አሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ የአገሪቱ ዲፕሎማቶች በሌሎች አገራት ምርጫዎችና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠቡ የሚደነግገውን መመሪያ ይፋ ካደረገ ቆይቷል።
እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2025 በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ ተፈርሞ ለሁሉም የአሜሪካ ኤምባሲዎች የተላከው ይህ ይፋዊ መመሪያ፤ አሜሪካ ለረጅም ዓመታት በሌሎች አገራት ምርጫዎች ላይ ስታደርግ የነበረውን የቁጥጥር፣ የክትትልና የትችት ሚና በከፍተኛ ሁኔታ የገደበ ነው።
የመመሪያው ዋና ዋና ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፦
- የአገራትን ሉዓላዊነት ማክበር፦ መመሪያው የአሜሪካን “ቅድሚያ ለአሜሪካ” (America First) የተሰኘውን መርህ የሚከተል ሲሆን፣ የሌሎችን አገራት ብሔራዊ ሉዓላዊነት ማክበር እንደሚገባና አሜሪካ የራሷን የፖለቲካ አስተሳሰብ በሌሎች ላይ መጫን እንደሌለባት ያሳስባል።
- ከአስተያየት መቆጠብ፦ የአሜሪካ ኤምባሲዎችና ዲፕሎማቶች በማንኛውም አገር ስለሚካሄድ ምርጫ ፍትሐዊነት፣ ግልጽነት ወይም ስለታዩ ጉድለቶች በይፋ አስተያየት መስጠት አይችሉም። አስተያየት መስጠት የሚቻለው ጉዳዩ “የአሜሪካን ቀጥተኛ የውጭ ጉዳይ ጥቅምን የሚነካ” መሆኑ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ሲረጋገጥ ብቻ ነው።
- የምስጋና መልዕክት ብቻ፦ አሜሪካ በሌላ አገር ምርጫ ላይ መግለጫ መስጠት በሚኖርባት ጊዜም ቢሆን፣ መግለጫው አጭር፣ አሸናፊውን ዕጩ “እንኳን ደስ አለህ/ሽ” የሚልና በጋራ ጥቅሞች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን አለበት። የምርጫውን ሂደት መተቸትም ሆነ መገምገም በጥብቅ የተከለከለ ነው።
- የታዛቢ ድርጅቶችን አለመደገፍ፦ ቀደም ሲል የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እንደ ካርተር ሴንተር (Carter Center) ያሉ ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢ ድርጅቶች የሚያወጧቸውን የትችት ሪፖርቶች ይደግፉና ያሰራጩ ነበር። ነገር ግን ከዋሽንግተን ቀጥተኛ ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር አሁን ላይ እነዚህን ሪፖርቶች መደገፍ ተከልክሏል።
መመሪያው በኢትዮጵያ ምርጫ ላይ ያለው ተጽዕኖ
ይህ የአሜሪካ የፖሊሲ ለውጥ ሰኞ ግንቦት 24፤ 2006 ዓም ለተካሄደው ምርጫ ትልቅ ትርጉም አለው። ቀደም ባሉት ዓመታት ዋሽንግተን በኢትዮጵያ ምርጫ ወቅት ስለ ሂደቱ ዲሞክራሲያዊነት፣ ስለ ሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እና ስለ ምርጫው ነጻና ፍትሐዊነት ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን ትሰጥ ነበር።
ነገር ግን በዚህ አዲስ መመሪያ መሠረት፣ በኢትዮጵያ በሚካሄደው ምርጫ ማንኛውም የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣን ወይም በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በምርጫው ሂደት ላይ ምንም ዓይነት የትችትም ሆነ የድጋፍ አስተያየት አይሰጥም። ይህም ማለት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ የውስጥ የፖለቲካ ውድድር ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ሙሉ በሙሉ ይቆጠባሉ ማለት ነው።
ይህ የአሜሪካ አካሄድ በተለይ በዳያስፖራ የሚገኘውን ተቃዋሚ አንገት ያስደፋና ያለ ተስፋ ያስቀረ ሆኗል። መመሪያው የዛሬ ዓመት የወጣ መሆኑን የማያውቁ ግን ፖለቲካ እንተነትናለን የሚሉ አሁንም ከአሜሪካ የውግዘት መግለጫ እየጠበቁ እንደሆነ ጎልጉል ባደረገው ማጣራት ለመረዳት ችሏል።
በመሆኑም ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ምርጫ ቦርድ አሸናፊውን ፓርቲ ይፋ ሲያደረግ ከአሜሪካ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ለፓርቲውና ለፕሬዚዳንቱ የሚደስር ይሆናል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






