አዲስ ሪፖርተር – ኤርትራ ሙሉ በሙሉ ወደ ጦርነቱ እንደምትገባ ማረጋገጫ መስጠቷን ኢንጂነር ግደይ ዘርዓጽዮን አስታወቁ። ከሻዕቢያ ዘንድ የጠራ መረጃ እንደሚያገኙ ቀደም ሲል ጀምሮ የሚነገረላቸው ኢንጂነር ግደይ ይህን ያሉት በጋራ መድረክ ስብሰባ ላይ ነው። በስብሰባው ላይ አቶ ጂሬኛ እና አቶ ነዓምን መጣላታቸው ታውቋል።
“የሰላማዊ ትግል አደራጅ እና ሕዝባዊ እምቢተኛነት አቀጣጣይ ነን” በሚል የተሰባሰቡት የጋራ መድረክ አባላት ባለፈው ሰኞ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ኢንጂነሩ ይህን ያሉት ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት ለአጭር ደቂቃ በሚደረገው የመረጃ ልውውጥ ላይ ነው።
ከሁለት ሳምንት በፊት በጋራ መድረኩ ትህነግን የሚወክሉት አቶ አባይ ግደይ “የቀናት ጉዳይ ነው፤ ውጊያው ይጀመራል” ሲሉ፣ ኢንጂነር ግደይ “ይፎክራሉ እንጂ አይዋጉም” በማለት ሻዕቢያ የሚያራምደውን አካሄድ አስተጋብተው ነበር።
ከቀድሞ የትህነግ መስራቾች መካከል አንዱ ናቸው የሚባሉት ኢንጂነር ግደይ ከሻዕቢያ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው በተለያዩ ጊዜያት መረጃዎች ወጥተውባቸዋል። ግደይ ዘርዓጽዮን ከEPLF ጋር የተሻለ ትብብር እንዲኖር የሚደግፍ አቋም ነበራቸው፤ ይህም ከሌሎች የትህነግ መሪዎች ጋር የአመለካከት ግጭት ፈጥሮ እንዳስነሳባቸው የሚያመለክቱ መረጃዎች አሉ።
ከአቶ አባይ ግደይ ጋር በተመሳሳይ አቋም ትህነግ የሚከተለውን መንገድ ለማንጸባረቅ በጋራ መድረኩ ውስጥ ከሌላ አደረጃጀት የተወከሉት ኢንጂነሩ፣ ትህነግን አስመልክቶ አቶ አባይ “መስመራቸውን ጠብቀው” ሲናገሩ፣ እሳቸው ግን ትህነግን በማያስደስት መልኩ በስብሰባው ላይ ሃሳብ እንደሚሰጡ የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ የስብሰባ ተሳታፊዎችን በመጥቀስ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።
“ከማን ጋር እንደምንዋጋ ያወቅን አይመስለኝም” በማለት የመንግስትንና የአሜሪካን ግንኙነት እሳቸው ባላቸው የዲፕሎማቲክ መስመር እንደሚያጠሩት መናገራቸውን፣ ይህም በወቅቱ የትህነግ አቋም ሆኖ ሲነገር ከነበረው ጋር ይጋጭ እንደነበር ያመለከቱ እንዳሉት ኢንጂነሩ ከሻዕቢያ ጥርት ያለ መረጃ እንዳላቸው ጥርጥር የለውም። በጋራ መድረኩ የሻዕቢያ ወኪል ከሆኑት ከአቶ ነዓምን ጋር ተናበው እንደሚንቀሳቀሱም አብይ ማስረጃ ነው።
በዕለቱ ስብሰባ ላይ ከሸረሪናው ጥቃት በኋላ የሻዕቢያ አመራሮች በቀጥታ ጦርነቱ ውስጥ እንደሚሳተፉ ማረጋገጣቸውን የገለጹት የዜናው ባለቤቶች፣ ከላይ በተገለጸው አግባብ መሰረት መረጃውን ተቀብለውታል።
እሳቸው ይህን ከተናገሩ አንድ ቀን በኋላ የኤርትራ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በትግራይ አቀባበል ሲደረግላቸው የሚያሳይ ቪዲዮ ይፋ ሆኗል። በትግራይ ክልል በጉሎመኸዳ ወረዳ ዝባን ሁጻ በተባለ ስፍራ የኤርትራ ሰራዊት እና ወታደራዊ መሪዎች በትግራይ ተዋጊ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ሲደረግላቸው ከሚያሳየው ቪዲዮ ጋር ተያይዞ የተሰማው፣ ኢንጂነሩ ካሉት ጋር ተመሳሳይ ነው። ኢንጂነር ሙሉጌታም ግደይ ዘርዓጽዮንን ተከትለው፣ የትህነግ ኃይሎች የድሮን ድጋፍ አግኝተዋል በማለት “ሰማሁ” ያሉትን ለትህነግ ሰዎች አጋርተዋል። መረጃውን የሰጡት እንዳሉት ኢንጂነር ሙሉጌታ ለሻዕቢያና ትህነግ ተወካዮች ይህን መረጃ ማካፈላቸው አስደምሟቸዋል።
በሌላ በኩል በዚሁ ስብሰባ ላይ መነጋገሪያ በሆነውና በአዲሱ ዓመት በመላው አገሪቱ ረብሻ ለማስነሳት እንዲቻል በተለያዩ ሚዲያዎች በሚደረጉ የቅስቀሳ ዘመቻ ምደባ ላይ አቶ ነዓምን “ጃዋር አይመደብም” ማለታቸውን ተከትሎ አቶ ጂሬኛ “ምን አገባህ አንተ? እሱ ተጠይቆ እምቢ ይበል እንጂ አንተ ምን ቤት ነህ?” በማለት አክርረው መሞገታቸው ተሰምቷል።
በዚሁ መነሻ በተጀመረ እሰጥ አገባ፣ አቶ ነዓምን ዘለቀ “ጃዋር ብዙ ጊዜ ሲጋበዝ ስለማይገኝ እሱን ከአሁን በኋላ አናስተናግድም” በሚለው አቋማቸው በመጽናት ሲመልሱ፣ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት ቃል አቀባይ አቶ ጂሬኛ “ይህን ማለት አትችልም” በማለት ለጃዋር ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል። በተደጋጋሚ ጃዋር ከሰራዊቱ ጋር እየሰራ እንደሆነ ተጨማሪ ማሳያ ተደርጎ የተወሰደውን የአቶ ጂሬኛ ንግግር ተከትሎ፣ አቶ ያሬድ ሰብሳቢ በመሆናቸው ለማስማማት ሲሞክሩ ታይተዋል። ጭቅጭቁ በማካረሩ እየተመናመነ ባለው የጋራ መድረክ ውስጥ ሙግቱ ሌሎችን አካቶ ጭራሽ እንዳይበተን አቶ ያሬድ በአቶ ነዓምን የጽሁፍ መልዕክት ተልኮላቸው ስብሰባውን በትነዋል።
ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ “ጃዋር አይታመንም፤ የዱርዬ ስብስብ ይዞ ነው የሚመራው” በማለት በስብሰባ ላይ ኢንጂነር ሙሉጌታ በመናገራቸው አቶ ጂሬኛ ተቃውመው በተመሳሳይ ስብሰባው መበተኑ አይዘነጋም። ከስብሰባው በኋላ ሁለቱን አካላት ለማግባባት እንደተቻለ የዜናው ባለቤቶች አመልክተዋል። ለመስከረም አዲስ ዓመት የሚደርስ የአመጽ ጥሪ ለማስተላለፍ የተደረገውን ምደባና የሚዲያ ድልድል ከወዲሁ የማናሳውቅ መሆኑን እናስታውቃለን።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






