አዲስ ሪፖርተር – የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር አንድ ክንፍ በትግራይ አክሱም፣ ሌላው የዚሁ ክንፍ አካልና ደጋፊ ማህበራት በውጭ አገር ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ስብሰባዎችን አካሂደዋል። ትህነግ በትግራይ ስብሰባ ሲቀመጥ በውጭ ላሉት ደግሞ የመሰብሰቢያ ሰነድ ተዘጋጅቶላቸው ነበር።
ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩት ትህነግ ስብሰባውን ሲጨርስ ያሳለፈው ውሳኔ እና በውጭ አገር ሲደርግ በነበረው ውይይት ላይ የተያዘው አቋም ተመሳሳይ ሆኗል። በውጭ አገር የትህነግ ደጋፊዎች ልክ በአገር ቤት እንደተከፋፈሉት ሁሉ ከሚታወቁት “የትህነግ አባቶችና ተጠቃሚ ቤተሰቦቻቸው” ካልሆነ በቀር በብዛት ድጋፉ እንደሞተም ይነገራል።
ህጋዊ ዕውቅና የሌለውና በምርጫ ቦርድ የተሰርዘው ትህነግ በማዕከላዊ ኮሚቴው ደረጃ ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠቃልል፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መፍረሱን፣ በዚሁ መሰረት የተዋቀረውን ጊዜያዊ አስተዳደርንም እንዲበተን መወሰኑ ተሰምቷል።
በተመሳሳይ በውጭ አገር በዙም በተካሄደ ስብሰባ “ትግራይ ነፃ አገር መሆኗ አይቀርም። እኛ የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደማገገሚያ ቤት ነው የምንቆጥረው” በማለት የቀድሞ አምባሳደር ፍሰሃ አስገዶም መናገራቸው ታውቋል። የሰሜን አሜሪካ የትግራይ ተወላጆች ማህበር/ UTNA እና በገረአልታ ኢንስቲትዩት አማካኝነት በተዘጋጀ የዙም ስብሰባ ላይ ትህነግ ባዘጋጀው ውይይት ላይ ነበር አምባሳደሩ ይህን ያሉት።
በዙም ስብሰባው ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል አንዱ አምባሳደር ፍስሃ አስገዶም ትህነግ ወደ አማራና አፋር ክልል እየገፋ በነበረበት ወቅት በዶክተር ደብረጽዮን አማካይነት የድርጅቱ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ተደርገው መሾማቸው የሚታወስ ነው። እኚሁ ሰው ሰሞኑን “ኢትዮጵያን እናድን” በሚል አቶ ልደቱና አቶ ነዓምን ባቀናጁት የአምጽ አመቻች ቴክኒክ ኮሚቴ ባዘጋጁው የሰማይ ላይ ሰለፍ ላይ ቀርበው ንግግር ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።
“እኛ በፕሪቶሪያው ስምምነት አጥር ስር ለመኖር ፍላጎት የለንም። የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንደ ማገገሚያ ቤት ነው የምንቆጥረው። ከበሽታችን ተፈውሰን ሙሉ ጤናችን እስኪመለስልን ድረስ እንደ ማቆያ የምንጠቀምበት ማገገሚያ ቤት ማለት ነው” በማለት ሰፊ ትንተና የሰጡት አምባሳደሩ፣ ይህ የሚሆንበት ጊዜ መቃረቡን አመልክተዋል።
ይኸው ዕውቅና የሌለው የትህነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አግባብ ተደራጅቶ ስራ የጀመረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲፈርስ የወሰነው በአብላጫ ድምፅ እንደሆነ ታውቋል። ከስብሰባው ተሳታፊዎች በወጣው መረጃ መሰረት 39 አባላት ሲደግፉ፣ 4 ተቃውሞ እና 2 ድምፀ ተአቅቦ ተደርጓል።
ከሚያዚያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በጄኔራል ታደሰ ወረደ በሚመራው የጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ላይ በሁሉም ዘርፎች የተቀናጀና ጠንካራ ተቃውሞ ለማሰማት መወሰኑ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ኮሚቴው “ጽምዶ” በሚል መጠሪያ በይፋ ወደ ጦርነት ለመግባት አቋም መያዙም ታውቋል።
የአፋብን ከፍተኛ አመራሮች ከነበሩት መካከል “ትግሉ ተጠልፏል” በሚል ወደ ሰላማዊ ትግል የተመለሱት እነ አቶ ጌራ ወርቅ፣ የፋኖ አመራሮች ወልቃይትን ለትህነግ ለመስጠት ውል ማሰራቸውን ባስታውቁበት የጋራ ቃለ ምልልስ ላይ፣ ፋኖና ሻዕቢያን አሸማግለው አንድ ላይ እንዲሰሩ ያስቻሉት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ እንደሆኑ መስክረዋል። በዚሁ መሰረት ትህነግ፣ ሻዕቢያና ፋኖ አንድ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያን ሊወጉ ዕቅድ መንደፋቸውና ዓላማው ኢትዮጵያን አፍርሶ የጎበዝ አለቆች የሚፈነጩባት ምድር ማድረግ እንደሆነ አጋልተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ስልጣን የተራዘመው ከፕሪቶሪያ ስምምነት በፊት በወጡ ሕጎች መሆኑን በመጥቀስ ትህነግ በሹመቱ ላይ የህጋዊነት ጥያቄ በማንሳት እንደማይቀበለው ማስታወቁ አይዘነጋም።
ህገወጥ የሚባለው ትህነግ የሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደን ሹመት “እኔ ያልተሳተፍኩበት የፌደራል መንግስት የተናጠል ውሳኔ ነው” ሲል ባጣጣለበት መግለጫው፣ በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት ትህነግ እና ፌደራል መንግስት በጋራ ተነጋግረው የክልሉን አስተዳደር እንደሚመሰርቱ ቢደነግግም የአሁኑ ለአንድ አመት የተራዘመው የጄ/ል ታደሰ ወረደ ሹመት ግን “በፌደራል መገናኛ ብዙሐን ሲነገር ከመስማት ውጪ እኛ ያልመከርንበትና ያልተሳተፍንበት ነው” ነበር ያለው።
“ትህነግ በሹመቱ ሂደት ላይ እንዳልተሳተፈ ህዝብ ይወቅልን” ከማለት ውጪ በቀጣይ ምን ዓይነት አቋም እንደሚይዝ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር አልነበረውም። ይሁን እንጂ ወዲያው አክሱም በዝግ ምክክር መጀመሩ ተሰምቷል። አዲግራትን ለምን እንደመረጠ ባይታወቅም፣ ከየአቅጣጫው የሚወጡ መረጃዎች ክሻዕቢያ ጋር ላለው ትስስር አመቺ በመሆኑ እንደሆነ ሲገለጽ ነበር።
ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ፣ ወደ አዲስ አበባ ከማቅናታቸው በፊት ስለጉዟቸው ከዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጋር አዲስ አበባ ሪፖርት ለማቅረብ እንደሚሄዱ፣ ሪፖርቱ ከየሴክተሩ በተሰበሰቡ መረጃዎች በካቢኔ መዘጋጀቱን፣ እና አዲስ አበባ ለመንግስት የሚያቀርቡትን ጉዳይ ዝርዝር አስመልክቶ ውይይት ማድረጋቸውንና፣ ስምምነት ላይ ደርሰው እንደነበር አመልክተዋል። ትህነግ የጄ/ል ታደሰን ሹመት ‘የፌደራል መንግስት የተናጠል ውሳኔ’ ሲል ማጣጣሉን “የማይገባ” በማለት አጣጥለዋል።
“አልቀበልም ማለት መብት ነው፣ አትቀበል ማለት ግን አይቻልም” ያሉት ጄኔራሉ፣ ከፌደራል መነግስት ጋር ስለተደረገው ውይይት ለትግራይ ሕዝብ ዝርዝር መግለጫ ሲሰጡ እንዳሉት የሌሎቹን ቡድኖች ዛቻ ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ሲሉ አጣጥለዋል።
ትናንት ማሻውን ከትግራይ የተሰማው ዜና የእነ ደብረጽዮን ቡድን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲፈርስ ወስኗል። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ህዝባዊ ተቃውሞ፣ ወታደራዊ ኃይልና ተቋማዊ አሰራር እንደሚጠቀም አቅጣጫ አስቀምጧል።
ይህ ቡድን የፕሪቶሪያው ስምምነት ፈርሷል በማለት ማስታወቂያ ማውጣት ከጀመረ ቆይቷል። ይህንኑ ተከትሎ የፌደራሉ መንግስት ይህ እስከተጻፈ ድረስ በይፋ ያለው ነገር የለም። የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን በተለያዩ ቋንቋዎች የተዘጋጀ መግለጫ ለማውጣት ኮሚቴ አቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ተሰምቷል። በውጭ አገር ያለው የዚህ ቡድን ክንፍም ድጋፍ ለመስጠት ተዘጋጅቷል።
የአዲስ ሪፖርተር የትግራይ ተባባሪ እንደሚለው በትግራይ ጦርነት የሚፈልግ የለም። ሕዝቡ ከዛሬ ነገ ጦርነት ይጀመራል በሚል ስጋት ውስጥ ነው። አብዛኛውን ወጣቶች ወደ ሌሎች ከተሞች አቅንተዋል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






