አዲስ ሪፖርተር – የጀርመን ድምጽ ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸውን ሰዎችና ድርጅት ተወካዮች በማቅረብ ሙያዊ ክብር የጎደለው ዘገባ ማሰራጨቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ካውንስል አቤቱታ ለማቅረብ ፒቴሽን እያሰባሰበ መሆኑን አስታወቀ። በጀርመን ሆነ በሌሎች አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሲሉ በተመሳሳይ የተቃውሞ ድምጽ እንዲያሰሙ ተጠይቋል።
“ኢትዮጵያን በተመለከተ ችግር ወይም ጉድለት አይዘገብ አንልም” ያለው ካውንስሉ፣ በኢትዮጵያዊያን ቋንቋ፣ ሆን ተብሎ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ፣ የሚለያይ፣ የጠላት አጅንዳ ያለበት ዝግጅት በማሰራጨት እየተፈጸመ ያለው ከሙያ ያፈነገጠ ዘገባ መታገስ ከማይችልበት ደረጃ መድረሱን አመልክቷል።
የጀርመን ድምጽ ኢትዮጵያዊ ባልሆኑና አቋማቸው በሚታውቅ አማርኛ ተናጋሪዎች ኢትዮጵያን ማቆሸሽና፣ ህዝብ እንዲለያይ የሚያደርግ ዘገባ በተደጋጋሚ እንደሚያቀርብ፣ በውይይት ስም አፋራሽ፣ እንዲሁም ሕዝብን ተስፋ የሚያስቆርጥ ፕሮግራም እንደሚያሰራጭ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራቲክ ካውንስል፣ “አገሬን እወዳለሁ” የሚል ዜጋ ሁሉ የሬዲዮ ዝግጅቱ አቋሙን እንዲያስተካክል የዘመቻው አካል መሆን እንዳለበት አሳስቧል።
በጀርመን ድምጽ በሚተላለፉት ተከታታይ አፍራሽና ሙያዊ ክብር የጎድላቸው ዘገባዎች ሳቢያ የዝግጅት ክፍሉን፣ በተለይም ነጋሽ መሐመድን ለማነጋገር ቢሞክሩም ምንም መሻሻል እንዳላየ ካውንስሉ ለአዲስ ሪፖርተር አመልክቷል።
በመሆኑም በሰሜን አሜሪካ የሚኖረው የካውንስሉ ስራ አመራር ፊርማ ማሰባሰብ መጀመሩን አስታውቋል። በቅርቡም በይፋ ፒቴሽኑን እንደሚያስገባ አስታውቋል። የጀርመን ድምጽ የአዲስ አበባ ዘጋቢዎች ሙያውን አክብረው አልሰሩም በሚል የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ፈቃዳቸውን መሰረዙ አይዘነጋም።
እንደ ቪኦኤ፣ ቢቢሲ፣ የጀርመን ድምጽ የመሳሳሉት ሚዲያዎች ውስጥ የሚሰሩ ውል ሲገቡ ለተቀጠሩበት አገር ፍላጎትና ብሄራዊ ጥቅም እንደሚሰሩ በመጥቀስ፣ በዚህ ውል መሰረት አገራቸው ላይ የማይረሳ ክህደት የፈጸሙ በደንብ ተጣርቶና ባለሙያዎች አጥንተውት በባንዳነት ሊፈረጁ እንደሚገባ ባለሙያዎች ለአዲስ ሪፖርተር በጽሁፍ አስተያየት ማቅረባቸው አይዘነጋም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






