አዲስ አበባ አዲስ ሪፖርተር ዜና – ሰባተኛው አገራዊ ምርጫ ሁለት መልክ ይዞ ወደ ፍጻሜው ደርሷል። ከመንግስት ወገን ከዚህ ቀደም አገሪቱ አይታ በማታውቀው ደረጃ የተቃዋሚና የግል ተወዳዳሪዎች ድምጽ በፓርላማና ክልል ምክር ቤቶች እንደሚታዩ ይናገራሉ። ከውጭ አገር በተቃውሞ ጎራ ያሉ ደግሞ “ይህ ምርጫ መካሄድ የለበትም የሽግግር መንግስት ይቋቋም” በሚልተቀባይነት ያለው መንግስት እንዳይመሰረት ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል።
እነዚህ ወገኖች በአገር ቤት እና በውጭ አገር ከሰላማዊ ሰልፎች ጀምሮ ምርጫውን እስከማወክ የሚደርስ አመጽ ለማቀጣጠል ከውጭ ኃይሎች ከሚያገኙት ሃብት በአብዛኛው አፍሰዋል። ምርጫው መካሄድ እንዳለበት የሚያምኑ ደግሞ ይህንን ሩጫ በማምከን እና ከውጭ ኃይሎች አጀንዳ በመቀበል አገሪቱን የመበተን አጀንዳ እያካሄዱ እንደሆነ በመግለጽ ዓላማቸው እንዳይሳካ ሲሰሩ ቆይተዋል።
ነገ የሚካሄደውን ምርጫ እንዳይካሄድ ከፍተኛ በጀት የመደቡ የውጭ ኃይሎች የሚችሉትን ያህል ሮጠዋል። ከግብጽና ኤርትራ ጋር በመሆን ምርጫ እንዳይካሄድ አገር ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር ተቆራኝተው ሲሰሩ የነበሩ የተለያዩ አደረጃጀቶች ህብረት ፈጥረው በይፋ በሰማይ ላይ “ምድር አንቀጥቅጥ” የሚል ዘመቻ ሲያካሂዱ እንደነበር ይታወሳል። እነዚህ አደረጃጀቶች ያቀዱት የሁከትና የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ለምን እንደከሸፈ ሪፖርት ባያቀርቡም እርስ በርስ ባለመግባባት እየተበታተኑ መሆናቸውን ከውስጥ ያሉ አባላት
ባለመግባባት ቢሸራረፉም እስከመጨረሻው ኃይላቸውን ያስተባበሩትና “የህዝባዊ አመጽ አመቻች” የሚል ስያሜ ይዘው ሲሰሩ የነበሩት ቡድኖች ከታጠቁ ኃይሎችና ምርጫውን ለማጨናገፍ ይረዱናል ካሉት ጋር በይፋና በሚስጢር እንደሚሰሩ የተለያዩ ሪፖርቶች ማመልከታቸው ይታወሳል።
የሻዕቢያ ወኪልና የኤርትራን ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆኑ በግልጽ በተለያዩ ስብሰባዎች የሚናገሩት አቶ ነዓምን ዘለቀ፤ ከወራት በፊት በተካሄደ የዙምና WhatsApp ስብሰባ የተለያዩ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶችን ሰብስቦ ምርጫውን ሕገወጥ ወይም ዲሌጂትማይዝ ስለማድረግ በግልጽ ያሰአውቅ ነበር። የሻዕቢያም ዓላማ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ነዓምን በተደጋጋሚ ይህንኑ ዘመቻ ሲመሩ የፋይናንስ ዝውውሩን እንደሚመሩ የሚናገሩ አብረዋቸው የሚሰሩ የግብረኃይሉ አባላት “እኛ ከግብጽ እና ኤርትራ የሚከፈለን ገንዘብ የለም መጠቀሚያ አታድርጉን double standard አይሰራም” ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ሁሉም አልፎ ኢትዮጵያውያን መጪውን አምስት ዓመት የሚያስተዳድራቸውን መንግሥት ለመምረጥና የማኅበራዊ ውላቸውን ለማደስ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያመራሉ።
ይህ 7ኛው አጠቃላይ ምርጫ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር፣ በጸጥታ ሁኔታና በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ አንድምታ ያለው በመሆኑ በዓለም አቀፍና በሀገር ውስጥ ታዛቢዎች ዘንድ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶታል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዝግጅት ምዕራፍ ማጠናቀቁን ባወጀበትና የምርጫ ቅስቀሳዎች በሕግ በተገደበው መሠረት ባበቁበት በዚህ ወቅት፣ የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት፣ የተመዘገቡ መረጃዎችንና ተግዳሮቶችን የሚተነትን ዝርዝር ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምን አሉ
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ እስከ ምርጫው ቀን ድረስ የሚደረገውን የመጀመሪያ የምርጫ ሂደት ፓርቲያቸው የሚችለውን አድርጓል። ሃሳቡን ለመራጮች በማስረዳትና በመቀሰቀስ የሚችለውን ሁሉ እንዳደረገ አመልክተዋል። የሚጠብቁት የምርጫውን ቀን ነው። መሰናክሎች ቢኖሩም ሁሉንም አልፈው ዛሬ ላይ መዳረሳቸውን አመልክተዋል።
የአራት ፓርቲዎች ህብረት የሆነው ትብብር ለአንድነት አጠቃላይ ቁመና አስመልክቶ ረቡዕ እለት በአቶ ጌትነት ወርቁ በኩል ለአዲስ ሪፖርተር እንዳለው የሚቻለውን ሳይሆን የማይቻለውን በማድረግ ምርጫው ላይ ደርሷል።
“ከምርጫ ራሳችሁን እንደምታገሉ በስፋት ሲነገር ነበር” ለተባሉት ከምርጫ መውጣት በአንድ ፓርቲ የሚወሰን እንዳልሆነ አመልክተው በጥምረቱ ደረጃ ስለመውጣት የተወስነ ወይም የተደረገ ውይይት እንደሌለ አመልክተዋል። ይሁን እንጂ ከመንግስት ጋር በአነዳንድ አሁን ሊገልጹት ባልፈለጉት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢህአፓ መሪ አቶ አብርሃም ሃይማኖትም የክፍፍሉን ኹኔታ በሚዲያ ቀርበው የተናገሩ ሲሆን በተለይ በአመራሩ መካከል ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተከሰተው አለመግባባት የከረረና እርሳቸውንም ከኃላፊነት እንዲወጡ እያስገደዳቸው መኾኑን ተናግረዋል።
አንከር በሚባለው ሻዕቢያ የሚያድጉመው ሚዲያ ላይ ቀርበው ለቀረበላቸው ስድብና ትችት የተሞላው ጥያቄ፣ “ከሃጂ ናቹህ እንዴት ከምርጫ አትወጡም” ለተባሉት አቶ አብርሃም ሰባት የሚያኽሉ የማዕከላዊና የሥራ አስፈጻሚ አባላት ሚስጥረሥላሴን ጨምሮ በምርጫው መቀጠል የለብንም የሚሉ ነበሩ። ሦስት ደምፀ ተዓቅቦ፤ በልዩ ሁኔታ ለምሳሌ ምርጫው ሁለት ቀን ሲቀረው እንውጣ የሚሉ ደግሞ ሁለት ነበሩ ይላሉ። በአጠቃላይ አስራ ኹለት ሰዎች ተመሳሳይ የሚባል ዓቋም ያዙ። የተቀሩት ደግሞ መቀጠል አለብን፤ ለሚቀጥለው መራራ ትግል መዘጋጀት አለብን የሚሉ በሌላ ቡድን ሆኑ። አብላጫው በምርጫው እንቀጥል የሚል ውሳኔ ማሳለፋቸውን አስታውቀዋል።
የኦሮሞ ፌደራል ኮንግራንስም በተመሳሳይ አዲስ አበባ ላይ እንደሚወድደር አስታውቆ ምርጫውን እየጠበቀ እንደሆነ አመልክቷል። የሚወዳደረው ግን ፓርቲያቸው እንዳይሰረዝ እንደሆነ በተደጋጋሚ አመልክቷል።
ሌሎች ፓርቲዎች ምንም እንኳን የተለያዩ ቅሬታዎች ቢያሰሙም ወደ ምርጫው ቀን ለመንደርደር ወስነው ዛሬ ል፤አይ ደርሰዋል።
ፋኖና ኦነግ መንገድ እንዲዘጋ መግለጫ ማውጣታቸውን ቢገልጹም፣ በየክልሉ ያሉ የጸጥታ ኃላፊዎች ከወሬ ያለፈ ምርጫውን ማወክ የሚችል ምንም አሳሳቢ ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል። የአገሪቱ የጸጥታና ደህንነት ከፍተኛ ባለስልጣናትም “ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል” ብለዋል።
የምርጫው አሃዛዊ መረጃዎችና መጠነ-ስፋት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ኢሰመቦ/NEBE) ሰብሳቢ መላትወርቅ ኃይሉ ሰሞኑን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ መሠረት፣ የዘንድሮው ምርጫ ከዚህ ቀደሞቹ በተለየ በከፍተኛ ቁጥርና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዝግጅት ተደርጎበታል።
የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር፦ ከ54 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ለምርጫው ተመዝግበዋል። ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2021 ከተደረገው 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር ሲነጻጸር በሲሶ (አንድ ሦስተኛ) ገደማ ብልጫ አለው። ከእነዚህ መራጮች መካከል ግማሽ ያህሉ የተመዘገቡት በኦሮሚያ ክልል ነው።
ልዩ የምዝገባ ሥርዓቶች፦ በቦርዱ ልዩ የዲጂታልና ማኑዋል ምዝገባ አማካኝነት 28,632 የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች (IDPs)፣ 126,498 የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም 20,122 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል።
የዕጩዎች ስብጥር፦ በድምሩ 10,438 ዕጩዎች ለምርጫው የቀረቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 2,080 የሚሆኑት ሴት ዕጩዎች ናቸው። ተፎካካሪዎቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (547 ወንበሮች) እና ለክልል ምክር ቤቶች ወንበሮች ይወዳደራሉ።
የፖለቲካ ምህዳሩና የፓርቲዎች እንቅስቃሴ
የገዥው ብልጽግና ፓርቲ (PP) በዋና ዋና የሀገሪቱ ከተሞችና በአዲስ አበባ፣ በተለያዩ የክልል ከተሞችና ደማቅና ግዙፍ የድጋፍ ሰልፎችንና የቅስቀሳ ማጠቃለያዎችን ሲያደርግ ሰንብቷል። የፓርቲው ፕሬዜዳንትና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በእነዚህ ትልልቅ የሕዝብ መድረኮች ላይ በአካል ባይገኙም ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በማስመረቅ እግረመንገዳቸውን ቀስቀሰዋል።
በሌላ በኩል፣ እንደ ትብብር ለአንድነት ፣ ኢዜማ (EZEMA)፣ አብን (NaMA) እና ሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች በምርጫው እየተሳተፉ ቢሆንም፣ የፖለቲካ ምህዳሩ እኩል አለመሆንና የተቃዋሚዎች የቅስቀሳ መድረኮች በገዥው ፓርቲ አስተዳደራዊ ጫናዎች መገደባቸውን በመጥቀስ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል። አንዳንድ የሲቪል ማኅበራትና የተቃዋሚ ጥምረቶች አንዳንድ ጉድለቶችን ቢያሰሙም ምርጫውን የሚያውክ መረጃ አላወጡም።
የተለያዩ ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ችግሮችን በመፍታት ያሳየውን ጥረት በገሃድ ያመሰገኑም አሉ። የትብብር ለአንድነት ለአዲስ ሪፖርተር እንዳለው “የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በግልጽ ማመሰገን እንፈልጋለን” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጠዋል።
የጸጥታ ስጋቶችና ምርጫው የማይካሄድባቸው አካባቢዎች
የጸጥታና ደኅንነት ጉዳይ የዘንድሮውን ምርጫ ጥላ ያረበበበት ዋነኛ ተግዳሮት ተደርጎ በስፋት ቢገለጽም ምርጫው ቀኑን ጠብቆ እንዳይካሄድ የሚያስችል መረጃ ይህ ሪፖረት እስከተጻፈበት ሰዓት ድረስ አልወጣም። በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የትጥቅ ግጭት በምርጫው አፈጻጸም ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ታጣቂ ኃይሎችና ተቃዋሚዎች እንዲሁም የውጭ ሚዲያዎች ቢያስታውቁም፣ ምርጫ ቦርድ በይፋ ምርጫ እንደማይካሄድ ይፋ ካደረጋቸው አካባቢዎች በስተቀር ምርጫው እንደሚካሄድ ይፋ ሆኗል።
የምርጫ ክልሎች መሰረዝ፦ በጸጥታ ስጋትና ቁሳቁስ ማጓጓዝ ባለመቻሉ በድምሩ 46 የምርጫ ክልሎች ላይ ግንቦት 24 ቀን ምርጫ አይካሄድም። ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው በአማራ ክልል መካሄድ ከነበረባቸው 138 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ8ቱ ላይ ምርጫው ተሰርዟል። በተመሳሳይ በትግራይ ክልልም በተወሰኑ አካባቢዎች ድምፅ የመስጠት ሂደት ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።
የፋኖ ታጣቂዎች ማስጠንቀቂያ፦ ራሱን «የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ» ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ምርጫውን “ሕገ-ወጥ” በማለት የትራንስፖርት እገዳ መጣሉንና ከዓርብ ጀምሮ እስከ ሰኞ (የምርጫው ዕለት) ድረስ በአማራ ክልል ምንም ዓይነት የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማስጠንቀቁ ይታወሳል። የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ እሸቱ ዩሱፍ ግን ማስጠንቀቂያውን የተለመደ የሽብር ፕሮፓጋንዳ በማለት አጣጥለውታል፤ ምርጫውን ለማስፈጸም የጸጥታ ኃይሉ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
የቀጠናውና የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ትኩረት
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የምሥራቅ አፍሪካ የጂኦፖለቲካ መልሕቅ በመሆኗ፣ ይህ ምርጫ ለአኅጉሪቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው የአፍሪክ ህብረት ታዛቢ ቡድን መሪ አመልክተዋል።
የኡሁሩ ኬንያታ መሪነት፦ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የ73 አባላት ያሉት የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድንን (AUEOM) በመምራት አዲስ አበባ ገብተዋል። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ “የኢትዮጵያ ምርጫ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ወሳኝ ነው፤ የራሳችንን አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካዊ ችግሮች የምናሳይበት ዕድል ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
የጋራ የጸጥታ ኮማንድ ፖስት፦ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስን ያካተተው የጋራ የጸጥታና ደኅንነት ግብረ-ኃይል፣ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅና ማናቸውንም ሁከት ለመከላከል ሙሉ ዝግጅት ማድረጉንና የምርጫ ታዛቢዎችን ደኅንነት እንደሚያስጠብቅ በይፋ አረጋግጧል።
ለግንቦት 24ቱ የኢትዮጵያ ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ሂደቱን ግልጽና ተዓማኒ ለማድረግ የአገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እንዲሁም የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች ተሰማርተዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ይፋዊ መረጃ መሠረት
የምርጫ ታዛቢዎች ስምሪት
የምርጫውን ገለልተኝነትና ነጻነት ለመከታተል በሺዎች የሚቆጠሩ ታዛቢዎች በተለያዩ ደረጃዎች ተሰማርተዋል።
የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበራት፦ በሕግ የተመዘገቡና ሙሉ በሙሉ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆኑ 55 የአገር ውስጥ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በታዛቢነት ሙሉ ዕውቅና አግኝተው በየጣቢያዎቹ ተሰማርተዋል።
የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች፦ በቀጠናውና በአኅጉር ደረጃ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ የአፍሪካ ኅብረት (AU) እና የምሥራቅ አፍሪካ በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (IGAD) ታዛቢዎቻቸውን ልከዋል። በዚሁ መሰረት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩት የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን 73 አባላትን (59 ዋና ታዛቢዎችና የቴክኒክ ባለሙያዎችን ጨምሮ) ያሰማራ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 61% ያህሉ ሴቶች ናቸው። የኢጋድ (IGAD) ልዑክ በበኩሉ 26 አባላት ያሉት ልዩ የታዛቢ ቡድን መድቧል።
የፓርቲ ወኪሎች፦ ከታዛቢዎች በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎችን ሂደት ለመታዘብ ከ220,000 በላይ የፓርቲ ወኪሎች (Party Agents) በምርጫ ቦርድ በኩል ዕውቅና አግኝተው በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተመድበዋል።
የሚዲያ ተቋማትና የጋዜጠኞች ቁጥር
ምርጫውን ለሀገር ውስጥና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የምርጫ ቦርድ ሰፊ የሚዲያ ዕውቅና መስጠቱን አመልክቷል።
የሚዲያ ተቋማት፦ በድምሩ 68 የሚዲያ ተቋማት የምርጫውን ሂደት በቀጥታ ለመዘገብ ዕውቅና አግኝተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 56ቱ የሀገር ውስጥ (የመንግሥትና የግል) ሚዲያዎች ሲሆኑ፣ 12ቱ ደግሞ ታዋቂ ዓለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮች ናቸው።
የጋዜጠኞች ቁጥር፦ ሂደቱን ከምርጫ ጣቢያዎች፣ ከማዕከላዊ ዕዝ እና ከሕዝብ ድምፅ አሰጣጥ ጀምሮ እስከ ቆጠራው ፍጻሜ ድረስ በቅርበት እንዲዘግቡ ከ1,800 በላይ (በትክክለኛው 1,814) የአገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች በይፋ ተመዝግበው ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ግንቦት 24 ቀን በሚሰጠው ድምፅ ሕዝቡ አዲሱን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመሰርት ሲሆን፣ አብላጫ ወንበር ያገኘው ፓርቲ ወይም ጥምረት በቀጣይ የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርና መንግሥት ይሰይማል። የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የመጀመሪያ ደረጃ መግለጫቸውን ግንቦት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






