ጄኔራሉ የገለጹት ሚስጢር – በቤኒሽንጉል በኩል ኢትዮጵያን የመብላት አጀንዳና የ”ሱዳን ለምን ተነካች” ለቅሶ!! የኦሮሞ ድርጅቶች “በንቃት እየተከታተልነው ነው”

Date:

አዲስ ሪፖርተር – ከሱዳን አቅጣጫ ለቅሶ ይሰማል። ለቅሶው የአንድ ወገን ሳይሆን ከሶስት ወገኖች ነው። አንደኛው የለየለት እና “ጥቅሜ ተነካ” የሚለው ጄኔራል አልቡርሃን የሚመሩት የሱዳን መንግስት ሲሆን፣ ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ “ኢትዮጵያዊ” የሆኑ ድርጅቶች እና ሚዲያዎች ናቸው። ከዚያ ሲለጥቅ እነዚህን ሁሉ የሚያሰማሩ፣ የሚደጉሙና የሚያዙት ስለመሆናቸው በገሃድ መረጃዎች አሉ። 

“ትህነግ የጥቃት አቅጣጫውን ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ለማዞር ዕቅድ አጋጅቷል” ከሚለው የሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ማብራሪያ በመነሳት አስተያየት የሰጡ፣ በጄኔራሉ ማብራሪያ ውስጥ ውለል ብሎ የሚወጣው ከላይ የተገለጹት ዋና ተዋኛኖች የሚጫወቱትን ድራማ ነው። ጽምዶ የሚባለውን ሻዕቢያ “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት” በማለት አይኑን ታጥቦ ለተባበሩት መንግስታት ያቀረብውን ተረት እና የተረቱን ተዋኞች ምስል ነው። 

ራሰ አርበኛ ዘመነ ካሴ በቤኒሻንጉል በኩል ህብረት ለመፍጠር ያደረገው ግንኙነት “በታላቅ ስትራቴጄክ ስኬት” ታጅቦ ዜናና የማህበራዊ ገጾች የቅሰቀሳ ቅመም ሆኖ ነበር። የትህነግ ጦር በተለይም አርሚ ሰባ የሚባለው በሱዳን በኩል ወደ ቤኒሻንጉል የሚያቀናውን መስመር በተለያም የቡሉ ናይል ጋዛትንና ዋና ቁልፍ ከተማ ኩምሩክን ለመያዝ ጥቃት መጀመራቸው የድሉ ጅማሬ ተደርጎ ተወስዶ ሲዘፈን ነበር። ለዚህ ሁሉ ምኞት ስኬት “ የእርስ በስር ጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ሱዳን ጋር በሚጎራበተው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የአማጺው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የሥልጠና ካምፕ መገንባቱን ከምንጮች እና ከሳተላይት ምሥሎች አረጋገጥኩ” ሲል ሮይተርስ በግብጽ በኩል የፈጠራ የምርመራ ሪፖርት አሰራጭቶ እንደነበር አይዘነጋም። 

አዲስ ሪፖርተር የሮይተርስ ዜና ከአዲስ አበባ የተሰራ መሆኑን፣ መረጃው ሁሉ ቅጥፈት እንደሆነ በመረጃና ማስረጃ በማስደገፍ ይፋ አድርጋ እንደነበር እዚህ ላይ ማስታወሱ አግባብ ይሆናል። 

ከላይ የቀረቡት ድርጅቶች ፍላጎት በጋራ በቤኒሻንጉል በኩል ጥቃት በመሰንዘር የመከላከያ ሰራዊትን ኃይል መበታተን እንደነበር፣ ለዚህም ዓላማ በዋናነት ኦነግ ሸኔ መካተት ስላለበት ጽምዶ ውስጥ እንዲገባና ከፋኖ ኃይሎች ጋር ተናቦ እንዲሰራ በትህነግ በኩል ስራው ተሰርቶ ነበር። 

የቤኒሻንጉልና ጋምቤላ፣ ሻዕቢያ፣ ፋኖ፣ ትህነግ፣ የጄኔራል አልቡርሃን ሰራዊት በግብጽ መሪነት የዝረጉት ዕቅድ የሱዳን ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይል (RSF) ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ድንበር ላይ የምትገኘውን ስትራቴጂካዊ የኩምሩክ (Kurmuk) ከተማ መቆጣጠሩን ሲያስታውቅ የዕቅዱ አካላት የሆኑት በሙሉ “የኢትዮጵያ መንግስት በስይዳን ጉዳይ ጣልቃ ገባ” በማለት በሮይተርስ ዜና እየታጀቡ ኢትዮጵያን እና መከላከያን ቀጠቀጡ። ለቅሶው የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ሲያደርግ የኖረውንና እያደረገ ያለውን ለሚረዱ አሳዛኝ፣ አስደንጋጭና አስገራሚም ነበር። 

የመጀመሪያ ወቃሽ ጃዋር መሀመድ ሲሆን፣ የፋኖ፣ የኦላ፣ የትህነግ ደጋፊ ሚዲያዎች አጥብቀው አወገዙ። “የሱዳን መንግስት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በነጻ አውጪ ስም የተደራጁትን እያግተለተለ ከሻዕቢያ ጋር አራት ኪሎ እስኪገባ ዝም ይባል” በማለት መንግስትን ከሰሱ። 

ኩምሩክ (Kumruk) በዳጋሎ የሱዳን ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይል – RSF እጅ መሆኗ ለህወሃት (TPLF) እና ኦእንግ ሸኔን ጨምሮ በስሩ ላሉ ታጣቂዎች መርዶ የሆነው በርካታ ስትራቴጂካዊ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ስለሆነባቸው ነው። ኩምሩክ በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት ውስጥ የምትገኝና ከኢትዮጵያ በተለይም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር የምታገናኝ ቁልፍ የድንበር ከተማ በመሆኗ በሌላ አነጋገር አሁን ሌተናል ጄኔራል ጻድቃን ይፋ ያደረጉት ዕቅድ በመክሸፉ ነበር። 

የሱዳን ጦር መሪ ጄኔራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት በግብጽ ገፋፊነት መሻከሩን ተከትሎ፣ ትህነግ ከSAF ጋር ሊፈጥር የሚችለው ስልታዊ ወታደራዊ ወይም የደህንነት ትብብር ነበረ። ህወሃት መንግስት እያለም ቀደም ሲል ከበረሃ ጀምሮ የነበረውን ግንኙነት ጠብቆ የኖረው አገር ለመሆን ለያዘው ዕቅድ ብቸኛዋ አምራጭ በመሆኗ ሲሆን፣  RSF የብሉ ናይልን የድንበር አካባቢዎች ሲቆጣጠር፣ ህወሃት ከሱዳን መደበኛ ጦር ጋር በቀጥታ በመሬት ላይ ገጠመ። ተዋጊዎቹ ተማርከው ታዩ። ሊደበቅ በማይችል ደረጃ የዓለም ሚዲያዎች ተቀባበሉት። 

ከዚህም በተጨማሪ የድንበር አካባቢዎች ለህወሃት የህገወጥ ንግድ፣ የገንዘብ ዝውውር እና የተለያዩ የሎጂስቲክስ ፍላጎቶችን ለማሟላት ወሳኝ ናቸው። የኩምሩክ በRSF እጅ መግባት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን የኮንትሮባንድ፣የሎጂስቲክስ መስመሮች ያሰናክላቸዋል ወይም የተጠቀሱት አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በRSF ቁጥጥር ስር ሲወድቁ ለትህነግና አጃቢዎቹ ውድቀት ይሆናል። ይህ ደግሞ የድርጅቱን የፋይናንስና የደህንነት ያደርቀዋል። 

በቅርቡ በሸረሪና አቅጣጫ የትህነግ አርሚ 70 እና የአልቡርሃን ኃይሎች ቁልፍ ቦታ ሲይዙ በደስታ የአርሚ 70 ኃይሎች ሲጨፍሩ፣ የተቃዋሚ ሚዲያዎች “ወደ ሁመራ መንደርደሪያ ቦታ ተያዘ” በሚል ልክ የኢትዮጵያ መከላከያ ተዋግቶ የተሸነፈ፣ ኢትዮጲያም ድል የተደረገች ያህል ተደርጎ ሲሰበክ የነበረው በዚሁ ስሜት መሆኑን ልብ ይሏል። 

የትህነግ ታጣቂዎች ወደ መሀል ሀገር ሰብሮ ለመግባት ከውጭ ወደ ውስጥ፣ በሱዳን በኩል በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት ለመክፈት የሚያስችል ሰፊ ወታደራዊ ስትራቴጂ መንደፉን የቀድሞው የጦር አዛዥ ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ይፋ ማድረጋቸው በዚህ ዕቅድ ዙሪያ የተሰባሰቡት ኃይሎች በሙሉ “መንግስት ለምን የRSF ኃይሎችን ይረዳል? የሚለውን ተቃውሞ እና ውግዘት ገልጦ የሚያሳይ ይሆናል። 


ይህንን ተጨማሪ ያንብቡ

የጥፋት መዝጊያ [ኩሙሩክ] የጩኸቱ ሁሉ ቁልፍ!! ሚስጢር ይፋ ሆነ  ኩርሙክ በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት ውስጥ የምትገኝና ከአሶሳ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋር የምትዋሰን ስትራቴጂካዊ ከተማ በመሆኗ፣ ይህቺ ከተማ በኢትዮጵያ ወዳጅ በሆኑ ኃይሎች እጅ መውደቋ በቤኒሻንጉል በኩል የሚገባውን የተቃዋሚ ኃይሎች እንቅስቃሴ ለማገድ ይረዳል። በተለይም የአባይን ግድብ ደህንነት አስተማማኝ ከማድረግ አንጻር ጠቀሜታው ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። እናም ኩምሩክ ልትያዝ ትችላለች በሚል ስጋት ነበር ጩኸቱ።


ጄነራሉ በትህነግ የወታደራዊ ዝግጅትና ወቅታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ቀደም ሲል በወልቃይት ግንባር ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ጥቃት አቅጣጫውን በመቀየር ባልተጠበቀ ሌላ ግንባር ሊሰነዘር እንደሚችል ሰሞኑን ቢናገሩም፣ መከላከያ አስቀድሞ የሚደረገውን ሁሉ ማድረጉን ኣዲስ ሪፖርተር ዘገባ ነበር። 

አካባቢው ሜዳ በመሆኑ ለድሮንም ሆነ ለሌሎች ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ ዘዴዎች ስለማያስቸግር፣ ዘመናዊ የጦር ተሽከርካሪዎችን ለመጠቀም የሚያመች በመሆኑ ብዙም ስጋት እንደሌለ ያስታውቁን የጸጥታ ሰው፣ በደቡብ ሱዳን በኩል መንግስት ቁጥጥሩን፣ ዲፕሎማሲውን ማጠናከሩና የግብጽ ጦር ከአካባቢው እንዲለቅ መደረጉ መንግስት በቂ መረጃ ስላለው እንደሆነ አመልክተው ነበር። 

እንደ ጄነራል ጻድቃን ገለጻ፣ ቡድኑ በአፋርና በአማራ አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ሲፈጸማቸው የቆዩትን ትንኮሳዎች አቁሟል።

ትህነግ አሁን ላይ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በኩል ሰፊ ጥቃት ከፍቶ ወደ መሀል ሀገር ለመገስገስ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የጠቆሙት ጄነራሉ፣ ይህ በትህነግ በኩል የተመረጠው አዲስ የጥቃት አቅጣጫ መንግሥት ትኩረት ባልሰጠበትና በቂ ኃይል ባላሰማራበት መስመር ድንገተኛ ወረራ ለመፈጸም የታለመ መሆኑን ማመልከታቸው እንደ መረጃ ቁልፍ ጉዳይ ቢሆንም  ሻዕቢያ ግጭትን ከኤርትራ ለማራቅ፣ ትህነግ ግጭትን ከትግራይ ለማራቅ እና አማራና ኦሮሚያ ክልል ለማስገባት የያዙት ዕቅድ አስቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን የኦነግ ስራ አስፈጻሚ ለአዲስ ሪፖርተር አመልክተዋል። የሚመለከታቸው የየአካባቢው ነዋሪዎችም ይህንን እንደማይፈቅዱ፣ አስቀድሞ የተሰራ ስራ እንዳለም አመልክተዋል። 

ከተረፈው የትህነግ ኃይል ጋር የተደባለቀው አርሚ 70 የተባለው የጦር ክፍል፣ ከሱዳን ጦር ጋር በጋራ በመሰለፍ በቤኒሻንጉል ጉምዝ መስመር እስከ ኩርሙክ ድንበር ድረስ ዘልቆ በመግባት ውጊያ ማድረጉንና ተመትቶ ወደ ኋላ ማፈግፈጉን ጻድቃን ባመለከቱበት ቃለ ምልልሳቸው፣ የፌደራል መንግሥት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ግንባሮች ኃይሉን በንቃት አሰማርቶ በተጠንቀቅ ይጠብቃል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ትህነግ አጃቢዎቹን ይዞ በጎረቤት ሱዳንን እንቅስቃሴ መጀመሩ አዲስ እንዳልሆነ፣ ለዚህም ተጨባጭ መረጃዎች እንዳላቸው አስቀድመው ሙሉ መረጃ እንዳላቸው ያመለከቱት የኦፌኮ ስራ ሌላ አመራር እንቅስቃሴውን እያጤኑ እንደሆነ አመልክተዋል። በቅርቡ ባወጡት መግለጫም ይህንኑ ጉዳይ ጠቀስ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ለዓመታት ሱዳን ውስጥ ተደራጅቶ የቆየው አርሚ 70 በቀጠናው ያለውን ወታደራዊ ሚዛን ለማስጠበቅና ከውጭ ወደ ውስጥ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመምራት በዋናነት እየተዘጋጀ ሲሆን፣ በቅርቡም አርሚ 13 የተባለው ሌላኛው ክፍለ-ጦር ድንበር ተሻግሮ ሱዳን መግባቱን ጄነራሉ አረጋግጠዋል። ሌሎች ተጨማሪ ኃይሎችም ሊከተሉ እንደሚችሉ ፍንጭ ተሰጥቷል። 

ይህ የጦር ክፍል ወደ ሱዳን ለመሻገር በሚንቀሳቀስበት ወቅት በሽራሮና ሱዳን ከገባ በኋላ በሸረሪና አካባቢዎች ሁለት ጊዜ በድሮን ጥቃት መመታቱን የገለጹት ጄነራል ጻድቃን፣ ይህ ከውጭ ወደ ውስጥ የመግባት ወታደራዊ እቅድ ከትህነግ ጀርባ ያሉና ድጋፍ ይሰጣሉ ተብለው የሚታሰቡት የግብፅ፣ የሻዕቢያ እና የጄነራል አል-ቡርሃን ጦር በቀላሉ የቅርብ የሎጀስቲክስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ታስቦ የተሰላ መሆኑን አስረድተዋል። 

የቡድኑ ዋና የጥቃት ትኩረት በቤኒሻንጉል በኩል ከውጭ ወደ ውስጥ መግባት ቢሆንም፣ በተከዜ በኩልም ወደ ወልቃይት ሰብሮ ለመግባት ሊሞክር እንደሚችልና መንግሥትም በዚህ ግንባር ከፍተኛ ወታደራዊ ኃይል አሰማርቶ እንደሚገኝ ጄነራሉ ማብራሪያቸውን አጠቃለዋል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related