አዲስ ሪፖርተር – የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት መቀሌ ከተማ አቅራቢያ የድሮን ጥቃት እንደፈጸመ ሕወሃት አስታወቀ፤ ክልሉን በኃይል እያስተዳደረ ነው የሚባለው የትግራይ ክልል ባለስልጣናት ክሱን ያሰሙት ዛሬ ነው። ደረሰ ስለተባለው ጥቃት ከመንግስት ወገን ምንም የተባለ ነገር የለም። ከገለልተኛ ወገንም አልተረጋገጠም።
አንድ ተመልካች፣ እና የክልሉን ባለስልጣን ጠቅሶ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ እንዳለው የድሮን ጥቃቱ ያደረሰው ጥቃት ዝርዝር አልተገለጸም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው ምሞቱን ምስክሩ እንደነገሩት አመልክቷል። ከዛሬ ነገ ጦርነት እንደሚነሳ፣ ለጦርነቱ የሚያስፈልግ ዝግጅት መጠናቀቁና መሳሪያ በኤርትራ በኩል እየተጋጋዘ እንደሆነ እየተገለጸና የሳታላይት መረጃዎች ይህንኑ እያጋለጡ ባለበት ወቅት የተሰማው ዜና የውጥረቱ አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
በሸረሪና፣ በራያ ግንባር ሃለዋ የድሮን ጥቃት ስለመሰንዘሩ እንጂ ስለደርሰው ጉዳት ያላስታወቀው ህወሃት፣ በዚህም ጥቃት በተመሳሳይ ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጠም። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉል ከላሊ ሃጋዚን፣ የፌደራል ኃይሎች ከመቀሌ በግምት 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዳንደራ በተባለች መንደር ውስጥ ባለ የአርሶ አደሮች ማሰልጠኛ ማእከል ላይ ጠዋት በግምት 4:00 ገደማ የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመ አመልክተዋል። “ተፈጸመ” ስላሉት የድሮን ጥቃት ውጤት ባለስልጣኑ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዳልሰጡ ዘገባው አመልክቷል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአካባቢው ካህን ግን በጥቃቱ ቢያንስ አንድ ሰው መገደሉን ተናግረዋል። በድሮን ጥቃቱ የተወነጨፈው ሚሳኤል በአንድ ትምህርት ቤት አቅራቢያ መውደቁን መመልከታቸውን የተናገሩት ካህን “በጥቃቱ የተገደለ አንድ ታጣቂ በቁስለኛ ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ሲወሰድ አይቻለሁ” ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት አመልክቷል።
የድሮን ጥቃት ሲፈጸም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ይህ ሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ ይታወሳል። ህወሃት ጥቃቱ መድረሱን ጠቅሶ መግለጫ ሲሰጥ፣ ከፌደራል መንግስትም ሆነ ከአገር መከላከያ ምንም ዓይነት ምላሽም ሆነ ማስተባበያ አይሰጥም። ይሁን እንጂ ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ሚዲያዎችና የመንግስት ልሳኖች አልፎ አልፎ በዘጋቢ ፊልም ደረጃ ዘግበውታል። በዘገባቸውም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምርኮኞችና የተወሰኑ ቁስለኞች አሳይተዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






