አዲስ ሪፖርተር ዜና – ሰውየው ሰላማዊ ሰው ነው። ከሆሚቾ አምቦ ሄዶ ባላሰበውና ባልጥበቀው መልኩ ይቀጠቅጡታል። ዱላውን ችሎ ወደ መጣበት ይመለሳል። ከዛም የሆነውን ለባልደረቦቹ ይናገራል። የደረሰበትን ድብደባ ያሳያል። ይህ ሰው ሆመቾ ባለው የመከላከያ ካምፕ የተመደበ የሰራዊቱ አባል ነው።
የመከላከያ አባሉ ሙሉ ልብሱን ለብሶ፣ ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን የአምቦ ከተማ ከንቲባ ቢሮ በመሄድ የደረሰበትን ያስረዳል። አክሎም የተደራጁ መሆናቸውን ገልጾ ጉዳዩን በቀላሉ እንደማይተወው ያስታውቃል። ባልደረቦቹም በብስጭት ስሜታቸውን ይገልጻሉ። በመጨረሻ ከንቲባው የሚቻላቸውን ሁሉ አድርገው ወንጀሎኞቹን ወደ ህግ እንደሚያቀርቡ ቃል ይገባሉ፣ እነሱም ጉዳዩን በሳቸው ላይ ጥለው እንዲተውት ይማጸናሉ።
ከንቲባው “እንክሳለን” ቢሉም ያልተዋጠላቸው የመከላከያ አባላቱ ጉዳዩን መስመራቸውን ተከትለው ለሚመለከታቸው አደረሱ። ይህ ሲሆን በከተማዋ መረጃና ማስረጃ ይዘው ፈርተው አድፍጠው የነበሩ “እኔም ተድብድቤያለሁ” እያሉ እጃቸው ላይ ያለውን መረጃ ለቀቁ። ለሚቀርባቸው አካላት ላኩ። ዜጎች ሲደበደብ የሚያሳይ የፊልም ማስረጃ በማህበራዊ ገጾች ተሰራጨ። ይህ ሁሉ የሚሆነው በአምቦ ነው።
“ወዲያው ይህ ጉድ ከተማ እምብርት ውስጥ እየተፈጸመ፣ እንዴት የከተማዋ የጸጥታ ኃይሎችና አስተዳደሩ ዝም አሉ” የሚለው ጥያቄ በስፋት ከየአቅጣጫው ተነሳ። እስካሁን በይፋ ስለ ጉዳዩ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጥም የአምቦ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ፣ “ካሳዬ ቀነኒሳ” የተባለና በተለያዩ ወንጀሎች ሲፈለግ የነበረ ግለሰብ በጸጥታ አካላትና በሕዝብ ጥቆማ መያዙን አስታውቋል።
ስሙን ደብቆ ለአዲስ ሪፖርተር ምስክርነቱን የሰጠ ሌላ ሰለባ “ቤቴ መጡ” ይላል እንዴት ተደራጅተውና ቡድን መስረተው እንደሚሰሩ ሲናገር። “ቤቴ መጡና ቤትህ ለቀቅ። ቦታውን እንፈልገዋለን አሉኝ፤ የት እኖራለሁ? ይህ ቤቴ ነው። መኖሪያዬ ነው። ቤተሰቦች አሉኝ ብዬ መልስ ሰጠሁና በድንጋጤ ወደ ሚዲያ አመራሁ” ቦታው የቀድሞ 04 ነው።
ሚዲያ በሄደ በበነጋው እነዚሁ ህጋዊ የቡድኑ አባላት “ለምን ሚዲያ ጋር ሄደክ” ብለው አሰሩት።ያደረጉትን አድርገው በመጨረሻ “ሁለተኛ ወደ ሚዲያ አልሄድም” ብሎ ተናዞ ተፈታ። ለካ ቤቱ እንዲፈርስና እሱ እንዲባረር የተፈለገው አጠገቡ ያለ አንድ ባለሃብት መሬት ጠበበኝ በማለቱ ነበር። ይህም የሆነው የአምቦ ከተማ ከንቲባና የጸጥታው አካላት እያዩና እየሰሙ ነበር።
ሌሎችም ጉዶች አሉ። በአምቦ ከተማ የተደራጁ ጉልበተኞች ሰዎች በዘፈቀደና የሆነ ነገር ፈልገው እንደሚደበድቡ ይፋ ሲሆን ዜናው አስደንግጧል። በአብዛኛው የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት ይህን ወንጀል ቀድመው የሚያውቁትና እየተሳቀቁበት ያለ ጉዳይ ነው። አንድ የከተማው ነዋሪ ለጀርመን ድምጽ “ብትናገር ትሞታለህ” ሲሉ የሁኔታውን አደገኛነት አስረድተዋል። ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው “መናገር አንችልም ነበርና፤ ሳንናገርን ኖርን። ፈጣሪ እውነቱን ያወጣዋል ብለን ነበር ዝም ያልንው” ይላሉ።
በርካቶች ከስጋት አንጻር ስማቸውን መጥቀስ እየፈሩ እንዳረጋገጡት ከሆነ አምቦ መሃል ከተማ መቀጥቀጥ፣ መዘረፍ፣ በተደራጁ ጉልበተኞች መሰቃየት የተለመደ ነው። አንድ ምስኪን በደቦ ሲደበደብ አይቶ ለመገላገል መሞከር ዋጋ ስለሚያስከፍል አይሞከርም። እናም በአደባባይ ያለገላጋይ መደብደብ፤ ንብረት መንጠቅ እና የሰውን ልጅ ሰብዓዊ መብትን መርገጥ የዕለት ተዕለት ተግባር መሆኑን መመለከት ለአምቦ ነዋሪዎች ዜና አይደለም።
ያዩትን በወጉ ለመናገር እንኳ የማይችሉ፣ “የከተማ አስተዳዳሪ፣ ፖሊስ እና ሁሉም ዓይነት የአስተዳደር እና ጸጥታ መዋቅር ባለበት ከተማ ነዋሪዎች አስፓልት ላይ ይደበብደባሉ። ይወጋሉ። አንድ ሰላማዊ ከተማ ውስጥ ይህ ይሆናል ብሎ ማን ያምናል? እንደሚሰማውና አዲስ ሪፖርተር ወደፊት ይፋ በሚያደርገው መረጃ ይህ ተገባር በሌሎችም ከተሞች አለ። የባሌው እርምጃ እየተወሰደበት ሲሆን ሌሎች ላይ እንደሚቀጥል ይጠበቃል።
አንድ ቀን በከተማዋ መሃል ጎዳና ስምንት የሚጠጉ ተደባዳቢዎች፣ አንዱን ተረኛ ይከባሉ፡፡ ከከበቡት መካከል አንዱ እስኪበቃው ይደበድበዋል፡፡ በድብደባው ብዛት ደም በደም የሆነውን ተጠቂ ለመታደግ የሞከረ አንድ መንገደኛ እንኳ በቅጽበት ተመቶ አስፓርልት ተዘረረ፡፡ በወቅቱ እነዚህን ተደባዳቢዎች “ለምን” ያላቸው የፀጥታ አካልም አልነበረም፡፡ የሚገርመው ይህን ሲያደርጉ ደግሞ ቪዲዮ እየቀረጹ ነበር፡፡ አስተያየት ሰጪው “ስለዚህ እናንተ አሁን በቪዲዮ ያያችሁትን እኛ በቀጥታ በአይናችን ያየነው፣ አይተንም አዝነን ቤታችን ገባን፡፡ ብንናገር የሚደርስበን የሚታወቅ ነው። ለማንም መንገርም አይቻልልም። ትቅምም የለውም” ብለዋል።
የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች አሁን ፋታ አግኝተዋል?
ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተጋራውና አንድ ለፍቶ የሚያድር ዜጋ ድብደባ ቁጣ ፈጥሯል። ሰለባ የሆነው ሰው የቀን ሰራተኛ ነው። ይህ ሠራተኛ ያን አስከፊ ቀን እንዲህ ያስታውሰዋል “የጭቃ ቤት ለመመረግ ኮንትራት ወስጄ ሥራ ላይ ነበርኩ። ድንገት ጎራዴ የታጠቁና ማንነታቸውን የማላውቃቸው በርካታ ወጣቶች ከበቡኝ። በተለይ የደበደበኝን ሰው ቀደም ሲልም በተመሳሳይ ድርጊቱ ስለ ማውቀው፣ በድንጋጤ ቆሜ ነው የቀረሁት”
በከተማዋ የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እጅግ መጠነ-ሰፊ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ጉዳዩ ወደ አደባባይ በመውጣቱ ትንሽ እፎይታ ቢሰማቸውም አሁንም ስጋቱ እንዳልቀለለ ያስረዳሉ። አንዱ ነዋሪ በቁጭት ሲናገሩ፦ “በገዛ መሬቱ ላይ ግንባታ የጀመረን ግለሰብ፣ የተደራጁ ወጣቶች በአደባባይ መሬቱን ቀምተው ግንባታ ሲጀምሩበት አይተናል። ‘ለምን?’ ብሎ የጠየቀው ባለቤት ‘እንገድልሃለን’ ተብሎ ተዝቶበታል። የጸጥታ አካላትም ቢሆኑ ለተበዳዩ መፍትሔ ሊሰጡት አልቻሉም።” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።
አዲስ ሪፖርተር በርካታ መርጃዎች ስላላትና መረጃው በቀጥታ ከንቲባውንና እሳቸው የሚመሩትን ካቤኔ የሚመለከት በመሆኑ ማብራሪያ እንዲሰጡ የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹን ለማነጋገር ጥረት ተደርጓል።በግልና በቢሮ ስላካቸው ተሞክሯል። ይሁን እንጂ ምላሽ የለም።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ፣ ጉዳዩን እስካሁን የተከታተለው ከማህበራዊ ሚዲያ ፍንጮች መሆኑን ገልጿል። እስካሁን በግል መጥቶ አቤቱታ ያቀረበ ተጎጂ ባይኖርም፣ ኮሚሽኑ በራሱ መንገድ ምርመራ በማድረግ ጉዳዩን እንደሚያጣራው ምልክት ሰጥቷል።
በአምቦ ከተማ የታየው ይህ ድርጊት “ከባህላችንና ከእሴታችን ውጪ ነው” የሚሉት ነዋሪዎች፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብርላቸውና ከዚህ “የቀንና የሌሊት ስጋት” እንዲገላግላቸው ይማጸናሉ። መሻሻል ቢኖርም ስሩ ካተነቀለ ተመልሶ ወደ ነበበረበት ላለመመለሱ ማስተማመኛ የለም።
የአምቦ ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ገጹ እንዳጋራው “የተለያዩ ወንጀሎችን ሰርቶ የተሰወረው ካሳዬ ቀነኒሳ የሚባል ግለሰብ” የጸጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል የህግ ቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን አስታውቋል፡፡ የኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤቱ ግለሰቡ የተያዘው በጸጥታ አካላት ቅንጅት እና በህብረተሰብ ጥቆማ እንደሆነ ከአምቦ ከተማ የፀጥታው ምክር ቤት መረዳቱን አሳውቋልም፡፡
የአምቦ አካባቢ ተወላጅ የሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል፣ “ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ባይ ናቸው። ሲያስረዱም በዚህ ደረጃ በአንድ ሰላማዊ ከተማ ወንጀል ሲፈጸም የማይመለከት አስተዳደር ወይም የጸጥታ መዋቅር “አላየሁም፣ አልሰማሁም ለማለት የሚያስችል ምን ምክንያት ሊያቀርብ ይችላል” በማለት ጉዳዩ መዋቅርራዊ እንደሚመስል ይናገራሉ። የአገር መከላከያ አባሉ ላይ ጥቃቱ ባይደርስ ኖሮ ማንም ደፍሮ ሊያነሳው እንደማይችል ይናገራሉ፤
“በዚህ ደረጃ በአደባባይ የሚፈጸምን ወንጀል የማያስቆም፣ ወዲያውኑ ስብስቡን ለይቶ የማይቆጣጠር የጸጥታ መዋቅር ነገ ሌላ ችግር ለመከላከል ያለው ዝግጅት ጥርጥር ውስጥ የሚጥል ነውና ክልሉ ይህን ጉዳይ እንደ ምልክት ሰጪ ኩነት ተጠቅመው ከንቲባዎችን እንዲመረመሩ ጥሪ አቀርባለሁ” ሲሉ እኚሁ ፖለቲከኛ አመልክተዋል። “ምክንያቱም” አሉ “ምክንያቱም ተመሳሳይ ነገር በሻሸመኔ፣ በባሌ፣ እና በአርሲ አቅጣጫ ስለመኖሩ መረጃዎች አሉና”
ከነዋሪዎች የተሰብሰበው በርካታ አስተያየት “የክልሉ መንግስት ውስጡን ይፈትሽ፣ አስተዳደሮቹን ይመርምር” የሚል ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






