አዲስ ሪፖርተር – የኤርትራ የደህንነትና መረጃ መዋቅር በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ካሉ ጠንካራ እና በቀላሉ የማይበገሩ ተቋማት ተደርጎ ይወሰድ የነበረው ሁሉ ተረት ነው። ትርክት ነው። ስለላው ኋላ ቀርና የተወላጆችን መልካም ፈቃድ እንዲሁም ቁርጠኝነት የተመረኮዘ ነው። አሁን ላይ ራሳቸውን ከውትድርና ያገለሉ የትህነግ ከፍተኛ ጄነራል እንደሚወራው ባይሆንም ሻዕቢያ በHuman intelellegence ወይም ሰው ተኮር ስለላ ጎበዝ ነበር። አሁን ግን ተፈረካክሷል ሲሉ ለአዲስ ሪፖርተር ይናገራሉ።
Human intelellegence ወይም ሰው ተኮር የሚባለው የሻዕቢያ የስለላ መዋቅር በጥንካሬ የሚነሳው በየደረጃው ካለው ማህበረሰብ ጋር ከተቆላለፈው የአመራር ዘይቤ እና በስርዓቱ ህልውና ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ የተሰራ በመሆኑና ዜጎቹን ከበረሃ ጀምሮ ለዚሁ ተግባር በፍቃዳቸው የተሰጡ በመሆናቸው ነው። በዚሁ ተፈጥሮው ሳቢያ ስለላው በሰውና በንግድ ተቋማት ላይ የተተከለ መሆኑ ከቴክኖሎጂ ጋር እንዳይገናኝ አድርጎታል።
የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመልክቱት የኤርትራ የስለላ ቢሮ በሰው ተኮር የተደገፈውን የስለላ ተቋሙን ማዘመን ባለመቻሉ በዜጎቹ ሲሰጠው የነበረው ድጋፍ ሲከዳው ስለላውንም አብሮ እየተንኮታኮተበት ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2026 መጀመሪያ ላይ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ይህ “አይበገሬ” የተባለውና በዘመድ፣ በጋብቻ፣ በስጋና በቅርብ ዝምድና የተተበተበ የስለላ ድርጅት እየተፈረካከሰ መሆኑን ያጋልጣሉ። ገና ከጅምሩ የኤርትራ ብሔራዊ የደህንነት ጽሕፈት ቤት (NSO) እና የወታደራዊ የስለላ መዋቅር ጥንካሬ በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች ላይ የተነተራሰ ነበር።
የመጀመሪያው የትግል ውርስ እና ወታደራዊነት በሚለው መርህ በበርሃ የተጀመረ የስለላ መዋቅር ነው። ይህ የደህንነት መዋቅር የተቀረጸው ለ30 ዓመታት በተካሄደው የነጻነት ትግል ወቅት ነበር። ይህ ከፍተኛ ቁጥጥር፣ ምስጢራዊነትን እና በጦር ሜዳ ላይ የታየ የቁርጠኝነት ባህል የፈጠረ እንደነበር መረጃዎች ያመልክታሉ።
ሁለተኛው ደግሞ ስር የሰደደ የቁጥጥር ስርዓት ላይ የተመሰረተው የስለላ መዋቅር መሆኑ ነው። ይህ የደህንነት መዋቅሩ በሁሉም የኑሮ ዘርፎች ውስጥ የገቡ የመረጃ አቀባዮች (ሰላዮች) አሉት። የሰፈር ለሰፈር ወይም የመንደር ለመንደር ክትትል፣ትናንሽ ህዋሳት ያሉት ነው። ይህ መዋቅር በየአካባቢው የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመንግስት ወዲያውኑ ያቃጥራል። ልክ ትህነግ አንድ ለአምስት አድርጎ እንዳደራጀው ዓይነት ማለት ነው።
ሶስተኛው የመገናኛ ዘዴዎች ቁጥጥር ሲሆን፣ በኤርትራ መንግስት የኢንተርኔት እና የስልክ ግንኙነቶችን በጥብቅ ያፍናል። የሲም ካርድ ፍቃድ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። የኢንተርኔት ካፌዎችም በደህንነቶች የሚጠበቁ ናቸው። በጥቅሉ ቴክኖሎጂ በኤርትራ ውግዝ ነው። ይህ በአገር ውስጥ ሲሆን፣
ከሀገር ውጭ ያሉት ላይ ቁጥጥር ይበረታል። ሻዕቢያ በውጭ ሀገራት (አውሮፓ፣ ሰሜን አሜሪካ እና ባሕረ ሰላጤው) የሚኖሩ ዜጎቿን በመከታተል፣ ተቃውሞዎችን በማዳፈን እና “የዲያስፖራ ታክስ” በማስከፈል ይቆጣጠራል። በውጭ አገር ስለሚኖሩ ብቻ ከዚህ የሻዕቢያ ቁጥትርና መመሪያ የሚያፈነግጡ በአገር ቤት ባሉ ቤተሰቦቻቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል። በዚሁ አግባብ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ጥቂት አይደሉም።
የኤርትራ የስለላ መዋቅር በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቁጥጥር ስር ያለና ምንም ዓይነት ቁጥጥር የሚያደርግበት መንግስታዊ አደረጃጀት ስለሌለ እንዳሻው ያስራል። ያፍናል። ይገላል። ዕድሜ ልክ በማይታወቅ እስር ቤት በአሰቃቂ ሁኔታ ያሰቃያል። ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ኤርትራ ለህዝቧ ገሃነም በመሆኗ ከቀን ወደ ቀን ሻዕቢያ ከህዝብ ልብ እየወጣ ዛሬ ወደ መፍረካከሱ እያመራ ነው።
በዚሁ የብሶት መደራረብና የተስፋ መቁረጥ ስሜት የተነሳ የደህንነት አባላት መክዳት (Defection) ለሻዕቢያ አሁን ላይ ስጋት ሆኖበታል። በጥር 2026 የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የኤርትራ የደህንነት መኮንኖች ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት (NISS) እየሸሹ ነው። እነዚህ ከስርዓቱ የወጡ አባላት ምስጢራዊ አሰራሮችን፣ የክትትል ስልቶችን እና ስጋቶችን ለኢትዮጵያ እያጋሩ እንደሆነ ተነግሯል። ይህንኑ መረጃ ቁልፍ መረጃዎችን በማሰራቸት የሚታወቀው ሆንር ሪቪው በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ይፋ አድርጓል።
ስትራቴጂካዊ መዛል የታየበት የሻዕቢያ የስለላ መዋቅር ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ወሰን የሌለው ብሔራዊ አገልግሎት (ግዳጅ) በደህንነት አባላቱ ውስጥ “ተስፋ መቁረጥን” መፍጠሩ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው። ለውጡን ተከትሎ ድንበር በተከፈተ በሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ300 ሺህ በላይ የኤርትራ ወጣቶች ወደ ኢትዮጵያ የፈለሱት በዚሁ በተስፋ መቁረጥ ሳቢያ ስለመሆኑ ጥርጥር የለም።
የቴክኖሎጂ ኋላቀርነት ሌላው ቁልፉ የሻዕቢያ የስለላ መዋቅር መፈራረስ አንዱና ቁልፉ ጉዳይ ነው። ሻዕቢያ በሰው ኃይል መረጃ በመሰብሰብ የታወቀ ቢሆንም፣ ከዘመናዊው የሳይበር እና የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ስልጣኔ አንጻር ኋላ ቀር መሆኑ የሰው ስለላ ላይ የገጠመውን መከዳት ሊቋቋም አልቻለም። በመሆኑም አናሎግ የነበረው “የነጭ ለባሽ” ስለላ በምሬት፣ በመዛል፣ በተስፋ መቁረጥ ሲዝርከረክ ሻዕቢያ አማራጭ የቴክኖሎጂ ስለላ እንዳይጠቀም ከቴክኖሎጂ ጋር የተጣላ መሆኑ ውድቀቱን አፍጥኖለታል።
ሻዕቢያን ከበረሃው ጊዜ ጀምሮ የሚያውቁት የትህነግ ታጋይ የነበሩ ጄኔራል እንደሚሉት ሻዕቢያ ስለላው ሰው ተኮር ነበር። አሁን እሱም ፈርሷል። ባዶ ቤት ነው። እኚሁ ጄኔራል እየሳቁ “ቴክኖሎጂን ሻዕቢያ አያውቃትም፣ እንዲያው ይፈራታል” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። አሁን በሰሙት ዜናም እንዳልተገረሙ አመልክተዋል።
ጠንካራ ተብሎ የሚፎከርለት የሻዕቢያ ስለላ ምን ነካው ?
የኤርትራ የስለላ ተቋም “ዝግ” የሚባል፣ በወዳጆቹና በደጋፊዎቹ የሚደነቅ፣ እንደሆነ ላለፉት ሁለትና ሶስት አስርት ዓመታት ይወራል። ስለ ሻዕቢያ የስለላ ተቋም ለአዲስ ሪቪው ከዛሬ ስድስት ወር በፊት መግለጫ የሰጠ አንድ የቀድሞ ሰላይ እንደሚለው ጉዳዩ በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ተለይቶ ሊታይ የሚገባው ነው።
ሻዕቢያ ሳህል ሆኖ ከተለያዩ ታሪካዊ ጠላቶች በሚያገኘው ዕርዳታ ኢትዮጵያን ሲወጋ በስፋት ይጠቀምበት የነበረው ሰው ተኮርና የንግድ ተቁማትን መሰረት ያደረገ የስለላ ስራ እንደነበር ይኸው የቀድሞ ሰላይ ይናገራል።
Human intelellegence ወይም ሰው ተኮር የሚባለው የኤርትራ የስለላ መዋቅር ቀደም ሲል በአገር ስሜት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል የሚኖሩ ኤርትራዊያንን በበጎ ፈቃድ ሰላይ ያደረግ መዋቅር ነው። በማህበራዊ ጉዳዮች፣ በኃይማኖታዊ ግንኙነቶች፣ የበዓል ቀናትን፣ በቤተሰብ ጉዳዮች፣ በጋብቻ፣ ጾታ ላይ የተመሰረት ወጥመድና በመሳሰሉት አግባቦች መሰለል የሻዕቢያ ልዩ መለያው ነው።
ሌላው የሻዕቢያ የስለላ መዋቅሩ ደግሞ የንግድ ተቋማቱ ናቸው። ድሮ እንደሚታወቀው ከተራ የችርቻሮ ስራ ጀምሮ በጭነት መኪናዎች፣ በአውቶቡሶች፣ በታክሲ ፣ በሆቴል፣ በጋራዥ፣ በቡና ቤቶች፣ በካፊቴሪያና በመሳሰሉ ዘርፎች የራሱን ሰዎች ባለቤት እያስመስለ የስለላ ስራ ይሰራ እንደነበር መረጃዎች አሉ።
በራሳቸው ሰዎች ስምና በሚቀጥሯቸው ሌሎች ተባባሪዎቻቸው አማካይነት ሻዕቢያ የሚከፍታቸው የንግድ ተቋማቱ የንግድ ሳቦታጅ ወይም ማጭበርበርን በማከናወን ከፍተኛ ዝርፊያ የሚያካሂደበት ዋና የገቢ ምንጩ ናቸው። በዚህ አግባብ ዶላር ያጥባል፣ ኮንትሮባንድ ይነግዳል፣ መሳሪያ ያጋግዛል። ለሽብር ተግባር የሚውሉ ምልምሎችን ያሰለጥናል። ሽብርን እያስፋፋ ገቢ ያገኛል። ዛሬ ላይ ግን ይህ የቀድሞው ስልቱ በቴክኖሎጂ ተደግፎ ማደግ ባለመቻሉ እየሟሟ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ ነው።
“ከሻዕቢያ አፋኝነት፣ አምባገነነት፣ ፍጹን ኢዴሞክራሲያዊነትና አጠቃላይ ባለው የከፋ ባህሪው ሳቢያ ወደው በአገር ፍቅር ሲሰሩ የነበሩትን የኤርትራ ተወላጆች በሂደት እየተነጠሉት ነው” በማለት ራሱን እንደ አንድ ምሳሌ አቅርቦ ከዛሬ ስድስት ወር በፊት የተናገረው የሻዕቢያ ሰላይ ያለው እውነት እየሆነ ነው።
ከስድስት ወር በሁዋላ በያዝነው ሳምንት በኤርትራ የመረጃና ደኅንነት መዋቅር ውስጥ ተሰግስገው የነበሩ ቁልፍ የስለላ መኮንኖች ከመዋቅሩ በመውጣት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት (NISS) መረጃዎችን ማቀበል መጀመራቸውን ሆርን ሪቪው (Horn Review) ይፋ አድርጓል።
ጥብቅ መረጃ በማውጣት የሚታወቀው ሆርን ሪቪው እንዳለው በኢትዮጵያ ለውጥ በተካሄደበት ወቅት በኤርትራው ገዥ ፓርቲ አማካኝነት በኢትዮጵያ እና በአጎራባች አገራት ውስጥ ስልታዊ በሆነ መንገድ ተሰግስገው የነበሩ ሰላዮች፣ አሁን ላይ አቅጣጫቸውን በመቀየር ከኢትዮጵያ የደኅንነት ተቋም ጋር በቅርበት እየሠሩ ነው።
በኢትዮጵያ የተካሄደውን ለውጥ ተከትሎ የተጀመረውን አዲስ ወዳጅነት፣ እንዲሁም ትህነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የከፈተውን የክህደት ጦርነት በመንተራስ የኤርትራ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ልኮት የነበረውና በመጨረሻ ዱባይ አቅንቶ ኑሮውን መምራት የጀመረው የስለላ መኮንን፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ሻዕቢያ የንግድ ተንኮል የሚፈጽም የስለላ መዋቅሩን በቅጽበት መዘርጋቱን፣ አክሎም ይህ መዋቅር በኤምባሲው ሽፋን እንደሚሰጠውና በባህር ዳር ቅርንጫፍ ቢሮ እንደነበረው ገልጾ ነበር።
አሁን ላይ እየታየ ያለው የሰለላ መዋቅሩ አባላት ፍልሰት የስርዓቱ ውድቀት ማሳያ እንደሆነ ባለሙያዎችን በማናገር ትንተና ያቀረበው ሆርን ሪቪው፣ ለፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ቅርብ የሆኑ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና የፖለቲካ ሰዎች ሳይቀሩ፣ የፕሬዝዳንቱን ሥልጣን ሊያበቃ የሚችል ማንኛውንም እንቅስቃሴ ለመደገፍ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ፍላጎታቸውን እንደገለጹ አስነብቧል። ፍልሰቱ ተራ ስደት ሳይሆን በኤርትራ የደኅንነት መዋቅር ውስጥ የታየ ሥር የሰደደ ሥርዓታዊ ውድቀት እንደሆነም አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እነዚህን የደኅንነት መኮንኖች ወደ ራሱ የስለላ መዋቅርና ስልት በመግለበጥ የኤርትራን ሚስጥራዊ የአሠራር ዘዴዎች፣ የክትትል ካርታዎች፣ በውስጥና በውጭ ያለውን ትስስር ለመረዳት እና የውስጥ ስጋቶችን በሚፈልገው መጠን ለማወቅ እየተጠቀመበት መሆኑን ነው ሪፖርቱ ያስረዳው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በዝምታ ይህን አግባብ ተከትሎ መረጃውን ሲያጠናቅርና የስለላ መዋስቅሩን ሲጠባ ከመቆየት ባለፈ የወሰደው አንዳችም እርምጃ እንዳልነበርም ተመልክቷል።
ለዚህም ይመስላል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ መንግስት ሚስጢሮች የአየር ሲሳይ ሲሆኑ የሚሰማው። ባልተለመደ መልኩ “ዝግ” ከምትባለው ኤርትራ መረጃ በገፍ እንደሚዘረፍ ለሚከታተሉ “አናሎግ” የሚባለው የኤርትራ የስለላ ድርጅት እየተበረጋገደ መሆኑን ማሳያ ነው።
ይህ ኩነት በኤርትራ የደኅንነት አባላት ዘንድ “የታማኝነት መዛል” እንደነገሰ ያሳያል። አፋኝ የሆነውን ሥርዓት እንዲጠብቁ የተሰማሩ መኮንኖች ሥርዓቱን ጥለው መውጣታቸው፣ የሻዕቢያ ውስጡ ሙሉ በሙሉ እየፈረሰ ስለመሆኑ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
በአሁኑ ወቅት በኤርትራ የደኅንነት መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ መጠራጠር የሰፈነ ሲሆን፣ እያንዳንዱ መኮንን እንደ ስጋት፣ እያንዳንዱ ታማኝ ደግሞ እንደ “ድርብ ሰላይ” የሚታይበት ደረጃ ላይ መደረሱ ታውቋል።
የኤርትራ ህዝባዊ ግንባር ለዲሞክራሲና ለፍትህ (ህግደፍ) ታማኝ የነበሩ በርካታ የስለላ መኮንኖችና የደህንነት ባለሙያዎች መዋቅሩን በመተው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር ግንኙነት መጀመራቸው ስለፈጠረው ስጋትም ብዙ እየተባለ ነው።
ይህ የደህንነት ባለሙያዎች ፍልሰት በድንገት የተከሰተ ተራ ክስተት ሳይሆን፣ ታቅዶበትና ስልታዊ በሆነ መንገድ የተከናወነ እንደሆነ ይነገራል። በተለይም ባለፉት የሽግግር ዓመታት በኢትዮጵያና በተለያዩ የቀጠናው ሀገራት ተሰማርተው የነበሩ የኤርትራ የስለላ አባላት አሁን ላይ መረጃዎቻቸውን ለኢትዮጵያ ደህንነት ተቋም እያጋሩ ይገኛሉ።
ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ቅርብ የሆኑ ከፍተኛ የፖለቲካና የጦር መሪዎች ሳይቀሩ፣ አሁን ያለውን አገዛዝ ለመለወጥ ለሚደረግ ማንኛውም አስተማማኝ ጥረት ድጋፋቸውን ለመስጠት ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት በምስጢር ፍላጎታቸውን መግለጻቸው ተመላክቷል።
ኢትዮጵያ ይህን መሰል ወሳኝና የጠለቀ መረጃ በእጇ ቢገባም፣ በቀጠናው ሊፈጠር የሚችለውን ከፍተኛ አለመረጋጋትና ጦርነት በመስጋት የአስመራውን መንግስት በሃይል ለመገልበጥ ከሚደረጉ ቀጥተኛ እንቅስቃሴዎች እስካሁን እራሷን ገድባ ቆይታለች።
ለበርካታ አስርት ዓመታት የኤርትራ የደህንነት መዋቅር ሊደፈር የማይችል እና በከፍተኛ ጥርጣሬና ቁጥጥር ላይ የተገነባ እንደሆነ ቢነገርም፣ አሁን የታየው የመኮንኖች መክዳት ግን በመዋቅሩ ውስጥ ያለውን ከፍተኛ የስነ-ልቦና መላላትና የአመራር መበታተን እንደሚያሳይ የአዲስ ሪፖርተር ምንጮች ያብራራሉ፡፡
ይህ ጽሁፍ በአዲስ አበባ ሻዕቢያ እንዴት ይሰለል እንደነበር በግርድፉ ያሳያል። በቀጣይ በማህበር፣ በጽዋ፣ በዕቁብ፣ በዕድር ወዘተ ሻዕቢያ ያሰማራቸው ቁርጠኛ ሰላዮቹ እያሳሳቁ ጎረቤቶቻቸውን፣ ባልደረቦቻቸውን፣ የሚቀርቧቸውን እንዴት እንዳታለሉ በስፋት ለትምህርት ይሆን ዘንዳ እናቀርባለን።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






