የፕሪቶሪያው ስምምነት ስንቴ ይፍረስ፤ በሽራሮ የድሮን ጥቃት መፈጸሙን የትግራይ ክልል አስታወቀ፤ ከመንግስት ወገን የተሰማ ነገር የለም

Date:

አዲስ ሪፕርተር ዜና – “በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ሸራሮ አከባቢ የድሮን ድብደባ በመፈፀም በተለመደ ስምሪት ላይ በነበሩ የትግራይ ሰራዊት ላይ የህይወትና የአካል ጉዳት እንዲሁም በንብረት ላይ ውድመት አድርሷል” ሲል የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጽህፈት ቤት መንግስትን ከሰሰ። ከመንግስት ወገን የተባለ ነገር የለም።  

“መላ የትግራይ ህዝብ አሁንም አንድነትህ በማጠናከርና ከመኸተ ዓቅሞች ጎን ተሰልፈህ ሉእላዊነትን ለማክበርና የትግራይ ህልውና ለማረጋገጥ በሚደረገው ትግል በፅናት እንደምትሰለፍ በመተማመን ነው” ሲል የትብብር ጥሪ ያቀረበው የትግራይ ክልላዊ መንግስት፣ የአካባቢው ሕዝብ የጦር መሳሪያ በጫኑት ከባድ ተሸከርካሪዎች ላይ በደረሰው ጥቃት መቆጨቱን አመልክቷል።  

ግንቦት 29 ቀን 2018 ዓ.ም አጥቢያ ላይ የድሮን ጥቃት መደረሱን ያመለከተው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጽህፈት ቤት የከሰሰው “የብልጽግና ስርዓት” ሲል የጠራውን የኢትዮጵያን መንግስት ነው። ክልሉ በመግለጫው፣ የድሮን ድብደባው “… በተለመደ ስምሪት ላይ በነበሩ የትግራይ ሰራዊት ላይ የህይወትና የአካል ጉዳት እንዲሁም በንብረት ላይ ውድመት አድርሷል” ከማለት ውጭ የጉዳቱን መጠን አላብራራም። የጠቀሳቸው “የትግራይ ሰራዊት” እንቅስቃሴንም ከየት ወዴት እንደሆነና ጥቃቱ የደረሰበትን ከምፕ አልዘረዘረም።  

ዜናውን ቀደም ብለው ያሰራጩ የማህበራዊ ገጾች እንዳሉት የድሮን ጥቃቱ የተፈተመው በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ገምሃሎ አካባቢ፣ መሣሪያና ሎጂስቲክስ ጭኖ ወደ ባደመ ይጓዝ በነበረ የህወሓት ወታደራዊ ኮንቮይ ላይ ነበር። እንደመረጃው ከሆነ “የተጠና” በተባለው የድሮን ጥቃት ዘጠኝ የሚሆኑ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እና ሶስት ቀላል ወታደራዊ ፒካፕ ተሽከርካሪዎች እስከ ጫኑት ጭነት ወድመዋል። ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወታደሮችም ህይወታቸው አልፏል።  

ከትግራይ ክልላዊ መንግስት የተሰጠው መግለጫ “ጄኖሳይድ” መፈጸሙን አንስቶ መንግስትን ከሷል። ጥቃቱ በወታደሮችና በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ለምን ወደኋላ ሄዶ ህወሃት ለሶስት ተከታታይ ጊዜያት የአፍርና የአማራን ክልል በወረራ በያዝበት፣ ባወደመበት፣ ኮሚቴ አቋቁሞ ዘረፋ የፈጸመበትን፣ በርካታ ሰብአዊና ቁሳዊ ወንጀሎች ለመቀልበስ በተካሄደው የህልውና ዘመቻ ማስታወስ የፈለገበት ምክንያት መግለጫው በተጋራባቸው አውዶች በስፋት የተሰጡ አስተያየቶች ናቸው።  

“አንድም ክልል የራሱ መከላከያ ባላደራጀበት፣ ጦር ማደረጃት በህገመንግስቱ የፌደራል ስልጣንና ስራ መሆኑ በግልጽ ተቀምጦ ሳለ ከባድ መሳሪያ ሲያጓጉዝ የተወሰደ እርምጃ በምንም መስፈርት ህገወጥ ሊባል አይችልም። መንግስት ከልክ በላይ ታጋሽ ሆኗል” በማለት አስተየት የሰጡም አሉ። 

“የብልፅግና ስርዓት የትግራይ ህዝብ ለማጥፋት በፈፀመው ጀኖሳይድ በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለስደት፣ ለመፈናቀልና ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ውድመት መፈፀሙ ሳይረካ በማሕበረሰብ ዓለም ፊት የፈረመው የፕሪቶርያው ስምምነት በማፍረስ የትግራይ ህዝብ የማጥፋት ዓላማው በጦርነት ለመጨረስ እና የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ሁሉንም ግፍና በደል እየፈፀመ ቆይቷል። አሁንም እየፈፀመ ይገኛል” ሲል ክልሉ በመግለጫው አስፍሯል። ቀደም ሲል “ወሬ ነው በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አልሞተም” ያሉት ዶክተር ደብረጺዮን ዛሬ ደግሞ ሚሊዮን ሰዎች መሞታቸውን ማስታወቃቸውም ሌላው ለትችትና ለወቀሳ የዳረጋቸው ጉዳይ ሆኗል።  

የህወሃት ደጋፊ ሚዲያዎች፣ የቀድሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና የመቀሌ ዩኒዘርስቲ በትግራይ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ጄኖሳይድ የፈጸሙት ሻዕቢያና የአማራ ፋኖ ኃይሎች እንደሆኑ በጥናት ማረጋገጡን፣ መከላከያ የሚወነጀልበት አግባብ በመቶኛ አምስት ፐርሰንት እንኳን እንደማይሆን ይፋ ማድረጋቸውን ያወሱ፣ ከተጠቀሱት ሁለቱ አካላት ጋር “ጽምዶ” ብሎ አብሮ የሚሰራው ህወሃት እንዲህ ያለ መግለጫ ማውጣቱ በትግራይ ሕዝብ መቀለድ ነው በማለት የስምረት ፓርቲ አመራር ለአዲስ ሪፖርተር ተናግረዋል።  

“መንግስት በጀት፣ ነዳጅ፣ መድሓኒትና ጥሬ ገንዘብ በመከልከል ማምበርከክ ያልቻለውን ህዝብ በጎላጭ ሌላ ዙር ወረራ በማድረግ ጀኖሳይድ ለመፈፀምና ሰይጣናዊ ተግባሩ ለመከወን የሚያስችለው የማይሳካ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል” በማለት ክስ ያሰማው መግለጫው፣ የተዘረዘሩት ማዕቀቦች በትክክል ተፈጽመው ከሆነ ይህ የሆነበትን ህጋዊና ህገመንግስታዊ ምክኛቶች አልገለጸም።  

የስምረት አባሉ “ጽንፈኛው ቡድን ለክልሉ የሚላከውን በጀት ለታጣቂ ደሞዝና ቀለብ ያውልዋል እንጂ ለሕዝብ የሚያፈይደው ነገር የለም” ሲሉ አቶ ጌታቸው በስልጣን ላይ እያሉ “የሚላክልኝን በጀት የማውለው ለታጣቂዎች ደሞዝና ቀለብ ነው” ያሉትን አስታውሰዋል። “ዓላማው ጀርባ የሰጠውን ህዝብ ልብ ለማኘት ነው። እሱም መግለጫው መጨረሻ ላይ ሰፍሯል” ብለዋል።  

ስለተፈናቃዮች አለመመለስና በጦርነት ስለወደሙ የልማት ተቅቋማት ያነሳው መግለጫው “የብልፅግና ስርዓት በትግራይ ዳግም ለመፈፀም እየተዘጋጀ ያለው ወረራ የሚያረጋግጠው እውነታ ፣ ስርዓቱ ከጦርነት ውጪ መኖር እንደማይችል ሁነኛ ማሳያ ነው” ነው ሲል መሳሪያ በጫኑ ከባድ ተሸከርካሪዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የዳግም ጦርነት መነሻ አድርጎ አቅርቧል። 

አቶ ጌታቸውም ሆኑ የቀድሞ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላት ተፈናቃዮችን አግቶ የያዘውና የፖለቲካ መደራደሪያ ያደረጋቸው በዶከተር ደብረጽዮን የሚመራው ህወሃት እንደሆነ መናገራቸው አይዘነጋም።  

“የትግራይ ህዝብ ሉአላዊነቴ ይከበር፣ ወደቄዬ ልመለስ፣ ፍትሕና ተጠያቂነት ይረጋገጥልኝ፣ በዘላቂነት መልሶ የቋቋም መብቴ ይከበር፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቴ ይረጋገጥ በማለቱ ምክንያት፣ ከበባና ክልከላ፣ የድሮን ድብደባ ወዘተ የሚሉ ምላሾች እየተሰጡት ይገኛሉ። የትግራይ ህዝብ ለጠየቀው ፍትሕና ላሳየው ትዕግስት እንደ ፍርሐት ተቆጥሯል” ሲል ጦርነት ሽሽት ወደ አዲስ አበባና የተለያዩ አካባቢዎች ያመለቱትን የትግራይ ተወላጆች ጦርነት ናፋቂ አድርጎ መግለጫው አስታውቋል።  

መግለጫው በማሳረጊያው የዓለም መንግስታት በብልጽግና ላይ ጫና እንዲያሳድሩም ጠይቋል። የፕቲቶሪያው ስምምነት መፍረሱን ህወሃት በተደጋጋሚ መፈረሱን፣ በዚህም ሳቢያ የአገልግሎት ዘመኑ ያለፈውንና በስምምነቱ መሰረት ህገወጥ የተባለውን ምክርቤት መመለሱን መግለጹ ይታወሳል። በዚሁ መግለጫ ላይ “መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ ጥቃት ፈጽሟል” ሲል ከሷል። የስምረት አመራሩ እንዳሉት “ለጽንፈኛው ቡድን ህገመንግስት መጣስ ይፈቀዳል። ሲፈልገው ከሱዳንና ኤርትራ ጋር ይስማማል። ሲያሻው የሰላም ስምምነቱ ፈርሷል ብሎ ያውጃል። ሲያሻው ደግሞ የሰላም ስምምነቱ ተጥሶ ተጠቃሁ ይላል። ይህ ስብስብ ቀደም ሲል የሚያስበልት ያጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው” 

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related