አዲስ ሪፖርተር -በትግራይ ክልል እየተባባሰ የመጣውን ሁለንተናዊ ቀውስ ለማስቆም፣ እንዲሁም ለፌዴራል መንግሥትና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ ለማቅረብ አፈሳ ይቁም፣ ሰላም ይስፈን በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ።
የሰላማዊ ሰልፉ አዘጋጅ የሆነው የትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት እንዳስታወቀው፤ ይህ ታሪካዊ ሰልፍ በመጪው ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ይካሄዳል።
ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎች ሕይወት ከፍተኛ ምስቅልቅል ውስጥ መውደቁን ጠቅሶ፤ አካባቢው ለከፋ የኢኮኖሚ ድቀት፣ ለማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ቀውሶች መዳረጉን አመልክቷል።
ይህ አልበቃ ብሎም፣ በትግራይ የሚንቀሳቀሰው መንግሥት ሕገ-ወጥ ቡድን እያለ የሚጠራው ትህነግ ለሌላ አውዳሚ ጦርነት ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝና ወጣቶችንም ለአስገዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት እያፈሰ በመሆኑ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ስጋት መጋረጡን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።
ሰልፉ በዋናነት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ በትግራይ ወጣቶች ላይ እየተፈጸመ ያለው የግዳጅ አፈሳና እገታ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ እንዲሁም ጦርነት ይበቃል የሚሉ መልዕክቶችን በማስተላለፍ የፌዴራል መንግሥትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቀውሱን ለማስቆም የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለማሳሰብ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
በአዲስ አበባና በአካባቢው የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች በዕለቱ በመስቀል አደባባይ በመገኘት ድምፃቸውን እንዲያሰሙ የጠቆመው ምክር ቤቱ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከትግራይ ተወላጆች ጎን በመቆም አጋርነቱን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም በትግራይ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በዕለቱ ከቤታቸው ባለመውጣት የቤት ውስጥ አድማ እንዲያደርጉና ለሰላም ጥሪው ያላቸውን ድጋፍ እንዲገልጹ ምክር ቤቱ መልዕክቱን አስተላልፏል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






