የአሜሪካ ዲፕሎማት እና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች ህውሃትን ማዕቀብን እንደሚጣል አስጠነቀቁ

Date:

ወደ መቀለ የመጣው የአሜሪካ ልኡክ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች የተገኙበትና፣ ህወሃት በአሸባሪነት ከተፈረጀው የሱዳን መንግስትና ከሌሎች በሽብር ስማቸው ከሚነሳ ቡድኖች ጋር አብሮ እንደሚሰራ በይፋ እየተነገረ ባለበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩ ቀላል እንዳልሆነ አመላካች ነው” ብለዋል። አክለውም ጣጣው በውጭ የሚኖሩ ምስኪን ዜጎችንም ችግር ላይ እንዳይጥል ስጋታቸውን ገልጸዋል

አዲስ ረፖርተር ዜና – የአሜሪካ መንግስት ዲፕሎማቶችና ከፍተኛ ወታደራዊ አዝዦች መቀለ ተገኝተው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) ቁልፍ አመራሮችና የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን ማነጋገራቸውን የአዲስ ሪፖርተር የትግራይ ተባባሪ አስታወቀ። የሃብት እገዳና የዝውውር ማዕቀብን ጭምሮ ጠንካራ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል ተነግሯቸዋል። ከሳምንት በፊት ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደን አነጋግረው ነበር።

የውይይቱ ዝርዝር መረጃ ማግኘት ባይቻልም፣ የአሜሪካ ልዑክ ወደ መቀለ ያመሩት ህወሃት በክልሉ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እና “ወደ ጦርነት ሊያመሩ የሚችሉ ምልክቶች” ከፍተኛ ስጋት በመሆናቸው እንደሆነ ታውቋል።

ህወሃት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነቱን አደጋ ላይ የሚጥል እርምጃ የሚወስድ ከሆነ፣ አመራሮቹ በግላቸው ከባድ የኢኮኖሚ ማዕቀብና የሀብት እገዳ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ያመለከቱት የመረጃው ምንጮች፣ ጉዳዩ ከዚያም ሊሄድ እንደሚችል አመልክተዋል። ድርጅቱ በስም ከሚታወቁ የሽብር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዳለው ይፋ መሆኑ የሚቀጥለውን እርምጃ ሊያብሰው እንደሚችል አመልክተዋል።

በቅርቡ ከህወሃት ጋር ግንባር የፈጠረውና ህጋዊ መሰረት የለውም የተባለው ባይቶና መሪ አቶ ኪዳኔ ከህወሃት ጋር አብረው የሚሰሩ ድርጅቶችን ሲያብራሩ አልሸባብ፣ የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ እና የየመን ሁቲን መጠቀሳቸው ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወሳል። መቀለ ተቀምጠው የክልሉ ሚዲያ በተጋበዘበት መግለጫ ላይ ኤርትራ፣ ሰሜን ሱዳን፣ሶማሊያ፣ ኳታር፣ ሊቢያ ሳዑዲ፣ግብጽ፣ጅቡቲ ወዳጅ መሆናቸውን ያመልከቱት አቶ ኪዳኔ፣ ፋኖ፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ እና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊትም አብሯቸው እንደሆነ መናገራቸውን አይዘነጋም። ባይቶና ግለሰቡ በፓርቲው ስም የሚነገዱና የተባረሩ፣ ምርጫ ቦርድም ይህንኑ አረጋግጦ በፓርቲው ስም ማናቸውንም መግለጫ እንዳይሰጥ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ደብዳቤ ቢጽፍም አስተዳደሩ ተገባራዊ ሊያደርግ እንደማይችል ጠቅሶ ለአዲስ ሪፖርተር መግለጹም የሚታወስ ነው። አቋሙና መረጃው ግን የህወሃት እንደሆነ ባይቶና ቅንጣት እንደማይጠራጠር፣ አቶ ኪዳኔም የተነገራቸውንና የሰሙትን ሳያስቡት እንዳጋለጡ ባይቶና እምነቱን ይፋ አድርጓል።

ወታደራዊ አዛዦቹ ጦርነት የሚባል ነገር በፍጹም ሊቀሰቀስ እንደማይገባ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፣ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ፣አምባሳደር አዲስ አለም ባሌማ እና ሌሎች አራት አመራሮችን፣ እንዲሁም  ሁለት ወታደራዊ አዝዦችን  አስቀምጠው መክረዋል።

በትግራይ የተቃዋሚ ድርጅት አመራር የሆኑ ዜናው ትክክል መሆኑን አረጋግጠው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። አሜሪካ በአሁን ወቅት ቀጣናዊ የፀጥታ ስጋት ሊፈጥር የሚችል አዲስ ጦርነት የሚቀሰቅስ ከሆነ፣ በተመረጡ የድርጅቱ የፖለቲካ እና የወታደራዊ አመራሮች ላይ የሀብት እገዳ ልትጥል እንደምትችል ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንና እርምጃው ከዚያም ሊያልፍ እንደሚችል ምስማታቸውን ግን አላስተባበሉ፣።

ዜናውን ተከትሎ በመቀለ የሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር “ዝርዝሩን መናገር ባይቻልም፣ ወደ መቀለ የመጣው የአሜሪካ ልኡክ ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊዎች የተገኙበትና፣ ህወሃት በአሸባሪነት ከተፈረጀው የሱዳን መንግስትና ከሌሎች በሽብር ስማቸው ከሚነሳ ቡድኖች ጋር አብሮ እንደሚሰራ በይፋ እየተነገረ ባለበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩ ቀላል እንዳልሆነ አመላካች ነው” ብለዋል። አክለውም ጣጣው በውጭ የሚኖሩ ምስኪን ዜጎችንም ችግር ላይ እንዳይጥል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

አሁን ላይ አዲስ አበባ ያሉ ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ዜናውን እንደሚያውቁት ጠቁመው መልዕክቱ አጭር መሆኑን ተናግረዋ። አሜሪካ ዲፕሎማቶቿን እንዲሁም ከፍተኛ የጦር አዛዦቿን ወደ መቀለ ስትልክ ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ አመልክተው “መልዕክቱ እኛ ከእናንተ ጋር አይደለንም” የሚል አጭርና ግልጽ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሰሞኑን ይፋ በሆነው የአምባሳደር አዲስ ዓለም ቤሌማ ከትግራይ የዴያስፖራ አባላት ጋር ያደረጉት የድምጽ ማስረጃ እንደሚያስረዳው፣ ህወሃት በዲፕሎማሲ ውድቀት ገጥሞታል። አስተያየት ሰጪው እንዳሉት የአምባሳደሩ መልዕክት “ተባበሩና ጩኹ” ነው። ዶክተር ደብርጽዮንም ከዚህ በፊት በዲፕሎማሲው አግባብ ውድቀት እንደገጠማቸው መናገራቸውን የሚያስታውሱት እኚሁ አስተያየት ሰጪ “የህወሃት አመራር ራሱን ብቻ የሚያዳምጥ በመሆኑ በዚህ ሁሉ ችግር ተከቦ ጦርነት ለመክፈት ደፋ ቀና እያለ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።

ይህ በንዲህ እንዳለ ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ በሰላማዊ መንገድ ስልጣናቸውን እንዲያስረክቡ ዛሬ ጥያቄ ቀርቧል። “ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ርክክብ ፈጽም ጊዚያዊ አስተዳደሩ ፈርሷል” በማለት የህውሃት ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም አመልክተዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጄነራል ታደሰ ወረደ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ርክክብ የማይፈጽሙ ከሆነ ስህተት እንደሚሆን የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ አስጠንቅቀዋቸዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ ሚካኤል አስገዶም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርም “እየፈረሰ በመሆኑ” ከፌደራል መንግሥት ጋር ያለው የግንኙነት “ገመድ መበጠሱን” መልክተዋል።

ህወሃት በተደጋጋሚ ለሚሰጠው ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ፣ እንዲሁም የፕሪቶሪያ ስምምንት መፍረስ ከፌደራል መንግስት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም። ሌተናል ታደሰ ወረደ ግን “በጩኸት ስልጣኔን አልለቅም” ብለው እስክዚህ ሰዓት ድረስ በኋላፊነታቸው ላይ ናቸው።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related