የኢሳያስዋ ኤርትራ [የቀይ ባህር ስጋት] ሆና አስከመቼ? የኃያላኑ ጥያቄ ሆኗል፤ የኢትዮጵያ ባልተመረጠ መንግስት የተሸጠባትን ወደቧን ብሄራዊ አጀንዳ የማድረግ ግጥምጥሞሽ

Date:

የኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የቴክኖሎጂ አካላት በኤርትራ በኩል ወደ ቀጠናው እና ለሁቲዎች እንደሚተላለፉ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ሪፖርቶቹ የቀይ ባሕርን የክትትል ጥብቅነት ለማምለጥ የኢራን የጦር መሣሪያ አቅርቦቶች በኤርትራ ደሴቶች እና የባሕር ወሰኖች በኩል ተሸሽገው ለሁቲዎች የሚደርሱበት የድብቅ ዝውውር (Smuggling Network) መኖሩ ይነገራል። አንዳንዶቹ ዘገባዎች ኤርትራን፣ የየመኑን ሁቲዎች እና ኢራንን በጥቅም የተሳሰሩ የኢ-መደበኛ አጋሮች አድርገው ይፈርጇቸዋል። አሥመራ ከምዕራባውያን ማዕቀብ እና መገለል ጋር በተያያዘ የራሷን የህልውና እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማስጠበቅ ስትል ከኢራን እና ከሁቲዎች ጋር ድብቅ የደህንነት ትብብር እንደምታደርግ መረጃ ዘርዝረው የሚሞግቱ ሪፖርቶች ጥቂት አይደሉም። እናም የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር መመለስ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሚመለከታቸው አገራት ህልውና ጉዳይም ነው

አዲስ ሪፖርተር ምዕራባውያን፣ አሜሪካና እና እስራኤል ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ኃይል ሆና እንድትወጣ ያላቸውን ፍላጎት በገሃድ ማስታውቀ የጀመሩት እንዲሁ በአንድ ጀንበር ሳይሆን፣ ከቀን ወደ ቀን በቅጣናው ላይ የሚስተዋለው የህልውና ስጋት እያየለ ሲመጣ፣ ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት፣ የጥናት ቡድኖች፣ ታላላቅ ሚዲያዎች እና የፖለቲካ ተንታኞች የሚሰጡት የስጋት ማስጠንቀቂያዎች እውን መሆናቸውን ተከትሎ ነው። ከዚያም ባሻገር የኢራን ፕሮክሲ የሆኑት አካላት ቀይ ባህርን ለማነቅ በይፋ እንቅስቃሴ ማሳየት ሲጀምሩ ነው። 

በሕዝብ ብዛት እና በምስራቅ አፍሪካ ባላት ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ አቅም የተነሳ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ቦታ ማግኘቷ፣ የቻይና እና የሩሲያ የበላይነት በቀይ ባሕርና በህንድ ውቅያኖስ ላይ እንዳይነግሥ ትልቅ ማቀቢያ (Buffer zone) ይሆናል ከሚለው እሳቤ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ያለ የባሕር በር መቅረቷ ለወደፊት ህልውናዋ እና ለኢኮኖሚዋ ትልቅ ስጋት በመሆኑ፣ በቀጠናው ላይ ዘላቂ ሰላም እንዳይኖር እና ግጭቶች እንዲበራከቱ ያደርጋል የሚል ስጋትም ስላላቸው ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፍላጎቱን “ማንም የማይገታውና ጊዜውን ጠብቆ ይፈነዳል” በማለት እንደጠቀሱት!!

ኢትዮጵያ የባሕር በር አግኝታ ከምዕራባውያን ጋር በቅርብ ከሰራች፣ አጠቃላይ የቀይ ባሕር ዓለም አቀፍ የንግድ መስመር (Bab al-Mandab) የተረጋጋ እንዲሆን እና በባሕር ላይ ዘረፋ (Piracy) እና ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ ያግዛል የሚል እምነት መያዙን በርካታ ሪፖርቶች ያስረዳሉ። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምዕራባውያን እና በእስራኤል የፖሊሲ አውጪዎች እና የምርምር ተቋማት፣እንደ Washington Institute, JNS, እና Atlantic Council ባሉ መድረኮች፣ ኤርትራ ከኢራን እና ከየመኑ ሁቲዎች ጋር ያላትን የምስጢርና የታክቲክ ግንኙነት አስመልክቶ የቀረቡት ዋና ዋና ስጋቶች እና ሪፖርቶች ከላይ የተገለጸውን እውነት ያጠናክራሉ። ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ መንግስት በገሃድ “የቀይ ባህር ጉዳይ ማንም የማያስቆመው፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እውን የሚሆን” በማለት እየገለጹ ያሉት።

“የምዕራባውያንና የእስራኤል የደህንነት ሪፖርቶች ኤርትራ ለኢራንና ለሁቲዎች የሎጂስቲክስ፣ የድሮን ማስተላለፊያ እና ድብቅ የባሕር በር አገልግሎት በመስጠት በቀይ ባሕር ላይ ትልቅ የስጋት ደሴት ልትሆን ትችላለች” ብለው ሲያስጠነቅቁ፤ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ይህን ውንጀላ የኤርትራን ጥብቅ የቀይ ባሕር ቁጥጥር እና የፖሊሲ መስመር ያላገናዘበ ድምዳሜ እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። አብዛኞች የሚስማሙበት ግን የአስመራው መንግስት ለሃውቲ እና ለሱዳን የአልቡርሃን ኃይሎች መሳሪያ በማቀባበል፣ እና ከኢራን ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለውና በዚሁ አቋሙ የተነሳ በቀይ ባህር ላይ ጥቅም ላላቸው አገራት ስጋት የመሆኑ ጉዳይ ነው። 

ኤርትራ ሽብርተኞችን ከሚፈለፍለው የኢራን አገዛዝ ጋር የምታደርገው የቅርብ ግንኙነት የአሜሪካን እና የምዕራባውያንን የጂኦ-ፖለቲካ ፍላጎት በቀይ ባሕር አካባቢ አደጋ ላይ ይጥላል የሚለውን ስጋት የሚጋሩ፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ሊወገዱ እንደሚገባ እየገለጹ ነው። 

ከሰማኒያ ዓመት የዘለሉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በእድሜ ወይም በጤና ምክንያት ድንገት ቢነሱ ሀገሪቱ በከፍተኛ የፖለቲካ እና የወታደራዊ ክፍተት (Power Vacuum) ውስጥ ልትወድቅ እንደምትችል እና ይህም አጠቃላይ የመካከለኛውንና እና አፍሪካ ቀንድን፣ ሙሉ የቀይ ባህር ቀጠናን ወደ ከፋ ምስቅልቅል ሊከተው እንደሚችል የሚያስጠንቅቁ፣ ኢትዮጵያ ከፊቷ ብዙ ኃላፊነቶችና ፈተናዎች ሊያጋጥማት እንደሚችል ይገልጻሉ።

ኤርትራን ከሰሜን ኮርያ ጋር በማመሳሰል የከፋ የስጋት ትንተና በማቅረብ የሚታወቀው የአሜሪካው ትልቅ የምርምር ተቋም ከፍሪደም ሀውስ፣ በተጨማሪም የአትላንቲክ ካውንስል እና CSIS (Center for Strategic and International Studies) የመሳሰሉ ተቋማትም በተለያየ ጊዜ ይህንን ተመሳሳይነት አጀንዳ በማንሳት ትንተናዎችን አቅርበዋል። 

ኤርትራ ከኢራንና ከሁቲዎች ጋር ያላትን ጥምረት በማንሳት በቀይ ባሕር አቅራቢያ የሚገኘው የኃይል አሰላለፍ በእስራኤልና በአሜሪካ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ አደጋ መሆኑን በመግለጽ ከዓመት በፊት ሃአሬትዝ – እስራኤል ጠንካራ ሪፖርት አቅርቦ ነበር። ይህ ታዋቂ ጋዜጣ በሪፖርቱ ኤርትራ ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም አመልክቶ ነበር። 

“Eritrea Has Become Iran’s Proxy – and a Strategic Threat to Israel and the U.S.” በሚል ርዕስ ኤርትራ ለአሜሪካና እስራኤል ጥቅም ጠንቅ መሆኗን የዘበው ሃአሬትዝ ጋዜጣ፣ ይኸው የጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም ሪፖርቱ ተራና ዝም ተብሎ የተሰራጨ ሳይሆን፣ ፖሊሲ ተኮር ይዘት እንዳለው አስቀድመው እንደተናገሩት እስራኤልና ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያና አሜሪካ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነት መጠናከር የዚሁ የቅድመ ዝግጅትና ትነተና ውጤት እንደሆነ ያሰምሩበታል። 

ሃአሬትዝ ይህን ባለ በዓመቱ የጣሊያኑ ላ ቬሪታ የተባለ ታዋቂ ጋዜጣ በኤርትራ መንግሥት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ የሚጠይቅ ጽሁፍ አትሟል። በተገባደደው ሳምንት ይፋ የሆነው የጋዜጣው ጥሪ በሀገሪቱ ከፍተኛ መነጋገሪያ መሆኑን የሚያመለክቱ ሪፖርቶችም እየወጡ ነው።  

ሰፊ ተነባቢነት ያለውና በጣሊያን የሚታተመው ላ ቬሪታ (La Verità) ጋዜጣ በኤርትራ አስተዳደር ላይ አሜሪካ የማያዳግም እርምጃ እንድትወስድና አገዛዙን በኃይል ከሥልጣን እንድታስወግደው የጠየቀበት ዘገባ፣ በሀገሪቱ የፖለቲካና የሚዲያ ምህዳር ውስጥ የዕለቱ ዋና መነጋገሪያ ርዕስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከወቅቱ የቀይ ባህር ውጥረት ጋር ተያይዞ ጥሪው መቅረቡ የአውሮፓ አገራትን ስጋትና አቋም የሚያንጸባረቅ ተደርጎ ተውስዷል። 

ጋዜጣው ባሰራጨው ሰፊ ሐተታ፣ ኤርትራ ከኢራንና ከየመኑ ሁቲ ቡድን ጋር በመተባበር በቀይ ባህር ቀጠና ላይ ደቀነችው ያለውን ከፍተኛ ስጋት በዝርዝር አስፍሯል። ከኢራን ጋር በመጣመርና የኢራንን ስልት በመከተል አማጺና አሸባሪ በማደራጀት ስሟ የሚነሳው የኢሳያስ ኤርትራ፣ በዚህ ወቅት እንዲ ባለ ደረጃ እርምጃ እንዲወሰድባት የቀረበው ጥያቄ መነጋገሪያ የሆነው በበርካታ ወቅቱን ተከትሎ በሚነሱ መሰረታዊ ጉዳዮችን ተንተርሶ ነው። 

በሀገሪቱ የዜና አውታሮችና የፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ ሰፊ ትኩረት ባገኘው በዚህ ዘገባ ላይ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች፤ኤርትራ ከኢራንና ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር በጥቅም በመጋመድ በቀይ ባህር ቀጠና የሚታየውን አለመረጋጋት በማባባስ ረገድ ቀዳሚውን ድርሻ እየተጫወተች መሆኑ ተመልክቷል። በዚሁ መነሻና መዳረሻ ለቀይ ባህር ቀጠና ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ሲባል የኤርትራ አስተዳደር በኃይል ከሥልጣን መወገድ እንዳለበት ጋዜጣው አሳስቧል። 

ከፍተኛ መነጋገሪያ የሆነውን ይህ የጣሊያኑ ጋዜጣ ዘገባ፣ በቀይ ባህር ቀጠና የሚታየውን የኃይል ሚዛንና የወደፊት የጂኦ-ፖለቲካ እንቅስቃሴ በተመለከተ አዲስ አጀንዳ የተከለ ሆኗል። ጋዜጣው የጠቀሳቸው በጣሊያን የኤርትራ አምባሳደር ወቀሳው ከኢትዮጵያ መንግስት ፕሮፓጋንዳ የተነሳ መሆኑን በመጥቀስ አስተባብለዋል። 

በእስራኤል የሚታተመው ሃአሬትዝ ከዓመት በፊት «ኤርትራ የኢራን ተላላኪ (Proxy) እና በእስራኤልና በአሜሪካ ላይ ስትራቴጂካዊ ስጋት ሆናለች» በሚል ርዕስ የትችትና የትንታኔ ጽሁፍ ሲያወጣ በዋነት ያነሳው ኤርትራ የኢራን መሳሪያ ሆና በቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጉዳዮች ከየመን ሃውቲ አማጺዎች ጋር በመሆን እየፈጠረች ያለውን እንቅፋት በማሳየት ነበር። 

1. የቀይ ባሕር ደህንነት እና የወደብ ስትራቴጂካዊ ስጋት

ጋዜጣው እስራኤል ለቀይ ባሕርና ለኤደን ባሕረ-ሰላጤ የባሕር ላይ ንግድ መስመር የምትሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት መሰረት አድርጎ እንዳለው ከሆነ  ኤርትራ በደቡባዊ ቀይ ባሕር ላይ የምትገኝ ረጅም የባሕር ዳርቻና ስትራቴጂካዊ ደሴቶች ያሏት ሀገር በመሆኗ፣ እዚያ የሚፈጠር ማንኛውም የኃይል ሚዛን መዛባት የእስራኤልን የባሕር ላይ ንግድና የደህንነት እንቅስቃሴ በቀጥታ ይነካል። ይህ ለእስራኤል ቀይ መስመር ነው። 

2. የኢራን እና የሁቲዎች (Houthi) የጋራ ግንኙነት ስጋት

በየመን የሚንቀሳቀሱት የሃውቲ አማፂያን በኢራን ድጋፍ በቀይ ባሕር በሚያልፉ ዓለም አቀፍና ወደ እስራኤል በሚያመሩ መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ የሮኬትና የድሮን ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል። ጋዜጣው እንደሚያመላክተው፣ ሁቲዎች በኤርትራ የባሕር ክልል ውስጥ ጥቃት ሲፈጽሙና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ሲጥሱ የኤርትራ መንግስት አውግዞ አያውቅም። 

ኤርትራ ከኢራን መንግስት ጋር ያላትን ጥብቅ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ እንዲሁም ኢራን በቀጣናው ለምታራምደው የኢራን (Axis of Resistance) አካልና ተላላኪ ሆናለች የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱን ሪፖርቱ በመረጃና በትንታኔ አስረድቷል።

3. የእስራኤል እና የአሜሪካ የጋራ የደህንነት ስጋት

ጽሁፉ ኤርትራ በቀጠናው የምታደርገው ወታደራዊና ፖለቲካዊ አሰላለፍ የእስራኤልን ብሔራዊ ደህንነት ብቻ ሳይሆን፣ በቀይ ባሕርና በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ ያለውን የአሜሪካን ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ጥቅም አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ስጋት ስላለው ጋዜጣው ለምዕራባውያንና ለእስራኤል ፖሊሲ አውጪዎች ማስጠንቀቂያ አቅርቧል።

4. የኤርትራን አቅም እና ሚና ማሳየት

ጽሁፉ ኤርትራ የየመንን ቀውስና አለመረጋጋት ለማስቆም ተባባሪ መሆን ሲገባት፣ ከቴህራ አምባገነን መንግስት ጋር ወግኖ የቀጠናውን ውጥረት ማባባስን መርጧል ሲል ያስጠነቅቃል። ኤርትራ ከቴህራን የሚሰጣትን መመሪያ በማክበር፣ ከየመን ሃውቲ ጋር ባለት ግንኙነት፣ ለሱዳን ቀውስ ዋንኛ መሳሪያ ማስተላለፊያ በመሆኗ በቀይ ባህር ቀጣና ሰላም ለማስከበር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ላይ እንቅፋት መሆኗን አመልክቶ ነበር። 

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከግብጽ ጋር በመሆን ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ድርሽ እንዳትል በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ያደረጉት አቋም፣ ቀደም ሲል ጀምሮ ኢትዮጵያን በግፍ ከቀይ ባህር የማግለል ስሌት አካል መሆኑን በመጥቀስ የኢትዮጵያ መንግስት ተቀባይነት የሌለው አካሄድ እንደሆነ በይፋ ደጋግሞ አሳውቋል። 

በቅርቡ በዓመቱ የፓርላማ መቋጫ ንግግራቸው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ህጋዊ ሃብቷን ህዝብ ውክልና ባልሰጠውና በላተመረጠ መንግስት በግፍ እንደተወሰደባት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህንኑ የከረረ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር “ህዝብ በቁጭት” ምላሽ እየሰጠ ባለበት ሰዓት በአገራዊ ምክክሩ ላይ ጉዳዩ ብሄራዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ መደረጉ፣ ጥያቄው የፓርቲ፣ የመሪዎች ወይም የተቋማት ሳይሆን ህልውናውን በግፍ የተነጠቀ ህዝብ በመሆኑ የቀይ ባህር ጉዳይ የህግ ጥያቄም የሚነሳበት እንደሆነ እየተገለጸ ነው። 

“ከኢትዮጵያ ይልቅ ከኤርትራ ላይ መውሰድ ይቀላል” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የወቅቱን የህወሃትን አቋም በመቃወም ጥያቄ ላነሱ ባልደረቦቻቸው ምላሽ ሰጥተው እንደነበር የሚያስታውሱ ምስክሮች፣ በወቅቱ ጉዳዩን በህግ ማየት የሚቻልበት አግባብ እንዳለ አንስተው ለጠየቁ “መንገዱን ጨርቅ ያድስርግላቹህ” የሚል ምላሽ ሲሰጥ ህዝብ ግብር በሚከፍልበት ብሄራዊ ቴሌቪዝን ይሰማ እንደነበር “ጊዜ ደጉ” በማለት እየገለጹ ነው። 

ዛሬ ላይ ያለው መንግስት የያዘው አቋም ያሳሰበው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መንግስት፣ ኢትዮጵያ ላይ ታጣቂ በማደራጀት፣ በማስታጠቅና በማሰማራት፣ ራሱም በትግራይ ክልል መንግስት አፍርሰው አመራሩን በጨበጡ ተባባሪዎቻቸው አማካይነት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ወታደሮቹን በማሰማራት በኢትዮጵያ ጦርነት ለማቀጣጠል እየሰራ ነው። 

“ኢትዮጵያን በውስጥ ግጭት መጥመድ” በሚለው የውክልና መርሁ መነሻነት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያደራጃቸው የታጠቁ ኃይሎች አማካይነት ሁከት ለመፍጠር ደፋ ቀና የሚለው ሻዕቢያ፣ አሁን ላይ ባለው የቀይ ባህር ጣጣ፣ በተለይም የየመን ሃውቲዎች ሳዑዲ አረቢያ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሳቢያ ሊጋጭ ከማይገባው ወዳጁ ጋር ሊጋጭ እንደሚችል እየተጠቆመ ሲሆን፣ ሳዑዲ እና ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ አብረው ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ይፋ ሆኗል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addisreporternews
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related