“ለኢትዮጵያ ስንል እንተው” ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ፤ የ2019 በጀት 2.339 ትሪሊየን ብር ሆኖ ፀደቀ፤ “አንራብም”

Date:

አዲስ ሪፖርተር –“ስኬት የሰጠን በዕቅዳችን ልክ ውጤታማ እንድንሆን፣ ያደረገን ፈጣሪያችን የተመሰገነ ይሁን፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና እስኪረጋገጥ በጋራ የምንቆም እንሁን።” ሲሉ በፓርላማ ንግግራቸው ማብቂያ ላይ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ የሚመሰረተው መንግስታቸው አዳዲስ አመራሮች ወደፊት እንደሚመጡ ፍንጭ ሰጥተዋል። ዕርቅን አስመልክቶ “የምንተወው ለኢትዮጵያ ነው” ሲሉ ከሁሉም ወገን የምህረት እጆች እንዲሰነዘሩ ተማጽነዋል።”ዛሬ ኢትዮጵያ አትወደቅም አልላችሁም፤ የመውደቅን ዘመን ተሻግራለች። ዛሬ ኢትዮጵያ ህልውናዋን አጽንታ የወደቁትን ለማንሳት የሚያስችል አቅም ገንብታለች” ብለዋል። “እመኑኝ ይራባሉ ይሉናል። እነግራቸዋለሁ ይስሙ አንራብም” ሲሉ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻሏን አስታውቀዋል።

ሌብነትን ኮንነው በመረጃ የተደገፈ ጥቆማ በአፈ ጉብዔ ቢሮ አማካይነት እንዲላክላቸው ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባቀረቡት ሪፖርቶች መሰረት ኢትዮጵያ ለዚህ በመድረሷ አምላካቸውን አመስግነዋል፤ ፓርላማው ቆሞ ያጨበጨበላቸው አብይ አህመድ ዶክትውር ደሳለኝ ጫኔን ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎችን አመስስግነዋል። ዶክተር ጫኔን የፓርላማ ዘመናቸው ቢያቆምም አብረው እንዲሰሩ ጋብዘዋቸዋል። ዶክተር ብርሃኑ ነጋን በይፋ የብልጽግናን የትምህርት ፖሊሲ በማስፈጸማቸውና እየለመኑ ቦርዲንግ ትመህርት ቤቶችን በመገንባታቸው ፓርላማው እንዲያወድሳቸው ጠይቀው ተጨብጭቦላቸዋል።

“የምንተወው ለኢትዮጵያ ነው። ለኢትዮጵያ ሲባል ልክ ለውጡን ስንጀምር የነበረው ዓይነት አካሄድ መከተል ያስፈልጋል። ብዙዎቹ ሲናገሩ የምንሰማቸው ተስፋ ከመቁረጥ ነው፤ የኛን ሁኔታ በማየት ዕድል የለም በማለት ነው። ዕድል እንዳለ፣ ተስፋ እንዳለ ካሳየናቸው፣ አብሮ መሥራት እንደሚቻል ካሳየናቸው ከውስጣቸው መጥፎ ሆነው አይደለም፡፡ ልባችን ክፍት ሆኖ አብዛኛዎቹን ለማቀፍ ለመተው፣ ሀገራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን፣ ኢትዮጵያ ሰላማዊ ሀገር እንድትሆን፣ ብልጽግና የተረጋገጠባት ሀገር እንድትሆን በጋራ መሥራት መኖር የምንችል ሰዎች መሆናችን ዓለም እንዲያይ መተባበር፣ ልባችን ማስፋት ይኖርብናል። ህወሓትም ጭምር ቀልብ ከገዛ ለመነጋገር እና ሰላም ለማምጣት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል!!” ሲሉ የተደመጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸው ቀልብ የሚስብ ሆኗል።

በውጭ አገር ሆነው በተለያዩ ማህበራትና ድርጅት ስም የተሰባሰቡ ሰሞኑን “መንግስት የምንጠይቀውን አጀንዳ ካነሳና ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ካደረገ ለምን እንቃወማለን” በሚል ካነሱት አሳብ ጋር ተስማሚ የሆነ መግለጫና ይቅር የመባባል ግብዣ ላቀረቡ ጥሪው መልካም አጋጣሚ ሆኗል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የ2019 የፌዴራል መንግሥት በጀትን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

በአዋጅ ቁጥር 1437/2018 የፀደቀው አጠቃላይ በጀት 2.339 ትሪሊየን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1.49 ትሪሊየን ብር ከታክስ ገቢ እንደሚሰበሰብ ተገልጿል። ቀሪው ገንዘብ 93.7 ቢሊየን ብር ከልማት አጋሮች በሚገኝ ብድርና ድጋፍ፣ 320 ቢሊየን ብር ደግሞ ከሀገር ውስጥ ብድር እንደሚሸፈን ተጠቁሟል።

መንግሥት የበጀት ጉድለቱ ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 1.4 በመቶ ብቻ መሆኑ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የተያዘውን የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚያሳይ ገልጿል።

በበጀቱ ድልድል 30 በመቶ ያህሉ ለትምህርት፣ ለመንገድ፣ ለጤና፣ ለግብርና፣ ለኃይል እና ለከተማ ልማት የተመደበ ሲሆን፣ ለክልሎች 187.3 ቢሊየን ብር ወይም 15.1 በመቶ የበጀት ድጋፍ ተመድቧል።

ይህ ለክልሎች የተመደበው ድጋፍ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ28.4 ቢሊየን ብር ወይም 17.8 በመቶ ማደጉ ተገልጿል። በተጨማሪም በኢኮኖሚ ዘርፍ 18.1 ቢሊየን ብር ወይም 34.1 በመቶ ጭማሪ፣ በማኅበራዊ ዘርፍ ደግሞ 106.4 ቢሊየን ብር ወይም 35.2 በመቶ ጭማሪ ያለው መደበኛ ወጪ መመደቡ ተገልጿል።

መንግሥት የፀደቀው በጀት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት፣ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን እና የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማስፋፋት እንደሚውል ገልጿል።

ኢትዮጵያ በቡና ኤክስፖርት ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም 3ኛ ደረጃ ላይ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ በቡና የወጪ ንግድ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር መሆኗን፣ በዓለም ደግሞ ከብራዚል እና ኮሎምቢያ በመቀጠል 3ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት ከቡና ኤክስፖርት 3.1 ቢሊየን ዶላር ገቢ አግኝታለች። ይህም ሀገሪቱ ባለፉት 17 ዓመታት በድምሩ ካገኘችው 3.3 ቢሊየን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር በዘርፉ የተመዘገበ ከፍተኛ እድገት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና መገኛ ሀገር መሆኗን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለተመዘገበው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዕድገት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ የቡና ምርት ማስፋፋት እና የእሴት ሰንሰለቱን ማጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል።

በተጨማሪም በአገር ውስጥ የቡና ፍጆታ በፍጥነት እየጨመረ ባለበት ሁኔታም ይህን ያህል የኤክስፖርት ገቢ ማሳካት ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፣ ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የቡና አቅም የበለጠ በመጠቀም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት እንደሚቻል አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ የነባር ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ወደ 67 በመቶ አደገ

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ትኩረት ከተሰጣቸውና በርካታ ሥራዎች ከተከናወኑባቸው ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀዳሚው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ገልፀዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ከሀገራዊ ለውጡ በፊት በኢትዮጵያ የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የማምረት አቅማቸው ከ47 በመቶ በታች ነበር።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም እያንዳንዱን ኢንዱስትሪ በየቦታው በመጎብኘትና ያሉባቸውን እክሎች በመለየት ሰፊ የድጋፍ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል።በዚህም ቀደም ሲል የነበሩት ነባር ኢንዱስትሪዎች ብቻ በአሁኑ ወቅት የማምረት አቅማቸውን ወደ 67 በመቶ ማሳደግ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መስፋፋት በተመለከተም ከኮምቦልቻ ፣ መቐለ እና ከሐዋሳ ውጭ ከአሥር ያላነሱ አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።ቀደም ሲል በጣም በጥቂት ባለሀብቶች ተይዞ የነበረውን ስፍራ አሁን ላይ ከ80 በመቶ በላይ አዳዲስ ኢንቨስተሮችን በማሰማራት ረገድ መንግሥት ስኬታማ ሥራ ማከናወኑንም ገልጸዋል።

በቀጣዩ ዓመት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ የወጪ ንግድ ብቻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህም በዘርፉ ላይ የተሰሩትን ሰፋፊ ሥራዎች ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት መጀመሯን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም እንደ ሴራሚክ፣ ሲሚንቶ፣ ብረትና መስታወት ባሉ ምርቶች ላይ ሰፋፊ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉ በዚህ ዓመት ብቻ የ24 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ይህም በአሁኑ ወቅት ዘርፉ ይበል የሚያሰኝና ተስፋ ሰጪ በሆነ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ያመላክታል ብለዋል።

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related