በደቡብ ጎንደር ተደጋጋሚ ሰቆቃ ለምን ፤ የደቡብ ጎንደር የውሃ ፖለቲካ፣ የረብ መስኖ ግድብና የግብጽ ረዥም እጆች

Date:

“እንደዚህ አይነት ጉድ ተሰምቶም አይታወቅም:: አማራ አማራን ገድሎ አንዱ አማራው በደስታ ሲፎክር ሌላኛው አማራ ደግሞ በሀዘን ሲማቅቅ መስመት በጣም ይከብዳል:: እናት አንዱ ልጇ በሌላኛው ልጇ ተገድሎ ስትቀበር፣ ወንድም በውንድሙ የቀብር ሥነስርዓት ላይ መገኘት ሲያቅተው፣ ጎረቤቱ ግራ ሲጋባ፣ ዘመድ አዝማዱ በዓይነቁራኛ ሲተያይ መመልከት በጣም ከባድ ነው:: በፊትስ የፈረደበት ኦሮሞ ነበር ጠላት ተብሎ የተፈረጀው:: አሁንስ ማን ይሆን የአማራ ጠላቱ?”እያለየሚጠይቀው ወጣት የብዙዎች ጥያቄ ነው። በስሙ የሚማልበትን ሕዝብ ማራቆት፣ መግደል፣ ማሸበር፣ በሃዘን ማጥ ውስጥ መክተት ከዚያም አልፎ የማይሽር የነገ ቂም በየጓዳው ማዳፈን።

አለባቸው ጉብሳ- ነጻ አስተያየት

ከላይ እንደ መነሻ የስፈረው ልብ የሚነካ፣ ህሊናን የሚፈታተን ተማጽኖ ከኔ ከዚህ አስተያየት ሰጪ አንደበት ወይም ብዕር የፈለቀ አይደለም፣ ትላንት ፋኖ በደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳዎች በፈፀመው የግፍ ግድያ የተንገፈገፈ የአካባቢው ኑዋሪ በማህበራዊ ሚድያ ሳግ እያነቀው፣ እንባ በጉንጮቹ ላይ እየፈሰሰ ያጋራው የጭንቀት ሃሳብ ነው። ግራ ገብቶት የምጥ ያህል እየታመመ “ጎበዝ ወዴ ወዴ እየሄድን ነው” ያለበት ነው። ይህ ገና በነበልባል ዕድሜ ላይ የሚገኝ የአካባቢው ነዋሪ ልትኩስ፣ ላውድም፣ ልግደል ከሚለው መረን የወጣ ቀረርቶ ይልቅ አሻግሮ በማየት ምን ሊመጣ እንደሚችልም ያሳሰበበት ነው፤ ጎንደርን አስቢበት ሲል ዋቢ ጠቅሶ ያስጠነቀቀበት ነው።  

ደቡብ ጎንደርን ለይቶ እየበላ ያለው ጥቃት የተፈጸመው ረቡዕ መጋቢት 19/2018 ዓም ሲሆን የመከላከያ ሠራዊት ከአካባቢው ከወጣ ከአንድ ወር ገደማ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ቀደም ሲል የተፈጸመው ውድመት አልበቃ ብሎ ድጋሚ የተፈረደበት ይህ አካባቢ የመረጃ ምንጮች እንደሚገልጹት ጥቃቱ ያነጣጠረው በአካባቢው አመራሮች ላይ ነበር። የደራ ወረዳ አስተዳዳሪ፣ የደራ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ፣ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ፣ የስማዳ ወረዳ አስተዳዳሪ እና የሐሙሲት ከተማ ከንቲባ በዚህ አሳዛኝ ጥቃት ከተገደሉት መካከል ይገኙበታል። ከላይ እንደተባለው ወንድም ወንድሙን ገደለ።

ዓርብ ዕለት መግለጫ ያወጣው የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር፣ ታጣቂዎቹ “ሕዝቡ መሪ እንዳይኖረው እና ሥርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን” ሆን ብለው በመሥራት ላይ መሆናቸውን አጥብቆ ኮንኗል። አስተዳደሩ የተሰውት አመራሮች “ለባንዳ እጅ አንሰጥም፣ ሕዝባችንን ጥለን አንሄድም” በማለት የአጼ ቴዎድሮስን ጽናት ይዘው እስከ መጨረሻው የታገሉ ጀግኖች መሆናቸውን ገልጿል። አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት ወደ ላይ ጋይንት እና ነፋስ መውጫ አካባቢዎች ዳግም መግባቱ የተነገረ ሲሆን፣ መንግሥት የፈረሰውን ሰላም ለመመለስ እና ጸረ-ሰላም ኃይሎችን ለማጽዳት ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ይህን ጽሁፍ ለሚያነቡ ሁሉ ቅድሚያ “እናት አንዱ ልጇ በሌላኛው ልጇ ተገድሎ ስትቀበር፣ ወንድም በውንድሙ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ መገኘት ሲያቅተው፣ ጎረቤቱ ግራ ሲጋባ፣ ዘመድ አዝማዱ በዓይነ ቁራኛ ሲተያይ…ሲል እየባባ በግራ መጋባት ስሜት ሃሳቡን ያጋራው ጎረምሳ ያነሳው ህሊናን የሚፈታተን፣ ልብ የሚሰብር ጉዳይ እንዲመረምሩ ጥሪ አቀርባለሁ። አማራ ክልል ሃዘን ቅጥ ያጣበት፣ ወንድም ወንድሙን ገሎ ባሩድ እያሸተተ የሚፎክርበት፣ ወንድምን ገሎ፣ ንብረትን አውድሞ በኩራት መገማሸር ትልቅ ወግ የሆነበት አማራ ክልል ምን እንዲሆን ነው የተደገሰለት? የሚለውን በጥሞና እንዲመረምሩ አሳስባለሁ።

በደቡብ ጎንደር ዞን እንደዚህ አይነት ጥቃት ሲፈፀም ይህ ሁለተኛ ጊዜ ነው። ይህ ዞን ከሌሎቹ የክልሉ ዞኖች ተለይቶ ለምን ኢላማ ሆነ? ብሎ መጠየቅ አግባብ ይሆናል። መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ሕመሙን ማወቅ የበሽታው ግማሽ የፈውስ መድሃኒት እንደመረዳት ይቆጠራል። በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ ፋኖ በአካባቢው ለምን ሊጠናከር እንደቻለ እና መንግስት በዚህ አካባቢ መከተል ስላለበት የፀረ ሽምቅ ስልት (doctrine) ለማመላከት እንሞክራለሁ።

ደብረታቦር፡ የውሃ ፓለቲካ ማዕከል

ከታሪካዊቷ የደብረታቦር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘው የረብ መስኖ ግድብ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተስፋ ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣናዊ የውሃ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ የትኩረት ማዕከል ነው።  ይህ ግድብ ከግማሽ ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር በላይ ውሃ የመያዝ አቅም ያለውና ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን ማልማት የሚችል ግዙፍ የልማት አውታር ነው። ሆኖም፣ የዚህ ፕሮጀክት መኖር ለአካባቢው ማህበረሰብ ሰላምና መረጋጋት በረከት መሆን ሲገባው፣ በተቃራኒው የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ተላላኪዎች የጥፋት በትር ሰለባ እየሆነ መምጣቱ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በአባይ ተፋሰስ ላይ ያለ እኛ ፈቃድ አንዲት ጠብታ ውሃ መጠቀም አይቻልም በማለት ያስተላለፈው መልዕክት በረብ ግድብ አካባቢ ከሚስተዋለው አለመረጋጋት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት እንዳለው መረዳት አይከብድም። ግብፅ በናይል ተፋሰስ ላይ የሚገነቡ ማናቸውንም የመስኖና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን እንደ ስትራቴጂካዊ ስጋት ስለምትመለከታቸው፣ እነዚህን የመንግስት የልማት ጥረት ለማደናቀፍ የምትጠቀመው ዋነኛ ስልት የውስጥ ግጭቶችን ማፋፋም ነው። በዚህም ምክንያት የረብ ግድብ የሚገኝበት ደብረታቦርና አካባቢው የማህበራዊ እረፍት እንዲያጣ እያደረጉት ይገኛሉ።

ለዚህ የውጭ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት ደግሞ “የህልውና ትግል” የሚል የማይጨበጥ ውል አልባ  መፈክር አንግቦ በአካባቢው እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን የአማራ የፋኖ ሽምቅ ተዋጊ ኃይልን እንደ ትሮይ ፈረስ እየተጠቀሙበት ይገኛል። ይህ ኃይል የራሱን ወንድም ለመግደልና የህዝብን ንብረት ለማውደም ወደኋላ የማይመለስ የሞራል አቅጣጫ የጠፋበት በመሆኑ የሃገርን ብሄራዊ ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት አያቅማማም። ይህም ለግብፅ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጠላቶች ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ተጨባች ያልሆነውን የፖለቲካ ግቡን ለማሳካት ሲል የልማት መሰረተ ልማቶችንና የማህበረሰቡን ሰላም መስዋዕት የሚያደርገው ይህ ቡድን፣  የኢትዮጵያን የውሃ ሉዓላዊነት ለማሳጣት ለሚሰሩ ሃይሎች ሁነኛ መጠቀሚያ ሆኗል።

ሰሞኑን በደብረታቦርና በአካባቢው ወረዳ አስተዳደሮች ውስጥ ፋኖ የፈፀመው ግድያና ያደረሰው የንብረት ውድመት እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በሰጡት ወታደራዊ የመረጃ ድጋፍ (Military Intelligence Support) ስለመሆኑ ለመረዳት ብዙም አያዳግትም። መከላከያ ሰራዊት ከአካባቢው መውጣቱን ተከትሎ፣ የፋኖ ኃይል ወደ ከተሞች በመግባት የወረዳና የዞን አመራሮችን በመግደል፣ የመንግስትና የህዝብ ንብረት በማውደም ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ይህ ዓይነቱ ተግባር ዓላማው ግልጽ ነው፤ የአስተዳደር መዋቅሩን በማዳከም አካባቢው የሁከት ቀጠና ሆኖ እንዲቀጥልና ትኩረት በልማት ላይ ሳይሆን በጦርነት ላይ ብቻ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ፋኖ የአካባቢውን ማህበረሰብ በእርስ በርስ የሚያባላ ግጭት ውስጥ እንዲገባ በማድረግና ማህበረሰቡን በማሸበር የረብ ግድብ ያለምንም እንቅፋት ለታለመለት የልማት ዓላማ እንዳይውል የማድረግ ተልዕኮውን እየፈፀመ ይገኛል። ይህም ኢትዮጵያ በአባይ ተፋሰስ ላይ ያላትን የውሃ የመጠቀም መብት በተዘዋዋሪ መንገድ የመግታት ተግር ነው።

ይህ የጥፋት ስሌት በተለይ በደብረታቦርና በረብ ግድብ አካባቢ ከአንድም ሁለት ጊዜ ተደጋግሞ ሲፈጠር ፣ ዓላማው ህዝቡን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ህይወቱ ደካማ አድርጎ ማስቀረት ነው። የግብፅ “አንዲት ጠብታ ውሃ” ዛቻ በተግባር እየተተረጎመ ያለው በፋኖ ኃይል በሚፈጠሩ ትርክቶችና ጥቃቶች ነው። ማህበረሰቡ ለዘመናት የጠበቀውን የረብ ግድብ ፍሬ ሳይቀምስ፣ በግጭትና በከፋ ድህነት ውስጥ እንዲማቅቅ መደረጉ የታቀደ ስልታዊ ጥቃት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ሱዳን ድረስ ቲኪዶ የትደረሰው ስምምነትም ይህና ይህ ብቻ ነው።

የአመራር ቁርጠኘነትና ድጋፍ

በዚህ የፀጥታ ችግር ተጠቂ የሆኑ የአከባቢው አመራሮች በማህበራዊ ገጾች ላይ ጨዋነትና ሞራል በጎደለው መልኩ እየተተቹ ይገኛል። ይህ የአመራር መተካከትን የሚጎዳ እና በአመራር ውስጥ ያሉትንም የስራ ተነሳሽነት እና የፀረ ሽምቅ ትግሉን ጥረት የሚያቀጭጭ ነው። በፀረ-ሽምቅ ውጊያ ዶክትሪን ውስጥ “የመንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር” የጦርነቱ የስበት ማዕከል (Center of Gravity) ነው። ሽምቅ ተዋጊዎች ዋነኛ ግባቸው የአካባቢውን አመራር በማሸበር፣ በመግደል ወይም ከህዝቡ በመነጠል የአስተዳደር ክፍተት (Governance Vacuum) መፍጠር ነው። ይህ ክፍተት ከተፈጠረ የጥፋት ኃይሉ የራሱን ጥላ-መንግስት በመዘርጋት ህዝቡን ለራሱ የፖለቲካ ፍጆታና ለውጭ ኃይሎች ተላላኪነት ይመቻችለታል። በመሆኑም በዚህ ወቅት የአካባቢው አመራር እንዳይደናገጥና በቆራጥነት ስራውን እንዲቀጥል ማድረግ ለወታደራዊው ድል ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካዊ ሉዓላዊነታችንም ወሳኝ ነው።

በተቃራኒው፣ አመራሩን እንደ ጥፈተኛ መተቸትና ማዳከም ለሽምቅ ተዋጊዎች “ያልታሰበ ስጦታ” የመስጠት ያህል ነው። በፀረ-ሽምቅ ውጊያ መርህ መሰረት፣ በታችኛው መዋቅር ላይ የሚገኝ አመራር ሲብጠለጠልና የሞራል ስብራት ሲደርስበት፣ በራሱ መተማመኑን ያጣል፤ ይህም ለጠላት ፕሮፓጋንዳ በር ይከፍታል። አመራሩ በራሱ መንግስትና ህዝብ እንደሚደገፍ ካላመነ፣ ለደህንነቱ ሲል ወደ ጠላት ሊያጋድል ወይም በስራው ላይ ዳተኝነት ሊያሳይ ይችላል። ይህ ደግሞ የጥፋት ኃይሎች ያቀዱትን “የመዋቅር መፈራረስ” ዓላማ ከግብ ለማድረስ ቀጥተኛ መንገድ ስለሚሆን፣ አመራሩን ከወቀሳ ይልቅ በስነ-ልቦና እና በቁሳቁስ ማጠናከር ብልህነት ነው።

የችግሩን ምንጭ በሚገባ መረዳት ደግሞ የአካባቢው አመራር ለቀጣናዊ ሴራዎች መጋለጫ እንዳይሆን ይከላከላል። ፀረ-ሽምቅ ውጊያ ከጠመንጃ ጦርነት ይልቅ “የአዕምሮና ልቦና ጦርነት” (War of Hearts and Minds) በመሆኑ፣ አመራሩ በረብ ግድብና መሰል ስትራቴጂካዊ ሀብቶች ላይ የሚሰነዘሩ የውጭ ጫናዎችን ጠንቅቆ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል። አመራሩ በሴራው ላይ ግልጽ ግንዛቤ ሲኖረው፣ የሚገጥሙትን ትንኮሳዎች እንደ ተራ የአገር ውስጥ ግጭት ሳይሆን፣ አገርን የማፍረስ ትልቅ ዓላማ አካል አድርጎ ስለሚመለከታቸው ጽናቱ ይጨምራል። ይህ ግንዛቤ አመራሩ በተፈጠረው ቀውስ ውስጥ ሳይደናገጥ፣ ለህዝቡም የችግሩን ምንጭ የሚያስረዳበትን የሞራል ልዕልና ይሰጠዋል።

በአጠቃላይ የደብረታቦርና የአካባቢው ማህበረሰብ የረብ ግድብ የህልውናው መሰረት መሆኑን ተረድቶ፣ ከማንም በላይ ሰላሙን በንቃት ሊጠብቅ ይገባል። ይህ ግድብ  ዛሬ ካልተገነባ እስከነ አካቴው ሃሳቡም መክኖ ሊቀር እንደሚችል በመረዳት ለህልውናና ለአካካባቢው የወደፊት ተስፋ ሲባል ከማናቸውም የጥፋት ኃይሎች በተቃራኒ መቆም አዋቂነት ነው። የውጭ ኃይሎች ፍላጎት ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት አዳክሞ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም ማድረግ መሆኑን በማወቅ፣ የፋኖንና መሰል የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ተግባር በጋራ መመከት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ የሚረጋገጠው የአካባቢን ሰላምና የስትራቴጂካዊ ተቋማትን ደህንነት በማስጠበቅ ብቻ ነው። ለዚህ ነው ደቡብ ጎንደር ተለይቶ ዒላማ የሆነው፣ የወደመው፣ ከውጭ የመጣ ጠላት እንኳ በማይፈጽመው መልኩ ተደራራቢ ግፍ ይተፈተመው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related