ዐቢይ አህመድ አስራት ወልደየስን ከሰላሳ ሶስት ዓመት በኋላ አነገሱ፤ ያልተመረጠ መንግስት ተውኔት በብሄራዊ አጀንዳ ሊግለበጥ ነው፤ ህገመንግስት ይቀየራል!

Date:

አዲስ ሪፖርተር – ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በህክምና ሳይንስ ታላቅነታቸው ብቻ ሳይሆን ትውልድ ሁሉ ሊዘነጋው በማይችል ታላቅ የታሪክ አሻራቸው ይታወቃል። እኚህ “ታላቅ የአገር ዕንቁ” ግንባራቸውን የሰጡበት፣ ውስጣቸው በግኖ፣ ህሊናቸውን ሸፍጥና ባንዳነት አሳርሮት በሰባ አንድ ዓመታቸው ቢያልፉም፣ ዛሬ አደዋ አዳራሽ ውስጥ ከሞት ተቀሰቀሱ። 

በአገር ሉዓላዊነትና አንድነት ጉዳይ ላይ ያሳዩት የማያወላውል አቋም በታሪክ መዝገብ የሰፈረላቸው የኢትዮጵያዊያን ፈርጥ፣ ሐምሌ ስምንት ቀን ዳግም መወለዳቸው ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ኩራታቸው ነው። በ1985 ዓ.ም. (በአውሮፓውያኑ 1993) የተካሄደውን የኤርትራን የማገንጠል ሴራ ላይ በአርቆ አሳቢነት፣ የተናገሩትና የያዙት ጠንካራ አቋም ታሪካቸው በደማቅ ቀለም ከታተማቸው የኢትዮጵያ ጥቂት ምርጦች ተርታ አስቀምጧቸዋል።

የኤርትራ ሪፈረንደም ወይም “ሕዝበ ውሳኔ” ተብሎ ስም የተለጠፈለት የክህደት ትዕይነት ከመጀመሩ በፊትም ሆነ ካበቃ በኋላ፣ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ሽግግር አቅጣጫ አገሪቱን ወደ ከፋ አደጋ እንደሚመራት አስቀድመው የተነበዩ ጥቂት አርቆ አሳቢ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። ከእነዚህም ግንባር ቀደሙ የላቀው ቀዶ ጠጋኝና የአማራ ድርጅት (መዐህድ/AAPO) መሥራች ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ነበሩ።

ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ኤርትራ እንድትገነጠል የተደገሰውን ድግስ መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገለለ መሆኑን በመጥቀስ፣ ውሳኔው በሕግም ሆነ በታሪክ ተቀባይነት እንደሌለው ሞግተዋል። ባንዶች እያቅለሸለሻቸው ይህ የክህደት ውሳኔ በታሪክ እንዲመዘገብላቸው ጠይቀዋል። 

“የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አስገዳጅ አይደለም። ምክንያቱም ጉዳዩ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ፣ መሬትና ጥቅም የሚነካ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥበት አልተደረገም። ያለ ሕዝብ ይሁንታ የሚደረግ ማንኛውም የመገንጠል ውሳኔ አገራዊ ሕጋዊነት ሊኖረው አይችልም።”

የግፈኞች ሴራ ኢትዮጵያን ወዴት እንደሚነዳት አስቀድመው በዓይነ ህሊናቸው እያዩ፣ ኢትዮጵያ ላይ ከሃጂዎች የሚገምዱባት የማሰሪያ ገመድ ከባድነትነት እያሰሉ፣ ይህን ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ሲናገሩ፣ ያነቡ፣ ጽጉራቸውን የነጩ፣ የታመሙ ዜጎች ጥቂት አልነበሩም። ያ ዘመን አልፎ ዛሬ ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ በታሪካዊው አደዋ እምብርት ውስጥ አብይ አሕመድ የተባሉ ጀግና ፕሮፌሰር አስራትን ዳግም አዋለዱ።

“ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር እንድትገለልና የጂኦግራፊ እስረኛ እንድትሆን የተደረገችው ባልተመረጠ መንግሥት ሸፍጥ ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ ጠ.ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሲሉ በይፋ የአርበኛውን አስራት ወልደየስ መንፈስ ቀሰቀሱ። አርበኛውን ዳግም በአደዋ የክብር ስፍራ አዋለዱ። ባንዶች በዘመን ሁሉ ስማቸው በተገረደዱበት ልክ ሲነሳና ዘር ማንዘራቸው በዘመን ሁሉ ሲያፍሩ እንደ አስራት ያሉ የአገር ኩራቶች እንደዚህ በክብር ዳግም ሲወለዱ ማየት የኢትዮጵያ ትንሳዔ ጅማሮ ለመሆኑ አብይ ማሳያ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በታሪካዊው የአገራዊ ምክክር ጉባኤ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “ኢትዮጵያ ለዘመናት ያስከበረችውን ቀይ ባህር ያልተመረጠ መንግሥት በሸፍጥ አሳልፎ በመስጠት የጂኦግራፊ እስረኛ ያደረገበት ምክንያት በውስጣችን ባለ ስንፍና እንጂ የኢትዮጵያን መሻት እና ጥቅም ማስቆም የሚችል ኃይል ስለነበረ አይደለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህዝብ፣ አገር በቁጭት በደሉን አስቦ ለመፍትሄ እንዲተባበር ጥሪ አቅርበዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በልበ ሙሉነት ያቀረቡትን ጥሪና የጥሪው መሪ እንደሆኑ ባሳዩበት መድረክ፣ “ኑ! አብረን ተስፋን፣ ይቅርታን፣ ፍቅርንና በጋራ የመኖርን ውበት እንትከል፤ በሀገር ውስጥ በሚደረግ ውይይትና ይቅርታ ችግሮቻችንን በራሳችን በመፍታት ሀገራችንን ከማንኛውም የውጭ ጣልቃ ገብነትና ተጽዕኖ እንጠብቅ። ተሳታፊዎች በሙሉ ለኢትዮጵያ ብርሃን፣ ለአፍሪካ አህጉር ታላቅ ተምሳሌት፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደግሞ እውነተኛ እረፍትንና ሰላምን የሚያመጣ ታሪካዊ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የክብር ጥሪዬን አቀርባለሁ” በማለት አንድ የመሆንን አስፈላጊነት አስያተዋል። 

ፕሮፌሰር አስራት፣ እሳቸውን መሰሎች፣ ከሃጂዎችንና ባንዳዎችን የታጋሉና ያለፉ፣ ዕድሜ ሰጥቷቸው ይህን ያዩ ሁሉም ኢትዮጵያ የተዘረፈችውን ንብረቷን ፈርሞ ያስረከበው በሕዝብ ያልተመረጠ መንግስት በመሆኑ ዳግም የመብትና የባለቤትነት ጥያቄ ለማንሳት በቅታለችና ሁሉም አንድ ላይ ህያው ናቸው። 

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1993 የኤርትራን እንድትገነጠል ሲደረግና ህጋዊ ወደቧን ከተነጠቀችበት ጊዜ ጀምሮ፣ ለዕቃ ገቢና ወጪ ንግድ የጅቡቲ ወደብ ጥገኛ ሆናለች። በዚሁ በከሃጂዎች ውሳኔና አጋፋሪነት በተወሰነ ውሳኔ ጅቡቲ እንኳን በአቅሟ ኢትዮጵያ ላይ የምትደንስ አገር እንደትሆን አድርጓታል። ለጅቡቲ አንገታችንን እንድንደፋ ያደረጉን ከሃጂዎች ብሄራዊ ክብራችንን ብቻ ሳይሆን በየዓመቱ እስከ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለጅቡቲ እንድነገብር አድርገውናል። በየቀን በአማካይ ከ4 ሚሊዮን እስከ 5 ሚሊዮን ዶላር ለወደብ ኪራይና ተያያዥ አገልግሎቶች እንድትከፍል የተፈረደባት ኢትዮጵያ ላለፉት ሰላሳ ሶስት ዓመታት የበተነችውን ይህ ሃብት ለሌላ ልማታዊ ተግባራት አውላው ቢሆን በሚል የማይቆጭ ካለ የዛሬው የምክክር አጀንዳ አባጫጓሬ የሆነባቸው ከሃጂዎች ብቻ ናቸው።

ፕሮፌሰር አስራት ጉዳዩን የሚመለከቱት በስሜት ብቻ ሳይሆን በረቀቀ ስልታዊ ትንተና ጭምር ነበርና፣ ኤርትራ ያለ ግልጽ ድርድር፣ ስምምነትና ዋስትና መገንጠሏ ኢትዮጵያን ወደፊት የማያባራ ቀውስ ውስጥ እንደሚከታት አስጠንቅቀው ነበር።

በተለይም ስለ ወደብ አጠቃቀም ሲናገሩ ስለ ወደፊቱ የኢኮኖሚ ግንኙነት፣ምንዛሬና ንግድ እንዲሁም ስለ ቀጣናው የደኅንነት ዋስትና አስቀድሞ ግልጽ የሆነና ለአገር ዘላቂ ጥቅም የሚበጅ የመንግሥታት ስምምነት መኖር እንዳለበት አበክረው አሳስበው ነበር። ይህ ቅድመ ስምምነት ሳይደረግ መለያየቱ ወደፊት አገሪቱን በኢኮኖሚና በደኅንነት ረገድ ከፍተኛ ዋጋ እንደሚያስከፍላት የተናገሩት ትንቢት፣ ከዓመታት በኋላ በ1990 ዓ.ም. የተከሰተው የድንበር ጦርነትና የወደብ እጦት ቀውስ ያስታውሳል። ዛሬ ቀጠናው ያለበትን የውሃ ላይ ፖለቲካ ለሚመለከቱ አስራትን “ነብይ በአገሩ” እንዲሉ እንዳደረጋቸው በቁጭት ያስባል። 

ለፕሮፌሰር አስራት የአገር መሠረቷና ጥንካሬዋ “አንድነቷ” ነበር። የብሔር ፖለቲካ አገሪቱን ወደ መበታተን እንደሚመራትና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማህበራዊ ትስስር እንደሚያላላው ሲያስጠነቅቁ “የኢትዮጵያ መሠረታዊ ጥንካሬ አንድነቷ ነው። ሕዝቡን በብሔር ከፋፍሎ ማስተዳደር አገሪቱን ወደማያልቅ የእርስ በርስ ግጭትና መበታተን ይመራታል። እኛ የምንታገለው ኢትዮጵያዊነትን ለማዳንና ታሪካዊ አንድነቷን ለማስጠበቅ ነው።” በማለት ነበር 

ዛሬ ላይ መለስ ብለን ታሪኩን ስንመረምረው፣ የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ድምፅ የብቸኛ ተሟጋች ድምፅ ብቻ አልነበረም፤ ይልቁንም ከአሥርተ ዓመታት በኋላ የሚመጣውን አገራዊ ቀውስና የወደብ እጦት መከራ አስቀድሞ ያየ የብልህ መሪ የሳይንሳዊ ትንበያ ድምፅ እንጂ።

ወደ ስልጣን በመጡ አካባቢ “የምናደርገውንና ለናደርግ ያሰብነውን የሚረዱት ጠላቶቻችን ናቸው” የሚል አስገራሚ ንግግር ያደረጉት አቢይ አህመድ የቀድሞውን የባንዳ ትርምስ፣ አሁን ላይ ያለውን የቀደመው ባንዳና ከሃጂ ጀሌ “አሞራ” በማለት “ቁራጭ ስጋ አንሰጥም” ሲሉ የተወሰደውን ህጋዊ የኢትዮጵያ ወደብ የማስመለስ ብሄራዊ አጀንዳ ተክለዋል። ያልተመረጠ መንግስት የሸጠውን ወደብ የተመረጠ መንግስት በሕዝብ ውሳኔ የሚያስመልስበትን ወቅት ላይ መደረሱን አብስረዋል። 

የፕሮፌሰር አስራትን ፎቶ ከፊት አስቀድመው የከሃጂዎችን ዓላማና ምኞት የሚያራምዱ ዛሬ ምን ይሉ ይሆን? “ንገራቸው። እኛ የወደብ ጥያቄ አናነሳም። በደን አድርገህ አረጋግጥላቸው የወደብ ጥያቄ አጀንዳችን አይደለም” በማለት ወኪል ወደ ሻዕቢያ ሲልኩ የሰማናቸው ጥይት ለማኞች፣ አርበኛ አስራት ዳግም በተገባር ሲወለዱ፣ እነሱ ላይነሱ ተቀብረዋል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related