የአሜሪካ እና ኢራን ጦርነት የሚያስቆመው የመጀመሪያ ደረጃ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈረመ

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና – የዓለምን የነዳጅ እና የኃይል አቅርቦት ገበያ እጅግ አስከፊ ወደሆነ ቀውስ ውስጥ ጥሎ የቆየው የአሜሪካ እና የኢራን ጦርነት፣ ሁለቱ አገራት ጦርነቱን በአስቸኳይ የሚያስቆም የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ በመፈራረማቸው ይፋ ሆኗል።

ይህ ስምምነት የተደረሰው ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከአራት ወራት በላይ ከቆየ በኋላ ነው። አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃቱን የጀመሩት የካቲት 21 ቀን 2018 ዓ.ም. የነበረ ሲሆን፣ በጥቃቱ የመጀመሪያ ቀን የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች መገደላቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስትራቴጂካዊው የሆርሙዝ ወሽመጥ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ ምክንያት የዓለም የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀቡና በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ስጋት መፍጠሩ ለአሁኑ ስምምነት መገፋፋት ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

ፕሬዚዳንቶቹ የፈረሙት የመጀመሪያ ደረጃ ሰነድ የሚከተሉትን ወሳኝ እርምጃዎች ያካትታል፦ የሆርሙዝ ወሽመጥን መክፈት፦ ለዓለም የነዳጅ ትራንስፖርት ቁልፍ የሆነው ወሽመጥ በድጋሚ ክፍት ይደረጋል። የማዕቀቦች መነሳት፦ አሜሪካ በኢራን ላይ የጣለቻቸውን “ሁሉንም ዓይነት ማዕቀቦች” በአስቸኳይ ታነሳለች። የመልሶ ግንባታ በጀት፦ በጦርነት ለተጎዳችው ኢራን የሚውል የ300 ቢሊዮን ዶላር “መልሶ የመገንባት” ዕቅድ ተይዟል።

ያልተቋጨው የኒውክሌር ጉዳይ፦ የዚህ ጦርነት መቀስቀስ ዋነኛ መንስኤ የሆነው የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራም ጉዳይ በዚህ ስምምነት ውስጥ ገና መፍትሔ አላገኘም። ይልቁንም ጉዳዩ ሊራዘም በሚችል የ60 ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ በዝርዝር ድርድር የሚካሄድበት ሆኖ ተመድቧል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈረንሳይ በተካሄደው የቡድን ሰባት (G7) ጉባዔ ላይ በተሳተፉበት ወቅት በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩ ሲሆን፣ ዕቅዱ በጦርነቱ ምክንያት ሊከሰት የነበረውን “ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ድብታ (Economic Depression)” የሚቀለብስ ነው ብለዋል።

ትራምፕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “የምጣኔ ሃብት ቀውስ ማየት አልፈልግም፤ ጦርነቱ እንዲቀጥል የሚደረግ ከሆነ የሚከተለው ያ ነበር” ሲሉ የተኩስ አቁሙ አስፈላጊነትን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ስምምነቱ ካልተሳካ አሁንም የኃይል እርምጃ ዝግጁ መሆኑን ሲገልጹ፦ “ከኢራን ጋር የመጨረሻው ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ በቦምብ እንደበድባቸዋለን” ሲሉ ዝተዋል።

በሌላ በኩል የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ረቡዕ ዕለት በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸውን የቴህራን ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ የኢራን ቁልፍ ተደራዳሪ እና የፓርላማው አፈ ጉባዔ ሞሃመድ ባግሃር ጋሊባፍ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ አሁንም ለአሜሪካ ያላቸው ጥርጣሬ ከፍተኛ መሆኑን አልሸሸጉም። አፈ ጉባዔው ለፋርስ ኒውስ እንደተናገሩት፦

“ጣቶቻችን አሁንም ቃታ ለመሳብ ዝግጁ ናቸው። ጠላት የተጠየቀበትን የሰላም ቋንቋ ካልተረዳ፣ እኛ ወደ ኃይል ቋንቋ ተመልሰን ለመግባት ወደኋላ አንልም”

ይህ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ለጊዜው የዓለምን ኢኮኖሚ ካንዣበበበት የቀውስ አፋፍ የታደገው ቢሆንም፣ በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ በሚደረገው የኒውክሌር ድርድር ላይ የሚኖረው ውጤት የጦርነቱን ሙሉ በሙሉ ማክተም ወይም በድጋሚ ማገርሸት የሚወስን ይሆናል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related