አዲስ ሪፖርተር ማይጨው — ህወሃት አዲስ መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ጦርነት ለመጀመር በወሰነው መሠረት አለኝ የሚለውን ኃይል በስም በሚታወቁ ዝርዝር ቦታዎች ማሰማራቱ ከመረጃ ጋር ይፋ ሆነ። የሀገር መከላከያ ሠራዊትም አሰላለፉን በመከታተል ላይ እንደሆነ ተመልክቷል። ሲካሄዱ የነበሩ የድሮን ጥቃቶችም የዚሁ አካል እንደሆኑ ተገልጿል።
ህወሃት ሰፊ ዝግጅት አድርጎ በሸረሪ በኩል ወደ ሁመራ ለማቅናት ያደረገው ሙከራ በከፍተኛ ሰብአዊ፣ ቁሳዊ እንዲሁም ስትራቴጂካዊ ሽንፈት ከተጠናቀቀ በኋላ ሙሉ ትኩረቱን ወደ ራያ ቆቦ ማድረጉ አይዘነጋም። የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ያለባቸውን ስድስት ወረዳዎች ማለትም ራያ አላማጣ፣ አላማጣ ከተማ፣ ኦፍላ፣ ባላ፣ ኮረምና ዛታን ከተቆጣጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ የወታደራዊ ስምሪት እያካሄደ መሆኑን ምስክሮች ለአዲስ ሪፖርተር ገልጸዋል።
ህወሃት “ደቡባዊ ትግራይ” በሚላቸው እና የማንነትና የወሰን ጥያቄ ሲስተናገድባቸው ለሦስት አስርት ዓመታት ባስቆጠሩት አካባቢዎች፣ በሰሜን ወሎ እና በዋግ ኸምራ አዲስ መንግሥት ከመመስረቱ በፊት ፈጣን የማጥቃት ውጊያ ለመክፈት ያለመ ከፍተኛ የኃይል ስብስብና የተቀናጀ የጦር ዝግጅት እንደሚያካሂድ አቶ አባይ ግደይ መናገራቸውን ዘግበን እንደነበር ይታወሳል።
ይህንኑ ዜና ያጠናከሩት የአዲስ ሪፖርተር የአካባቢው ተባባሪዎች፣ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ የተስተዋሉት የመስክ ቅኝቶች የህወሃት ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ከቀናት በፊት በአማረ ከበደ እና በሸዊት ሆቴል ተሰብስበው ያሳለፉትን ውሳኔ የሚያጸኑ ሆነው አግኝተዋቸዋል።
በስብሰባው የሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት የአዲስ መንግሥት ምስረታ ከመጠናቀቁ በፊት ሰሜን ወሎን፣ ዋግን እንዲሁም ላሊበላን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደሚገባ መወሰናቸውን የስብሰባው ሙሉ መረጃ እንዳላቸው የሚናገሩ ወገኖች አስታውቀዋል።
ህወሃት “ደቡብ ግንባር” የሚለውን ቀጠና የሚሸፍኑ አመራሮች በጨርጨር እና በቢሶበር ቀጠናዎች በአካል በመገኘት ከክፍለ ጦርና ከኮር አዛዦች ጋር በዚሁ ውሳኔ ዙሪያ መክረዋል። ለታቀደው የማጥቃት እርምጃ የቀጣይ ውጊያ መመሪያዎችንም አስተላልፈዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል በዓድጉደም አካባቢ ተከማችቶ የነበረው “አርሚ 44” ሙሉ በሙሉ ስምሪቱን በመቀየር ወደ ደቡብ ግንባር መጓዙን አዲስ ሪፖርተር አረጋግጣለች። ከዚህ ውስጥ የተወሰኑ ክፍለ ጦሮች ወደ ማይጨው አቅጣጫ ሲያመሩ፣ የኮር 2 አባላት ደግሞ ወደ መኾኒ አቅጣጫ ተንቀሳቅሰዋል። በተጨማሪም ከመቀሌ የተነሱ ተጨማሪ የሠራዊት አባላት በእግርና በተሽከርካሪ ወደ ደቡባዊ ቀጠናዎች መንቀሳቀሳቸው ተመልክቷል።
በማይጨው ከተማ በሚገኙት አማረ ከበደ እና ሸዊት ሆቴሎች ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ተገኝተው ባሳለፉት ውሳኔ መሠረት፣ በከተማዋ በሚገኙት በጥላሁን ይግዛው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በማይጨው ግብርና ኮሌጅ ግቢዎች ውስጥ ኃይል አስፍረዋል። ከሰፈሩበት ስፍራ ምሽት ላይ ተዋጊዎችን ወደ ግንባሩ አጓጉዘዋል። ከማይጨው የተነሳው ኃይል ወደ ሰቆጣ ግንባር፣ እንዲሁም በመኾኒ በኩል የመጣው ተጨማሪ ኃይል ወደ ራያ ግንባር በመጠጋት ሌሊቱን ሲጓዝ ማደሩ ታውቋል።
የሕወሓት አመራሮች በኮረም፣ በወፍላ፣ በሰቆጣ እና በራያ አቅጣጫዎች ከፋኖ ኃይሎች ጋር በመሆን የተባበረ የማጥቃት እርምጃ ለመውሰድ ማቀዳቸውን የተረዳው የሀገር መከላከያ የራሱን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ዜናውን ያቀበሉን ተባባሪዎች አመልክተዋል።
የድሮን ቅኝትና ጥቃትን ለመከላከል ሲባልም መሣሪያና ተተኳሽ አቅርቦቶችን በስውር በአህያና በጋሪ ለማጓጓዝ የአካባቢውን ባለ አህያዎችና ባለ ጋሪዎች የመመዝገብ ተግባር መከናወኑን ያመለከቱት ተባባሪዎቻችን፣ ከዚህ በተጨማሪም ለታቀደው የጦርነት እንቅስቃሴ የሚሆን የፋይናንስና የሎጅስቲክስ ድጋፍ ከአካባቢው ነጋዴዎች በግዴታ እንዲሰበሰብ መደረጉን አስታውቀዋል። “ጦርነት ከተነሳ ይፈርሳል” የሚል ሥጋት ስላለ የሠራዊቱን ሥነ-ልቦና ለመገንባት ይጠቅማል የተባሉ የቅስቀሳ ንግግሮች እየተደረጉላቸው ነው።
ከማይጨውና ከመኾኒ ለአዲስ ሪፖርተር ዝርዝር መረጃ የላኩ ወገኖች እንዳሉት ከሁሉም አቅጣጫ ሕዝቡ በሥጋት ውስጥ ይገኛል። በሥጋት ከአካባቢያቸው የሸሹት እና ራሳቸውን “የራያ ዘብ” በሚል ያደራጁ ደግሞ ከውስጥ ባላቸው መረጃ መሠረት ከአዲስ መንግሥት ምስረታ በፊት ጦርነት ለመክፈት ስምሪት የወሰዱ አርሚዎች የአሰላለፍ ዕቅድ እንደሚከተለው መሆኑን በመረጃ አስደግፈው ይፋ አድርገዋል። በዚህም መሠረት ከሀገር መከላከያ ጋር ተናበው እየሠሩ መሆኑን አመልክተዋል። የአሰላለፍ ዕቅዱም፦
አርሚ 26 – ከዋግ አበርገሌ በመነሳት ፀፀራ እና ሰቆጣ + ከተወሰነ የአገው ሸንጎ ኃይል ጋር ፃግብጂ፣ እቅልዋን፣ ብርብር እና ሰቆጣ ከአገው ሸንጎ ጋር በመሆን የማጥቃት ዕቅድ።
አርሚ 31 – ኮረም ዛታ ግንባር በማይማዕዶ ወደ በለቃ ጊዮርጊስ በማድረግ ጥራሪን ተሻግረው መረዋ – ወለህ፤ ቀጥሎ ያለው መስመር ላሊበላ። ከዛታ ወደ ግራ መስመር አሙሲት እና ሰቆጣን፣ በዛታ ዋና መስመር ጥራሪን በመሻገር ድብሪ ሳይድ – ቲያ አድርገው ወደ ላሊበላ መስመር (ጋዝጊበላ፣ አስከተማ፣ ቢልበላ ጊዮርጊስ፣ ላሊበላ እስከ ጋሸና)፤ አይናቡግና ካለው የፋኖ ኃይል ጋር አንድ ላይ በመሆን የማጥቃት ዕቅድ።
አርሚ 24 – ከአላማጣ በመነሳት ጥቁር አስፋልቱን ይዘው አማያ፣ አሞራ ገደል፣ ሰይራ፣ ተኩለሽ፣ በላጉ (ከወልድያ በላይ)፣ ሙጃ፣ ድልብ በማድረግ ቀበሮ ሜዳ ከፋኖ ጋር አንድ ላይ በመሆን የማጥቃት ዕቅድ።
አርሚ 33 – ዋናው የቆቦ መስመር እስከ ወልድያ ከፋኖ ጋር በመጣመር የማጥቃት ዕቅድ።
አርሚ 43 – በጨርጨር፣ ቢሶበር፣ ሸቃይ ከተማ፣ ያሎ (ጉጉብዶ) ከአርሚ 44 የተወሰነ ኃይል ጋር አንድ ላይ በመሆን፤ ባላ፣ ትግሬ መንደር፣ አዲስ ቅኝን በመስበር ወደ ዞብል በርከት ያለ የፋኖ ታጣቂ ተመድቦ የማጥቃት ዕቅድ።
አርሚ 44 – ወጀራት፣ ጎንኳ፣ ጎነቕ፣ ቶንሳ፣ መጋሌ መስመር ዓዲቀይሕ፣ ጋራርሳ እና ቶንሳ የማጥቃት ዕቅድ። አሁን ወደ ደቡብ ግንባር ሙሉ በሙሉ ተንቀሳቅሰዋል።
ከአርሚ 33 – አንዲት አሃዱ እንደ አስፈላጊነቱ ድጋፍ ለመስጠት መቻሬ ተቀምጣለች።
አርሚ 15 – በመረብ ሚኢቲ በሓዳለ፣ ሰንዓለ፣ ሸጓላ እና ላሖት የተባሉ የዓፋር ቦታዎችን በመቁረጥ የማጥቃት ዕቅድ።
አርሚ 92 – ከአራ ጉሬ እና በአራ ዓሰገዳ እስከ ሂድሞ የሚባል የዓፋር ቦታ ለመዝጋት ከኡጉጉሞ ጋር እንዲገናኙ ታቅዷል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ሁለት ጊዜ በማፍረስ መፍረሱን ያመለከቱ “ህወሃት ቀደም ሲል ከመንግስት መረጃ ነበረው። ከህወሃት መረጃ ማግኘት አዳጋች ነበር። አሁን ግን ጦርነት የሰለቻቸው ወገኖች የህወሃትን መረጃ በየደቂቃው ለአገር መከላከያ ያደርሳሉ። በቴክኖሎጂ ስለላ እንቅስቃሴያቸው ሁሉ ክትትል ይደረግበታል። በዚህ መነሻ ህወሃት ትንሽ ተጨማሪ መሬት ይዞ ይደራደራል እንጂ ወደ ጦርነት ግፍቶ አይሄድም። የፕሪቶሪያው ውል ፈርሶ አዲስ ድርድር ለማድረግ እስከ ቆቦ ዝቅ የማለት እንጂ ከዚያ የዘለለ ዓላማ የለውም። ቆቦ ከተደረሰ ደግሞ በይዞታ ባለቤትነት ከፋኖ ጋር ወደ ግጭት መግባታቸው አይቀርም” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
መረጃውን የላኩት ወገኖች እንዳሉት ሻዕቢያ የሚያስተላልፈው መሣሪያና ኃይል ተጣምረው ለመክፈት ያሰቡት አዲስ ውጊያ ሰላማዊ ዜጎችን አሁን ካሉበት በላይ ለስቃይ የሚያዳርግ፣ ከቀድሞው የበለጠ ሕይወት የሚቀጥፍ፣ ከሚሰማው የዝናብ እጥረትና ራብ ጋር ተያይዞ ለተጎዳው ሕዝብ እልቂትን ማወጅ በመሆኑ፣ ጦርነት የሚያስቡ ወገኖችና ቡድኖች ሊያስቡበት እንደሚገባ አመልክተዋል።
“ልጆቼ በሙሉ የሉም። እኔ ዕድሜ ጠግቤያለሁና በግድ ዝመች የሚለኝ ስለሌለ እዚሁ ቀርቻለሁ። ሞት ከመጣ እዚሁ እቀበለዋለሁ። ያለኝ አንድ አማራጭ ጸሎት ብቻ ነው” በማለት ሲናገሩ የተሰሙ የአላማጣ ነዋሪ፣ “አሁን ያለው ነገር አያምርም” ሲሉ ማለቀሳቸውን ከተባባሪዎቻችን መካከል አንዱ መስክሯል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






