ልደቱ ግበናውን ገፈፈ፤ በድብቅ ሲሰራበት የነበረውን ግብጽ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ … ያሉበትን ጽምዶ “የኢትዮጵያ ትንሳዔ” አለ – ከጋራ መድረክ የተሰጠ ምስክርነቴ አንድ

Date:

አሁን አሁን ፈርሰናል። የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ / ህወሃት፣ የአማራ ፍኖ “ወኪል ነን” በነገራችን ላይ የፋኖ ወኪል መሆናቸውን የሚገልጹ ብዙ ናቸው፤ እነሱና የሻዕቢያ ተወካዮች እንጂ ሌሎቹ መምጣት አቁመዋል። የጋራ መደረኩ ኢትዮጵያ ላይ በሚያሴሩ፣ ለኢትዮጲያ የሚጨነቁ፣ ስብስቡ ያልገባቸው ወዘተ የተሰባሰቡበት ሲሆን መግባባት የሚባል ነገር አያውቀውም። አሁን አሁን ኢትዮጵያን ለማተራመስ ቀርቶ ራሱ ተተራምሶ ስብሰባ ማድረግ የማይችልበት ደረጃ ደርሷል። አሁን ሁሉንም በዝርዝር ይፋ ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ በዚህ ጀመርኩ። የስብሰባዎቹን የድምጽ ቅጂዎች ሁሉ አቀርባለሁ። ኢትዮጵያ ላይ እንዴት እንደሚቆመር አጋልጣለሁ።

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ — “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እንዴት ይታያል? ከኤርትራ ጋር በሕወኃት በኩል የተጀመረውን ሕብረት በጥንቃቄ መመርመር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። መርህ አልባ እንዳንሆን…” በኢትዮጵያ ትርምስ ለመፍጠር ሻዕቢያ ባደራጀው የጋራ መድረክ ላይ የተነሳ ጥያቄ ነበር። ይህ ጥያቄ ሲነሳና “አርፋቹህ ቁጭ በሉ” ሲባል እዛው ነበርኩ። “ይህንን ጥያቄ እዚህ አታንሱ!” በሚል የሻዕቢያ ወኪል አቶ ነዓምን በገሃድ ሲያስቆሙ፣ ከተቆጡትና ስብስቡን ሻዕቢያ እንደሚነዳው ካልገባቸው “ቀና” ሰዎች መካከል አንዱ መሆኔን እወቁልኝ።

ከሻዕቢያ አንጻር በሚነሱ ጉዳዮች የሚሰጡ መልሶች ሲጎረብጡኝ ኖረዋል። በስብሰባው ላይ በተሳተፍኩበት ሁሉ መረጃውን ለአዲስ ሪፖርተር ሳስተላልፍና ሕዝብ እንዲያውቀው ሲደረግ ቆይቶ፣ ዛሬ ይህንን ለመጻፍ ተገድጃለሁ።

አቶ ልደቱ “አብሮነት”ን፣ አቶ ነዓምን ደግሞ “የአንድነት ስብስብ”ን ይዘው ምርጫውን ለማጨናገፍ በየፊናቸው ሲሮጡ፣ “መጣመር አለባቸው” ተብሎ በሻዕቢያ ትዕዛዝ ተጣመሩ፤ ስሙም “የጋራ መድረክ” ተባለ። በዚህ መልኩ ጥምረቱ መፈጠሩን ከማያውቁት መካከል ብሆንም፣ በኋላ ላይ ጨዋታው የገባኝ ከተለያዩ አካላት “ወደ እኔ ሕብረት ግባ፣ እነ እገሌ እንዲህ ናቸው” የሚለው የጎንዮሽ ጅንጀና በተደጋጋሚ ሲቀርብልኝ ነው።

በነገራችን ላይ፣ በአሜሪካ በሁሉም አቅጣጫ ታጣቂዎችን ወደየራሳቸው ለመጎተትና ተጠሪ ለመሆን ያለው ግብግብ እጅግ አስገራሚና የክህደት ሁሉ ጥግ መሆኑን የሚያሳይ መረጃ በተከታታይ እንደማቀርብ ከወዲሁ ቃል እየገባሁ፣ ወደ ዛሬው አጭር መረጃ ላምራ።

በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ትርምስ ለመፍጠር አገር ቤት ካሉ ፓርቲዎችና የፓርቲ አመራሮች ጋር በመናበብ ሲሰራ፣ በዋናነት መሸሸጊያችን “ሰላማዊ ትግል፣ ሕዝባዊ አመፅ” የሚል ነበር።

“ታጣቂዎችን እናግዝ” በሚል በውይይቱ ላይ ግልጽ አቋም ሲነሳ አቶ ልደቱ ቀድሞ ተቃዋሚና ተከላካይ ነበር። አቶ ልደቱ የሕወኃትን መስመር፣ አቶ ነዓምን ደግሞ የሻዕቢያን መስመር ይዘው በተመሰረተው “ትርምስ አመቻች የጋራ መድረክ” ውስጥ፣ አቶ ልደቱ ራሱን “የሰላም ታጋይ” አድርጎ ቢያቀርብም፣ ወደ መጨረሻው አካባቢ ግን “ከትጥቅ ትግሉ ውጪ መሆን አንችልም” የሚል ዳርዳርታ ጀመረ።

“እናንተ ከሻዕቢያና ከግብፅ ገንዘብ እየተቀበላችሁ እኛን አታታሉን፤ እኛ የምናገኘው አንዳችም ጥቅም የለም” በሚል በተለምዶ “አጋር” ከሚባሉት ድርጅቶች የተወከሉ አባላት ጉዳዩ የጥቅም መሆኑንና “Double standard” (ሁለት መደበኛ) ጨዋታው መቆም እንዳለበት በገሃድ ሲናገሩ፣ አቶ ልደቱ በአንድ በኩል እየተከላከለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአቶ ነዓምን አማካይነት የቤትና የሆድ አበል ስለሚከፈላቸው ጠቅልለው ሻዕቢያ ደጅ ወደቁ።

ከዚህም አልፈው እስከ ሱዳን የተዘረጋ ኃላፊነት በመያዝ መንቀሳቀስ ጀመሩ። ይህንን ኃላፊነት ሲጀምሩ ቀርተውበት ከማያውቁት ስብሰባ መቅረት (መፎረፍ) አበዙ። ይህንን ያልኩት እነ ኢንጂነር ሙሉጌታ፣ የሻዕቢያ ሌላው ወኪል ኢንጂነር ግደይ፣ እንዲሁም የሕወኃት ሌላው አንደበት የሆኑት አቶ አባይ ግደይ “የታጠቁትንና መሬት ላይ ያሉትን እንደግፍ” ሲሉ አቶ ልደቱ “አይሆንም” በማለት ሲከላከሉ ቆይተው የታጠፉት “ፅምዶ” የሚባለው ትልቁ ኢትዮጵያን የሚበታትን አደረጃጀት እንደሚመሰረት ሲያውቁ መሆኑ የገባኝ አሁን ነው።

“…በዚህ ጦርነት የሕዝባችን ሕልውና፣ የትውልዱ ሕልውና ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ገብቷል። አሁንም ሕዝብ እያለቀ ነው። አሁን ያፈጠጠው ከሰሜን አቅጣጫ እየመጣ ያለው ጦርነት ደግሞ ልንገምተው የማንችለው እልቂት ይዞ ነው እየመጣ ያለው። በየፊናቸው አገዛዙን እየታገሉ ያሉ ኃይሎች ዝም ብለው ወደ አዲስ አበባ ቢገሰግሱ (ማርች ቢያደርጉ)፣ አዲስ አበባ ላይ ሲደርሱ እርስ በርሳቸው ነው የሚዋጉት። ያ ደግሞ መንግሥት-የለሽ ሁኔታ ነው የሚፈጥረው… በትጥቅ ትግል ተካሂዶ የሚመጣ ለውጥ ዘላቂ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያመጣል የሚል እምነት የለኝም” — ይህ ቃለ-በቃል ከአቶ ልደቱ አንደበት የወሰድኩት ነው።

በዚህ እሳቤ ውስጥ ሆነው ሲሰቃዩ (በነገራችን ላይ ሕይወታቸው ነው) የቆዩት አቶ ልደቱ፣ ማስካቸውን ገፈው “ፅምዶን እደግፋለሁ” አሉና አረፉት። ዘመናቸውን ሙሉ የአቶ ስብሐትን ካሴት ጎርሰው፣ ያለ ምንም መሸማቀቅ አደባባይ እየወጡ የሚተፉት አቶ ልደቱ፣ ነውር ማዕረጋቸው ነውና ሌሎች እናፍርላቸው ካልሆነ በቀር ለእሳቸው “ነውር ጌጣቸው” ነውና በገሃድ ደመቁበት።

በኢትዮጵያ መርህ ላይ የተመሰረተ ሕብረት ተፈጥሮ ለውጥ እንዲደረግ ፍላጎት አለኝ። ይህን ፍላጎቴንና እምነቴን ለማሳካት ስል “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚለውን የአቶ ልደቱን ቀመር አልጋራም። በየትኛውም መስፈርት ሕወኃትና ሻዕቢያ የሚመሩት ትግል ኢትዮጵያን ይታደጋል የሚል ቅዠት ውስጥ አልገባም። ለምን ቢባል አገሬን እወዳለሁ! በዚህ መለኪያ ነበር ውስጣቸው ሆኜ መረጃ ለሕዝብ ሳቀርብ የነበረው።

አዲስ ሪፖርተር በተከታታይ ስብሰባችንን እየነቀሰ አደባባይ ሲያወጣው “ለኤፍ.ቢ.አይ (FBI) እንክሰሰው” ተብሎ ውይይት ሲደረግ፣ አቶ ልደቱን ጨምሮ የዚሁ የድብቁ አጀንዳ አባላት “ውስጣችንን እናጥራ፤ ከአሁን በኋላ በሲግናል (Signal) እንገናኝ፤ ኮድ እንቀይር” ወዘተ ሲሉ፣ “ለሕዝብ እንሰራለን ካላችሁ ምን አስፈራችሁ?” ተብሎም ነበር።

ዛሬ ነካ ነካ በማድረግ ይህችን አጭር ማስታወሻ የጫጫርኩት፣ አቶ ልደቱ ሽፋናቸውን ገልጠው ፅምዶን መደገፋቸውን በማስታወቃቸው፣ “እንኳን ለዚህ ወግ አበቃዎት! ድሮም እኛ እናውቅ ነበር፤ እርስዎን የማያውቅ የለም። ከአትላንታ ወደ ዲሲ ዝውውር ሲያደርጉና የሻዕቢያ ሽርፍራፊ እየቀመሱ መኖር ሲጀምሩ መረጃው በአቶ ነዓምን ወዳጆች አማካይነት ደርሶን ነበር” ለማለት ነው።

ሊጣመሩ የማይችሉ ወገኖች የመጣመራቸው ዜና ተሰምቶ ሳያልቅ መፍረሳቸው እየታወጀ ባለበት በዚህ ሰዓት፣ አቶ ልደቱ የፅምዶ ባንዲራ ሰቃይ መሆኑን ለማታውቁ፣ ካቀረቡት ጽሑፍ ላይ ቆንጠር አድርጌ ሕሊና ላላቸው ጥያቄ ቢጤ ላንሳና ልቋጭ።

፩. የሰላማዊ ትግል መርህ እና የታጣቂ ጥምረት ድጋፍ እርስ-በርስ መጋጨት

አቶ ልደቱ ራሱን የሰላማዊ ትግል አቀንቃኝ አድርጎ እያቀረበ፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ አካላትን ስልታዊ ጥምረት (ፅምዶ) መደገፉ ትልቅ የአቋም መናጋትና አመክንዮአዊ ግጭት ውስጥ መውደቁን ያሳያል። “ሕይወቱ ነውና አትጃጃሉ” ልላችሁ እወዳለሁ። ሰላማዊ ትግል በመርህ ደረጃ የትጥቅ ትግልንና የጦርነት ስልቶችን እንደ አማራጭ የማይቀበል እንደመሆኑ መጠን፣ የታጣቂዎችን ስብስብ “የሰው ሕይወት ያድናል” በሚል ምክንያት መደገፍ፣ የትጥቅ ትግሉን ሕጋዊነት (Legitimacy) ከመስጠት ባለፈ ጦርነትን እንደ ዋና የፖለቲካ መፍትሔ የመቀበል ያህል ይቆጠራል።

፪. የውስጥ የፖለቲካ ልዩነቶች እና የርዕዮተ-ዓለም አለመጣጣም

በትግራይ (ሕወኃት)፣ በአማራ (ፋኖ) እና በኦሮሚያ (ኦኤልኤ/ኦነግ ሸኔ) መካከል ያሉት ልዩነቶች ቀላል የፖለቲካ ልዩነቶች ሳይሆኑ፣ ሥር የሰደዱ የታሪክ፣ የወሰን፣ የብሔር-ብሔረሰብ መብት እና የሀገር መንግሥት አወቃቀር ስትራቴጂካዊ ቅራኔዎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች የጋራ ርዕዮተ-ዓለም ወይም የረጅም ጊዜ የሀገር ግንባታ ራዕይ ሳይኖራቸው፣ በጊዜያዊነት “ገዢውን ፓርቲ ከመንበር ለማውረድ” ብቻ የሚያደርጉት ጥምረት፣ ከሥልጣን ለውጥ በኋላ የባሰ የሀገር መፍረስና የእርስ-በርስ ጦርነት (Civil War) የመፍጠር ዕድሉ ከፍተኛ እንደሆነ እሙን ነው።

ከዚህ ቀደም በሀገራችንም ሆነ በሌሎች ሀገራት እንደታየው፣ ያለ ወጥ የፖለቲካ ስምምነት የሚደረግ የኃይል አሰላለፍ ጥምረት አገዛዙ ሲወድቅ እርስ በርስ ወደ ባሰ እልቂት ያመራል። የኛዎቹ እዚያ ሳይደርሱ መባላት የጀመሩ መሆናቸው ከሌሎች ተሞክሮዎች ይልቅ የከፋ እንደሆነ አቶ ልደቱ ጠንቅቆ እያወቀ “እደግፋለሁ” ማለቱ፣ በዚህ አጋጣሚ በሕወኃት በኩል የተቀበለውን “እኛ የማንገዛት ኢትዮጵያ ትበታተን” የሚለውን አጀንዳ ተሸካሚነቱን ከማሳየት አይዘልም።

፫. የውጭ ኃይሎች ጣልቃ-ገብነት እና የጂኦ-ፖለቲካ ሥጋት

ጥምረቱ በኤርትራ፣ ሱዳን ወይም ሌሎች የውጭ ሀገራት ድጋፍና አስተባባሪነት የሚደረግ ነው የሚለው ሥጋት በከፍተኛ ደረጃ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ወይም የራሳቸውን ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም የሚያሳድዱ የውጭ ሀገራትን አጀንዳ የሚያስፈጽም ጥምረት መደገፍ፣ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሕልውና አደጋ ላይ ይጥላል።

የሀገር ውስጥ ችግርን በውጭ ኃይሎች እጅ በማስገባት የሚደረግ የትጥቅ ትግል፣ ሀገርን ከመታደግ ይልቅ ወደ ተኪ ጦርነት (Proxy War) እና መፍረስ (Disintegration) ያመራል። ይህንንም እውነት አቶ ልደቱ ያውቃል። ዓላማውም ይህ ስለሆነ ድጋፉን ሰጥቷል።

፬. የመፍትሔው አቅጣጫ ግራ መጋባት

የሰው ሕይወትና ንብረት እንዳይጠፋ ከመቆርቆር አኳያ የሚሰጡ ምክረ-ሐሳቦች ተቀባይነት ቢኖራቸውም፣ መፍትሔው ታጣቂዎችን ማስተባበር ሳይሆን የትጥቅ ትግል አጥፊነትን በማጋለጥ ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላማዊ ድርድርና ብሔራዊ መግባባት እንዲመጡ ጫና መፍጠር፣ መንግሥትን ጨምሮ ወደ ንግግር እንዲመጡ መግፋት፣ እንዲሁም የውጭ አካላትን ጣልቃ-ገብነት በአደባባይ ማውገዝ ነው።

እንዲሁም የሀገርን ሕልውና በጊዜያዊ የኃይል አሰላለፍ ሳይሆን በቋሚ ሕግና በዴሞክራሲያዊ ሲቪል መዋቅር ላይ መገንባት ስላለበት፣ በዚህ አግባብ ትልቁን ሥዕል በመመልከት መትጋት ያስፈልጋል።

ስለሆነም፣ የአቶ ልደቱ አያሌው አቋም የጦርነቱን ጉዳት የመቀነስ በጎ ምኞት እንዳለው ቢያስታውቅም፣ በተግባር ግን የታጣቂዎችን ጥምረት በመደገፍ የሀገርን ሕልውና ለበለጠ አደጋ የሚያጋልጥና ከሰላማዊ ትግል መርህ ጋር የሚጋጭ አቋም እያራመደ፣ “ሕዝባዊ እምቢተኝነት” በሚል የጀመረውን መሸሸጊያ እንዲያፈርስ በዚህ አጋጣሚ አሳስባለሁ።

በገሌ በእነሱ ስብስብ ውስጥ የገባሁት ሥራቸውን ለማፈራረስና ለማጋለጥ በመሆኑ፣ ከዚህ በኋላ በአደባባይ የማውቀውን ሁሉ እንደምዘከዝክ አስታውቃለሁ። ለውጥ እንደሚያስፈልግ አምናለሁ፤ ለውጡ ግን ኢትዮጵያን እንዲበላ አልፈቅድም!

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related