የሚመለከት ሲሆን የሚገዛውም በቤተሰብ ህጉ ድንጋጌዎች ነው፡፡ የሚነሱት ጭብጦች የግል እና የጋራ ንብረት ከመለየት አንጻር ብቻ ነው፡፡ በሌላ በኩል በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያለው ጉዳይ የኩባንያን የሚመለከት ሲሆን የሚነሱት ጭብጦች ከባለአክሲዮንነት መብት እና ከኩባንያ አስተዳደር ጋር የሚገናኙ እና በንግድ ህጉ መሰረት የሚዳኙ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ እነዚህ በተለያዩ የህግ ማዕቀፎች የሚገዙ እና የተለያዩ ጭብጦች የሚነሱባቸው ናቸው” ሲል ያብራራል። ስለዚህ በጉዳዮቹ ተፈጥሯዊ ባህሪ የተነሳ ሁለቱም ጉዳዮች ተነጣጥለው ሊታዩ፣ ሊወሰኑ የሚችሉ እና የሚገባቸው መሆኑን ይጠቅሳል። ሊጣመሩ የማይገባቸውን ጉዳዮች ማጣመር ፍትህን እንደሚያዘገይ መመሪያ ጠቅሶ ያመላክታል።
“….በስር በከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 236419 የጋብቻ ንብረት ክፍፍል እና የኩባንያ አስተዳደር ጥያቄ ተዳብለው በመቅረባቸው ጥያቄዎቹ እንዲነጣጠሉ መቃወሚያ ቀርቦ እያለ ጉዳዩ ስርዓት ባለው ሁኔታ ባለመቅረቡ መዝገቡ ተንቀሳቅሶ አቤቱታ ከቀረበበት ከሰኔ 2017 ዓ.ም. አንስቶ እስከዛሬ ሰኔ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ለአስር ወራት መቃወሚያዎች ላይ ሳይሰማ እና ብይን ሳይሰጥ ቆይቷል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው አብረው ሊቀርቡ የማይገባቸው ጉዳዮች አንድ ላይ ቀርበው ጉዳዩ እንዲወሳሰብ በመደረጉ ነው፡፡ መልስ ሰጭ በስር ፍ/ቤት ጉዳዮቹ ተነጣጥለው መቅረብ አለባቸው በማለት መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ መቃወሚያው ላይ ብይን ሳይሰጥ ሌላ መዝገብ እንዲጣመር ማለት የስር ፍ/ቤት የያዘውን የክስ ሂደት ከወዲሁ ማሰናከል፣ ህገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ነው። ከዚህ በፊት የተፈጠረውን ሥነ-ስርዓታዊ ግድፈት በማባስ ጉዳዩን የበለጠ ያወሳስበዋል፣ በፍጥነት ፍትህ እንዳያገኝ ያደርጋል እንዲሁም ጉዳዩ ሥነ-ስርዓትን በተከተለ ሁኔታ እንዳይመራ ያደርገዋል” መልስ ሰጪ ከፍትህ መዘግየት በተጨማሪ አካሄዱ ህግ የማይደግፈው ጣልቃገብነት እንደተፈጸመ እንደሚቆጠር አስተያየቱን አስፍሯል።
የሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 34945 (ቅጽ 9) ላይ በሰጠው ውሳኔ የንግድ ማህበር ራሱን የቻለ የህግ ሰውነት ያለው በመሆኑ እንደ ባልና ሚስት ንብረት ሊቆጠር የማይችል በንግድ ህጉ መሰረት የሚታይ እንደሆነ ትርጉም ሰጥቶበታል። ማህበሩ በባልና ሚስት ብቻ የተቋቋመ መሆኑ ጉዳዩን በቤተሰብ ህግ መሰረት የሚታይ እንደማያደርገው የጠቀሰው የመልስ ሰጪ ማመልከቻ፣ ሌሎች ደጋፊ ማስረጃዎችና የህግ ትርጓሜዎችን በማንሳት አንደኛ ወገን ሳይጠየቅ የተወሰነው ውሳኔ እንዲመክን ሞግቷል።
ህዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም የምስጋና ብሌን ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር “ለዋናው ሥራ አስኪያጅ ሥልጣን መጨመርን” አስመልክቶ በተካሄደ ስብሰባ “የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ በማኅበሩ ስም የሦስተኛ ወገን የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት አስይዘው ገንዘብ እንዲበደሩ እና በብድር ውሉ ላይ እንዲፈርሙ የሚል ተጨማሪ ሥልጣን እንዲሰጣቸው አባላት በአንድ ድምፅ ተስማምተው ወስነዋል። ይህ ውሳኔ ለሦስተኛ ወገን እንዲታወቅም ስምምነት ላይ ተደርጓል” ይላል። ይህ ውሳኔ ከጋብቻ መፍረስ በፊት ወ/ሮ ብሌን ተስማምተው ፈርመውበት የጸደቀ መተዳደሪያ ደንብ እንደሆነ መልስ ሰጪ አስገንዝቧል። መረጃውን ለሪፖርት አቅራቢው በኮፒ ልኳል። ይህንኑና ከላይ የተዘረዘረውን መከራከሪያ በማቅረብ ይግባኝ ባይ ቀደም ሲል ከሁለተኛ ፈራሚነት እንዲነሱ መደረጉ ይታወሳል።
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል። ሰራተኞቹ ያለ ደመወዝ እስከ አርብ ከቆዩ ሶስተኛ ሳምንታቸውን ይሆናል። እንባ ጠባቂ ጉዳዩ እንዳልቀረበለት አመልክቷል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ ጉዳዩ ከቀረበለት ከመብት አንጻር ጉዳዩን ሊመለከተው እንደሚችል አመልክቷል።
ሰራተኞቹ እንዳሉት አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ከመቶ ሃያ በላይ ሰራተኞችንና ቤተሰቦቻቸውን ጉዳይ ቸል ማለት ፍትህን በአደባባይ መስቀል ነው። ሰራተኞቹ እንዳሉት በሰላማዊው ቤት “የፍትህ ያለህ” የሚለውን አቤቱታ ሲያቀርብ ሪፖርተራችን ወ/ሮ ብሌንን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ሞክሯል። ይሁን እንጂ ምላሽ አላገኘም። በዚሁ መነሻ የዝግጅት ክፍሉ በግል ስልካቸው የጉዳዩ አጭር መግለጫ ተጠቅሶ ምላሽ እንዲሰጡ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት “ጠቃሚ መረጃ አለኝ” ቢሉም መረጃውን ሌላው ወገን በዲጂታል አውድ እንደላከው ሊልኩ አልወደዱም።
ወ/ሮ ብሌን በቅርቡ የዘጉት ሆቴል ሰራተኞችና ሌሎች አቤቱታዎች የቀረቡ በመሆኑ ሁሉንም አካተን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ከሆኑ በቀጣይ የምናትም ይሆናል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






