የኤርትራ ብ.ባንክ አዋጅ እና “ጽምዶ” የወለደው የፎርጅድ ናቅፋ መዘዝ “ኤርትራ የናቅፋ ስርጭትን የምታውቅበት ዲጂታል ስርዓትና ኤቲኤም የላትም ህዝቡ ብሩን ካስገባ በኋላስ?”

Date:

“የሚገርም እኮ ነው። ኢንተርኔት የሌለበት አገር፣ ስማርት ስልክ በወጉ የማይሰራባት አገር፣ የቀላል ገንዘብ መቀባበያ ወይም መክፈያ መተገበሪያ የሌላት አገር፣ ኤቲኤም የሌለበት አገር እንዴት ነው ብራሁን በሙሉ አስገቡ ብሎ የሚያዘው? ስው እንዴት ዳቦ ይግዛ? ምን እያደረጉ፣ ምን እያሰቡ፣ ወዴት እየወሰዱን እንደሆነ አይገባኝም። ሰውየው ጃጅቷል” የሚለው ሃያ ሁለት ማዞርሪያ ከጓደኞቹ ጋር ቁጭ ብሎ ያገኝነው ሃብቶም ነው። ሃብቶም “መቼ የኤርትራ ህዝብ ብሩን እንደፈለገ ተጠቅሞ ያውቃል? ቤቱስ ያስቅምታል? ለድግስ እንኳን ተቆንጥሮ ነው የሚሰጠው” ሲል ያክላል።

አዲስ ሪፖርተር ዜና – አንድ አዋቂ ሰው በአማካይ ከ 4.5 እስከ 5.5 ሊትር ወይም የጠቅላላ የሰውነት ክብደቱ 7% ገደማ የሚሆን ደም በሰውነቱ ውስጥ አለው። ከዚህ ደም ውስጥ ሁለቱ ሊትር ቢጎድል ያ ሰው ለሕይወት አደገኛ የሆነ ሁኔታ (Severe Shock ወይም Coma) ውስጥ እንደሚገባ የሚያስረዱት እውነታዎች፣ ለኤርትራ ብሔራዊ ባንክ “ብር ሰብስቡ” አዋጅ አግባብ ያለው ምሳሌ ያደርጉታል።

ኤርትራ እጅግ አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር ስላላት የምታተመውም የመጠቀሚያ ገንዘብ (ናቅፋ) አነስተኛ ነው። ከዚህ አነስተኛ ገንዘብ ላይ ልክ እንደ ደሙ ሲጎድል፣ የሀገሪቱን “በውል የማይታወቅ ነው” የሚባለውን ኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ ያናጋዋል።

በኤርትራ በአሁኑ ወቅት የኤቲኤም (ATM) ካርድ አገልግሎትም ሆነ አውቶማቲክ የገንዘብ ማውጫ ማሽኖች የሉም፤ በኤርትራ ያለው መንግሥት የሀገሪቱን የገንዘብ ፍሰት የሚቆጣጠረው በዲጂታል ሲስተም ሳይሆን በጠንካራ የመንግሥት አስተዳደራዊ ሕጎችና በእጅ በሚሰሩ (Manual) አሠራሮች በመሆኑ፣ ከባንክ ውስጥ ክምችቱ መመናመኑን እንጂ ብሩ የት እንዳለ የሚያውቅበት አንዳችም ዘዴ የለውም። በቅርቡ አቶ ጌታቸው እንዳሉት “የመንግሥትነት ቅርጽ የሌላት አገርና በሕዝብ ቁጥር ተመናምና በመፍረስ ላይ ያለች” የምትባለው ኤርትራ፣ በተለያዩ ወቅቶች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ገብታ እንደነበር አሁን በስደት በዱባይ የሚኖረው የቀድሞ የሻዕቢያ አባል ይናገራል።

የናቅፋ እጥረት ታሪካዊ ማሳያና የአሁኑ መንስኤ

“ሰላምም ጦርነትም ያልነበረበት ዘመን” በሚባለው የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት ወቅት፣ ሕወሃት በድንበር አካባቢ ሽያጭ በመፈጸም ከፍተኛ ናቅፋ በመሰብሰብ የኤርትራን መንግሥት አቀዝቅዞት አስመራ በመገበያያ እጥረት ታውካ ነበር። ይህንን የሚያስታውሱት የዱባዩ ነዋሪ፣ እሳቸው ባላቸው መረጃ አሁን ላይ በሁለት ምክንያቶች ናቅፋ ጣጣ ውስጥ ገብቷል።

የኤርትራ ብሔራዊ ባንክ ማንኛውም ዜጋም ሆነ ተቋም በእጃቸው የሚገኘውን ጥሬ ገንዘብ እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ወደ ባንክ እንዲያስገቡና የባንክ ሂሳብ የሌላቸው ዜጎች በበኩላቸው መታወቂያቸውን በመያዝ በአስቸኳይ እንዲከፍቱ ያስተላለፈው አስገዳጅ መመሪያ፤ በሀገሪቱ የፋይናንስ ሥርዓት ላይ የተጋረጠውን ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እና በብዛት ተረጨ የተባለውን የፎርጅድ (የሕገ-ወጥ/ሐሰተኛ) ገንዘብ ስርጭት ለመግታት የታለመ መሆኑን ይገልጻሉ።

ቢቢሲ እንዳለው ባንኩ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ ከባንክ ውጪ ከፍተኛ ጥሬ ገንዘብ መያዝ የተከለከለ መሆኑንና ማንኛውም ግብይት በናቅፋ ብቻ መከናወን እንዳለበት አሳስቧል። ትዕዛዙ በእጅ ያለ ናቅፋ ወደ ባንክ እንዲገባ፣ ግብይቱም በናቅፋ ብቻ እንዲሆን ከማዘዙ ውጭ “ይህ ነው” ብሎ ያስረዳው ምክንያት የለም።

ዜናውን የሰሙ ከአገሪቱ የግብይት ሥርዓት በስተጀርባ ትልቅ የደኅንነትና የኢኮኖሚ ቀውስ መኖሩን አመላካች እንደሆነ የሚናገሩ ተስተውለዋል። ይህን የሚሉ ወገኖች በእነ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የሕወሃት አንዱ ፍንካች ደጋፊ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች፣ “ትግራይ በናቅፋ ለመጠቀም ዝግጅቷን አጠናቃለች፣ በምጽዋና አሰብ የወደብ አገልግሎት ተፈቅዷል” በማለት በገሃድ ሲያሰራጩ የነበረውን መረጃ ከኤርትራ አዲስ አዋጅ ጋር ያያይዙታል።

የምስጢር ስምምነቱና የሐሰተኛ ገንዘብ ስርጭት ተጽዕኖ

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የደኅንነትና የፋይናንስ ምንጮች ለአዲስ ሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለዚህ አስቸኳይ ውሳኔ መነሻ የሆነው በትሕነግ እና በአስመራ ለሚገኙ ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል የፌደራሉን መንግሥት ለመውጋት የተደረገው ምስጢራዊና ሕገ-ወጥ የጦር ኃይሎች ጽምዶ ጥምረት ተከትሎ ሕወሃት በውጭ ምንዛሬ ናቅፋ ገዝቷል።

ላይ ላዩን “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት” የሚባለውን ጽምዶ ተከትሎ በድንበር አካባቢዎች ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድና በናቅፋ መገበያየት መጀመሩን የሕወሃትና የሻዕቢያ ደጋፊዎች በገሃድ ሲናገሩ እንደነበር፣ ዜናው የፌደራል መንግሥትን ግራ እንዳጋባው፣ ሂደቱ ጅማሬ እንጂ ወደ ቀጥተኛ የኢኮኖሚ ትስስር እንደሚያመራ እያስታወቁ ባለበት ወቅት ከኤርትራ የወጣው ዜና ሌላ ጉዳይ አስነስቷል። የዱባዩ የቀድሞ የሻዕቢያ ሰላይ እንደሚለው ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም በትግራይ ክልል የሚገኙ ሕገ-ወጥ መረቦችና የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ፎርጅድ የናቅፋ የገንዘብ ኖቶችን በስፋት ገበያው ላይ መርጨታቸውን አመልክቷል።

የኤርትራ መንግሥት ለሕወሃት የሸጠው ናቅፋ ከፎርጅድ ጋር ተቀላቅሎ በኤርትራ ገበያ ውስጥ መረጨቱ ከፍተኛ ቀውስ በማስከተሉ፣ ኤርትራ ምንም ዓይነት የብር ስርጭትን መቆጣጠሪያ ሲስተም የሌላት አገር በመሆኗ በሰዎች እጅ ያለውን ናቅፋ በአዋጅ መሰብሰብ ግድ ሆኖባታል። እነዚሁ ወገኖች እንደሚጠቁሙት፣ ትሕነግ በዶላር ከገዛው ሕጋዊ የኤርትራ ናቅፋ በተጨማሪ፣ ማዕከላዊ ባንኩ ከሚያውቀው በላይ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሐሰተኛ ናቅፋ ታትሞ እንዲገባ በመደረጉ የኤርትራን መንግሥት ይህንን አዋጅ ከማወጅ የዘለለ ሌላ ሊያደርግ እንደማይችል አመልክተዋል።

የባለሙያዎች እይታና የፋይናንስ ቀውሱ መፃኢ ዕድል

አቶ ጌታቸው ረዳ “የሚጨበጥ ኢኮኖሚና የመንግሥት ቅርጽ የላትም” በማለት በቅርቡ አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሕዝብ ብቻ እንዳላትጠቅሰው እየሟሟች ነው ያሏት ኤርትራ፣ የፎርጅድ ገንዘብ ስርጭት እያደረሰ ያለው ቀውስ ዘርፈ ብዙ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለወትሮውም በጨለማ ውስጥ ለነበረውና በሳይንሳዊ መለኪያዎች ለማይለካው የኤርትራ ኢኮኖሚ ክፉኛ አደጋ እንደሆነ ያስረዳሉ። ግሽበት ኤርትራ አሁን ባለችበት ሁኔታ ደሙ ከውስጡ እንዳለቀ ሰው ምሳሌ እንደሆነም አመልክተዋል።

ዋና ዋናዎቹ የፋይናንስ ቀውሶች መካከል ካለ ምንም የኢኮኖሚ ምርታማነትና ያለ ማዕከላዊ ባንኩ ዕውቅና ከፍተኛ መጠን ያለው የሐሰተኛ ገንዘብ ወደ ገበያ መግባቱ፣ የናቅፋን እውነተኛ የመግዛት አቅም እያዳከመውና የዕቃዎች ዋጋ በአስመራ ገበያ የማይጨበጥ ያደርገዋል።

ሻዕቢያ አዲስ አበባና በውጭ አገር ባሉት ወኪሎቹ አማካይነት ከኢትዮጵያ ብር በኮንትሮባንድ እየሰበሰበ፣ የጥቁር ገበያን ዋጋ በማናር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ነዳጅ ሲያርከፈክፍ መኖሩ፣ አሁንም ይቀንስ እንጂ አዲስ አበባም ሆነ በውጭ አገር በገንዘብ አጠባ የሚሰሩለት ኤጀንቶች እንዳሉት የሚገልጹ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር በመሆኗ ተቋቋመች እንጂ የኢኮኖሚ ግዝገዛው ዓላማ ሌላ ነበር።

እውነተኛውና ሕጋዊው የናቅፋ ኖት በሐሰተኛው ገንዘብ እየተዋጠ በመምጣቱና ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ገንዘቡን ከባንክ ውጪ ስለሚያንቀሳቅሱት፣ መደበኛው የኤርትራ የባንክ ሥርዓት ከፍተኛ የፈሳሽ ገንዘብ እጥረት ማጋጠሙን የሚያመለክተው የዱባዩ ነዋሪ፣ እሱ ባለው መረጃ ሻዕቢያ ቀደም ሲል እንዳደረገው የብር ለውጥ ያደርጋል። ለዚህም ከፍተኛ ወጪ ያወጣል። ይህ ሲሆን ሕወሃት የገዛው ናቅፋ ዕድሉ ወደ ወረቀትነት መቀየር ይሆናል።

የኤርትራ መንግሥት በቀጣዮቹ ቀናት ጥብቅ የጊዜ ገደብ ያስቀመጠው፣ በዚህ በሕገ-ወጥ ስምምነቶችና በፎርጅድ ገንዘብ ሳቢያ የመጣውንና የሀገሪቱን ሕልውና የፈተነውን የፋይናንስ ቀውስ ለመቀልበስ መሆኑን የሚጠቁሙት ክፍሎች፤ የኤርትራ ብሔራዊ ባንክ በትዕዛዙ ላይ በሚያምፁና እጃቸው ላይ ያለውን ናቅፋ ወደ ባንክ በማያገቡ አካላት ላይ ጥብቅ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ይህንኑ ዜና ተከትሎ ሕወሃት የገዛውን ናቅፋ ተመላሽ ስለማድረጉ ቀደም ሲል ዜናውን ካሰራጩት አካላት የተሰማ ነገር የለም።

ቀደም ሲል አቶ መለስ በድንገት ብር እንዲቀየር በማድረጋቸው ሳቢያ ሻዕቢያ ወረራ ፈጽሞ በኢትዮጵያውያን ኅብረት በዘመቻ ፀሐይ ግባት መመታቱ አይዘነጋም። አሁንም ሕወሃት በሚሊዮን ዶላር አውጥቶ የገዛውን ናቅፋ ተሸክሞ ይቀመጣል ወይስ ምን የመፍትሔ አማራጭ ይፈልጋል የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።

ከኤርትራ መንግሥት ጋር የሚሰሩ ሚዲያዎችና የተቃዋሚ ድርጅቶች ወኪሎች፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዘወትር የሚተቹ በውጭ አገር ያሉ ባለሙያዎች ይህ እስከተጻፈ ድረስ በይፋ ማብራሪያ ሲሰጡ አልተሰማም። የኤርትራ መንግሥት ይህንን ውሳኔ የወሰነው ኢኮኖሚውን “ለማረጋጋትና ለመቆጣጠር” በሚል እሳቤ ቢሆንም፣ በተግባር ግን በነጻ ገበያ እና በዜጎች የመግዛት አቅም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እጅግ ከባድ ነው። ከምንም በላይ ስጋቱ ቤርትራ ኤቴኤም የለም። በስልክ የፈጣን ገንዘብ መቀያየሪያ ወይም ክፍያ መፈጸሚያ ሲስተም የለም። በግል ስልክ ኢንተርኔት መጠቀም አይቻልም። ይህ ባልተሟላባት ጨለማዋ ኤርትራ ህዝብ ያለውን ለቃቅሞ ባንክ ካስገባ እንዴት ይገበያያል? የሚለው በውጭ አገር የሚኖሩ ስደተኛ ኤርትራዊያኖችን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ጄኔራሉ የገለጹት ሚስጢር – በቤኒሽንጉል በኩል ኢትዮጵያን የመብላት አጀንዳና የ”ሱዳን ለምን ተነካች”

አዲስ ሪፖርተር - ከሱዳን አቅጣጫ ለቅሶ ይሰማል። ለቅሶው የአንድ...

በትብብሩ ውስጥ የሚሰማው “ውዥንብር” በአጭሩ “እሰሩንና አጀግኑን” ነው “እስር ሲያምራችሁ ይቅር”

"ልብ ላላችሁ እውነቱ ይህ ነው። ብዙ ዝርዝርም አለ። "መጀመሪያ...

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ደህንነት ሲባል የአስመራውን አምባገነን መንግስት ለመጣል ቀናት አይፈጅም፤

አዲስ አበባ (አዲስ ሪፖርተር) — የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ያለው...