አዲስ ሪፖርተር l መቀሌ — ከትግራይ የሚወጡ ዜናዎችና እማኞች የሚሰጡት ጥቆማ ሕወሓት የሲቪል ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ጣቢያዎችን እና የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ምሽግ፣ የመሣሪያ ማከማቻና የጦር ስንቅ ማደረጃና ማሰራጫ ማድረጉን የሚያረጋግጡ ናቸው።
“አካል ጉዳተኞችን ከፊት አሰልፎ የጥይት ማብረጃ ሊያደርግ አቅዷል” በማለት የሚናገሩት እማኞች፣ የጦርነት ቀጠና ሊያደርጋቸው ባሰባቸው አካባቢዎች ዕድሜ ሳይለይ ነዋሪዎችን በሌሊት ወረራ በመፈጸም ማፈሱንም አመልክተዋል።
በራያ ዓላማጣ የሚገኙ ነዋሪዎችና አርሶ አደሮች እንዳሉት ሕወሓት እንደገና በየቀበሌው የገንዘብና የቁሳቁስ መዋጮ በመጣል ሰላማዊውን አርሶ አደር እያንገላታ ነው። ግዳጅ የተጣለባቸው ቀበሌዎች 12 ሚሊዮን ብር እንዲሰበስቡና ገቢ እንዲያደርጉ የታዘዙ ሲሆን፣ የማይከፍሉት በነፍስ ወከፍ 5,000 ብር እንዲቀጡ ተነግሯቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አርሶ አደሮቹ ከጤፍ እስከ ማሽላ ያሉ የእህል ምርቶችን ለተዋጊዎች ስንቅ እንዲያቀርቡ፣ ለጭነት የሚያገለግሉ ግመሎች፣ አህዮች፣ በቅሎዎችና በሬዎችን ገዝተው ገቢ እንዲያደርጉ ታዘዋል።
የአካባቢዎችን ስም፣ ልዩ መጠሪያ፣ ተቋማትን ወዘተ ለይተው በመጥራት ሕወሓት ለጦርነት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነ የሚናገሩት የዓይን እማኞች፤ የፌደራል መንግሥት ከበባ እና የድሮን ጥቃት እያደረሰበት እንደሆነ የሚናገረው ሕወሓት፣ ዳግም ወደ ወታደራዊ ግጭት ለማስገባት በመረጣቸው አካባቢዎች የጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አመላክተዋል። ከትግራይ ወታደራዊ ምንጮች እንደተሰማው አዲስ ስምሪት እየተደረገ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ግንባሮች ስም የሚከዱት ተዋጊዎች ቁጥር ሥጋት ሆኗል።
እንደ መረጃው ከሆነ፣ ድርጅቱ በደቡባዊ ትግራይ ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰኑ አካባቢዎችን ለጦርነቱ ዝግጅት መርጧል። በተለይም በራያ ዓላማጣ አካባቢ የተደራጁ ታጣቂ ኃይሎችን እያሰማራ መሆኑን እማኞች አመልክተዋል። ለዝግጅቱ ቅርብ የሆኑ ምስክሮች እንዳሉት ከሆነ “አርሚ 31” የሚባለው ኃይል በተጠቀሰው አካባቢ መሰማራቱ ተገልጿል።
የዚሁ ስምሪት አካል የሆነው ሌላው የ“አርሚ 15” “ቀለበት” ክፍለ ጦር በዛታ አካባቢ እንደተሰማራ ዜናውን ካጋሩት ወገኖች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
በሰሜን ምዕራብ ዞን እንደባጉና ከተማ ከአዲገብሩ አቅጣጫ በሚወጣው ዋና መንገድ ተከትሎ ስምሪት ወስዶ የነበረው የ“አርሚ 11” ተዋጊዎች፣ ከዛሬ ነገ ጦርነት ይጀመራል በሚል ሥጋት የተነሳ ከቡድኑ እየተለዩ ወይም እየከዱ መሆናቸውን ለሕወሓት አመራሮች ቅርብ የሆኑ ወገኖች አመልክተዋል። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት መክዳትና መፍለስ በሕወሓት አመራሮችና ዋናዎቹ የጦር አዛዦች ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት ከሆነ ከራርሟል። የሠራዊቱ መክዳትም ሆነ የመክዳት አሳሳቢነት በገሃድ ከሕወሓት በኩል ሲገለጽ ተሰምቶ አያውቅም። ይሁን እንጂ በሸረሪና ግንባር የታየውን የምርኮኛ ብዛት የገመገመው ሕወሓት “ጦርነቱ ከተጀመረ ጦሩ ይፈርሳል” በሚል ሰሞኑን ግምገማ አድርጎ ነበር።
በኮረም ከተማ በደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ሕንፃ ውስጥ ይገኙ የነበሩ የ“አርሚ 26” የስታፍ አባላት ወደ ዓላማጣ ከተማ መግባታቸውና እንቅስቃሴዎችን ከቅርብ ርቀት ለመምራት በዝግጅት ላይ መሆናቸው ተገልጿል። ይህ ወደ ከተማ የሰረገ የሠራዊቱ አካል ራሱን በሕዝብ መገልገያ ተቋማት ውስጥ በመሸሸግ ከቀደመው ጦርነት የተረፈ መሠረተ ልማት እንዲወድም ዕቅድ መያዙ በስፍራው ሆነው የሚሆነውን ለሚከታተሉ ድርብ ሕዘን መሆኑ ተመልክቷል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የ“አርሚ 15” ሜካናይዝድ ወታደራዊ መሣሪያዎች በኮረም አካባቢ በሚገኙ ጤና ተቋማት ውስጥ መከማቸታቸውን የገለጹ እማኞች፤ የሀገር መከላከያ ስለሚያውቅ እርምጃ ቢወስድ ወይም በድሮን ቢያጠቃ “መንግሥት ጤና ተቋም አወደመ፣ ንጹሐንን ገደለ፣ ትምህርት ቤቶችን አቃጠለ” በሚል ሰበብ እንደሚያቀርብበት በመረጃ አስደግፈው ገልጸዋል። የሀገር መከላከያ ጥቃት እንዳያደርስባቸው መሣሪያዎቹ ጨርቃጨርቅ፣ ቅጠላ ቅጠል እንዲሁም ቆርቆሮ እንዲለብሱ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የአካባቢውን ስምና ዝርዝር መረጃ ጠቅሰው ያቀበሉ ዜጎች እንዳሉት፣ በደቡባዊ ዞን ዛታ ወረዳ፣ አዲስ መንደር ቀበሌ በሚገኘው የሕይወት ዛታ ብድርና ቁጠባ ሕንፃ ውስጥም በተመሳሳይ “አርሚ 15 ኮር 3” የሚባለው የጦር መሣሪያ ምድብተኛ ክፍል መመሸጉን ተናግረዋል። በኮረም ከተማ ቀበሌ 02 የሚገኘው መስኮተ ብርሃን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት “አርሚ 15” እና “አርሚ 22” ተብለው የተጠቀሱ ታጣቂዎች የጦር መሣሪያና ሎጂስቲክስ ማዕከል አድርገው እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ከነዚሁ ወገኖች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል።
በሲቪል መገልገያዎች፣ በተለይም በትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት ውስጥ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መኖሩ ለሰላማዊ ነዋሪዎቹ ከፍተኛ የደኅንነት ሥጋት እንደሆነባቸው ዜናውን ያቀበሉ ወገኖች አስረድተዋል።
ዜናውን ከላኩት ወገኖች የተሰማው ሌላው ጉዳይ “ሕወሓት አካል ጉዳተኛ ታጣቂዎችን ወደ ጦርነት ለማስገባት አስቦ እየተንቀሳቀሰ ነው” የሚለው አስደንጋጭ መረጃ ነው። “ሕወሓት በመቀሌ አዋሽ አካባቢ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ አክሱምና አዲግራት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች በማስገባት በሚቀጥለው ግጭት የፊት መስመር ላይ ሊያሰልፋቸው ተዘጋጅቷል” የሚሉት ወገኖች፣ ይህንኑ ተከትሎ “ካለንበት አንወጣም” በማለት የአካል ጉዳተኞቹ ተቃውሞ ሲያሰሙ የሚያሳይ መረጃ ልከዋል።
“ያማል” ሲሉ እነዚሁ ወገኖች የላኩት መረጃ እንደሚያስረዳው ሕወሓት መሣሪያ ባከማቸባቸው ቦታዎች ዙሪያ ሲቪል ሰዎች እንዲሰፍሩ በማድረግ የድሮን ጥቃት እንዳይፈጸም ለመከላከልና ሰዎችን እንደ ጋሻ ለመጠቀም ዝግጅት እያደረገ ነው። ይህ መረጃ ደርሷቸው ይሁን በሌላ ባይታወቅም የትግራይ አክቲቪስት የሆኑ የፌስቡክ ገጾች ሕዝቡ ራሱን የድሮን ጥቃት ሊሰነዘርባቸው ይችላሉ ከተባሉ አካባቢዎች እንዲያርቅ ደጋግመው ሲያሳስቡ ነበር። ተግባሩ ሲቪሎችን ለወታደራዊ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረግ አደገኛና በዓለም አቀፍ ሕግ የሚያስቀጣ እንደሆነ የሚገልጹም አሉ።
በሱዳን ያሉ የሕወሓት ተዋጊዎችን የሚከታተሉ የሕወሓት ሹም፣ “ጦርነት መጨረሻው ስለማይታወቅ ተተኪ ኃይል ያስፈልጋል” ማለታቸውን በማስታወስ መረጃውን ያጋሩት ወገኖች እንዳመለከቱት፣ ሕወሓት ዕድሜና ጾታ ሳይመርጥ ያገኘውን ሁሉ አስገድዶ በአፈሳ ወደ ወታደራዊ ማጎሪያዎች እያጋዘ ነው።
በትናንትናው ዕለት በራያ አዘቦ ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ሌሊቱን ሙሉ ንጹሐን ዜጎች በድንገት መኖሪያቸው እየተከበበ ሲታፈሱ ማደራቸውን እማኞች በስልክ ተናግረዋል።
መረጃውን የላኩት እማኞች እንዳሉት፣ ሕወሓት በግዳጅ እያፈነ የወሰዳቸው ዜጎች የተጋዙት ወደ ማሰልጠኛ አካባቢዎች ነው። ሕወሓት በቀናት ሥልጠና መሣሪያ አታጥቆ በየግንባሩ የባሩድ ማብረጃ ሊያደርጋቸው ማቀዱን ከሚቀርቧቸው መስማታቸውን እነዚሁ ወገኖች አመልክተዋል።
በተደጋጋሚ በድሮን ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ሕወሓት በዚሁ ብስጭት አፈሳ ማካሄዱን ያመለከተው መረጃ፣ በራያ አዘቦ ወረዳ ባካሄደው አፈሳ ዕድሜያቸው የገፉ አባቶችን እንኳን ምሕረት አላደረገላቸውም።
በዚሁ መሠረት አፈሳ የተካሄደባቸው ቦታዎች ዓራዳሜግዶ፣ ኦናብልደ፣ ጋንዳ ጫፈ፣ ደልዎ፣ ዓድ ኣህማድ፣ ጥዋሃዬ፣ ፀእዳ መይዳ፣ ባላ፣ ዓድ ኣዳ ምማልደ፣ ዓራዴ፣ ዓባኩሪ፣ ኩኩፉቶ፣ በይሩቃል፣ ዋራባዬ፣ ፋጫ ጋማ፣ ዋሪግባ፣ ባቡር ሃድድ፣ ጨቋን፣ ካራ ዓድሻቦ፣ ዓድዶጓዓ፣ ዓድ ጋልሞ እና ዳጋጋ ቀበሌዎች እንደሆኑ ታውቋል። በወረራ ሌሊቱን ሙሉ በድንገት በተካሄደው አፈሳ የተጋዙት ዜጎች ቁጥር ለጊዜው አልታወቀም።
ሕወሓት ከመደበኛ የፖሊስ አባላት መካከልም ሰዎችን በግዳጅ ወደ ታጣቂ ኃይል ማስገባት መጀመሩን ተከትሎ በአባላቱና በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ መከሰቱን ሌሎች መረጃ ሰጪዎች አካባቢ ለይተው አመልክተዋል።
ከተጠቀሱት መረጃዎች በመነሳት፣ ቀደም ሲል ከቀረቡትና የሕወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ሕወሓት በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች ወታደራዊ ኃይሎችን እያሰማራና የሎጂስቲክስ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። ከዚህ የተጠናከረ ወታደራዊ ዝግጅት የተነሳ በትግራይ እና በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች አዲስ ግጭት የመነሳት ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ መረጃ የሰጡት ወገኖች ይናገራሉ።
ዲፕሎማቶች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ አሜሪካ እንዲሁም ሥጋት የገባቸው ወገኖች በሙሉ የሰላም ጥሪና የድርቅ ሥጋትን በማንሳት በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢልኩም ሕወሓት በከፍተኛ ደረጃ የጦርነት ዝግጅቱን አፋፍሟል። ጦርነት የሰለቻቸው የትግራይ ተወላጆችና አዋሳኝ የአማራ ክልል ነዋሪዎች በዚሁ የጦርነት ፍርሃት ሳቢያ እየተሰደዱ ነው።
ሻዕቢያ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ካለው የተልዕኮ አጀንዳ አንጻር፣ በአማራና በትግራይ ክልል ላይ ጦርነቱ እንዲጀመር ባለፈው ሳምንት አስመራ ላይ በተደረገ ስብሰባ አቋም ማስያዙ ይታወሳል። የሕወሓትና በዘመነ ካሴ የሚመራው የአፋብን (ፋኖ) አካል በተገኙበት በዚሁ ስብሰባ ውሳኔ መሠረት ሕወሓት ወደ ጦርነት እየተንደረደረ መሆኑ ታውቋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






