አዲስ ሪፖርተር ዜና – የቅድመ-ጦርነቱን የክልል ምክር ቤት በድጋሚ ወደ ሥራ የመለሰው ትህነግ ፣ የዜጎችን መሠረታዊ መብት የሚጋፉ የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት እና በሞት የሚያስቀጡ ድንጋጌዎችን ያካተተ አዋጅ በአስቸኳይ ስራ ላይ እንዲውል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ይህ የትህነግ ውሳኔ ቀደም ሲል በነበረው የሰላም ስምምነት መሠረት የተቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር ወደ ጎን በመግፋት፣ ክልሉን እና ዜጎችን ወደ ከፋ የፖለቲካ እና የደኅንነት ቀውስ ውስጥ የሚከት መሆኑ ተመልክቷል።
የፌደራል መንግሥት ሕገ-ወጥ ነው ብሎ በፈረጀውና ከስድስት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ተመስርቶ የነበረው የክልሉ ምክር ቤት፣ ይህንን አዋጅ ያጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር ላይ እንደነበር ይታወሳል።
ምንም እንኳን አዋጁ እስካሁን በክልሉ ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ይፋ ባይደረግም፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ምሕረት በርሀ ግን ሰኔ 17/2018 ዓ.ም. ለፍትሕ አካላት በጻፉት አስገዳጅ ደብዳቤ ሕጉ በጊዜያዊነት ሥራ ላይ እንዲውል መመሪያ ሰጥተዋል። ይህ በምስጢራዊ አሠራር መመሪያ የተላለፈበት ባለ 46 ገጽ አዋጅ፣ ለክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ለፖሊስ ኮሚሽንም ግልባጭ ተደርጓል።
በዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የትህነግ ካቢኔም ላለፉት ሳምንታት ለፍትሕና ፀጥታ አካላት አዋጁን በተመለከተ ሥልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ሕጉን ጨቋኝ ሲል የፈረጀው ሲሆን፣ አዋጁ በትግራይ ውስጥ ሰዎችን ያለፍላጎታቸው ለጦርነት ለማገዝና ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት ሰፊ ሥልጣን የሚሰጥ መሆኑን አጋልጧል።
በአዋጁ ውስጥ የተካተቱትና እስከ ሞት ቅጣት የሚያደርሱት አስፈሪ ድንጋጌዎች ፣ በጦርነት ወቅት በመንግሥትና በሕዝብ ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረስ። ከጠላት ጋር መተባበር፣ ምስጢር ማሹለክ እንዲሁም በትህነግ ባለሥልጣናትና ታጣቂዎች ላይ ጉዳት ማድረስ።
በትህነግ ጦር ላይ በማንኛውም መንገድ ፕሮፓጋንዳ ማካሄድ፣ የትግራይ ተወላጆችን ለሌላ አካል መመልመልና ጦሩ እንዲከዳ ማነሳሳት። ዕድሜና ጤናው የሚፈቅድለት ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ የክተት ጥሪን የመቀበል ብሔራዊ ግዴታ አለበት። ይህንን ትዕዛዝ ያልተቀበለ ዜጋ ከ10 ሺህ እስከ 50 ሺህ ብር ተቀጥቶ በግዴታ ወደ ውትድርና እንዲገባ ይደረጋል ተብሏል።
በጣም አነጋጋሪና መሠረታዊ የሕግ መርህን የጣሰው ድንጋጌ ደግሞ፣ አዋጁ ወደ ኋላ ተመልሶ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ ጭምር ተፈጻሚ እንዲሆን መደረጉ ነው።
የትህነግ ምክትል ፕሬዝዳንት አማኑኤል አሰፋ ግን ይህንን ሕግ የተከላከሉ ሲሆን፣ ሕጉ ሊታይ የሚገባው ሕዝብን ለማዳን ከሚደረግ ትግል አንጻር ነው በሚል ድርጊቱን ለማጽደቅ ሞክረዋል። ትህነግ በፌደራል መንግሥቱ የተሾሙትን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ፕሬዝዳንት ከሥልጣን ካነሳ በኋላ በክልሉ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ውጥረት እጅግ በርትቷል።
የፌደራል መንግሥቱና ትህነግ በጦርነት ዝግጅት እርስ በርስ እየተካሰሱ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ በክልሉ ውስጥ ሰፊ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እየተካሄደ መሆኑ ዜጎችን ለአዲስ ቀውስና ስጋት አጋልጧል።






