በሱዳን የኩርሙክ ግንባር የቀጠለው ጦርነት በርካታ ተዋጊዎች ያለቁበት መሆኑ ተሰማ፤ የአርሚ 70 ተዋጊዎችም ከባድ ጉዳት ድርሶባቸዋል

Date:

አዲስ ሪፖርተር | አዲስ አበባ/ካርቱም | ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በሱዳን የብሉ ናይል ክልል በሚገኘው ስትራቴጂካዊ የኩርሙክ አካባቢ ያለው የጦርነት ሁኔታ የኢትዮጵያን ትኩረት እየሳበ ነው። ኩርሙክ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ የምትገኝ ቁልፍ ስፍራ በመሆኗ፣ መንግሥት ጦርነቱን በንቃት እየተከታተለ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሱዳን የቀጠለው ግጭት በድንበር ደኅንነት፣ በሕዝብ እንቅስቃሴ፣ በስደተኞች ፍሰት እና በታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ በኢትዮጵያ በኩል ክትትል የሚሻው ጉዳይ ከመሆኑ ጎን ለጎን፣ በጦርነቱ በተሰለፉ የ”አርሚ 70″ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱም ተሰምቷል።

አዲስ ሪፖርተር ከሕወሓት የጦር ክንፍ ጋር ቅርበት ካለው ከፍተኛ ባለሥልጣን ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አርሚ ሰባ ኩርሙክን ለመያዝ የጄነራል አልቡርሃን ጦር በሚያደርገው ውጊያ ላይ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፏል።

በዚሁ መረጃ መሠረት የአርሚ 70 አባላት በጦርነቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል። መረጃውን ያጋሩ ምንጮች በውጊያው ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ አባላት መገደላቸውንና መቁሰላቸውን አመልክተዋል። የቆሰሉ የአርሚ 70 አባላት በመኪና ወደ ካርቱም ተወስደዋል። ከቆሰሉት መካከል አንዳንዶቹ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉም ተናግረዋል።

በጦርነቱ የበላይነት መያዙን ያመለከተው የአልቡርሃን ጦር ከተማዋን መቆጣጠሩን ቢያስታውቅም፣ ከታጣቂዎቹ ወገን የተሰጠ ማረጋገጫ ወይም ማስተባበያ የለም። የተጠቀሰችውን ቁልፍ የመሣሪያና የኮንትሮባንድ ማስተላለፊያ መስመር ለመያዝ በተደረገው ውጊያ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ግን ከሱዳን የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል።

በሱዳን የተለያዩ ኃይሎች ስትራቴጂካዊ ቦታዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ውጊያ በቀጠለበት ወቅት፣ የድንበር አካባቢዎች ለአጎራባች አገራት የደኅንነት ሥጋት ሆነዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ሉዓላዊነትንና የአገር ግዛታዊ አንድነትን መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን፣ ለዚህም በማናቸውም መልኩ ዝግጅት እንዳለ በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኗን ሲገልጹ፣ ችግር የሚፈጥር አካል ካለ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አቅም መደራጀቱን አመልክተዋል።

ተንታኞች እንደሚገልጹት፣ ኢትዮጵያ በሱዳን ድንበር አካባቢ ያለውን ሁኔታ በቅርብ እየተከታተለች ሲሆን፣ ስፍራው የሱዳንን ቀውስ ተከትሎ፡ የስደተኞች ፍሰት፣ የመሣሪያ ሕገወጥ ንግድ፣ እና የታጣቂ ቡድኖች እንቅስቃሴ የሚበረታታበት ሊሆን ይችላል።

ቀደም ባሉ ሪፖርቶች በኩርሙክ በኩል ኢትዮጵያን ለሚያጠቁ ኃይሎች ድጋፍ በማድረግ ለማስረግ ዕቅድ መያዙን የታጣቂዎቹን መሪ ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም። “ጽምዶ” በተባለው ኅብረት የተካተቱ “ነጻ አውጪ” የሆኑ ታጣቂዎች ይህንን ኮሪዶር እንዲጠቀሙ ለማስቻል፣ ውጊያው ከሌሎች አቅጣጫዎች ይልቅ በዚህ በኩል እንደሚያመዝንም አመላክተን ነበር።

በሁመራ አቅጣጫ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት እንዳለና የፋኖ፣ የቅማንትና የሻዕቢያ ጦር በቅርብ ርቀት አብረዋቸው እንዳሉ በመግለጽ የአርሚ 70 ወታደር ቃለ ምልልስ የሰጠበት መረጃ ይፋ መሆኑም አይዘነጋም።

በድንበር አካባቢ ስላለው ሁኔታ በይፋ ከኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የተባለ ነገር የለም። ይሁን እንጂ አካባቢው ወደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አቅጣጫ የሚያቀና በመሆኑ፣ ከአየርና ከምድር አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደሚደረግ በተደጋጋሚ ተመልክቷል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

“ለኢትዮጵያ ስንል እንተው” ዐቢይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ፤ የ2019 በጀት 2.339 ትሪሊየን ብር ሆኖ ፀደቀ፤ “አንራብም”

አዲስ ሪፖርተር –“ስኬት የሰጠን በዕቅዳችን ልክ ውጤታማ እንድንሆን፣ ያደረገን ፈጣሪያችን...