አዲስ ሪፖርተር ዜና – አቶ ኑሪ ሁሴን ኢንደሳ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (CBE Noor) ምክትል ፕሬዝደንት ነበሩ። በከባድ የሙስና ወንጀል፣ በስልጣን አላግባብ መገልገል እና ያልተመጣጠነ ሀብት ማፍራት ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸዋል። ተከሳሹ ካላቸው ህጋዊ ገቢ በላይ 264,141,491.19 (ሁለት መቶ ስልሳ አራት ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ አንድ ሺህ አራት መቶ ዘጠና አንድ ብር ከ19 ሳንቲም) ብር እና ንብረት አፍርተዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀሎች ዐቃቤ ህግ የመሰረተውና ክስ የመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው። ክሱ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሽ አስራ ሁለት በስም የተዘረዘሩ የሰው ምስክሮች፣ ባለ አርባ አምስት ገጽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የምርመራ ሪፖርት የሰነድ ማስረጃ ፣የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት የኢንተለጀንስ ሪፖርት፣ የቤቶች ካርታ፣ የሽያጭ ውል እና የጋብቻ ምስክር ወረቀቶች፣ የአሜሪካን ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የክፍያ ማስረጃ፣ እና አስረጂ ወይም “ገላጭ ማስረ” ቀርቦባቸዋል። ይህም በመገንባት ላይ ያሉትን ባለ 8 ወለል ህንፃዎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና የቪዲዮ ማስረጃዎች ተያይዘዋል።
የክስ ዝርዝሩን በየፈርጁ ለይቶ የቀረበው የክስ መዝገብ፣ ተከሳሹ ከሚያዝያ አንድ ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ እንደሚገኙ ያትታል። ተከሳሽ አቶ ኑሪ ከ18 በላይ ለሚሆኑ ተበዳሪዎች መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር እንዲለቀቅ ማድረጋቸው አመልክቷል።
የአርባ አምስት ዓመት ጎልማሳው ተጠርጣሪው አቶ ኑሪ ሁሴን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ሲያገለግሉ በህገወጥ አካብተውታል የተባለው ሃብትና ህገወጥ አሰራር ዘርዝሮ ክስ የተመሰረተባቸው፣ “የመንግስት ልማት ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራትና ከባድ ሙስና ወንጀል” እንደሆነ ተመልክቷ።
ተከሳሹ የብሔራዊ ባንክ መመሪያን (FIS/04/2021) እና የባንኩን አሠራር በመጣስ፣ ለ18 ተበዳሪዎች ብድር ሲሰጡ ተገቢውን የቁጥጥር (Enhanced Due Diligence) እና የድህረ-ክትትል ሥራ አልተሰራም። በጥቅም ትስስርም ከፍተኛ ሃብት እንዲመዘበር አድርገዋል።
በዚሁበጥቅም ትስስርወንጀል ስርለ18ቱ ተበዳሪዎች ከተለቀቀው ብድር ውስጥ ብር 2,803,961,000.00 (ሁለት ቢሊየን ስምንት መቶ ሶስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ስልሳ አንድ ሺህ) በተዘዋዋሪ መንገድ ወደ ተበዳሪዎቹ ሂሳብ ተመላሽ እንዲሆን አድርገዋል።
አቶ አብዱሰመድ ነጋሽ የተባሉ ለተበዳሪዎች ዕቃ አቅራቢ የሆኑ ገለሰብ ወደ ተከሳሹ ወንድም ላዚም ሁሴን የባንክ ሂሳብ ብር 5,280,000.00 ማስተላለፋቸውን የክሱ መዘገብ ያስረዳል። ወደ ተከሳሹ ባለቤት ወ/ሮ ሀቢባ ወርቅነህ የባንክ ሂሳብ ብር 680,000.00 ገቢ እንደተደረገላቸው የሰነድ ማስረጃው ያሳያል። ወደ ተከሳሹ ባለቤት እህት ወ/ሪት ሪሀና ወርቅነህ ድርጅት አና ትራቭል ኤጀንሲ(Ana Travel Agency) ብር 3,000,000.00 ገቢ ተደርጓል።
ከመመሪያ ጥሰት ጋር በተያያዘ የቀረበው የክስ ዝርዝር በአቅራቢ እና በተበዳሪ መካከል የቅርብ ትስስር (Connected Party) መኖር እንደሌለበት የበባንኩን መመሪያ ጥቅሶ የተፈጸሙትን ጥሰቶች ይዘረዝራል።
ቲኬ ግሩፕ – ዕቃ አቅራቢው አቶ ሬድዋን ቶፊቅ የተበዳሪው ባለአክሲዮን ልጅ መሆናቸው። ናዝሬት ጋርመንት- ዕቃ አቅራቢው ራሱ ተበዳሪው ድርጅት እንደሆነ፣ ኒው ፍላወር አጠቃላይ ንግድ፣ ዕቃ አቅራቢዋ ወ/ሮ አበበች አሸቴ የተበዳሪው ድርጅት ባለአክሲዮን እንደሆኑ በመጥቀስ የክስ መዘገቡ የመመሪያ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል ያላቸውን አሰራሮች ለአብነት ያነሳል።
አቶ መስፍን ባዘዘው፣ እቃ አቅራቢው ድርጅት (GIM) ፕሬዝደንት ራሳቸው ተበዳሪው ናቸው። አቶ መኳንንት ምስለው እቃ አቅራቢው የተበዳሪው የወንድም ልጅ ናቸው። አል አመተራህማንት ትሬዲንግ ሥራ አስኪያጁ እና ባለአክሲዮኑ ከወለድ ነፃ ብድር እንዲያገኙ ተደርጓል።
በዚህ መሰሉ መመሪያን የጣሰ አሰራር ብር 1,270,330,000.00 (አንድ ቢሊየን ሁለት መቶ ሰባ ሚሊዮን…) የባንኩ ሃብት ከፖሊሲው ጋር በማይጣጣም መልኩ ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል መደረጉን የክስ ፋይሉ ያስረዳል።
ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በገፍ በዓይነትና በስም ተዘርዝሮ የቀረበባቸው ተከሳሹ በስራ ዘመናቸው ካገኙት ህጋዊ ገቢ (13.9 ሚሊዮን ብር) ጋር የማይመጣጠን ሀብት በስማቸው እና በባለቤታቸው ስም ተመዝግቦ መገኘቱን የክስ ፋይሉ አመልክቷል። በዝርዝርም አስረድቷል።
የክስ መዘገቡ ተከሳሽ በስማቸው የተመዘገቡ ንብረቶች በሚል ባሰፈረው ዝርዝር ስር የተለያዩ ዓይነት ቤቶችን ከሚገኙበት አካባቢና ዓይነታቸው ጋር ዘርዝሯል
- በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ አንድ ባለሁለት መኝታ ኮንዶሚኒየም፣
- በሰበታ ከተማ በ2.5 ሚሊዮን ብር የተገዛ G+2 ቤት
- በለገጣፎ ከተማ 140 ካ.ሜ ላይ ያረፈ መኖሪያ ቤት። ከዚህ በተጨማሪ ተከሳሽ
በሌላም በኩል ተከሳሽ በራሳቸው ስም የተመዘገብ አክሲዮንም አላቸው። በኦሮሚያ ባንክ 1,718,000 (አንድ ሚሊዮን ሰባት መቶ አስራ ስምንት ሺህ) ብር የአክሲዮን ድርሻ የእሳቸው ነው።
ግምቱ 3.7 ሚሊዮን ብር የሆነ ቶዮታ ኮሮላ ክሮስ ሀይብሪድ 2017 ሞዴልእና ዋጋው ያልተገለጸ ኒሳን መኪና አላቸው። የክስ መዘገቡ በባለቤታቸው ወ/ሮ ሀቢባ ወርቅነህ ስም የተመዘገቡ ንብረቶችንም በተመሳሳይ ዘርዝሯል።
- ህንፃዎች፦
- በቦሌ ወረዳ 12 የሚገኙ ሁለት ግዙፍ ህንፃዎች፦
- 450 ካ.ሜ ላይ ያረፈ B+G+8+T ህንፃ (ግምቱ 74,014,960.67 ብር)።
- 500 ካ.ሜ ላይ ያረፈ B+G+8+T ህንፃ (ግምቱ 103,711,582.35 ብር)።
- የባንክ ሂሳብ
- – በተለያዩ ባንኮች (ንግድ ባንክ፣ ዳሽን፣ አቢሲኒያ፣ ዘመን) ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠጋ የገንዘብ ዝውውር እና በሂሳብ ላይ የሚገኝ ቀሪ ገንዘብ።
- – ወደ ውጭ ሀገር ንግድ፦ በቡና ላኪነት 466,881.37 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ቡና ወደ ውጭ የላኩ መሆኑ በክስ መዘገቡ ላይ ዝርዝር ከቀረቡት መካከል ይጠቀሳል። ትምህርት ቤት ክፍያ እና የሀብት ልዩነት
ተከሳሹ አራት ልጆቻቸውን በአሜሪካን ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት (AISE) የሚያስተምሩ ሲሆን፣ ለ2018 የትምህርት ዘመን ብቻ 2,220,000 (ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሀያ ሺህ) ብር ከፍለውላቸዋል።
ተከሳሹ ካላቸው ህጋዊ ገቢ በላይ 264,141,491.19 (ሁለት መቶ ስልሳ አራት ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ አንድ ሺህ አራት መቶ ዘጠና አንድ ብር ከ19 ሳንቲም) ብር እና ንብረት አፍርተዋል።
አቶ ኑሪ ሁሴን ኢንደሳ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው ሲሰሩ፣ የጣሱት ህግ ተብሎ የተዘረዘረው ባንኩ የተቋቋመለትን ኃይማኖታዊ ዓላማ በሳተ መልኩ ነው።
ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት (Interest-Free Banking) የሚቋቋምባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች በጥቅሉ እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል፦
ከወለድ ነጻ የሆኑባንኮች በዋናነት የሚቋቋሙት ሸሪዓ ሕግ መሠረት ወለድ (ሪባ) መከልከሉን ተከትሎ፣ አማኞች ከእምነታቸው ጋር የማይጋጭ የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሆነ ይታወቃል።
በዚሁ የተቋቋመበት ደንቡ መሰረት ባንኩ ገንዘብን አበድሮ ወለድ ከመቀበል ይልቅ፣ እንደ እቃ ገዥና ሻጭ ወይም እንደ ንግድ አጋር በመሆን ከደንበኛው ጋር በትርፍና በኪሳራ የመሳተፍ መርህን ይከተላል። ሃብት በጥቂት ሰዎች እጅ ብቻ እንዳይከማች እና በኢኮኖሚው ውስጥ በተጨባጭ የንግድ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት እንዲዘዋወር ያበረታታል። በሃይማኖታዊ ምክንያት ከመደበኛው የባንክ ሥርዓት ርቀው የቆዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደ ኢኮኖሚው መዋቅር ውስጥ በማስገባት የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል። ከምንም በላይ ለተበዳሪዎች የሚሰጠው ብድር ለታለመለት የንግድ ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እና በአቅራቢና በተበዳሪ መካከል ተገቢ ያልሆነ የጥቅም ትስስር እንዳይኖር ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግን እንደሚጠበቅበት ከወለድ ነጻ ባንኮችን አስመልክቶ የወጡ ዘገባዎች ያስረዳል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






