ደህንነትን ለማጠናከር ሲባል ለNISS ስልጣን የሰጠው “የአቪዬሽን ደኅንነት” ማሻሻያ አዋጅ ፀደቀ

Date:

አዲስ ሪፖርተር አዲስ አበባ – ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ደኅንነት ሥራዎችን በመሪነት እንዲያስፈጽም ሥልጣን የሰጠው ማሻሻያ አዋጅ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ጸደቀ። አዋጁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለመንገደኞች ደኅንነት ሲባል ተጓዦች ከሚከፍሉት የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ ላይ ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ እንዲያስከፍል ይደነግጋል። በአየር መንገዱ የሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ ወደ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ቋት ገቢ የሚደረግ ሲሆን፣ ገንዘቡ የበረራ ደኅንነትን ለማስጠበቅ እንደሚውል ሰፍሯል። የአገልግሎት ክፍያውን ከትኬት ዋጋ ላይ ደርቦ መሰብሰቡ የገንዘብ ሚኒስቴርን ሥልጣን የሚጋፋ እንዳይሆን በሚል ከምክር ቤት አባላት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦበታል። ለቀረበው ጥያቄ አሠራሩ አለምአቀፍ መሆኑ፣ ከመንግሥት የገንዘብ አሰባሰብ ሥርዓት ጋር የማይጋጭ እና ፍትሐዊ ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቶበታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ፣ በ2 ተቃውሞና በ2 ድምፀ ተዐቅቦ፣ በአብላጫ ድምፅ ያፀደቀው “የኢትዮጵያ አቭዬሽን ሴኩዩሪቲ ማሻሻያ አዋጅ” ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በዘርፉ ላይ ሰፊ የአስፈፃሚነት ሥልጣን የሰጠ ነው። በዚህ መሠረት ተቋሙ የአየር እንቅስቃሴ አገልግሎት ሰጪዎችን እና ሌሎች የሚያወጧቸውን የደኅንነት መርሐ ግብሮችና መመሪያዎችን የመገምገም፣ የማፅደቅ እንዲሁም ተገቢውን የጥራትና የቁጥጥር ተግባራትን ያከናውናል።

ኢትዮጵያ አየር መንገድ “የዓለም አቀፍ ሲቪል አቭዬሽን ድርጅት አባል” እንደመሆኑ አባል ሀገራት የበረራ ላይ የሽብር እና የሳይበር እንዲሁም የድሮን ጥቃት ሥጋቶችን ለመከላከል የተጣለባቸውን ግዴታ ለመወጣት በሕግ መደንገግ በማስፈለጉ እና የዘርፉን ደኅንነት የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ ይህ ማሻሻያ ስለመደረጉም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ መነጋገሪያ የነበረው የድንጋጌው ክፍል አዋጁየኢትዮጵያ አየር መንገድግሩፕ ለመንገደኞች ደኅንነት ሥራ ለሚውል የደኅንነት መሣሪያ ግዢ ሲባል ተጓዦች ከሚከፍሉት የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ ላይ ተጨማሪ የአገልግሎት ክፍያ እንዲያስከፍል የሚያደርገውን የተመለከተው ነው።

ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር ) ይህ አሠራር አለምአቀፍ መሆኑን እና ከመንግሥት የገንዘብ አሰባሰብ ሥርዓት ጋር የሚጋጭ እንዳልሆነ ገልፀዋል።


አዋጁ የያያቸው አንኳር ጉዳዮች


ዛሬ የፀደቀው አዋጅ  በአውሮፕላን ማረፊያዎች “አስተማማኝ ፍተሻ ላለፉ መንገደኞች ዳግም ፍተሻን በማስቀረት የተሳፋሪዎችን እርካታ ለመጨመር እና የኤርፖርቶችን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ የሚያስችሉ” የተባሉ ድንጋጌዎች ተካተውበታል። ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት“በአይሮፕላንና በአይሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎች ላይ ሕገ-ወጥ ጣልቃ ገብነት ሊፈፀምባቸው የሚችሉ ከትከሻ የሚተኮስ የአየር መከላከያ መሣሪያ ወይም ሥጋት ማድረስ የሚችል ማንኛውም ነገር ወይም ሰው አልባ አውሮፕላን ዝውውር ቁጥጥር ያደርጋል፤ ሊቃጣ የሚችል አደጋን ለመከላከል የደኅንነት ርምጃ ሥርዓት ይዘረጋል፤ እርምጃም ይወስዳል።” ከዚህ ባሻገር ተቋሙ “የመንገደኞችን ምዝገባ እና ቅድመ-በረራ መረጃ የመሰብሰብና የማሰራጨት ትግበራን ይመራል፤ ያስተባብራል። በሀገር ውስጥ ከሚያከናውናቸው የመረጃና ደህንነት ተግባራት በተጨማሪ ከሌሎች አቻ ተቋማት በመተባበር አለም አቀፍ የወንጀል ሪከርድ ያላቸውን ተጠርጣሪዎችን የሚመለከት መረጃ በመለዋወጥ ክትትል እና ቁጥጥር በማድረግ ሽብርተኝነትና የተደራጁ ወንጀሎች በመከላከል ረገድ እንደ ሀገር ያለበትን ኃላፊነት” ይወጣል።

በተሻሻለው አዋጅ “በኢትዮጵያ በኩል የሚጓዙ ተላላፊ መንገደኞች ከመነሻ ሀገር የሚደረግላቸውየደኅንነት ርምጃ አስተማማኝ መሆኑ ሲረጋገጥ መንገደኞች እና የጉዞ እቃዎቻችው ከፍተሻ ነፃ ሊሆኑ የሚችሉበት ድንጋጌ” ተካቷል።


በአዋጁ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ሥልጣን


በረቂቁ ላይ ከዚህ በፊት በተደረገ ውይይት ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትን ሥልጣን እንዳይጋፋ ጥያቄ ቀርቦ ነበር። በፀደቀው ድንጋጌ ኢሚግሬሽን የዘርፉን ቁጥጥር የሚከናወንባቸውን “የኤርፖርት ኢሚግሬሽን ኬላዎችና ስፍራዎች ይቆጣጠራል፤ የመንገደኞች ምዝገባ እና ቅድመ በረራ መረጃን
ይሰባስባል፤ የተሰበሰበውን መረጃ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተደራሽ ያደርጋል፤ ለኤርፖርቱና ለአየር ትራንስፖርት ሥርዓት ደህንነት ስጋትበሆኑ ጉዳዮች ላይ መረጃ ይለዋወጣል” በሚል በግልጽ ተቀምጧል። ዘገባው የዲድብሊው ነው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related

ሳዑዲ አረቢያ ለሱዳኑ አልቡርሃን የፈቀድችውን የጦር መሳሪያ ግዥ ፋይናንስን ሰረዘች

አዲስ ሪፓርተር- ፓኪስታን ለሱዳን ጦር ኃይል ልታቀርበው የነበረውን የ1.5...

አብን በአማራ ክልል “ትህነግን በማባባል ስሌት መዋቅራዊ በደል እየደረሰ ነው” ሲል የተቃውሞ ድምጹን አሰማ

የወልቃይት-ጠገዴ-ሰቲት ሁመራ፣ እና የጠለምት ሕዝብ በህዝብና በሀገር መስዋዕትነት የተገኘውን...

የጃልመሮ አማካሪና የኦነሰ ቃለ አቀባይ “የሕዝባዊ እምቢተኛነት” አመቻች ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚ ሆኑ

የጃልመሮ አማካሪና የኦነሰ ቃለ አቀባይ የሕዝባዊ እምቢተኛነት አመቻች ስራ...