አዲስ ሪፖርተር -ወጠጤ በማሰር ማጀገን? ዓላማው በመታሰር “መታወቅ” ነውና ትምህርት ይቅደም!!አዲሱ ትውልድ እስር ብዙም ትርጉም አይሰጠውም። የምክር አገልግሎት ተመራጩ መፍትሄ ነው። እስርን ለዝና፣ ለዕውቅና የሚጠቀሙ ወጠጤዎች ስር እየተሯሯጡ የእስር ዋራንቲ መቁረጥ የመንግስት የመጀመሪያ ትግባር ከሚሆን መልካሞችን የሚያበረታታ የሽልማት ድርጅት በማቋቋም ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉትን ወጣቶች ማበረታታት ይቅደም!!
ዩሪ ቢስሜኖቭ በቀደመችው ሶቪየት ህብረት ኬጂቢን ሲያገለግል የነበረ፣ በጋዜጠኛናት የሰራ ሰው ነው። አሱ አንደሚለው አንድን አገር አንበርክኮ ለመግዛት ትውልድን ማላሸቅ፣ ትውልዱን አላሽቆ አውነትን እንዳይቀበል ማድረግ፣ የላሸቁትን በኃላፊነት በመመደብ ተቋማትን ማንኮታኮትና መበተን፣ ኢኮኖሚውን ማናጋት፣ ቀውስ መፍጠር፣ በቀውስ ሕዝብ ማህበራዊ እረፍት እንዲያጣ ማድረግ ክፉ የሚባሉ ገዢዎች የሚመሩትን ሕዝብ ቀጥቅተው ለመግዛት የሚጠቀሙበት ስልት እንደሆነ ነው።
ይህ የቀድሞ የሩሲያ ሰላይ የአንድን አገር መላክም ገጽታዎችና ማህበራዊ ውብ ውቅሮችን፣ የዕምነት ተቋማትን እሴቶች፣ የትምህርት ተቋማትን መሰረት አናግቶ ለማፈራረስና በፈራረሱት ተቋማት ውስጥ ያሻቸውን ዓይነት የላሸቀ ትውልድ ለማፍራት ከ18 እስከ 20 ዓመታት እንደሚፈጁ አገሩን ጠቅሶ ያትታል።
በዚህ ስሌት መሰረት የማይጠይቁ፣ የማይመራመሩ፣ ግራና ቀኝ አይተው የማይመዝኑ፣ የተሰጣቸውን የሚቀበሉ፣ የተጫነባቸው ሁሉ የሚስማማቸው፣ ኃላፊነት ቢሰጣቸው “አልችልም” የማይሉ ደነቋቁርቶች ይመረቱና አገር በዚህ መልኩ እንድትመራ ይሆናል። ይህ ሲተገበር አገር እንደ አገር ትከሽፋለች። ትውልድ እንደ ትውልድ ይላሽቃል። ዓላማው ከሚገባቸው በቀር ሌሎች ላሽቀው ዓላማ ላላቸው መሳሪያ ሆነው ይቀራሉ። መኮራረጅን ያስወገደው የመጀመሪያ የሁለተኛ ደረጃ ፈተና ሶስት ከመቶ የሚሆኑ ተማሪዎች እንኳን ማለፍ እንዳልቻሉ ይፋ ሲሆን ያረጋገጠው ይህንኑ ሃቅ ነበር። በወቅቱ ይህ መርዶ ሲነገር አገር ድንኳን ጥላ ለቅሶ መቅመጥ ሲገባት እንዴት ተደርጎ ብለው የተንጫጩት ዓላማቸው የከሸፈባቸው ብቻ እንደሆኑ ስንቶቻችን ገብቶን ይሁን?
ያለፉት ሰባት ዓመታት ግጭቶችና ግጭቶቹን ተከትለው ሲወጡ የነበሩት መረጃዎች ሰላዩ ዩሪ የዘረዘራቸው የትውልድን ማላሸቂያ ውጤቶች ስለመሆናቸው አሁንም የምንጠራጠር ካለን ልንነቃ ይገባል። ሽማግሌዎች የሉንም፣ ወይም እንዳይኖሩን ተደርገዋል። የዕምነት አባቶች ያው ያየናቸው ዓይነት ናቸው “ገንዘብ ወይም ሞት” ባዮች። ፖለቲካ ውስጥ ገብተው የሚንቦጫረቁ፣ ባደባባይ መስቀል ይዘው “ጨፍጭፍ” የሚሉ “አባቶች”፣ በአደባባይ በክርስቶስ ስም የሚዳሩና የሚሻቀጡ፣ የዕምነት አውዶችን እንደ መንደር ሱቅ በደረቴ መሻቀጫ ያደረጉ ኪስ አውላቂዎች….. ተዘርዝሮ አያልቅም። በትምህርት ቤት፣ በዕምነት ተቋማት፣ በሰፈር፣ በሁሉ አቅጣጫ በዚህ አግባብ ከተገነባው ትውልድ የሚጠበቀው ምንድን ይሆን? እዚህ ላይ መልካሞች፣ አምላካቸውን የሚፈሩ፣ አገራቸውን የሚወዱ፣ ታታሪዎች፣ ቀናዎች ወዘተ የሉም ለማለት ሳይሆን እንደ ተቋም የደረሰብን ውድቀትና የውድቀቱን ውጤት ለማሳየት ነው።
ዛሬ ላይ የጦር ሠራዊት አሠማርቶ፣ ሳንጃ ወድሮ፣ ጦር ሰብቆ፣ አንድን አገር ማፍረሱ ውድመትን ወጪ የሚያስከትል ስልት ሆኗል። ከዚህ ይልቅ ቀላል ተብሎ የሚጠቀሰው ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ የማፍረስ ዘመቻ የሚያሳልጡትን መጠቀም ነው። ለዚህም ተግባራዊነት ዋናው መንገድ አንድ ማኅበረሰብ የተዋቀረበትን ዓውዶች ነጥሎ መለየት ቀዳሚው ሥራ ሲሆን፣ አንዲፈርስ የተበየነበትን ማኅበረሰብ “የሥበት ማዕከላት” በሚባሉት ጉዳዮች፣ ኣውዶች፣ ግንኙነቶች፣ አስከ ዕምነት ተቋማትና ወሳኝ መዋቅሮች በመዝለቅ እንዲፈርስ ይሰራል። ወደድንም ጠላንም ይህ ኢትዮጵያ ላይ ሆኗል።
አንድን ምስኪን ገደሉ፣ አይበቃም ብለው አስከሬኑን በድንጋይ ወገሩ፣ አስከሬኑን መውገር አያረካም ብለው ሰቀሉትና ደግመው በድንጋይ ናዳ አወረዱበት፣ እዚህ ላይ አላበቃም። ይህን ሲያደርጉ በኩራትና በጭፈራ ፊልም እየተቀረጹ በማህበራዊ ሚዲያ ይረጩ ነበር። የደሃ ደሳሳ ጎጆ እያቃጠሉ በመገልፈጥ ፊልም የሚሰሩ፣ ምን ቅጡ፣ የሚገርመውና ዩሪ ልክ እንደሆነ የሚያረጋግጠው የህን መስለ የርደት ቪዲዮ በደቂቃዎች ውስጥ ሚሊዮኖች ይቀባበሉታ። እንዴት ማሰብ የሚችል ሰው እንዲህ ያለ ክብረ ነክ፣ ሞራል ገዳይ፣ የስነ ልቦና ውቅርን የሚያዛባ ቪዲዮ ያያል፣ ሼር ያደርጋል ወይም ላይክ አድርጎ ይሳለቃል? ሰሞኑን ደግሞ “ታግቻለሁ” እያሉ የቤተሰብ ቅርስና ሃብት የሚያሸጡ ማጅራት መቺዎችን እያየን ነው። ይረዝማል እንጂ ብዙ ጉድ አለ። በኢቢኤስ ላይ የቀረበችውን የቀበሮ ባህታዊ ጨምሮ!! ለምን ይህን አልን?
ሰሞኑን ቲክቶከሮች ምናምን እየተባለ ገና በደንብ ያልተጸዳዱ ወጠጤዎችንና እነሱን ከጀርባ ሆነው የሚነዱ “ይቅርታ” በጅምላ የዘለለቻቸው ሌባ አርቲስቶች ጉዳይ አስመልክቶ እንደ ሚዲያ አቋማችንን ለመግለጽ ነው። ሰባት ዓመት ሩቅ መስሏቸው ይቅርታን ጅልነት አድርገው ዛሬም አዋራቸውን አራግፈው በየሚዲያው ከዘረፉት እየቆነጠሩ “የማህበራዊ ሚዲያዎች አጋፋሪና አዝማች” ለመሆን የሚራወጡትን ማጅራት መዚዎች ሌላ ጊዜ በስፋት እናያቸዋለን።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተረጨው የዘር ፖለቲካና ከላይ ከዩሪ ተውሰን ባስቀመጥነው ሲስተም ውስጥ ያለፈው ትውልድ ዛሬ ላይ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለሚቀጣጠሉ አጀንዳዎች የሚመች እንደሆነ ያለፉት ሰባት ዓመታት ያየናቸው ማስረጃዎች በቂ ምስክሮቻችን ናቸው። ጃዋር አምልጦትም ይሁን አውቆ “ለመንዳት ይመቻል” እንዳለው፡፡
ይህንኑ የሚረዱና በዚሁ ሲሰተም ያለፉ “ጋዜጠኛ” ተብዬዎች፣ የሚከፈላቸውና ስውር አጀንዳ ላላቸው የሚያገለግሉ አክቲቪስቶች፣ እንዲሁም ፓርቲዎችና ተቋማት፣ ራሳቸውን “ፖለቲከኛ” የሚሉና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም የሚሻቀጡ እርምጥምጦች ሁሉም ተዳምረው የሚርመሰመሱት መከረኛው ማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ ነው።
በዚሁ አውድ ውስጥ የሚረጨውን መርዝ፣ የሰበር ዜና አዋጅና የሳንቲም መልቀሚያ የፈጠራ ትርክቶች እየተጋቱ፣ እየተቀባበሉ ያደጉ ወጣቶች፣ ቀደም ሲል እንዲመጡ ከተመቻቸላቸው ሲስተም ከወረሱት መላሸቅ ጋር ተዳምሮ አዝሏቸዋል። ሰልችቷቸዋል። አንገፍግፏቸዋል። በዚህም የተነሳ ራሳቸውን ዘና ያደረጉ መስሏቸው ግብስብሱ ሰፈር ቢታደሙ አይደንቅም። ለዚህም ነው የትምህርት ሚኒስትሩ ይህን ወረሽኝ ለማራገፍ እንደ ቤተሰብ ይህን አትልበሱ፣ ይህን አታድርጉ፣ ትምህርት ቤት አካባቢ ይህን አትነገዱ … ወዘተ እየሉ የተሰበረውን ለማቃናት ደፋ ቀና የሚሉት፣ ከላይ የገለጽናቸው ባይወዷቸውም!!
መንግስት ሆይ አሁንም በቲክቶክና በሌሎች መሰል አውዶች እየታየ ያለው ትርምስ፣ ዕርቃን የሚያዘለለው ጉዳይ፣ እነዚህኑ ዥጉርጉር ማንነት ያላቸውን ተክትሎ የሚያላዝነውና ሳይገባው የሚያዳምቀው ወዘተ ሁሉም ከላይ የተባለው ፍሬ ውጤት ነውና ልክ እንደ ግሪን ሌጋሲ በርበርብ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ እንጂ ፖሊስ አሁን እያደርገ ባለው ይበልጥ እነዚህኑ ወጠጤዎች የማጀገንና ይበልጥ እንዲታወቁ የማድረግ ስራ ማረቅ ይቻላል ብለን አናስብም። አናምንም። ልምዱም ይህን አያስተምርም።
መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ችግር ቢኖርበትም፣ በቡድንና በትውውቅ የሚሰራ ቢሆንም፣ በብዙ ጎኑ ጥሩ ልምድ ሲያካፍል እንደነብረው የ”መልካም ሰው ሽልማት” እንደሚባለው ዓይነት ተቋም በመመስረት መልካሞችን የማበረታትና የመሸለም ስራ በመስራት፣ በማሰልጠንና በማስተማር፣ ከዛው ጎን ለጎን ወዲያውኑ ከፍተኛ የገንዘብ ቅጣት የሚያስጥሉ ህጎችን በማስተዋወቅ ማረቅ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ። ስለዚህ ወጠጤዎችን እያሰሩ ከማጀገን፣ ዓላማው እውቅና መሸመት ነውና ዓላማቸውን ከማሳካት ሌሎች አማራጮችን ማየቱ ያዋጣል።
የትምህርት ሚኒስትር የትውልዱን ነወር ለመቅረፍ እያደረገ ካለው ከፍተኛ ጥረት ባሻገር በፖሊሲ የተደገፈ፣ መልካም ወጣቶችን የማፍራቱ ስራ እንደ ግሪን ሌጋሲ ይታሰበበት። ከምንም በላይ የራሳችን የሆነ የማህበራዊ አውድ ፕላት ፎርሞች ባለቤት እንድንሆነ በጭምጭምታ የሰማነው ዜና እውን ይሁን!!
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






