የድሃ ቆዳ ገፈፋና ህጋዊ ማጅራት መቺነት / ለኢትዮጵያ ነጋዴዎች መረን መልቀቅ ማንን እንጠይቅ?

Date:

አዲስ ሪፖርተር – በአሁኑ ወቅት በአገራችን የኑሮ ውድነት የብዙዎችን ደጃፍ እያንኳኳ መሆኑ ግልፅ ነው። የዓለም አቀፍ ገበያ መዋዠቅ፣ የዶላር ምንዛሬ ለውጥ እና የሎጂስቲክስ መስተጓጎሎች ለዋጋ ንረት የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ። ሆኖም ግን፣ ከእነዚህ ምክንያታዊ ከሆኑ የምጣኔ ሀብት ሰንሰለቶች በስተጀርባ፣ በሀገር ውስጥ ነጋዴዎች ዘንድ የሚስተዋለው ትርፍን ብቻ የመከተል የስግብግብነት አባዜ፣ መርህና የቁጥጥር ክፍተቶች ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ እና ህመም የበዛበት አድርገውታል። በስመ “ነዳጅ ተወደደ” ስም እዚያም እዚህም የሚታየው ፈቃድ ያለው ዝርፊያ እስከመቼ?

በኢኮኖሚክስ ህግ መሰረት የአንድ እቃ ዋጋ እንደ ግብአቶች መወደድና መርከስ አብሮ ሊቀያየር ይገባል። በአገራችን ገበያ ግን የምናስተውለው ተቃራኒውን መሆኑ እጅግ አስገራሚ ነው። የትራንስፖርት ወይም የጥሬ እቃ ዋጋ በትንሹ ሲጨምር የሸቀጦች ዋጋ ወዲያውኑ በከፍተኛ ፍጥነት ሰማይ ይነካል። የሚገርመው ግን፣ እነዚያ የተባሉ ምክንያቶች ተቀርፈው ገበያው ሲረጋጋ እንኳን ዋጋው ለአንድም ቀን ቢሆን ዝቅ ሲል አይታይም። አንዴ የወጣ ዋጋ እዚያው የመርጋቱ ነገር፣ የነጋዴዎቻችንን አጋጣሚን የመጠቀም ፍላጎት እንጂ የገበያውን ተፈጥሯዊ ሂደት የማይከተል መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ገፋፊነት የተጠናወተው ተግባር ነው። አላዋቂነትና “ምን ይመጣል?” የሚል የሌብነት ሰነሰለት የወለደው ማጅራት መቺነትም ነው።

ይህን በነጋዴዎች ዘንድ ያለው የትርፍ ፍላጎት ወሰን አልባ መሆን የፈጠረው ችግር ዞሮ ዞሮ የሚወድቀው ህዝብ ላይ ሆኖ ሳለ ሚዲያዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የመብትና ተከራካሪዎች ወዘተ ከምንም በላይ ተቆታታሪ አካላቱ በዝርፊያው ማዕበል ውስጥ መቀውርቀራቸው ችግሩን ያጎላዋል። የተጠቀሱት አካላት እንኳ “ለምን” ሊሉ ቀዳሚ ከፋይ መሆናቸው “ነገሩ እንዴት ነው? ምን ልዩ ገቢ አላቸው?” ያሰኛል።
ነፃ ገበያ ውድድርን ያበረታታል እንጂ ፍፁም ህሊና ቢስ አያደርግም። በአሁኑ ሰዓት ከአንድ እቃ ላይ ከእጥፍ በላይ ማትረፍ እንደ ትልቅ የንግድ ብልህነትና ስኬት የሚቆጠርበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ንግድ ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን ማገልገልም ጭምር መሆኑ ቀርቶ፣ በአንድ ጀምበር ለመበልፀግ የሚደረገው ሩጫ ሆኗል። በሌላ ቋንቋ በፈቃድ የተደገፈ ሌብነት ሆኗል ማለት የሚቻልበት ደረጃ ደርሷል። ይህ አካሄድ የረጅም ጊዜ የንግድ ትስስርንና መተማመንን እያበላሸው ይገኛል። ይህ የትርፍ ጣሪያ የሌለው አካሄድ አምራቹንም ሆነ ሸማቹን የማይጠቅም፣ መሃል ላይ ያሉ ነጋዴዎችንና ደላሎችን ብቻ የሚያበለፅግ ህገወጥነት የፈጠረው ማህበራዊ ዕዳ ሆኗል።

ሰላማዊት አምሳሉ ከለንደን ለእረፍት የመጣች ትውልደ ኢትዮጵያዊ ናት። ለውሃ የምትከፍለው ገንዘብ ያስደንቃታል። አንድ ሩብ ሊትር ውሃ ከ30 ብር እስከ መቶ ብር ገዝታለች። በተመሳሳይ ደረጃ ባሉ ቤቶች ውስጥ ሩብ ሊትር ውሃ ከአርባ እስከ መቶ ይሸጣል። ቫትና ሰርቪስ ቻርጅ እኩል ነው። እሷ እንደምትለው ይህ “እብደት” ነው።
ሰላማዊት ታክላልች “ሽሮ እወዳለሁ። ቦሌ መድሃኒዓለም ፊት ለፊት ሽሮ ከ300 እስክ 1700 ብር ተመግቤያለሁ። እንዲህ ያለው የዋጋ ልዩነት ያስደነግጣል። መጠነኛ አይነቶች ቁጭ ቁጭ አድርጎ ከፈገግታ ጋር 1700 ብር የሚጠይቁ። ለማኪያቶ 499 ብር የሚያስከፍሉ …” እሷ እንደምትለው “ሌቦቹ” ነጋዴዎቹ ለሚጠይቁት ዋጋ ምክንያታዊ አይደሉም። ሰውም የተጠየቀውን ከመክፈል ውጭ “ለምን” ሲል አይሰማም። ይልቁኑም እሷ የምታውቃቸው የመንግስት አካላትና የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ “ቪአይፒ” መግባትና መስተናገድ ጀብድ ሆኖ ይሰማቸዋል።

በጎዳና ሻጮች እጅ ሃያ ብር የምትሸጠው የአንድ ሊትር የታሸገ ውሃ፣ ጥቂት ሜትሮች ተሻግሮ ወደ አንድ ካፌ ወይም ሬስቶራንት ሲገባ ሰባ ብር እና ከዚያ በላይ ሆና ትሸጣለች። የአገልግሎት ክፍያ እና የቤት ኪራይ ታክሎበት የአንድ ውሃ ዋጋ በምን ስሌት ነው ከሦስት እጥፍ በላይ የሚጨምረው? ይህ ፍፁም ምክንያታዊ ያልሆነ ልዩነት የሚያሳየው ወጥ የሆነ የዋጋ አተማመን ስርአት እና የዋጋ ዝርዝር ግልፅነት ምን ያህል በቀማኞች በዘፈቀደ እንደሚነዳ ነው። የቤት ዋጋን ደላሎች እንደሚያንሩት ሁሉ ቤታቸውን እየቀባቡና እያዥጎረጎሩ፣ መስታወቶችን ደርድረው ኪስ የሚያወልቁ ነጋዴዎች ጉዳይ የመንግስት አጀንዳው ሊሆን እንደሚገባ የዚህ ሪፖርት እምነት ነው።

የተጋነነ የዋጋ ጭማሪዎችን የሚቆጣጠር፣ የትርፍ ህዳግን የሚወስን እና ህጋዊ አሰራርን የሚያሰፍን አካል የት ገባ? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀሬ በመሆኑ ንው ከላይ ለማለት እንደተሞከረው “መንግስት ሆይ ወደየት ነህ” የሚል ጥያቄ ማንሳት ግድ የሚሆነው።

ሸቀጦችን በመጋዘን በማከማቸት ሆን ተብሎ ሰው ሰራሽ እጥረት እንዲፈጠር የሚደረገው ጥረትም ልክ እንደ ዋጋ ቁለላው በተገቢው መንገድ ሲፈተሽ አይታይም። ምንም እንኳን የንግድ መመሪያዎች ቢኖሩም፣ መሬት ላይ ያለው ቁጥጥር ግን እጅግ የላላ ወይም በዘመቻ ስራዎች ላይ ብቻ የተመሰረተ በመሆኑ ከተመልካችነት አልዘለለም። እንደሚሰማው ከሆነ ተቆጣጣሪዎች በኪሳቸው ተደልለለዋል። ሸማቹ መብቱን የሚያስከብርበትና አቤቱታ የሚያቀርብበት ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ ሕዝብ ለነጋዴዎች ዓይን ያወጣ ዝርፊያ እጅ እንዲሰጥ ተገዷል።

“ከእኔ ጋር አንድ መስሪያ ቤት የሚሰራ ጓደኛዬ ስራ ቀይሮ ገቢዎች ገባ” የሚለው አስተያየት ሰጪ “እሁድ ጠዋት ተነስቶ በየንግድ ቤቶቹ እየሄደ ብር ይለቅማል። በአጭር ጊዜ መኪናና ቤት ገዝቷል” ሲል ሌብነቱ ቅጥ ያጣ መሆኑን ያመልክታል። ምንም እንኳን ጓደኛው ቢሆንም ህዝብ ላይ ከሚፈጸመው ምዝበራ ጋር ተያያዞ እሱም ዝርፊያ ላይ መሰማራቱ ትክክል እንዳልሆነ ይፋ መናገሩ የህሊና ነጻነት እንደሚሰጠው አክሎ ይገልጻል። በግል ብዙ ጊዜ እንደመከረውም ይናገራል።

መርካቶ ካሜራ የተገጠመላቸው ተቆጣጣሪዎች ሲመጡ ካሜራ ያለው አንዱ ብቻ ስለሆነ ከሌሎቹ ጋር ጨዋታው እንደሚያልቅ የሚያውቁ ይናገራሉ። ወደ ክፍለ ሃገራት የሚጫኑ ጭነቶች በማታ እንደሚጫኑና ቀን ላይ በሞተር ሳይክልና በኮንትራት መኪና ከመኖሪያ ቤቶች ሸቀጥ እየተጫነ ወደ ፈላጊው እንደሚሰራጭ አሰራሩን የሚያውቁ ይናገራሉ። በርካታ ወንጀሎች ይፈጸማሉ።

የንግድ ስርአት የአገር ህልውና መሠረት ነው። ነጋዴው ማግኘት ያለበትን ተገቢ ትርፍ እንዲያገኝ እየተደገፈ፣ ሸማቹ ማህበረሰብ ግን ያለ አግባብ እንዳይበዘበዝ ማድረግ ይገባል። ይህ እንዲሆን ግን መንግስታዊ ተቆጣጣሪ አካላት ከቢሮ ወጥተው ገበያውን በቅርበት ሊፈትሹት፣ ግልፅ የቁጥጥርና የክትትል ስርአት ሊዘረጉ ይገባል። ከሁሉም በላይ ግን፣ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ “ካለ አግባብ ማትረፍ በረከት የለውም” የሚለው የቆየው የኢትዮጵያውያን የሞራል እሴትና የህሊና ዳኝነት ሊያንሰራራ ይገባል።

ሞራል አልባነት የተጠናወተው የኢትዮጵያ የንግድ ስርዓት መላ ካልተባለ አሁን በያዘው አካሄድ የመንግስትንም ደጅ ድጥ ማድረጉ ጥርጥር የለውም። በኢትዮጵያ በርካታ ጉዳዮች ቀድሞ የነበራቸውን በጎ እሴቶች ለቀዋል። በቅርቡ “ሸማች” ተብሎ በመንግስት በጀት፣ በነጻ በተሰጠ ዓይን ቦታ፣ ምርት በብቃት እየቀረበላቸው፣ ቀበሌና የመንግስት አስተዳደሮች ባሉበት ከተቀመጠው በላይ ዋጋ የሚጠይቁ “መንግስት ያደራጃቸው ማጅራት መቺዎች” አያየን ነው። መንግስት ያገለግላሉ ያላቸው ምስኪኖች የወጡበት ምስኪን ቤተሰብ ቆዳ ሲገፉ የዝግጅት ክፍሉ ጥቆማ ቢያደርግም መፍትሄ አልተበጀም። ይልቁኑም “እገሌ የሚባል ጥቆማ ሰጥቶናል ተጠንቀቁ” የሚል ምክረ ሃሳብ ነው የተሰጠው። ለሁሉም የደሃውን ቆዳ የምትገፉ ወደ ቀላባችሁ ተመለሱ። ተቆጣጣሪዎችም ሁሉም ልክ አለውና ከ”አልጠግብ” ባይነት ስሜት ውጡ። የትልቁ ቤት አባላት ያመጡብን “ይዞ መገኘት ነው” ፈሊጥ በደሃው ቆዳ ገፈፋ ላይ አይሁን!!

በትዕይንት አባተ

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related