ከራያ አገረ ስብከት “ኢትዮጵያዊ ነን፤ ኢትዮጵያን እናነሳለን” ያሉ ከ500 በላይ ክህናት አስተዋሽ ማጣታቸውን አስታወቁ

Date:

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — ከአምስት መቶ በላይ ከህናትና ከ200 የማያንሱ ልጆቻቸው ምን ይብሉ? ይህ የራያ አገረስብከት ማህበረሰብ ጥያቄ ነው? ጥያቄውን ደግሞ የሚያጎላውና ለሰሚው ግራ የሚሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በዝምታ ላለፉት ዘጠኝና ከዚያም በላይ ወራት ከቁብ ነገር አለመቁጠሩ ነው። ካህናቱ ክብር ለሚገባው ክብር ሰጥተው ችግራቸውን በጨዋነት ቢያስረዱም፣ ታዛቢዎች የሲኖዶሱን ዝምታ “ሊገባን አልቻለም” ነው የሚሉጥ

የራያ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ ሊቃውንት ስዩማን ሃብቱ አየነው “ኢትዮጵያዊ ነን፤ ሃይማኖታችንን አንቀይርም በማለታችን ለዚህ ሁሉ መከራ ተዳርገናል” ይላሉ።

ስድስት ወረዳዎችን አጣምሮ የያዘው የራያ አገረ ስብከት ሐምሌ 15 ቀን 2015 ማመልከቻው ተቀባይነት አግኝቶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲኖዶስ ስር መተዳዳር እንደጀመረ፤ ይህም የሆነው በየትግራይ “ራሳችንን ችለን የትግራይ ሲኖዶስን / መንበረ ሰላምን መስረተናል” በሚል ሲታወጅ እንደሆነ ዋና ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

የትግራይ ሲኖዶስ ወይም አዲሱ መንበረ ሰላማ “የኢትዮጵያን አታንሱ፤ ኢትዮጵያ የሚባል አገር የለችም። ስሟን አትጥሩ” በማለት በታጣቂ እያስገደደ ጫና ሲያድርባቸው ቆይቶ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከአካባቢዎቹ ለቆ ሲወጣ በጠብመንጃ ኃይል ከውናዋ እናታቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲነጠሉ መደረጋቸውን በስደት ላይ ያሉ አመልክተዋል።

ዋና ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት ከግርፊያ፣ ከእስር፣ ከስቃይና ከመከራ ሸሽተው በቆቦ፣ ወልደያ፣ ሰቆጣ፣ ተሰደው በየቦታው በጥገኛነት የተቀመጡት ካህናት ቁጥር 500 ይበልጣል።

ህወሃት ዳግም አካባቢዎቹን ሲቆጣጠር፣ “አማርኛ አትናገሩ፤ አገረ ትግራይ በሉ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰየሙትን ጳጳስ ስም አታንሱ ወዘተ” የሚል አስገዳጅ መመሪያ ባለመቀበላቸው አሁን ድረስ እስር ላይ ያሉ መኖራቸውን ቄስ መመህር ናትናኤል ይናገራሉ። በመሆኒ፣ መቀለና ማይጨው እስር ላይ ሆነው እየተሰቃዩ ያሉ መኖራቸውን ቤተሰቦቻቸውም ይመሰክራሉ።

የራያ አገር ስብከት ወጣቶች ማደራጃ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ቄስ መምህር ሄኖክ እንደሚሉት ቅዱስ ሲኖዶስ ከታህሳስ 12 ቀን 2018 ጀምሮ ካህናቱ ምንም ዓይነት ክፍያ የላቸውም። እሳቸውን ጨምሮ በቀብር ቤቶች፣ ያዘኑ ሰዎች ዘንድ እና ዘመዶቻቸው ጋር ተበትነው በጥገኛነት የሚኖሩ ካህናትና በስራቸው ያሉ ልጆቻቸው የከፋ መከራ ውስጥ ናቸው።

በስድስቱ ወራዳዎች በ350 ደብሮች ውስጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት “ኢትዮጵያዊ ነን ስላሉ ተሰደዋል። ኢትዮጵያ ስላሉ ታስረው” ያሉት ኃላፊው፣ በዚህ መልኩ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ መደረሱን አስረድተዋል።

በጥቅምት ወር በሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ጩኸታቸው በአጀንዳ እንዲያዝና ቋሚ መፍትሄ እንዲበጅ፣ እስከዛም ድጋፍ እንዲደረግ የተማጸኑት የራያ አገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ፣ “ይህን የምታነቡ ሁሉ እርዱን፣ ኢትዮጵያዊ ነን ያሉ ካህናት ከልጆቻቸው ጋር በስደት ወድቀዋል፤ ልጆቻቸውንም ማስተማር አልቻሉም” ሲሉ በመላው ዓለም ለሚገኙ ወገኖች ሁሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑ አባት፣ “ቤተክርስቲያን አቅም እያላት በዚህ ደረጃ ዝም ማለቷ ሊገባኝ አልቻለም። ገሃድ ወጥቼ ብናገር ርካሽ ተወዳጅነት ፍለጋ ይመስልብኛል። በጥቅምቱ ጉባኤ አይ እኔን መሰል አባቶች ስላሉ ጉዳዩን በርግጠኝነት እንዲነሳ አደርጋለሁ” በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

እንደ እኚሁ አባት ሌሎች አስተያየት የሰጡ እንደሚሉት እንኳን ካህኖቿን፣ ሌሎች የተቸገሩን በመርዳት የምትታወቅ ቤተክርስቲያን፣ ኃዋሪያዊ ተግባሯና መሰረቷ በጎነት የሆነ ቤተክርስቲያን መሪዎች ለዚህ ጥያቄ ዝምታን መመረጣቸው እንቆቅልሽ ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የራያ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆንትን ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስን በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር ደጋግመን በግል ስልካቸው በንደውል አላነሱም። በጽሁፍ መልዕክት “አባታችን ልጆችዎ ራበን እያሉ ነው። ላለፉት ዘጠኘ ወራት ምንም ዓይነት ክፍያ አላገኙም። እባክዎን ስለሚመለከትዎ የበኩልዎን አስተያየት በመስጠት ይተባበሩን” በማለት ብንልክላቸውም መልስ አልሰጡም። በትኛውም ሰዓት አስተያየታቸውን ሊሰጡን ከፈቀዱ ልናካትት ፈቃደኞች ነን።

አቡነ ሳቢሮስ በርዳታ መልክ አንድ ጊዜ ስምንት መቶ ብር ከሰጡት በቀር ከላይ በተመለከተው አግባብ በችግር ላይ ላሉት ወገኖች መንግስትም ሆነ ቤተክርስቲያን ያደረጉት የተለየ ድጋፍ የለም። ከዚህ ስር በማህበራዊ ገጽ የተሰራጨውንና ችግሩን የሚያስረዳውን መረጃ እንዳለ አትመናል።

ስለ ራያ ካህናት ዝም አልልም!

፩. የሐዋርያዊት እምነት ጽናትና የዘመኑ ሰማዕታት ተጋድሎ

​የራያ ሀገረ ስብከት ከ500 በላይ ካህናት የቀደመችውን የሐዋርያት እምነት አፅንተው በመያዝ «ሃይማኖታችንን አንክድም! ለመንበረ ሰላማ አንሰግድም! ሲኖዶሳችንን አንከፍልም! አንድ ሲኖዶስ፣ አንድ መንበር!» በማለት በጽናት ቆመዋል።

​በተለይም በ2018 ዓ.ም የመስቀልና የጥምቀት በዓላትን «በሃይማኖት ከማይመስሉን ጋር አንወጣም» በማለት ከ13 በላይ ታቦታት ከቤተ መቅደስ እንዳይወጡ በማድረጋቸው ምክንያት የተከተለውን የመታፈን፣ የመደብደብና የእስራት መከራ ሁሉ በምስጋና የተቀበሉ፣ ሃይማኖታቸውን በሞታቸውና በደማቸው ያስከበሩ የዘመኑ አውነተኛ ሰማዕታት ናቸው። ስለ እውነት በያዙት አቋምም በመቀሌ፣ በማጨውና በመሆኒ እስር ቤቶች ሳይቀር ተሰቃይተዋል።

​፪. አሁን ያሉበት አሳዛኝ የሕይወት ሰቆቃ

​ዛሬ ግን እነዚህ ከ500 በላይ የሚሆኑ የእምነት አበው ከቀያቸው፣ ከቤተ መቅደሳቸውና ከተመደቡበት የሥራ መስክ ተፈናቅለው፡

​ትዳራቸውና ልጆቻቸው ተበታትነው፣ ህፃናት ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ተለይተው፣

​በቆቦ፣ በወልድያና በሰቆጣ በየበረንዳውና በየመቃብር ቤቱ በመጠለል ለአንድ ዓመት ሙሉ በከባድ ሰቆቃና እንግልት ውስጥ ይገኛሉ።

​ይህ ሁሉ መከራ እየደረሰባቸው ቢሆንም፣ እስካሁን በመንግሥት የተወሰነ ድጋፍ ብደረግም በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ግን ምንም ዓይነት ድጋፍ አልተደረገላቸውም።

​፫. የመማፀኛ ጥሪና የድምፅ ድጋፍ

​ለቅዱስ ሲኖዶስ፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት ወር በሚያደርገው የርዕሰ አበው ስብሰባ ላይ የራያ ሀገረ ስብከት ካህናት ጉዳይ ተቀዳሚ አጀንዳ እንዲሆን፣ አጣዳፊ ሰብአዊና መንፈሳዊ መፍትሔ እንዲበጅላቸው፣ እንዲሁም ወደ አገለገሉበት ቤተ መቅደስ እንዲመለሱ ውሳኔ ይሰጥ ዘንድ እንጠይቃለን።

​በውጭና በሀገር ውስጥ ላለው ማህበረሰብ፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የምትኖሩ ምዕመናን ሁሉ፣ ከእነዚህ ምስኪን አባቶችና ከተበታተኑ ቤተሰቦቻቸው ጎን በመቆም በጸሎት፣ በገንዘብና በቁሳቁስ የተቻለንን ሁሉ በማድረግ አለኝታ እንድናሆናቸውና ድምፅ እንድንሆናቸው በፈጣሪ ስም እንማፀናለን!

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ስምረት ከኋላቀር ቡድን ባህሪ ጋር ተያይዞ የመጣ ድርጅትን የማፍረስ እንቅስቃሴ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ አለ፤ የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሯል

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — የትግራይ ዴሚክራሲያዊ ስምረት ድርጅት በውስጡ...