በአዲስ አበባ ” የቢሮ ውስጥ ፋኖዎች አሉ” ግብር ከፋዮች፤ በሚታወቅ የባንክ ሂሳብ ክፍያ ይፈጸምላቸዋል፤ “ ሲጣራ መዘዙ ብዙ ነው” ቢሮው

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና – ሶስት ሆነው ምሳ እየተመገቡ “ የቢሮ ውስጥ ፋኖዎች ናቸው ያልተቻሉት” ሲል ከሶስቱ መካከል አንደኛው ሲናገር የዚህን ዜና ሪፖርተር ቀልብ ሳበ። የሚነጋገሩትን ካደመጠ በሁዋላ፣ ጨዋታውን በጋር መቀጠል የሚችልበት አጋጣሚ ተመቻቸና የምሬቱን ልክ በየፈረጁ ቀረበለት።

“ግብር አጉነው ይመጡና ድርድር ይገባሉ። እኔ ለምሳሌ የተጫነብኝ ብዙ ነበር። ከተደራደርን በሁዋላ በግማሽ ቀነሱልኝ። ከዛም የግማሹን ግማሽ ለመንግስት እንድከፍል አደረጉኝ፣ የቀረውን አካውንት ሰጡኝና አስገባ አሉኝ ” ሲል በአካውንት እንደ ህጋዊ ገቢ እንዲላክላቸው መተየቃቸው እያስገረመው ተናገረ።

አዲስ ሪፖርተር ካነጋገራቸው መካከል ከአስራ ሁለት የሚልቁ ነጋዴዎች ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው ናቸው። ይህንኑ ሪፖርት ለማጣናከር በእነዚሁ ሰዎች ምሪት ያገኘናቸው ሁሉ “ ህጋዊ አሰራር ነው የሚመስለው” እያሉ በመገረም የሚናገሩት ግብር ከፋዮች የተዘረጋው ሰንሰለት ጭራሹኑ ይበጠሳል የሚል ዕምነት የላቸውም።

“አስራ ሁለት ነን በዚህ የሂሳብ ቁጥር አስገባ አሉኝ” ይላል ሌላው ባልደረባው አስቀድሞ ማንነቱ እንዳይገለጽ እየተማጸነ፣ ገንዘቡን እንዲያስገባ የተላከለትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር እያሳየ። ሲያስረዳ መገረሙ የለቀቀው የማይመስለው ይህ አቤቱታ አቅራቢ “ነገር ሁሉ በህግ የተፈቀደ ይመስላል” ሲል የገጠመውን ያብራራል።

ነጋዴ ነውና እንደ ማንኛውም ግብር ከፋይ እሱም ላይ የሚደርሰበት ተተምኖበት ይላክለታል። የተጠየቀውና እሱ ሊደርስ ይገባል ያለው ግብር ለየቅል ናቸው። “ተጋኗል። በጣም የናረ ነው” የሚለው ግብር ከፋይ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሰራተኛ የሆኑትንና “አምጣ” ያሉትን “ የቢሮ ውስጥ ፋኖ ናቸው” በማለት ሌላ ገጠመኙን አንስቶ ምሬቱን ይገልጻል።

የአጎቱን የጭነት ተሽከርካሪ የሚነዳ ዘመዱና በርካታ የሚያውቃቸው የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ገንዘብ ያስገቡበትን የባንክ አካውንት እያሳዩ ለፋኖ የይለፍ እንዴት እንደሚከፍሉ አሳይተውታል። ባልደረቦቹ እንዳሉት ለፋኖ በባንክ ሂሳብ የሚጠይቀውን ማስገባት ነውር የለበትም።

“ታዲያ አዲስ አበባ ቢሮ ተቀምጠው ደሞዝ እየወሰዱ በተመሳሳይ ባብንክ አስገቡ ካሉ ከዋናው ፋኖ ምን ያለያቸዋል” የሚለው አቤቱታ አቅራቢ፣ “በርካታ ግብር ከፋዮች መንግስት ላይ እንዲነሱ እየተደረገ ነው። ሌብነቱ የሚፈጸመው በግልጽ ነው። ሃይ የሚል የለም ” ሲል ስጋቱን ይገልጻል።

አቶ ሰውነት አያሌው የገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዜናውን ማስተባበል እንደማይቻል አስታወቀው በሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ ቅድሚያ ያደረጉት “ ግብር ከፋዮችን አትታለሉ። ዳግም አጣሪ አጣርቶ ያውቀዋል። የዚያኔ ቅጣትና ወለድ ጭምር ነው የምትከሉት” በማለት በድርድር ግብር ማስቀነስ ጣጣ እንዳለው ያስረዳሉ።

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በራሱ አሰራር ቅሬታ ሰሚ ስላለው አስፈላጊ መረጃዎችን በመያዝ አቤት ማለቱ እንደሚበጅ ያስታወቁት አቶ ሰውነት፣ ባለፈው ዓመት በዚህ አሰራር ቅሬታ ያቀረቡ ከስልሳ በመቶ በላይ ጉዳያቸው ታይቶ የግብር ቅነሳ እንደተደረገላቸው አመልክተዋል።

ቅሬታ አቅራቢዎች “ ሌብነቱ በቡድን በመሆኑ ቅሬታ ማቅረብ ያስፈራል” ይላሉ። እነዚህ ቅሬታ አቀራቢዎች እንዳሉት ሰራተኞቹ “ የምንሰራው በጋራ፣ በቡድን ስለሆነ የምናካፈለው አብረን ነው። ለዚህ ነው አንድ አካውንት የምንጠቀመው” ማለታቸውን ጠቅሰው፣ አሰራሩ የተሳሰረ በመሆኑ ቅሬታ ማቅረብ ትርፉ ድካም እንደሆነ ይናገራሉ።

 የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር “ሌብነት የለም ማለት አይቻልም። በብዙ መልኩ ጥቆማው እኛም ጋር ይደርሳል። ነገር ግን መረጃና ማስረጃ ቢቀርብልን ቢሮው እርምጃ ለመውሰድ ይቀለዋል” ሲሉ ተበዳዮች ከሌብነት ጋር ከሚደራደሩ ወደ ህግ አግባብ ቢመጡ እንደሚሻላቸው አስታውቀዋል።

ሌብነትን ለመከላከል ብዙ እንደሚሰራ ያስታወቁት አቶ ሰውነትች “ግብር ካፋዮች የኦዲተሮች ውሳኔ የመጨረሻ እንዳልሆነ ይረዱ” ብለዋል። ኦዲተሮች ከወሰኑ በሁዋላ ዝቅ አድርገው መንግስት ላይ ኪሳራ ካደረሱ፣ ከፍ አድርገውም ግብር ከፋይ ላይ ጫና ካሳደሩ ከተጠያቂነት እንደማያልፉ አመልክተዋል። በዚህ አግባብ የተለያዩ እርምጃዎች የተወሰዱባቸው እንዳሉም ገልጸዋል።

ጥራት የስራ ክፍል ከኦዲተሮች ወይም ከሌሎች በቡድን ከሚሰሩት ጋር ላለመተባበሩ ምን ዋስትና እንዳለ ለተጠየቁት “ ለጥራት የሥራ ክፍል የሚላከው የግብር ከፋዮች ሰነድ የማን እንደሆነ እንዳይታወቅ በኮድ ነው የሚላከው። ይህ በሶስት ቅጂ የሚላከው ሰነድ አጣሪው እጅ ሲገባ የየትኛው ክፍለከተማ፣  ማን የሚባል ግብር ከፋይ፣ ወዘተ እንደሆነ የሚያውቀው ነገር የለም። አጣርቶ ብቻ ነው ለቢሮ ኃላፊው የሚልከው” በማለት ስራውም ሆነ አሰራሩ ግንኙነት ለመመስረት እንደማያመች አስታውቀዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቢሮው ስራውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ የእጅ ንክኪን በማስወገድ፣ ግብር ከፋዩ አለበት ሆኖ ግብር መክፈል እንዲችል እየተመቻቸ መሆኑ አቶ ሰውነት አስታውሰዋል። ከዚህም ጎን ለጎን የጥቆማ ስርዓት መበጀቱንና ይህንኑም ለግብር ከፋዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ የማስተማር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 7075 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል እየተሰጠ ያለው ጥቆማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑ አመልክተዋል።

ፌስቡክ፡ https://www.facebook.com/profile.php?id=61577410241403
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የአዲስ አበባ ሕዝብ የእናት ሀገር ጥሪ ተሳትፎና ኮሎኔል መንግሥቱ

የእናት አገር ጥሪ ከተደረገ በኋላ መላው የአዲስ አበባ ሕዝብ...

ቢሾፍቱ አለምአቀፍ አየር ማረፊያ፤ ኢትዮጵያን ወደ መፃኤ ዘመን የሚያሻግር የሎጂስቲክስ አብዮት

ኢትዮጵያ ከቢሾፍቱ ሰማይ ስር የኢኮኖሚና የሎጂስቲክስ ካርታዋን እንደገና ለመሳል...

“ጥርስ የሌለው ውሻ” የሆነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የዓለም መፃኢ እጣፈንታ

አዲስ ሪፖርተር - ፕሬዛዳንት ትራምፕ አሜሪካን ከተባበሩት መንግስታት ደርጅት...

በዘመነ ትራምፕ ጫና ውስጥ የወደቀችው ሶማሊያ እና ለሶማሌ ላንድ ተስፋን ያለመለመው አዋጅ

አዲስ ሪፓርተር - ከሶማሌላንድ የሉዓላዊነት ጥያቄ እና ከእስራኤል እውቅና...