በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ በተፈጥሮ ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለፖለቲካዊ ትርፍ የመጠቀም ልማድ ሥር የሰደደና አደገኛ አዝማሚያ ሆኖ ቆይቷል። በዚህ አደገኛ ቁማር ደግሞ እንደ ትህነግ የተካነና የነገደ የለም። ታሪኩ እንደሚያስረዳው ረሃብን ያለ አንዳች ርህራሄ ተጠቅሞ የስልጣን መወጣጫ አድርጎታል። ይህ ከራሱ የፖሊት ቢሮ አባላት አንደበት የወጣ ምስክርነት ነው።
በባለፈውም ሆነ አበአሁኑ የታሪክ አጋጣሚዎች የሚታየው ዋነኛ ሀቅ፣ ረሃብን እንደ ስልታዊ የጦር መሣሪያ (Weaponization of Famine) በመጠቀም፣ የሀገርን ሉዓላዊነት የመሸርሸር እና የሥልጣን ፍላጎትን የማሳካት አባዜ ነው። ይህ አዝማሚያ ችግሩን በጋራ ከመፍታት ይልቅ፣ የዜጎችን ስቃይ ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ በመስጠት ሀገርን የማዳከም ስሌት የተጠናወተው ክፉ፣ አልድን ያለ በሽታ ነው። ይህ በሽታ ነው ዛሬ የትግራይ ሕዝብ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ መከራ የሆነበት።
የትግራይ ተፈናቃዮች እንደ ፖለቲካዊ ጋሻ
ማንም ሊረሳው በማይችለው ደረጃ የአገር መከላከያ ላይ የክህደት እርምጃ ወስዶ አዲስ አበባ ለምግባት የሶስት ስምንት ቀጠሮ ይዞ የነበረው ትህነግ፣ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዳልሆነ ሆኖ ፈርሶ እንደነበር አይዘነጋም። “ለትግራይ ጦርነት ባህል ነው” በሚል የደነቆረ ቅስቀሳ ትግራይን ለዚህ ጉስቁልና የዳረገው ትህነግ፣ የለኮሰው ጦርነት ሲፈጀው ህዝብ ጉያ ተደብቆ ሲፈጥር የነበረው የረሃብና የተከበብኩ ድራማ ውጤት ገና ሳይሽር ዛሬም ያንኑ ድራማ ጀምሯል።

ፎቶ የትህነግ መሪዎች ለረሃብተኛ የመጣን የዕርዳታ እህል ሸጠው ገንዘብ ሲቆጥሩ የሚያሳይ ነው። የዛሬን አያድርገውና ማርቲን ፕላውት፤ ነበር ይህን የምርመራ ስራ ያተመው። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ አሁንም ለጦር መሳሪያ ግዢና ሻዕቢያ ለሚያበረክተው አስተዋጾ የትግራይ ህዝብ ቆዳውን እየተገፈፈ ነው
ከሽንፈቱ በሁዋላ ተደጋጋሚ ሰላም ሊያወርዱ የሚችሉ ዕድሎችን በማንጠፍ ከአንድ፣ ሁለት ሶስቴ ከሰራው ስህትት፣ ከደረሰው ቁሳዊና ሰብአዊ ቀውስ መማር ያልቻለው ትህነግ፣ ዛሬም አንድ እግሩን አዲስ አበባ በላከ ማግስት ሌላ የረሃብ ድራማ፣ የጦርነት አዋጅ፣ ጀምሯል። የሚያሳዝነው ሳልሳዊ ትግራይ እንዳለው ራሱ በፈጠረው ረሃብ፣ ራሱ አልቃሽ መሆኑ ነው።
ይህ ምስኪኖችን ሰብአዊ ጋሻ ያደረገ ወንጀለኛ ቡድን ዛሬ በወርቅ ንግድ፣ በሰዎችን ንግድ፣ “ጽምዶ” በሚለው አዲሱ ጥምረቱ ታጅቦ ከትግራይ ተፈናቃይ ሕዝብ ጉሮሮ እየነጠቀ ወደ ኤርትራ ቀለብ እያጋዘ፣ ቤንዚን እየቸረቸረ፣ ዞር ብሎ የፌደራል መንግስትን ይከሳል። ትግራይን አስራበ እያለ ቧልት ይቦልታል። ያስጨረሳቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆች ደምና አጥንት ላይ ቆሞ ሌላ የውክልና ጦርነት በረሃብ ዜና ስር ሆኖ ያቀጣጥላል። የባይቶና ፓርቲ እንዳለው ይህ ጦርነት መጥመቅና ህዝብን ሰብአዊ ጋሻ በማረግ ዓለምን ለማሳት የሚንቀሳቀስ አረም መነቀል አለበት።
“አለቀለን። ዛሬ ነገ ሳትሉ የሰላም ስምምነቱን ፈርሙ” ብሎ አልቅሶ የተረፈው የዘራፊዎች ስብስብ፣ ስምምነቱን ተከትሎ ከጥፋቱ ከመማር ይልቅ ሴራ እያመረተ፣ የሚያገኘውን ለታቂ እያቀረበ፣ ህዝብን አግቶ መኖርን በመምረጡ የትግራይ ተፈናቃዮች ለመከራ ተዳርገዋል። ለሕዝብ መፍትሄ በመፈለግ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በይደር መላ ለማለት ከማሰብ ይልቅ ” እኔ ከሞትኩ” እንዳለችው አሁያ ሆኗል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የትህነግ አመራር ተፈናቃዮችን ወደ ቀደመ ቀያቸው መልሶ በማቋቋም ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ይልቅ፣ በረሃብና በስቃይ ውስጥ ሆነው በስደተኛ ጣቢያዎች እንዲቆዩ ማድረጉን እንደ ዋነኛ የፖለቲካ ስትራቴጂ ተያይዞታል።
ተፈናቃዮችን በችግር ውስጥ አግቶ ማቆየት ለቡድኑ ለሁለት ትልልቅ ዓላማዎች ያገለግለዋል። በአንድ በኩል፣ የተጎሳቆሉ ዜጎችን ፎቶና ምስል ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በማሳየት “የመረጃ ጦርነት” (Information Warfare) ለመክፈትና በፌደራል መንግሥቱ ላይ ጫና ለመፍጠር ይጠቀምባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሕዝቡን ስቃይ እንደ ማስተዛዘኛ በማቅረብ የተቋረጠለትን ዓለም አቀፍ ድጋፍና የፖለቲካ ትኩረት መልሶ ለማግኘት የሚጠቀምበት የሞራል ጋሻ ሆኖታል። ይህ ተግባር ቡድኑ ለሰብዓዊ መርሆዎች ያለውን ንቀት የሚያሳይ ሲሆን፣ የሕዝብን ስቃይ ለድርድር ማቅረቢያነት (Political Bargaining Chip) የመጠቀም ክፉ ልማድ ማሳያ ነው።
ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ይመለሱ ዘንዳ ዲፕሎማቶችን በማሰባሰብ አሜሪካ ፣ ኢንግሊዝና አውሮፓ ወኪሎች የተካተቱበት ስድስት አባላት ያለበት የልዑካን ቡድን ወደ ትግራይ ተልኮ ሃሳቡን እንዲቀበል ሲለመን “እውቅናችን ተመልሶ ሳይሰጠን ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያቸው አይመለሱም” ማለታቸውን በወቅቱ የነበሩ ዲፕሎማቶች መስክረዋል። ከዚህ በላይ የሕዝብን ስቃይ ለድርድር ማቅረቢያነት (Political Bargaining Chip) የመጠቀም ክፉ አባዜና ማሳያ ማስረጃ የለም።
ይህ ብቻ አይደለም የ2015 ዓ.ም ክረምት ከመድረሱ በፊት ተፈናቃይ ለመመለስ ሚያዚያ ላይ ፌደራል መንግስት ዝግጅት አድረጎ የአማራ ክልል እና የትግራይ ጊዜያ አስተዳደር በጋራ እንዲመክሩ ተደርጎ ስምምነት ላይ ተደረሰ። ስምምነት ከተደረሰ በሁዋላ በኋላ አክራሪው ቡድን “መላው ሰራዊታችንና ከጦርነቱ በፊት የነበርውን አስተዳደር ይዘን ካልገባን በስተቀር ተፈናቃይ አይመለስም” ብሎ ውሉን ማፍረሱን የወቅቱ የክልሉ መሪ በይፋ ተናግረዋል። በእንዲህ መልኩ በስቃይ የሚነግድ ድርጅት ነው “ህዝብ ተራበ፣ ተጎሳቆለ” እያሉ የሚፎክረው።
በተለያዩ አግባቦች የማግባባት ስራ እየተሰራ ቆይቶ የቀደመውን ስምምነት ከረገጠ ከዓመት ተኩል በኋላ ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ በርካታ ሙከራዎችና ሴራዎች ቢኖሩም ተፈናቃዮችን ወደ ጸለምትና ራያ ማስፈር አቶ ጌታቸው ማነራቸውን ማስታውስ አግባብ ይሆናል። በዕቅዱ መሰረት በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ከወልቃይት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመመለስ ቢሞከርም ትህነግ ምስጋና ይጋባውና አልተቻለም።
የተፈናቃዮችን ስቃይ የፖለቲካ ግብአት አድርጎ እየሰራ ያለው ትህነግ፣ በአደጋ ስጋት አመራር በኩል ለተፈናቃይ የተላከን ድጋፍ ገና ለገና በኃይል ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ያደረጓቸውን አቶ የጌታቸው ረዳን እና አስተዳደራቸው በሕዝብ ዘንዳ ተቀባይነት ተቀባይነት ያገኛል ከሚል ስጋት በመነጨ አስተጓጉሎታል።
በተጨማሪም፣ በየጊዜው ለተፈናቃዮች የሚላከው ሰብዓዊ እርዳታ ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል ሥርዓታዊ የሆነ የምዝበራ መረብ ተዘርግቷል። ከተፈናቃዩ ምስኪን ሕዝብ ጉሮሮ እየተነጠቀ ለፓርቲ ማጠናከሪያና ለታጣቂዎች ቀለብ የሚውለው የእርዳታ እህል፣ ቡድኑ ለሕዝቡ ደኅንነት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ ለጦርነት ዝግጅቱ ምን ያህል ትኩረት እንደሚሰጥ ማረጋገጫ ነው።
እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የፌደራል መንግሥት የሚያቀርቡት ድጋፍ በተዘዋዋሪ መንገድ የቡድኑን ወታደራዊ አቅም መገንቢያ ሆኖ እንዲያገለግል መደረጉ፣ በክልሉ ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከማባባሱም በላይ ረሃብን እንደ ስልታዊ የጦር መሣሪያ የመጠቀም ዝቅጠት ነው። ይህ በደም የተነከረ ግድ የለሽነት ድርጅት ለጋሽ ሀገራት ድጋፋቸውን እንዲያቆሙ በማድረግ በትክክል እርዳታ የሚፈልገውን ሕዝብ ለከፋ አደጋ አጋልጦታል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ የፌደራል መንግሥት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በተደጋጋሚ የሚያደርገውን ጥረት ቡድኑ ሆን ብሎ እያደናቀፈ ይገኛል። የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት መሠረት በማድረግ ዜጎችን የማቋቋም ሥራ ሲጀመር፣ ቡድኑ “የእውቅና ጥያቄ” እና “የአስተዳደር ወሰን” የሚሉ የፖለቲካ ሰበቦችን በመደርደር ሂደቱን ያጓትታል።
የሰላም ሂደቱን እንደ መተንፈሻ ወይም ትንፋሽ መሳቢያ በመጠቀምና ጊዜ በመግዛት፣ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ይዞታቸው ተመልሰው የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ አይፈልግም። ይህ ከሆነ ትህነግ ሞትን ይሞታል። በመሆኑም የሕዝቡ መረጋጋትና ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ቡድኑ በትርምስ ውስጥ የሚስበውን የህልውና አየርና መተንፈሻ ቱቦውን ስለሚበጣጥስበት ተፈናቃዮችን ከዕግቱ አያስወታቸውም። በዚሁ ርህራሄ በነጠፈበት ባህሪው ሳቢያ የሕዝብን ስቃይ የፖለቲካ የበላይነት ለማድረግ ሌት ከቀን ያሴራል። ቡድኑ የሚፈልገው ለሕዝቡ መፍትሄ መስጠት ሳይሆን፣ ሕዝቡን ዘላቂ ሰለባ (Victim) አድርጎ በማቆየት የራሱን የሥልጣን ዕድሜ ማራዘም መሆኑን በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው። ለዚህ ይመስላል በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች “ትህነግ ካልተነቀለ የትግራይ ሕዝብ ሰላም አያገኝም” ውለው አድረውም ቢሆን ከድምዳሜ ላይ የደረሱት።
መማር ያልቻልንበት የታሪ ክአዙሪት
ታዋቂው ጸሐፊ በርናርድ ሾው በአንድ ወቅት እንዳለው፦ “ታሪክ ራሱን የሚደግም ከሆነና ያልተጠበቁ ነገሮች ሁልጊዜ የሚከሰቱ ከሆነ፣ ሰው ከታሪክ ለመማር ምንኛ ብቃት የሌለው ፍጡር መሆን አለበት!” ይህ አባባል ዛሬ በሀገራችን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ኢትዮጵያ ካለፉት መራራ የታሪክ ስህተቶቿ መማር ይኖርባታል። ረሃብንና ሰብዓዊ ቀውስን ለፖለቲካዊ ትርፍ መጠቀሚያ ማድረግ ሀገርን ወደ ማያልቅ አዘቅት ከመክተት እና የዜጎችን ስቃይ ከማራዘም ባለፈ ለሕዝብ የሚፈይደው ቅንጣት ታህል ጥቅም የለም። በንጉሡ ዘመን የተፈጸመው ስህተት ዛሬ በትግራይ ተፈናቃዮች ስም ዳግም ሲደገም ማየት፣ የታሪክን ትምህርት ወደ ጎን የገፉ “ገልቱዎች” በሕዝብ ሕይወት ላይ ቁማር እየተጫወቱ መሆኑን ያረጋግጣል።
አሁናዊ መፍትሄ
ስለሆነም፣ ለተፈናቃዮች መከራ ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ከተፈለገ፣ትህነግ እጁን ከተፈናቃዮች ላይ በአስቸኳይ ማንሳት ይኖርበታል። ተፈናቃዮችን እንደ ድርድር መሣሪያ አግቶ መያዝ እና ለፖለቲካዊ መጠቀሚያነት በስደተኛ ጣቢያዎች እንዲማቅቁ ማድረግ ሊቆም የሚገባው ሰብዓዊ ወንጀል ነው። ከዚህ ባለፈም፣ ለተጎጂ ወገኖች የሚላከው እርዳታ ያለ ምንም ጣልቃ ገብነት ለታለመለት ዓላማ መዋል ይኖርበታል። ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ እርዳታው በብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል በቀጥታ ለተጎጂዎች የሚደርስበት ግልጽ ሥርዓት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። እርዳታን ለፓርቲ ማጠናከሪያና ለታጣቂዎች ቀለብ የመመደብ አደገኛ አካሄድ ማዋል በጽኑ ሊገታ ይገባል። በዚህ ረገድ የፌደራል መንግስት ቆፍጠን ማለት ይገባዋል።
መላው ኢትዮጵያውያን በሐሰተኛ ወሬዎችና በተቀነባበሩ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች ሳይደናገር፣ የዚህን ጽንፈኛ ቡድን የክፋት አጀንዳ ነቅተው ሊጠብቁ ይገባል። ታሪክ ዳግም እንዳይበላንና ሀገራችን ወደ ሌላ ዙር ትርምስ እንዳትገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ዛሬ ለተፈናቃዮች መብት መቆም ማለት እነሱን ከረሃብ መታደግ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡን ለዳግም ጦርነትና ለጥፋት ከሚቀሰቅሰው ኃይል ነፃ ማውጣት ማለት ነው። እውነተኛ ሰብዓዊነትም ሆነ ሀገራዊ ወገንተኝነት የሚለካው፣ ሕዝብን ከፖለቲካ ቁማርተኞች መዳፍ ነፃ በማውጣትና ወደ መደበኛ ኑሮው እንዲመለስ በማድረግ ብቻ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






