አዲስ ሪፖርተር – “እንደ ልጅ መጫወት ናፈቀኝ፤ ተጫውቼ አላውቅም” የምትለው የ14 ዓመቷ እምብራቅ ሀፍቱ፣ ሕወሓት በግድ መልምሎ ለሻዕቢያ አቀብሏት፣ ሻዕቢያ ደግሞ ለሱዳን የአልቡርሃን ኃይሎች አስተላልፏት፣ የሱዳን ኃይሎች በጀልባ ተከዜን አሻግረዋት ወደ ሸረሪና ምሽግ ያስገቧት ታዳጊ ናት።
ከሁመራ ለያሃ ሚዲያ እያለቀሰች ቃሏን የሰጠችው ይህቺ ታዳጊ ከቤተሰቦቿ ጋር ከተለያየች አራት ዓመት ሆኗታል። በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት የተቋጨው ጦርነት ሲጀመር የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነበረች። በጦርነቱ ምክንያት ቤተሰቦቿ ሲፈናቀሉ እሷም አብራ ብትፈናቀልም፣ በውል ባልገለጸችው ምክንያት የሚኖሩት ተለያይተው በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ነው።
“እናትና አባቴን ለመርዳት መቀሌ ሊስቶር እየሠራሁ ሳለ ‘ና ጽዳት አጽዳ’ ብለው ጠሩኝና ጫኑኝ፤ ወደ ማሰልጠኛ ላኩኝ። ከሁለት ወር በኋላ ወደ ሸረሪና ተላክሁ” የሚለው የ16 ዓመቱ ታዳጊ ለያሃ ሚዲያ ሲናገር “እኔ ተኩስ የሚባል ነገር አላውቅም። ተኩሼም አላውቅም” ይላል። የሸረሪናውን ኦፕሬሽን ሲተርክ “ምን እንደሆነ አላውቅም” በማለት እንደ ህልም ነው የሚያስታውሰው።
አባቱ የሕወሓት ታጋይ የነበሩት የሽሬ ታዳጊ “አባትህን የገደለውን ብልጽግናን ተበቀል” ተብሎ እንደተመለመለ ለዚሁ ሚዲያ ሲናገር ይሰማል። እሱም ልክ እንደ ጓደኞቹ ወደ ሸረሪና የገባው ከላይ በተገለጸው መንገድ በቅብብሎሽ ነው።
“ጠፋ” የተባለው አርሚ 13 – (የሲኦል ባቡር) ወዴት ገባ?
ወዲ እንጥሩ “በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ አባላት የነበሩት” በማለት ማለቁን የገለጹለትና በተለያዩ አደረጃጀቶች ተዋቅሮ የነበረው አርሚ 13፣ አርሚ 70ን እንዲተካ ዕቅድ ተይዞ ገና ንቅናቄ ሲጀምር መነሻው ከሽራሮ ነበር። አርሚው ስንቁን ቋጥሮ፣ የነፍስ ወከፍ መሣሪያውን ይዞ፣ ቦምብ ተሸክሞ፣ ከኋላው በጭነት መኪና ተጨማሪ ሎጂስቲክስ ጭኖ ንቅናቄ ሲጀምር የመከላከያ የደህንነት መረጃ ስለነበረው በድሮን አጠቃው። ያሃ ሚዲያ እንደዘገበው አርሚው ገና ከጅምሩ በድሮን መመታቱ ብቻ ሳይሆን፣ ከድሮን ጥቃት የተረፈውን ሰብስቦ ወደ ኤርትራ ሲጓዝ ሸሸዊት ላይ የጫኑት ቦምብ መኪናቸው ውስጥ ፈንድቶ ጉዳት አደረሰባቸው።
ሐምሌ 20 ቀን ሸረሪና የደረሰው አርሚ 13፣ ሐምሌ 25 ቀን በሸረሪና ግንባር ስለተጀመረው ጦርነት አባላቱ የሚያውቁት ነገር ቢኖር እንዴት እንደተበተኑ እንጂ፣ የጦርነቱ ሁኔታ አሁንም ድረስ አልገባቸውም። ለማስረዳት ቢሞክሩም የሚሆንላቸው አልሆነም።
ከሽራሮ ወደ ኤርትራ ገብተው፣ የኤርትራ ወታደሮች በተሽከርካሪ ወደ ሱዳን ያጓጓዟቸው የአርሚ 13 አባላት “ከፋኖ ጋር ስምምነት ተደርሷል፤ የትግራይን መሬት በቀላሉ እናስመልሳለን” በሚል ከተነገራቸው ውጪ ሌላ የሚያውቁት ዝርዝር ነገር የለም። አንዳንዶቹ የት እንደሚሄዱም አያውቁም።
ሌሊት 12 ሰዓት ላይ ተጀምሮ ጠዋት 2 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀውን ፈጣን ውጊያ አስመልክታ እያለቀሰች ምስክርነቷን የሰጠችው የ14 ዓመቷ እምብራቅ ሀፍቱ እንዳለችው ሁኔታው ዘግናኝ ነበር። ሙያውም ሆነ ልምዱ የሌላት ይህቺ ታዳጊ “የቻለ ተከዜ ውስጥ እየዘለለ ገባ፤ የቻለ ተሻገረ፤ ያልቻለው ደግሞ ውኃ ውስጥ አለቀ። ያለቀው ሰው በጣም ብዙ ነው” እያለች ታለቅሳለች። ስለ ጦርነቱ የምታስታውሰው ይህንን ብቻ ነው። ውስጧ የቀረው የህወሃት በረከት ወገኖቿ ተከዜን ሲቀላቀሉ ማየት ነው። ጠያቂው ምላሹን እየሰማ ያነባል።
“አለቆች በጀልባ ኮበለሉ” ሲል የገለጸውና ራሱን የሚያውቅ የአርሚው አባል በሰጠው ምስክርነት፡ “የአገር መከላከያ የሰነዘረውን ምት አልቻልነውም፤ የምንመጣጠንም አልነበርንም። አስቀድመው ከበውናል። በጣጥሰውናል። መዋጋት ቀርቶ ለማምለጥም እንዳንችል አደረጉን” በማለት የደረሰውን ጉዳትና ያለቁት ወንድሞቹን እያሰበ ይተርካል። እንዲህ ያለ እሳት ውስጥ ሳያውቁና ሳይፈቅዱ የገቡ ንጹሃን የሚያልቁት እስከመቼ ነው? አይበቃም ወይ?
ምንድን ነበር የሆነው?
ወደ ሸረሪና ለመግባት ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው ያሉት። አንደኛው በጀልባ ተከዜን ማቋረጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው በተከዜ ድልድይ በኩል ነው። የመከላከያ ሠራዊት ጦርነቱ በተጀመረበት ቅጽበት ድልድዩን ተቆጣጠረ። ነድፎት በነበረው የቴክኖሎጂ ጦርነት ታግዞ እግረኛው በሸረሪና የተዘረጋውን ምሽግ ሦስት ጫፎች ዘጋ፤ ምንም ዓይነት የደጀን ድጋፍ እንዳይደርስም ከጀርባ ያለውን ኃይል በተመሳሳይ ሰዓት አጠቃ።
ደጀኑም ሆነ ምሽጉ ላይ ከፍተኛ ሎጂስቲክስ አከማችቶ የነበረው አርሚ 13 ከመከላከያ በደረሰባቸው ከባድ ምት ፈረሱ። ላለፉት አምስት ዓመታት በሕወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በነበረው ሸረሪና ላይ የሰፈረው አራት ሺህ የሚልቅ ሠራዊት ከየትኛውም አቅጣጫ ለመተንፈሻ የሚሆን ከለላ አጣ። በዚህ ጊዜ ታዳጊዋ እንዳለችው ሽሽቱ ወደ ተከዜ ወንዝ ሆነ። የአንድ አገር ልጆች በውይይት ችግራቸውን እንዳይፈቱ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት የተከማቸው እሳቤ የፈጠረው ጣጣ፣ ያለ ፍላጎታቸው ወደ ጦርነት እንዲገቡ የተደረጉ ሕፃናትን ሳይቀር በላቸው።

ከተማረኩት ከ600 በላይ የአርሚ 13 ኃይሎች ውስጥ ምስክርነታቸውን የሰጡት እንዳሉት ተከዜ ብዙ ምስኪኖችን በልቷል። ሕይወት በከፍተኛ አደጋ ውስጥ በነበረችበት በዚህ አጭር ነገር ግን ከባድ ጦርነት፣ የትግራይ እናቶች የደረሰባቸው ኪሳራና አገርም ያጣቻቸው ልጆች በሕወሓት የጦርነት ፍላጎት ምክንያት ነው።
የትግራይ የሰላም ኃይሎች መሪ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ (ወዲ እንጥሩ) “አጥፊው ቡድን በከፈተው አላስፈላጊ ውጊያ ምክንያት አርሚ 13 በመባል የሚታወቀው ዋና የጦር ክፍል ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ሆኗል” በማለት ሀዘናቸውን የገለጹት ሙሉ መረጃ ስላላቸው ነው።
«ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ጦርነት የመረጠው አቅዶበት ሳይሆን ማመዛዘን አቅቶት ነው» ያሉት ጄኔራሉ፤ ቡድኑ ከጦርነት በኋላ የሚመጣውን ኪሳራ እንደሚረዳ አልሸሸጉም። ሰላም ቢሰፍን ግን “ተጠያቂ እሆናለሁ” የሚል ሥጋት ስላለበትና በባሕሪው ያለ ጦርነት መኖር ስለማይችል ጦርነት መርጦ የትግራይ ምስኪን ልጆችን እንዳስጨረሳቸው አመልክተዋል።
እሳቸው ባላቸው መረጃ ከ500 በላይ የአርሚ 13 አባላት ቁስለኛና ምርኮኛ ሆነው በመከላከያ ሠራዊት ሕክምናና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፤ ሌሎቹስ የት ገቡ? ሕወሓትና ሕወሓትን አሁን እየመሩ ያሉት አካላት የሚመልሱት ጥያቄ ነው።
“ነገሩ አልቋል”
የሸረሪና ጦርነት በሁለት ሰዓት ውስጥ ከመጠናቀቁ አንድ ሳምንት በፊት ሻዕቢያ ባደራጀው፣ በጀትና አጀንዳ በሚመድብበት የዓመፅ አደረጃጀት የጋራ መድረክ ስብሰባ ላይ “ነገሩ አልቋል” ተብሎ ነበር። በተለያዩ የጋራ መድረኩ ውይይቶች ላይ ሱዳን ወዳለው የትግራይ ኃይል በመሄዳቸው በስብሰባው መካፈል እንዳልቻሉ የሚገልጹት አቶ አባይ ግደይ፣ የአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋና ኦባሳንጆ ቢያስፈራሩም ተቀባይነት እንዳላገኙና መሬት ላይ ከሕወሓት ጋር አብረው የሚሠሩ እርምጃዎች መጀመራቸውን ተናግረው ነበር። ዋናው ኃይል [ሕወሓት] በቀጥታ ወደ ጦርነት እንዳልገባና ሙሉ ጦርነቱ የቀናት ጉዳይ እንደሆነ መናገራቸውን አዲስ ሪፖርተር ዘግባ ነበር።
በዚሁ ዘገባ መደበኛ ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት በሚቀርበው የመረጃ ልውውጥ ወቅት ከዋናው ስብሰባ በላይ ምስጢርና የልብ መሻት ይሰማ ነበር። “የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የጋራ የትግል መድረክ” በሚባለውና በአቶ ነዓምና እንዲሁም በአቶ ልደቱ አያሌው በሚመራው የሻዕቢያ ክንፍ መደበኛ ስብሰባ ላይ “ጦርነቱ ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም፤ ተጠባባቂ ኃይል ያስፈልጋል። ይህ ተሠርቷል፤ የዓለም ሚዲያዎችና የእኛው ሰዎች ሳይቀር ከአዲስ አበባ ተንጫጭተዋል” በማለት አቶ አባይ ሲናገሩ አድናቆት ተችሯቸው ነበር።

ራሱን “የሰላማዊ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የጋራ የትግል መድረክ” በሚል ጥላ ሥር ያደራጀው ይህ ስብስብ፣ ምርጫ እንዳይካሄድ፣ ቅቡልነት እንዳይኖረውና ዓመፅ በማቀጣጠል የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም የሻዕቢያና የትሕነግ ክንፍ የሆኑ አመራሮች እንዲጣመሩ ተደርጎ የተዋቀረ እንደሆነና ከምርጫው በኋላ እንደሚከስም የተነገረለት ስብስብ እንደነበር አመራሮቹን ጠቅሰን መዘገባችን አይዘነጋም።
ከዚያስ?
ተጣምረው የኢትዮጵያን ታሪካዊ ጠላቶች ማሽመድመድ የሚችሉ ወንድማማቾች፣ የአንድ ሰፈርና የሥጋ ዘመዶች ሳይቀሩ እንዲባሉ የሚያደርገው የሕወሓት የአልባንያ ኮሙኒዝም እሳቤ በየትኛውም ምድራዊ አመክንዮ ተወያይቶ መፍትሔ እንዲፈልግ አያስችለውም። ከውስጡ የወጡ ሰዎች እንደሚሉት ራሱን በዚህ እሳቤ ችክ አድርጎ ወደ “ሽብርተኝነት” እየበረረ ነው።
ቀደም ሲል በቀን ሁለቴና ከዚያ በላይ “ሕወሓት መስመራችን” ሲሉ የነበሩ፣ ዛሬ ላይ “ካርቶን ራሶች” እያሉ ለመስማት በሚሰቀጥን ደረጃ “ማሰብ የማይችሉ፣ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም የዓለምን እውነታ ማገናዘብ ያቃታቸው” እያሉ እየተዛበቱባቸው ነው።
ይህ ቡድን “መጫወት ናፈቀኝ፣ ተጫውቼ አላውቅም” የምትለውን ዓይነት ሕፃናት እያገተና እያፈነ እያስጨረሰ ነው። ከኢትዮጵያ ላይ በግፍ የዘረፈውን፣ የዓሰብን ማንቁርት ይዘው ሊያስተፉት የተነሱ ጀግኖችን የፈራው ሻዕቢያ፣ ሲያሻው የሚጨፈጭፈውንና የሚዘርፈውን የትግራይ ሕዝብ ዳግም እየማገደበት ነው። ኤርትራ የጦርነት አውድማ እንዳትሆን፣ ትግራይንና የአማራ ክልልን የጦርነት ቀጠና ለማድረግ አቅዶ ከግብፅ ጋር ኢትዮጵያን ለሚያተራምሰው ሻዕቢያ የትግራይ ታዳጊዎች፣ አዛውንቶችና ወጣቶች የሚያልቁት እስከ መቼ ነው?
በነበረው ዕቅድ መሠረት የሸረሪናው ኦፕሬሽን ቢሳካ ኖሮ ከጀርባ ሆኖ ወደ ቤኒሻንጉል እንዲገሰግስ የተዘጋጀው ኃይል እንዲፈጥር የታሰበው ሁኔታ ሁሉ ጉዳዩን ለሚያውቁ ዘግናኝ ነው። ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንዲወረወር የተዘጋጀውና በመከላከያ ሠራዊት አመድ የሆነው የባዕድ ጦር መጠኑና ማንነቱ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የሸረሪና ኦፕሬሽን “የትግራይን ሕዝብ የመጨረስ ጦርነት ነው” በሚል ተከታታይ መግለጫ ያሰማው ሕወሓት፣ ግብረ-መልስ ያጣውና ዓለም ዝም ያለው ከጀርባ የታዘለው አጀንዳና ትርምስ ስለሚታወቅ ነው።

የሸረሪናን ኦፕሬሽን ጉዳዩን የያዘው አካል በቪዲዮ፣ በምስክሮችና ዕቅዱን ባሰሉት ባለሙያዎች ተደግፎ በዝርዝር ሲያቀርበው፣ አገራቸውን ለሚወዱ ሁሉ “ከምን ጉድ ወጣን!” የሚያስብል ስለመሆኑ ጥርጥር እንደሌለው እዚያው አካባቢ ያሉ የመዋቅር ሰው ለአዲስ ሪፖርተር ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉት መከላከያን ማራከስና መሪዎችን በመጥፎ በመሳል የሚረጨው ፕሮፓጋንዳ፣ የከሸፈባቸውን አካላት ብስጭት የሚወልደው ትርክት ነው።
በሸረሪና ከተደመሰሰውና ከተማረከው የጦር መሣሪያ ባሻገር፣ ከሸረሪና ካምፕ ወጣ ብሎ ግዴማ በተባለች ቦታ መጋዘን ውስጥ እንዲሁም ከመሬት በታች በኮንክሪት በተሠራ ግዙፍ ምሽግ ተከማችቶ የተገኘው ተተኳሽ፡ የቡድንና የነፍስ ወከፍ መሣሪያ፣ ሮኬት፣ የአጭርና መካከለኛ ርቀት ሚሳይሎች፣ RPG-7፣ የሳተላይት ስልኮች፣ የሬዲዮ መገናኛ፣ የቅኝት ድሮኖች፣ የድሮን ማደራጃ ጣቢያ፣ የመኪና መለዋወጫዎች እና ለጊዜው ምንነታቸውን ለመለየት ያልተቻሉ የጦር መሣሪያዎች ናቸው። አዲስ ሪፖርተር ባላት መረጃ የተማረኩት መሣሪያዎች ያላቸው የአገራት ንክኪና ብዛት “ከዚያስ?” የሚለውን ጥያቄ ዜጎች ሁሉ ሊጠይቁት የሚገባ ነው።
የወደፊቱን ትውልድ ለማዳንና የሕዝቡን እንግልት ለማስቆም ከግጭት ይልቅ ወደ ሰላማዊ መንገድ መመለስ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን የትግራይ ሰላም ኃይሎች መሪ አስታውቀዋል። በየአካባቢው የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ይህንን አደጋ ተረድተው የሕዝቡን ስቃይ የሚያስቆም ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረስ እንዳለባቸው አሳስበዋል። በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ ይህ መንፈስ ይሰፍን ዘንድ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ህብረት ግድ ነው።
“ተጫውቼ አላውቅም። መጫወት አማረኝ” የምትለዋ ታዳጊ ልጅህ፣ ልጅሽ፣ ቤተሰባችን ናት። ሕወሓት ባስተዋወቀን የዘር ፖለቲካ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት የሄድንበት የጭካኔ ጉዞ አልበጀንም። ያተረፈልን ዛሬ የደረስንበትን የርስ በርስና የውክልና ጦርነት ነው። ልጆቻቸውን ወደ ውጭ አገር እየላኩ የሚያስተምሩ፣ ሀብት የሚያፈሩላቸውና ሳያፍሩ የልጆቻቸውን የተቀማጠለ ምስል እያሳዩ ለሚሳለቁብን ጦርነት ጠማቂዎች ማንም ይሁን ማን “በቃን” ማለት አለብን። ዛሬ ጦርነቱ ሳይበቃ የዝናብ እጥረት ከዚያም ከዚህም ክፉ ዜናዎችን ሊያሰማን ዳር ዳር እያለ እንደሆነም ልብ ማለት አግባብ ነው።
አልጃዜራ የተወሰኑ የህወሃት ተዋጊዎች በተከዜ ወንዝ ተወስደው አስከሬናቸው መገኘቱን ከመናገሩ ውጪ ህወሃት ጸጥ ብሏል። ይባስ ብሎ ለትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ በመምስል በመግለጫ ለቅሶ ይደርሳል። ለተጨማሪ ጥፋት ኤርትራ ገብቶ እየመከረም ነው።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






