የቂርቆስ ክፍለ ከተማ “ሳያስፈቅዱ በቢሮ ውስጥ ድምጽ ሲቀዱ ተገኙ” ያላቸውን ወ/ሮ ብሌን ዓይኑን በሕግ ሊጠይቅ ነው፤ የቀረበባቸው አቤቱታ ለሕግ ተመራ

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና – የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወ/ሮ ብሌን ዓይኑን በሕግ ለመጠየቅ በጸጥታ ግብረኃይሉ አማካይነት ለጊዜው ይፋ ያላደረገውን ሥራ መጀመሩን አስታወቀ። ኃላፊዎችን ሳያውቁ ድምጻቸውን በመቅረጽ ለማኅበራዊ ሚዲያ ፍጆታ ማዋልና ለማስፈራራት መሞከር እየተለመደ መምጣቱን የጠቆሙት ኃላፊዎች “ይህ መሰሉ ተቋምን የመዳፈርና የሰዎችን መብት የመተላለፍ አካሄድ በቀላሉ አይታለፍም” ብለዋል።

የምስጋና እና ብሌን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ባለድርሻ የሆኑት ወ/ሮ ብሌን በቀረበላቸው የሠራተኞች ደሞዝ መክፈያ ሰነድ ወይም ፔይሮል ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ ሠራተኞች “በረሃብና በቤት ኪራይ አለቅን” በማለት ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ጽ/ቤት አቤቱታ አቅርበው ነበር።

በዚሁ መነሻ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 141 እና 142 በሚያዘው መሠረት በድርጅቱ እና በድርጅቱ ሠራተኞች መካከል የደመወዝ መዘግየት ምክንያት የተፈጠረውን መጉላላት በጋራ ለመፍታት ሐምሌ 06/2018 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 እሰከ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር 2ኛ ፎቅ ሥራ እና ክህሎት ጽ/ቤት አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ቢሮ በላይ በተገለጸው ቀን እና ሰዓት እንድትገኙልን ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” የሚል ደብዳቤ ለንግድ ድርጅቱ ሥራ አስኪያጅና ባለአክሲዮን አቶ ምስጋናውና ወ/ሮ ብሌን ደብዳቤ ይላክላቸዋል።

ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ጽ/ቤት በቁጥር ቂ/ክ/ከ/ስ/ክ/ጽ/ቤት/001/18 በቀን 03 / 11 / 2018 ዓ.ም “ለምስጋና እና ብሌን ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር” በሚል ርዕስ “ጉዳዩ፦ ለውይይት እንድትገኙልን ስለመጠየቅ” በሚል ሐምሌ 6 ቀን በላከው ደብዳቤ መሠረት ሦስት የሠራተኛ ተወካዮች፣ አቶ ምስጋናውና ወ/ሮ ብሌን “ወኪሌ፣ ጠበቃዬና አማካሪዬ” ካሏቸው አቶ ቴዎድሮስ ታዬ ጋር በመሆን ሰዓት አክብረው ይገኛሉ።

የኢንዱስትሪ ሰላምና የሙያ ደህንነት፣ ጤንነት ቡድን መሪው አቶ ተሸዋል መንግሥቱ ለአዲስ ሪፖርተር እንዳሉት ከሆነ ወ/ሮ ብሌን በሕግ የሚያስጠይቀውን ጥፋት የሠሩት ከሳቸውም ሆነ ከባልደረባቸው እውቅናና ፈቃድ ውጪ ነው።

“የተጣሰው ሕግና የሰዎች መብት ነው። የተደፈረው ተቋም ነው” ያሉት የቡድን መሪው፣ ወ/ሮ ብሌን ደብቀው እሳቸውም ሆነ በቢሮ የተጠሩት ሲናገሩ ይቀዱ እንደነበር ያጋለጠቻቸው አንድ ሠራተኛ ስትሆን፣ አቶ ምስጋናም “እየተቀዳችሁ መሆኑን ታውቃላችሁ?” በማለት በጥያቄ መልክ አቅርበዋል።

አስከትለዋቸው የመጡት ሰው ወኪል፣ ወይም ጠበቃ ወይም ሕጋዊ አማካሪ ለመሆናቸው ሲጠየቁ ምንም ዓይነት ማስረጃ ማሳየት እንዳልቻሉ ያመለከቱት የቡድኑ የቁጥጥር ባለሙያ አቶ ጤናው “ወ/ሮ ብሌን መስመር የሳተ አካሄድ የጀመሩት ይህንን ሕጋዊ ጥያቄ ሲጠየቁ በሚሰጡት በመረጃ ሊደገፍ ያልቻለ ምላሽ ነበር” ሲሉ አመልክተዋል።

“ጉዳያችን የሠሩበትን የወር ደመወዝ የተከለከሉት ሠራተኞች እንጂ ሌላ ባለመሆኑ ውይይቱን ለማስቀጠል ስንሞክር እሳቸው ድምጻችንን ይቀዱ ነበር” በማለት አቶ ጤናው፣ ቀደም ሲል ጀምሮ በመረጃና ማስረጃ ሊደገፍ ያልቻለ፣ እሳቸው ከሸሪካቸው አቶ ምስጋና ጋር ላላቸው የፍርድ ቤት ጉዳይ የሚረዳ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው ጠይቀው መከልከላቸውን አስታውሰዋል።

አቶ ምስጋና በንግድ ማኅበሩ ሥር ካለው ባለኮከቡ ዳቮር ሬስቶራንት ሠራተኞች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደሌላቸው ተደርጎ እንዲጻፍላቸው ላቀረቡት ጥያቄ መረጃ ሊቀርብ ባለመቻሉ ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ያመለከቱት አቶ ጤናው፣ በድጋሚ ወ/ሮ ብሌን የተጠሩት ሠራተኞች ደሞዝ አልተከፈለንም በማለት ባቀረቡት ማመልከቻ መነሻ ሆኖ ሳለ፣ ከተጠሩበት አግባብ ውጪ የሕግ ጥሰት መፈጸማቸውን አመልክተዋል።

አቶ ተሸዋል በበኩላቸው “እኛ በክስና በጭቅጭቅ ጊዜ እየባከነ ሠራተኞች እንዳይጎዱ የማስማማት ሥራ እየሠራን እያለ፣ የፈጸሙት ሕግ ያልተከተለ አካሄድ ምን ተማምነው እንደሆነ ሊጣራ ይገባዋል የሚል አቋም ተይዟል” ብለዋል። አክለውም በምክትል ሥራ አስፈጻሚ ደረጃ የሚመራውን ተቋም በዚህ ደረጃ ማናናቃቸው አግባብ ባለመሆኑ ወዲያውኑ ተቋሙ ውስጥ ያሉ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር አውለዋቸው እንዲያጣሩ ስልክ መደወላቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል “ቃል ጉባኤ እየያዝኩ ነው። ምን ችግር አለው?” በማለት ይዘዋቸው ከመጡት ሰው ጋር ሲከራከሩ የነበሩት ወ/ሮ ብሌን ፖሊስ ከመድረሱ በፊት ተጣድፈው በመውጣት ቢሮውን መልቀቃቸውን በስፍራው የነበሩ ለአዲስ ሪፖርተር ገልጸዋል።

“ለጊዜው ዝርዝር ጉዳዩን መግለጽ አያስፈልግም። ሥራ አስፈጻሚው ያሉበት የክፍለ ከተማው የጸጥታ፣ የደህንነትና የፖሊስ ግብረኃይል ጉዳዩን ይዞ እየመረመረው ነው። ጉዳዩ የመብትና የሕግ ጥሰት በመሆኑ የሚሆነውን ወደፊት ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

በአካላዊ ግንኙነትም ሆነ በስልክ ጥሪ ወቅት የአንድን ሰው ድምፅ ያለ እሱ እውቅና እና ፈቃድ መቅረጽ የግለሰቡን መብት የሚጥስ ከመሆኑም በላይ፣ ድርጊቱ በወንጀል ሕግ ሊያስቀጣ ይችላል። በተለይ የተቀረጸውን ድምፅ ማሰራጨት ወይም ሌላ ሰውን ለመጉዳት መጠቀም የወንጀል ተጠያቂነቱን በእጅጉ ያከብደዋል።

የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 26 ማንም ሰው የግል ሕይወቱ፣ ቤተሰቡ፣ መኖሪያ ቤቱ እንዲሁም የመልዕክትና የመገናኛ ግንኙነቶቹ የመከበር መብት እንዳለው ይደነግጋል። ያለ ግለሰቡ ፈቃድ ድምፅ መቅረጽ ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ የግል ሕይወት የመከበር መብት የሚጥስ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

የኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ (Criminal Code) የግል ምስጢርን መጋፋትንና ያለፈቃድ መቅረጽን በወንጀልነት ይቀጣል። በሕገ-ወጥ መንገድ መቅረጽ (አንቀጽ 604/605 እና ተያያዥ አንቀጾች) የአንድን ሰው የግል ንግግር፣ ስልክ ወይም ግንኙነት ያለ እሱ ፈቃድ መቅረጽ፣ ማዳመጥ ወይም ማስተላለፍ በወንጀል ያስጠይቃል። ቅጣቱ እንደ ድርጊቱ ክብደት እና እንደ አውዱ (ለምሳሌ የተቀረጸውን ድምፅ ለሌላ ሰው ማጋራት፣ ማሰራጨት ወይም ሰውን ለማስፈራሪያነት/ለማዋረጃነት መጠቀም) እንደ ጥፋቱ አግባብ እንደሚያስቀጣ የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አቶ ጤናው የሰዎችን ድምጽ እየቀዱ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ማሰራጨትና ማስፈራራት አሁን ላይ የተለመደ በመሆኑ፣ ይህም ድርጊት ከዚህ የተለየ ዓላማ ይኖረዋል ብለው እንደማያስቡ አመልክተዋል።

አቶ ተሸዋል ደሞዝ የተከለከለ አንድ ሾፌር ከነልጆቹ አከራዮቹ አባረውት ሜዳ ላይ መውደቁን አመልክቶ፣ “እኔን ዕረፍት የሚነሳኝ ይህ መሰሉ ችግር ነው። ከዚያ የዘለለው ማን አለብኝነት በሕግ መልስ ያገኛል” ሲሉ በታዘቡት ማዘናቸውን አስታውቀዋል።

ሠራተኞቹ ወ/ሮ ብሌን በያዙት አቋም ሳቢያ ደመወዛቸው ሊከፈላቸው ባለመቻሉ ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄዱ ምክር መሰጠቱን አቶ ጤናው አስታውቀዋል። ፍርድ ቤት ማብራሪያ ከጠየቀ ትክክል ነው ብለው የሚያምኑበትን አስተያየት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ የፍርድ ቤት ሂደታቸውን ለማስጀመር የውክልና ሥራ እየሠሩ መሆኑን ለአዲስ ሪፖርተር ገልጸዋል። ወ/ሮ ብሌን በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡ ቢደወልላቸውም አልመለሱም።

በሌላ አቤቱታ ወ/ሮ ብሌን ከእህታቸው ጋር በሽርክና የከፈቱት አዶር አዲስ ሆቴል በድንገት በመዘጋቱ በርካታ ሠራተኞች ደሞዝ ከተከለከሉ ወር ከሁለት ሳምንት እንደሆናቸው አመልክተዋል። ንብረትነቱ የኢትዮጵያ መካነ ኢየሱስ ኮሚሽን የሆነው ሕንጻ ያልተከፈለ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ ሳቢያ የድርጅቱ የሒሳብ አካውንት መታገዱን መረጃዎች ያስረዳሉ። በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ሪፖርተር ወ/ሮ ብሌንን በማነጋገር ሰፊ መረጃ ይዞ ለመቅረብ ይሞክራል።

ባለፈው ሳምንት 50 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ግብር የሚከፍል ድርጅት እንዴት “የፍትህ ያለህ” ጩኸት ተሰማበት በሚል ርዕስ የጉዳዩን መነሻ ጭብጥ ለማሳየት ሰፊ ሃተታ ማተማችን አይዘነጋም።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

የዘመን ክስተት አደዋና የምክክር ኮሚሽኑ ጥሪ!! ፓርቲም፣ መንግሥትም፣ ሰዎችም ያልፋሉ፤ ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች!

አዲስ ሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ - “...አንድ የአፍሪካ አገር በአውሮፓ...

50 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ግብር የሚከፍል ድርጅት እንዴት “የፍትህ ያለህ” ጩኸት ተሰማበት

አዲስ ሪፖርተር ዜና - የዚህ ሪፖርት አቅራቢ ወደ ሬስቶራንቱ...

ትህነግና ሻዕቢያ በጋራ የተቃውሞ መግለጫ አወጡ፤ “ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት አትፈቅድም”

አዲስ ሪፖርተር - በመጥረቢያው ብረትና በእንጨቱ እጀታ የተሳሉት ሻዕቢያና...