የቻይናና ግብፅ ባለ21 ነጥብ ስምምነት…የናይል ውኃና የቀይ ባሕር ጉዳይ ለኢትዮጵያ ምን መልዕክት አለው?

Date:

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ —  የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት በቻይናና በግብፅ መካከል ያለውን የ70 ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማክበር ከተደረገ የፕሮቶኮል ጉብኝት በላይ የቀጠናውን የፖለቲካ ስሌት የሚያሳይ ጉዳይ ሆኗል።

ቤጂንግና ካይሮ በዚህ ጉብኝት 21 ነጥቦችን የያዘ የጋራ መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ በመግለጫው ውስጥ ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚጠቅስ የፖለቲካ ቃል ባይኖርም፣ የናይል ውኃና የቀይ ባሕር አስተዳደር ላይ የተቀመጡት አቋሞች ለኢትዮጵያ በተለይ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው።

በጋራ መግለጫው ሦስተኛ ነጥብ ላይ ቻይና ናይል ለግብፅ “ዋና የሕይወት ምንጭ” መሆኑን መረዳቷን በመግለጽ፣ ግብፅ የውኃ፣ የምግብ ደኅንነቷንና የልማት ጥቅሞቿን ለመጠበቅ ሕጋዊ መብት እንዳላት አረጋግጣለች። በመቀጠልም ሁለቱ አገራት ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት ዓለም አቀፍ ሕግን፣ በተለይም “ጉዳት ከማድረስ መቆጠብ” የሚለውን መርህ እንዲያከብሩ ጠይቀዋል።

ይህ ነጥብ በውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲ ውስጥ ቀላል የሚባል ቃል አይደለም። ምክንያቱም ግብፅ በናይል ጉዳይ ላይ ለዓመታት ስታቀርበው የቆየውን የውኃ ደኅንነት አጀንዳ ከቻይና ጋር ባደረገችው ስምምነት ውስጥ ማስገባቷን ያሳያል። የግብፅ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫም ካይሮ የውሃ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በቅድመ ማሳወቅ፣ በምክክርና በመግባባት መመራት እንዳለበት የምታምን መሆኗን አስቀምጧል።

ነገር ግን የጉዳዩ ዋና ፖለቲካዊ ጥያቄ የቻይና መግለጫ በራሱ ምን እንደሚል ብቻ ሳይሆን፣ ይህ አቋም ከግብፅ ጋር ከተለያዩ ጉዳዮች ጋር በአንድ ሰነድ መቀመጡ ነው። በተመሳሳይ ነጥብ ላይ ግብፅ የ“አንድ ቻይና” መርህን በጽኑ እንደምትደግፍና ታይዋንን የቻይና የማይነጠል ክፍል እንደሆነች እንደምታምን አረጋግጣለች። በሌላ አነጋገር፣ ካይሮ በቤጂንግ አንዱን የ“ዋና ጥቅም” ጉዳይ በግልጽ በመደገፍ በምላሹ የራሷን ዋና ጥቅም አስገብታለች።

ይህ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ትልቁ ጥያቄ ቻይና በናይል ጉዳይ ላይ በተለይ ከግብፅ አጀንዳ ጋር የምትቀራረብበት ደረጃ ምን ያህል ነው? የሚለው ነው። ቻይና በቀጥታ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ ስም አልጠቀሰችም፤ ኢትዮጵያንም የሚያወግዝ አቋም አልወሰደችም። ነገር ግን “ጉዳት አለማድረስ” የሚለውን የግብፅ የዲፕሎማሲ ቃል በጋራ መግለጫ ውስጥ ማስገባቷ ካይሮ የምትፈልገውን የሕጋዊ ትርጓሜ ለማጠናከር የሚያገለግል የዲፕሎማሲ ካፒታል መሆኑ አይካድም።

በዚህ ሁኔታ ግብፅ የናይልን ጉዳይ በአንድ የውኃ ድርድር ውስጥ ብቻ ለማቆየት እየሞከረች አለመሆኗ ይታያል። የውኃ ጉዳዩን ከታይዋን፣ ከቀይ ባሕር፣ ከቀጣናዊ ደኅንነትና ከታላላቅ ኃያላን ጋር ካላት ግንኙነት ጋር በማያያዝ የምትጫወትበት የዲፕሎማሲ ጨዋታ ነው። በቻይናና ግብፅ ግንኙነት ላይ የወጣው መግለጫም ሁለቱ አገራት በ“እያንዳንዳቸው ዋና ጥቅም” ላይ የጋራ ድጋፍ እንደሚሰጡ በግልጽ አሳይቷል።

ከዚህ የበለጠ አስገራሚው ግን የቀይ ባሕር ጉዳይ ነው። ቻይናና ግብፅ የቀይ ባሕር አስተዳደርና ደኅንነት “በዋናነት የባሕሩ ዳርቻ አገራት ኃላፊነት” መሆኑን፣ የእነዚህ አገራት ፍላጎትና ፈቃድም መከበር እንዳለበት ገልጸዋል።

ይህ አቋም በኢትዮጵያ በኩል በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም። ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ዳርቻ የሌላት ቢሆንም፣ ከቀጣናው የምትለይ አገር አይደለችም። በቀይ ባሕር ዙሪያ የሚከሰት የደኅንነት፣ የንግድ፣ የትራንስፖርትና የወደብ ፖለቲካ በቀጥታ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና የውጭ ፖሊሲ ይነካል። ስለዚህ “የቀይ ባሕር ጉዳይ የዳርቻ አገራት ብቻ ጉዳይ ነው” የሚለው አቋም በአካባቢው ላሉ የባሕር ዳርቻ የሌላቸው አገራትን ከቀጠናዊ ፉክክሩ የሚያስወጣ እና ግብፅ ላሰበችው ኢትዮዺያን የማደከም ስራ ትልቅ አጋዥ ሀይል ነው።

በተለይም ግብፅ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር የባሕር በር ጥቅም እንዳይኖራት የምትፈልግ ሀገር በመሆኗ ይህ አቋም ለካይሮ የሚያገለግል የዲፕሎማሲ ቋንቋ ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ግን የባሕር በር ፍላጎቷን እንደ የጦርነት ፍላጎት ሳይሆን እንደ የኢኮኖሚና የንግድ ልማት ጉዳይ በማቅረብ ላይ ቆይታለች። በዚህ መሠረት ቀይ ባሕርን በጋራ የሚጋሩ አገራት ብቻ እንደሚወስኑበት የሚያመለክት አቀራረብ በቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስር እውነታ ጋር ይጋጫል።

ይህ የሚያሳየው ግብፅ የኢትዮጵያን ጉዳይ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በትልልቅ ኃያላን ዲፕሎማሲ ውስጥ ለማስገባት የምትጥር መሆኗን ነው። ቻይና በአንጻሩ በመካከለኛው ምሥራቅና በቀይ ባሕር ያላትን ተፅዕኖ እያሰፋች ነው። የሺ ጉብኝትም ከ70 ዓመት የቻይና-ግብፅ ግንኙነት በዓል በላይ፣ ቤጂንግ በመካከለኛው ምሥራቅ የምታሳድገውን ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ የሚያሳይ ጉዞ ነው።

እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር መለየት ያስፈልጋል። የቻይና አቋም ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚቃወም አዲስ የፖሊሲ ለውጥ እንደሆነ መደምደም አይቻልም። ቤጂንግ በመግለጫው ውስጥ የኢትዮጵያን ስም አልጠቀሰችም፣ የህዳሴ ግድብንም አልጠቀሰችም። ነገር ግን ካይሮ በቻይና ዋና የሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ግልጽ ድጋፍ ሰጥታ በተመሳሳይ ሰነድ የናይል የውሃ ደኅንነት ጥያቄዋን ማስገባቷ በራሱ የዲፕሎማሲ ስሌት ነው።

ቻይና በዚህ መግለጫ የተወሰነ ቃላት መጠቀሟ ኢትዮጵያ ከቤጂንግ ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲስ የዲፕሎማሲ ስሌት ማየት እንዳለባት የሚያሳይ ጉዳይ ነው። ቤጂንግ ከካይሮ ጋር ያላትን የስትራቴጂክ ግንኙነት ማሳደግ የራሷ ጥቅም ነው፤ ግብፅም የቻይናን የአለም አቀፍ ኃይል በመጠቀም የራሷን የናይል አጀንዳ ለማጠናከር ትሞክራለች። ይህ ግን ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም በሌሎች ኃያላን ስሌት ውስጥ እንዲወሰን መፍቀድ አለባት ማለት አይደለም።

በመጨረሻም፣ የካይሮና ቤጂንግ 21 ነጥብ መግለጫ ኢትዮጵያን በቀጥታ የሚያጠቃ ሰነድ ባይሆንም ግብፅ በናይል ጉዳይ ከትልልቅ ኃያላን የውጭ ፖሊሲ ጋር በማስተሳሰር የምታካሂደውን ዲፕሎማሲ የሚያሳይ አዲስ ምልክት ነው። የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ጉዳይም የአንድ አገር የውሃ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ ልማት፣ የኃይል ደኅንነትና የቀጣናዊ ተፅዕኖ ጉዳይ መሆኑን ይህ ክስተት እንደገና አሳይቷል።

በተመሳሳይም የቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ የሚወሰኑ አቋሞች ኢትዮጵያን ሳያካትቱ ለቀጣናው ዘላቂ የኢኮኖሚና ደኅንነት ሥርዓት መፍጠር የሚችሉ ሊሆኑ አይችሉም።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related