ADDIS REPORTER | አዲስ ሪፖርተር July 29, 2026| ዋናው ስብሰባ ከመጀመሩ ለተወሰኑ ደቂቃዎች መረጃ ለመለዋወጥ ሲፈቀድ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦላ) ቃል አቀባይ አቶ ጅሬኛ ቅድሚያውን ወስደው “እነ ጃዋር ያካሄዱትን የበይነ-መረብ ስብሰባ ብዙ ሺህ ህዝብ ተከታትሎታል፤ ይህ የሳምንቱ ትልቅ ዜና ነው” በማለት ይናገራሉ። ኢንጂነር ሙሉጌታ ቀበል አድርገው “ይህ ምን ትልቅ ዜና ነው? ሁሉም ሌቦች ናቸው፤ አቶ አባይም ያውቃል” በማለት አናንቀው ይመልሳሉ።
ኢንጂነር ሙሉጌታ አክለውም “አቶ አባይ ግደይ ያውቃል፤ የመንግስት እጅ አለበት” ሲሉ የሌባ ስብስብ እንደሆነ የጠቆሙትን የእነ ጃዋርን ስብስብ አጥብቀው አራከሱ።
ኤርሚያስ ዋቅጅራ ይፋ ባደረገው ሰነድ ጃዋር መሐመድ አሜሪካ ኤርፖርት ውስጥ በጸጥታ ኃይሎች ተያዞ በነበረበት ወቅት ከአሸባሪ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንዳለው ተጠይቆ፣ “አዎ፣ የተወሰነ ግንኙነት አለኝ፤ የሰዎችና የመሳሪያ ዝውውር ላይ እንደሚሰሩ፣ እገታና አፈና እንደሚፈጽሙ አውቃለሁ” በማለት ምላሽ መስጠቱን መረጃውን የሰጡት አካላት አስታውሰዋል። በዚህና በሌሎች ጉዳዮች በጃዋር ላይ የቀረበውን ሰነድ አስመልክቶ በህግ እንደሚጠይቅና ጠበቃው ጉዳዩን ይዞ እየሰራበት መሆኑ ከመገለጹ ውጪ፣ ይህ እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ አስተባባሪዎቹ አላስተባበሉም።
የኢንጂነር ሙሉጌታ መነሻ ይህ ጃዋር የተከሰሰበት ጉዳይ ይሁን ወይም በይፋ ያላስታወቁት ሌላ ምክንያት፣ ራሱን “የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የጋራ የትግል መድረክ” በሚል ስያሜ የሚጠራው ስብስብ ሰኞ ዕለት ሊያደርግ ያሰበው ውይይት በዚሁ የቃላት ጦርነት ሳቢያ ተበትኗል።
የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ዘጋቢ እንዳለው፣ አቶ ጅሬኛ ከዚሁ ጋር አያይዘው ኃይለ-ቃል በተሞላበት አግባብ ዶክተር አክሎክ ቢራራና አቶ መስፍንን ጠቅሰው ኮንነዋል።
ባለፈው ሳምንት “ጦርነት አይቀሬ ነው። ድሮን በመፍራት በጋማ ከብት ሎጂስቲክስ እያጓጓዝን ነው” ያሉት አቶ አባይ ግደይ (በብዛት ከሱዳን አርሚ አባላት ጋር እንደሚመላለሱ ይነገራል)፣ “ጦርነት አያስፈልግም። ሕዝብ ይጠብቀናል። አንድ መሆን አለብን…” በማለት ሲናገሩ፣ አቶ ጅሬኛ “ስቴት ዲፓርትመንት ሄደው አማራና ኦርቶዶክስ እያሉ ከሚያለቅሱ ጋር እንዴት አንድ እንሆናለን?” በማለት የራሳቸውን አጀንዳ ከማራመድ ውጪ ሌላ ፍላጎት እንደሌላቸው ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት የአማራ ወኪሎች ጠቅሰው ከሰሱ።
በዚህ ጊዜ አቶ አባይ “አቶ ጅሬኛ ትክክል ነህ። ይህን ሰምተን እኛም ቅር ተሰኝተናል። ትክክል ባለመሆኑ ሰው ልከናል” በማለት ድጋፋቸውን ሰጥተዋል። አቶ አባይ “ከእንግዲህ በኋላ ንግግር የለም” በማለት ትህነግ ወደማይቀረው ጦርነት ለመግባት ተጠባባቂ ኃይል እያዘጋጀ መሆኑን አመልክተው እንደነበር የሚታወስ ነው።
ራሱን “የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የጋራ የትግል መድረክ” በሚል ስያሜ የሚጠራው ስብስብ ሁለት ዋና ጫፎች አሉት። አንደኛው በቀጥታ ከሻዕቢያ ጋር፣ እና በሻዕቢያ በኩል ከግብጽ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ጋር የሚገናኘውን መስመር የሚመራ ሲሆን፤ ሁለተኛው ጫፍ ደግሞ ከትህነግ ጋር የዘለቀ ወዳጅነት ያለውና በትህነግ የሚመራ ነው። ሌሎች ጥቂቶቹ ደግሞ የሁለቱ ኃይላት ፍጥጫና መጠባበቅ ያልገባቸው ናቸው።
አቶ ነዓምን የሚመሩት የሻዕቢያው ወገን፣ አቶ ልደቱና ፕሮፌሰር ሕዝቅዔል ገቢሳ የሚወዘውዙትና በውስጡ ባሉ የትህነግ ወኪሎች ምሪት የሚሰጠው ቡድን ባሉበት ስብሰባ ውስጥ ምንም ሳይገባቸው ሲከተሉ የነበሩ አባላት እየተንጠባጠቡ መሆኑን ጠቅሰን በተከታታይ መዘገባችን ይታወሳል።
ቁጥሩ እየተጓደለና የስብሰባ ቀን እያዘዋወረ የሚገናኘው ይህ መድረክ ከውጭ ኃይሎች ገንዘብ እንደሚያገኝ በመጠቀስ፣ “እናንተ ብር ታገኛላችሁ፣ እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤ መጠቀሚያ አታድርጉን” በማለት ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩ አሁን ላይ ከመድረኩ ተለይተው የራሳቸውን ቡድን እንደፈጠሩም አመልክተን ነበር።
በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ አለመስማማት ቢኖርም፣ እንደ ሰኞው ዓይነት የቃላት ጦርነት ተከሰቶ እንደማያውቅ የገለጹት የስብሰባው ተካፋይ፣ “የመድረኩ አባላት ቀድሞም አንድ የሚያደርግ ፕሮግራምም ሆነ መርህ የሌላቸው ናቸው” በሚል ሲቀርብ የነበረው ትችት አግባብነት ያለው መሆኑን የተመለከቱበት አጋጣሚ እንደነበር አስታውቀዋል።
“ከብልፅግና ጋር ከተዋጋን በኋላ አማራና ፋኖን እንበቀላለን” በማለት በትግራይ በተለያዩ ወረዳዎች በተጀመሩ የፕሮፓጋንዳ ስብሰባዎች ላይ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር የተናገሩትን በማስታወስ፣ የስብሰባው የቃላት ጦርነት የሚጠበቅ እንደነበር ዜናውን ያጋሩት ወገኖች አመልክተዋል።
“ከፋኖና ከሌሎች ኃይሎች ጋር የሚያገናኘን እነርሱን እንደ ፈረስ የመጋለብ ዓላማችን ብቻ ነው” በማለት ሞንጆሪኖ መናገራቸውን ተከትሎ፣ ለፋኖ ቅርብ የሆኑ አካላት ቅሬታቸውን እየገለጹና በእነ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ላይ ዘመቻ ለመጀመር ዝግጅት ላይ መሆናቸውም ታውቋል።
የትህነግ ከፍተኛ አመራርና የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር፣ የወቅቱ የጋራ ስጋት የተባለው አካል ከተወገደ በኋላ የአሸናፊዎች አሸናፊን ለመለየት ከሌሎች ተጣማሪ ኃይሎች ጋር ሌላ ዙር የኃይል ፍልሚያ እንደሚኖር ሲያስታውቁ ነበር ይህን ያሉት። ትህነግ በአሁኑ ወቅት ከፋኖ፣ ከኤርትራ መንግሥት (ሻዕቢያ) እና ከሌሎች የፖለቲካና የትጥቅ ስብስቦች ጋር ያለው ትብብር ታክቲካዊ እና የጋራ ጠላትን ለመጣል ብቻ ያለመ መሆኑን መግለጻቸውን ተከትሎ፣ በመድረኩ አባላት መካከል ያልፈነዳ ልዩነት መነሳቱንም የዜናው ምንጮች አመልክተዋል።
በስብሰባው ላይ የተነሳውን የቃላት ጦርነትና የጠላትነት ስሜት ከሞንጆሪኖ ንግግር ጋር በማያያዝ የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ ያስታወቁት ወገኖች፣ ስብሰባው መቀጠል ባለመቻሉ በዕለቱ ምንም ባልተነፈሱት በአቶ ነዓምን የጽሁፍ መልዕክት መነሻ አቶ ያሬድ ለረቡዕ ሌላ ስብሰባ እንደሚደረግ ገልጸው ስብሰባውን እንደበተኑት ለማወቅ ተችሏል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






