አዲስ ሪፖርተር – ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለረጅም ጊዜ በዘለቁ የበርካቶች እጅ ያለባቸው ግጭቶች እተጋለጠች የዓለርማችን ሃብታም አገር ናት። የሟቾች ቁጥር እጅግ አስደንጋጭ ሲሆን መንስዔውም ይኼው ሃብቷ ነው። ከዚህ የሃብት ቅርምት ጦርነት ዜጎቿ ያተረፉት ሞት፣ ያለ ዕድሚያቸው በጦርነት መማገድ፣ መፈናቀል፣ በምግብ እጥረትና በበሽታ ለሚከሰት ሞት መጋለጥና የመሳሰሉት ናቸው።
የኮንጎ ከርስ አያ አራት ትሪሊዮን ዶላር ግምት ያለው ያልተገኘ የማዕድን የያዘ ነው። ይህም ሃብት ከአውሮፓ እና አሜሪካ ጂዲፒ የሚበልጥ እንደሚበልጥ ባለሙያዎች ሂሳብ አስልተው የሚናገሩት የዓለማችን እውነት ነው። የኮንጎ ከርስ ከያዛቸው ማዕድናት መካከል፣ ዋና ዋናዎቹ ኮልታን (ለስማርትፎኖች አስፈላጊ፣ ኮባልት ለኤሌክትሪክ መኪና ባትሪዎች ምርት የሆነ ማዕድን፣ መዳብ፣ ወርቅ፣ አልማዝ፣ ዩራኒየም እና ሃይድሮ ፓወር ይጠቀሳሉ። የሚያሳዝነው ግን ከሰባ በመቶ በላይ የሚሆኑት ዜጎቿ በቀን ከኡለት ዶላር በታች ገቢ ያላቸው፣ ጦርነት የሚጠብሳቸው መሆናቸው ነው። ከውጭ የደም ነጋዴዎች ጋር አብረው በራሷ ዜጎች የምትጠበሰው ኮንጎ ከዚህ የደም አዙሪት የማትወጣው በሃብቷ ዝርፊያ በተባበሩት “ልጆቿ” ሳቢያ ነው።
በኮንጎ፣ የታጠቁ ቡድኖች የጦርነት ወጪዎችን ለመሸፈን ማዕድን ማውጫዎችን ይቆጣጠራሉ። ይዘርፋሉ። አገሪቷን ወደ ማያበራ እልቂት ይሰዳሉ። ከ3.5 ሚሊዮን የሚልቅ ሕዝብ ሲፈናቀል ደንታ የማይሰጣቸው በዚሁ ከአለቆቻቸው ጋር ሆነው ማዕድን ስለሚዘርፉ ብቻ ነው።
አማጺያኑ ከነጮቹ አለቆቻቸውና ችግር ጠማቂዎች ጋር ሆነው ለሚዝቁት ሃብት ቁጥራቸው ከ40,000 በላይ ህጻናት በአሰቃቂ ሁኔታ በኮባልት ማዕድን ማውጫዎች ውስጥ ይሰራሉ። ይህ ሳያንሳቸው ፆታዊ ጥቃት፣ በጅምላ መደፈር የየዕለት መከራቸው ነው።
ያለምንም ማጋነን እያንዳንዱ በእጃችን የምንይዘው ስልክ፣ እያንዳንዱ ባትሪ፣ እያንዳንዱ ኤሌክትሪክ መኪና የኮንጎ ዜጎች ሥቃይ፣ ድምና መከራ አሻራ የታተመበት ነው።

ይህን እያሰብን የወርቅ ዝርፊያ ለመከራ የዳረገውንና ታናናሽ የጎበዝ አለቆች ለመከራ የዳረገውን የትግራይ ሕዝብ አሁናዊ ገጽታ ማስላት ግድ ይላል። በራሳቸው አክቲቪስቶችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ከተፈነከተው ትህነግ የወጡ እንደሚሉት ትግራይ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ልጆቿን በነዚሁ ታናናሽ የጎበዝ አለቆች ፋላጎት ከስራለች። ተፈናቅለው በረሃብ እየተንገላቱ፣ በሙቀትና ብርድ የሚሰቃዩ የትግራይ ወገኖች መከራ የሚቀዳው ከወርቅ ዝርፊያ ጀርባ መሆኑ እጅግ ልብ ይሰብራል።
የትግራይ አሳዛኝ ክስተት የጥይት ድምፅ ስለቆመ ብቻ አላበቃም፤ መልክ ቀየረ እንጂ። ከመልሶ ግንባታ እና ከዕርቅ ንግግሮች በስተጀርባ በዝምታ ከፍተኛ የሆነ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል። ይህ ጦርነት በመድፍ ሳይሆን በወርቅ ቁፋሮ፣ በኮንትሮባንድ መስመሮች እና በፖለቲካዊ ሽፋን የሚካሄድ ነው።
ትግራይ መሪዎች ነን በሚሉ አካላት በስልታዊ መንገድ የሚዘረፈው ወርቅ እንደ ኮንጎ ሃብት የሚነገርለትና እጅ በአፍ የሚያስጭን ባይሆንም፣ በትግራይ ዝርፊያው ለህዝብ መፈናቀል። ሞት፣ አስገድዶ መደፈር፣ ያለ ዕድሚያቸው ወታደር ሆነው እንዲመለመሉ ስለሚያደርግ መመሳሰሉን ልብ ይላል። ከምንም በላይ በከርሳም መሪዎቿ ሳቢያ በበሽታ፣ በረሃብና ብስቃይ እየደረሰ ያለው ግፍ ነገሩን ያመሳስለዋል።
ከሳምንት በፊት አዲስ ሪፖርተር “ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር / ትህነግ ብሎ የሚጠራው ቡድን ዋና መርሁ ማበስበስ እንደሆነ ተገለጸ። በቅርቡ ለአርሚ አዛዦች በሞሮኮ የንግድና መኖሪያ ቤት የተገዛላቸው በዚሁ መርሁ መነሻ ነው” ሲል ስም ዘዝሮ የሌብነቱን መረብ ማሳየቱ አይዘነጋም።
በሞሮኮ ንብረት የተገዛላቸውን የትግራይ ታጣቂዎች አርሚ አዛዦች ስም ዘርዝረው መረጃ የላኩ ክፍሎች እንዳሉት፣ “የትህነግ ርዕዮተዓለም ማበስበስ ነው”። ከህዝብና ከአገር በሚዘረፍ ሃብት ወታደራዊ አመራሮችን ታዛዥ ለማድረግ በውጭ አገር ንብረት እንዲያፈሩ ይደረጋል።
ከጦርነቱ በፊት የትግራይ ወርቅ የሕዝብ ሀብት ነበር ይባላል። በሕጋዊ መንገድ የሚተዳደሩ መአድን ቆፋሪዎች በዓመት 2.6 ሜትሪክ ቶን ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ለክልሉም ሕጋዊ ገቢ ያስገኙ ነበር። ይህ ሥርዓት ከጦርነቱ ጋር አብሮ ፈሷል። በእርሱ ምትክ የመጣው ስርዓት አልበኝነት ነግሷል።የታጠቁና ፖለቲካውን እንመራለን የሚሉ በቤተሰብ መዋቅር ተጠቃሚ ሆነዋል።
አፍሪካ ኢንተለጀንስ (Africa Intelligence) ያደረገው የምርመራ ዘገባ እንደሚያመለክተው የወርቅ ማዕድን ቁጥጥር በትህነግ ውስጥ ላለው የውስጥ ግጭት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል። ይህ በአጋጣሚ የሆነ አይደለም። በጦርነት በፈረሰችና ከመደበኛ የኢኮኖሚ ፍሰት በተገለለች ክልል ውስጥ ወርቅ በአሁኑ ጊዜ በጣም አስተማማኝ የጥሬ ገንዘብ ምንጭ ነው። ወርቁን የተቆጣጠረ ሥልጣኑንም ይቆጣጠራል። ስለዚህም ወርቅ ባለበት ሁሉ ወርቅ የሚዝቁ ማሽኖችና ረሃብ የጠናባቸው እኩል ሲጮሁ ይሰማል።
በትግራይ ታጣቂ ኃይል ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አዛዦች እና ከትህነግ ጋር ቁርኝት ያላቸው የፖለቲካ ሰዎች አብዛኛውን ሕገ-ወጥ የማዕድን ቁፋሮ እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን እንደሚቆጣጠሩ በስፋት ይዘገባል። በማዕድን የበለጸጉ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር የሚደረጉ አለመግባባቶች በንቅናቄው ውስጥ ወደ ግልጽ የቡድን ጦርነት የተቀየሩትም ለዚሁ ነው። በትግራይ ያለው “የሲቪል ሽግግር” ከፍተኛ የትግራይ መከላከያ ኃይል ጄኔራልን በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት በመሾም መጠናቀቁም ስለ አስተዳደር ሳይሆን የገቢ ምንጮችን ስለማረጋገጥ እንደሆነ ያሳያል። ወርቅ ከጦርነቱ በኋላ ያለውን ሥርዓት ማበላሸት ብቻ ሳይሆን፣ አዲስ መልክም ሰጥቶታል።
የዘረፋው መጠን እጅግ አስገራሚ ነው። ይህንኑ ዘረፋ አስመልክቶ የተለያዩ ሚዲያዎች እንዳሉት ኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ ስድስት ቶን የሚደርስ ወርቅ በኮንትሮባንድ ታጣለች። ከዚህ ጥቅል መረጃ ተቆንጥሮ የትግራይ ብቻ ሲታይ ያስገርማል። ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ በዲደብሊው (DW) ቴሌቪዥን በሰጡት ይፋዊ መግለጫ በየወሩ 38 ኩንታል ወርቅ በሕገ-ወጥ መንገድ ተቆፍሮ ከክልሉ እንደሚወጣ አምነዋል።
“እነዚህን ሕገ-ወጥ የማዕድን መስመሮች መቆጣጠር አንችልም” ያሉት ሌተናል ጀነራሉ ንግግራቸው ድክመትን ለማሳየት የታለመ ነበር፤ ነገር ግን ከጀርባው ያለውን ተባባሪነት ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የታጠቁ ኃይሎችን ማሰለፍ የሚችል ክልል ቶን የሚመዝን ወርቅ በድንበር የሚያሻግሩ ማዕድን አውጪዎችንና ኮንትሮባንደኞችን መቆጣጠር አልችልም ማለቱ የማይታመን ነው። ትርጉሙ ግልጽ ነው። መስመሮቹ ልቅ ሳይሆኑ በወጉ በዘረፋው በተሰማራ ኃይል ጥበቃ የሚደረግላቸው ናቸው።
ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ጉዳዩ እስከ ትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መድረሱን፣አብት እየተዘረፈ መሆኑን በማመልከት በግልጽ መወያየታቸውንና የፌዴራል መንግሥት እንዲረዳቸው መጠየቃቸውን አምነዋል። ሆኖም ንግዱ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በትግራይ ያለው የወርቅ ኮንትሮባንድ ቀውስ፣ ደካማ ቁጥጥር ውድ ማዕድናትን የትርፍ እና የግጭት መሣሪያ በሚያደርግላቸው ትናንሽ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ውስጥ የሚታየውን የታወቀ ታሪክ ያስታውሳል። ልክ በጦርነት እንደታመሱት የትግራይ ማዕድናት ሁሉ፣ እንደ ጊኒ ቢሳው፣ ሴራሊዮን እና ላይቤሪያ ባሉ ሀገራት ሕገ-ወጥ የወርቅ እና የማዕድን ኤክስፖርት ለታጠቁ ቡድኖች ስንቅ ናቸው። ዝርፊያው የታጣቂዎችን ቁንጮዎች ሲያበለጽግ የመንግሥትን ካዝና ሲያመነምን ይታያል። በሁለቱም አካባቢዎች እነዚህን ሀብቶች ለመቆጣጠር አለመቻሉ፣ ሊገኝ የሚችለውን ብልጽግና ወደ አለመረጋጋት እና ሙስና ቀይሮታል።
በርካታ የምርመራ ኢፖርቶች እንደሚያመልክቱት ወርቅን ከትግራይ ለማውጣት የሚያገለግሉ አራት ዋና ዋና መንገዶችን አሉ። አንደኛውና አወዛጋቢው መስመር በአዲያቦ እና በባድመ በኩል አልፎ መረብ ወንዝን ተሻግሮ ወደ ኤርትራ የሚሄድ ሲሆን፣ ከዚያም ወርቁ ያልተገለጸ የአፍሪካ ወርቅን በመቀበል ወደምትታወቀው ዓለም አቀፍ ማዕከል ዱባይ እንደሚላክ ይነገራል። ሌላው መስመር በአፋር በኩል ወደ ደቡብ አልፎ ወደ ሶማሊላንድ ይገባል፤ ከዚያም ወደ ኬንያ እና ኡጋንዳ በመሻገር ወርቁ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲገባ ይደረጋል።

የመድረሻ ቦታው ትልቅ ትርጉም አለው። የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተለይም ዱባይ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት እንደ ጦር ሜዳ ሳይሆን እንደ መድረሻ ነጥብ ነው። በጦርነት ከታመሰ ሕዝብ የተዘረፈው ወርቅ በትንሽ ፍተሻ ወደ ንጹሕ ወርቅነት የሚቀየርበት ቦታ።
ጀነራሉ ኤርትራን አንዷ ኮሪደር አድርገው በይፋ በጠቀሱ ጊዜ ከአስመራ የተሰጠው ምላሽ ፈጣንና ቁጣ የተሞላበት ነበር። የኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ክሱን “መሠረተ ቢስ” እና “አሳፋሪ ውሸት” በማለት ውድቅ አድርገውታል፤ የቀድሞ የህነግ አባላት ለ”ተንኮል ዓላማቸው” የፈጠሩት ክስ ነው ሲሉም ከስሰዋል። “የግጭት ነጋዴዎች” ውጥረቱን እንደገና እንዳይቀሰቅሱ ያስጠነቀቁት ሚኒስትሩ፣ ኤርትራ በወርቅ ኮንትሮባንድ ውስጥ ምንም ዓይነት ሚና እንደሌላት አረጋግጠዋል። ይህ ጩኸት በዝርፊያው ተዋናይ የሆኑት የጦር መኮንኖች ሊደብቂት ያልቻሉት የሞንጆሪኖ ወንድም የሚመሩት ስለመሆኑ ከበቂ በላይ ማስረጃ የሚቀርበበትን ዝርፊያ አቶ የማነ ለማስተባበል መሮጣጨው “የበላን ያብላል” እንዲሉ መሆኑን የትግራይ አክቲቪስቶች ሳይቀሩ ገልጸዋል።
ክህደቱ ፍጹም ነበር። ነገር ግን ዋናውን ጉዳይ ችላ ብሎታል። ወርቅ ከትግራይ በኢንዱስትሪ ደረጃ፣ በወታደራዊ መስመሮች፣ በታጠቁ አካላት ቁጥጥር ሥር እየወጣ ነው። ኤርትራ መተላለፊያ ትሁን፣ መድረሻ ትሁን ወይም አንዳቸውም አትሁን፣ ሃቁ ግን የትግራይ አተዳደር የገዛ ሀብቱን የመቆጣጠር አቅም ማጣቱ ወይም አሳልፎ መስጠቱ ነው።
የትግራይ ሕዝብ ላይ የወደቀው ቀምበር
ትግራይ በፈመራረሰ ቅርፅ ላይ ትገኛለች። ዕድሜ ለሻዕቢያ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል። የጤና ሥርዓቱ ተዳክሟል። እርሻም አለ ለማለት አያስደፍርም። የረድኤት ድርጅቶች ወጥተዋል።የሚዘረፈው ወርቅ መንገዶችን ለመሥራት፣ ሆስፒታሎችን ለመክፈትና መልሶ ግንባታን ለመደገፍ ሳይሆን የግል ሥልጣንን ለማጠናከር፣ የጦርነት ጊዜ የዕዝ መዋቅሮችን ለማስቀጠልና የፖለቲካ ውድቀትን ለማፋጠን እየዋለ ነው።
አፍሪካ ኢንተለጀንስ በግልጽ እንደታዘበው የትግራይ ወርቅ ለመልሶ ማገገሚያ ከማዋል ይልቅ የትህነግ የውስጥ ሽኩቻ ነዳጅ ሆኗል። በትግራይ ምንም ካልተማሩ ቡድኖች እጅ ወድቆ ለትግራይ ንጹሃን መከራቸው ሆኗል። የዝርፊያው ተዋኛኖች ሰላምን እንዲጠየፉም አድርጓቸዋል።
ይህ ዘረፋ ብቻ አይደለም። መስዋዕትነት እንዲከፍል ተቀስቅሶ በነበረው ሕዝብ ላይ የተፈጸመ ክህደት ነው። ሀብቱ በድብቅ ድንበር ሲሻገር ዝም ብሎ የማየት ክህደት ቻ ሳይሆን፣ ዋና አስተላላፊ በመሆን የሚፈጸም ክፉ ተባሳ!!
“በትግራይ ጦርነቱ ተቋማትን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን አንድ የነጻነት ንቅናቄ ነኝ የሚልን ቡድን የሞራል እሴቱን ሲያጣ ምን እንደሚያስከትል አሳይቷል። የሞራል መውደቁ ወርቅ በነጻነት እንዲታፈስ። ፍትሕ ግን እንዲከስም አድርጓል” ይላል የአፍሪካን ኢንተለጀንስ ዘገባ። ይህ እስካልተለወጠ ድረስ የትግራይ የወደፊት ተስፋዋ በእያንዳንዱ ጭነት በኮንትሮባንድ መጓዙ ይቀጥላል። ትህነግም “ትግራይ ትብለጽጋለች” እያለ እየዘርፈ ማላዘኑን ይቀጥላል። እስከመቼ? የትግራይ ምስኪንስ ዘራፊዎቹ በሚዝቁት ወቅ የተከለከለ ኬሚካል የሚሞቱት እስከመቼ ነው? መርዝ!!
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251981866434 / +251116393393






