አዲስ ሪፖርተር ዜና – በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ቋሚ መልዕክተኛ መሥሪያ ቤት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቢሮ ያለውን አክብሮት በመግለጽ”በማኅበረሰብ ላይ የተመሠረተ የሰላም ተነሳሽነት” (Community-based Peace initiative) የሚመለከት በዩኤስቢ ፍላሽ ድራይቭ (USB flash drive) የተጫነ የቪዲዮ መልዕክት የያዘ ደብዳቤ ልኳል።
ከሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ ጋር በመናበብ የትግራይ ክልልን የተረከበው የዶክተር ደብረጽዮን ቡድን አስተዳደር “የአፍሪቃ ቀጣናን ሊያተራምስ የሚችል አውዳሚ ጦርነት ሊነሳ ይቻል” ሲል ዲፕሎአምቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ አገራት መንግስት ላይ ጫና እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ደብዳቤ ካሰራጨ በኋላ፣ የኤርትራ መንግስት “ጽምዶ” የህዝብ ለሕዝብ መፋቀር መሆኑን፣ ለቀጠናው ሰላምም ትልቅ አስተዋጾ እንዳለው ማመልከቱ ሁለቱ አካላት ተናባው እንደሚሰሩ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ሜጀር ጄነራል ተሾመ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጽምዶ የምትባል ነገር የተጀመረችበት ሒደት መኖሩን አመልክተው እንቅስቃሴውን “ፀረ ሉዓላዊነት” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል። ሜጀር ጄነራል ተሾመ፤ “ጫንቃቸውን ለፈርኦን ቀንበር” በሰጡ የኢትዮጵያ አካላት እና “አካባቢው ላይ ባሉት ስብስብ” የተፈጠረ ያሉት ጽምዶ አካሄዱን በጥብቅ እየተከታተሉት እንደሆነ አስታውቀውም ነበር።
“መከላከያ ሠራዊት በራሱ ቻናል ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ “የአታሼ ማኅበረሰብ” አባላት ስለዚህ ጉዳይ “በደንብ እንዲያውቁ እና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሰፊ ሥራ ተሰርቷል” ተሰርቷል ያሉት ጄራሉ፣ ለዲፕሎማትና ከኢትዮጵያ ጋር ለሚሰሩ ወዳጅ አገራት መረጃ በብቃት እንዲሰጥ የተደረገው እርምጃ መውሰድ ቢያስፈልግ እንኳ የማንንም ፈቃድ መጠየቅ ስለማያስፈልግ ነው።
ይህ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት አስጊ ተደርጎ እንደማይወሰድ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ሐሳቡን ለመተግበር የሚደረግ እርምጃን በተመለከተ ግን አስጠንቅቀዋል። “እቺኛዋን የጽምዶ ሐሳብ በተመለከተ ግን፤ ይቺን ቅዠት ወደ መሬት እናወርዳታለን ብለው ስንዝር እንቅስቃሴ ቢያደርጉ፣ እንደ ሉዓላዊ አገር ይሄ ተቋም ደግሞ በመንግሥት ግዳጅ እንደተሰጠው፣ ኃላፊነት እንደተሰጠው፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሥራ እንደሚሠራ አካል፤ ሰም በእሳት እንደሚቀልጥ ይቀልጣሉ ብለን ነው የምናስበው፣ የምናምነው” በማለት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴሌቪዥን መናገራቸው ይታወሳል።
“ለጀርባ ታሪክ ያህል፣ ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀ ጊዜ ውስጥ፣ ጽምዶ ንሰላም (Tsimdo N’Salam) በሚል አገር በቀል መጠሪያ ተከታታይ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች፣ የማኅበረሰብ ውይይቶች፣ የባሕል ልውውጦች እና እምነትን የመገንባት ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል። ይህ በትግርኛ ቋንቋ ለሰላም መጣመር” (Engagement for Peace) የሚል ትርጉም አለው። ይህ ክቡር ሕዝባዊ ዘመቻ ዓላማው እምነትን መልሶ መገንባት፣ ማኅበራዊ ትስስርን ማደስ እና ለዓመታት በግጭትና በመለያየት ሕይወታቸው በእጅጉ በተጎዱ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ነው” የሚል ገዢ ትርጉም የሰፈረበት ደብዳቤ፣ በማህበረሰብ ደረጃ በራሱ ታጣቂዎች፣ የተፈጠመውን ግፍ፣ የመርመራ ሪፖርቶች ገሃድ እንዳደረጉት፣ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በማስረጃ ያረጋገጣቸውን በዓለም ዓቀፍ ወንጀለኛነት የሚያስፈርጁ ግፎች ያለው ነገር የለም።
የ”ትምዶ” (Tsimdo) አስፈላጊነት በግብሩ ብቻ ሳይሆን፣ በተፈጥሮአዊ እና በአገር በቀል መገለጫው ላይ ጭምር አስፈላጊ እንደሆነ ደብዳቤው አመልክቷል። አክሎም በማኅበረሰቡ አባላት፣ በተለይም በሚዋሰኑ ድንበሮች አካባቢ በሚኖሩ የአገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ቤተሰቦች የሚመራ በመሆኑ፣ በውይይት እና በቀጥታ የሰዎች ግንኙነት አማካኝነት ግንዛቤን፣ ፈውስን እና አብሮ መኖርን ለማጎልበት ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያንጸባር የሻዕቢያ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታ ዋና ጸሃፊ ጽምዶን ያብራራል። ስለጽምዶ ባህላዊ እሴትነት ያስረዳው ደብዳቤ በህወሃት ፈቃድ ትግራይ ውስጥ ጦር እያሰማራና ኢትዮጵያ ላይ ውጊያ የሚከፍቱ ኃይሎችን ማደረአጀት የጽምዶ አንዱ ተግባር ስለመሆኑ ያለው ነገር የለ።
“እርቅ በባሕላዊ እሴቶች፣ በጋራ መከባበር እና በጋራ ኃላፊነት ላይ በተመሠረቱ ተግባራዊ እርምጃዎች እንዴት ወደፊት ሊራመድ እንደሚችል ያሳያል። ይህ ተነሳሽነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘላቂ ሰላምን እና ሰውን ማዕከል ያደረገ የሰላም ግንባታን በተመለከተ ለገነባው ራዕይ መሠረት ከሆኑት መርሆዎች መካከል ትርጉም ያለው ምሳሌ ነው” ሲል ሻዕቢያ ለተመድ ዋና ጸሃፊ የላከው ደብዳቤ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ስለመግባትና ታጣቂዎችን ማደራጀት በምን መልኩ እንደሚደገፍ አላብራራም። ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ዓለም ዓቀፍ ወንጀሎች እንዴት እንደሚታዩም ያለው ነገር የለም።
በሱዳኑ የጽምዶ ስብሰባ ላይ ተዋናይ ከነበሩት መካከል አንዱ የነበሩት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ባንዳ” በሚል ለቀረበባቸው አቤቱታ “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በአህጉር አቀፍ ደረጃ ለማስፈን በተደረገ የትብብርቭ ስብሰባ ላይ ራሴን ወክዮ ነው የተገኘሁት” በማለት ድንበር ላይ ነዋሪዎች ሲሳሳሙ የሚያሳይ ፎቶ ማሰራጨታቸው ይታወሳል። ሻዕቢያ ይህንኑ ቪዲዮ በማያያዝ የተጀመረውን የጽምዶ ግንኙነት “ታድቅ” አድርጎ ለማቅረብ አባሪ አድርጎ መላኩን ቪዲዮውን ያዩ መስክረዋል።
ይህንኑ ቪዲዮ “አብሮ የተያያዘው ቪዲዮ የቀረበው የማኅበረሰቡን እንቅስቃሴዎች እንደ ምስላዊ መዝገብ ለማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ በአገር በቀል የሚመሩ የእርቅ ተነሳሽነቶች ክፍፍሎችን ወደ መለወጥ፣ እምነትን መልሶ ለመገንባት እና የዘላቂ ሰላምን መሠረት ለማጠናከር ሊጫወቱ የሚችሉትን የለውጥ ሚና ለማሳየት ጭምር ነው። በዚህ ረገድ፣ ይህ ተነሳሽነት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቢሮ ለግንዛቤ እና ለግምገማ የቀረበው፣ የተገኘው ተሞክሮ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በማኅበረሰብ ላይ በተመሠረቱ የሰላም ግንባታ፣ የእርቅ እና የመከላከያ እርምጃዎች ዙሪያ ለሚደረጉ ቀጣይ ነጸብራቆች አስተዋጽኦ ያበረክታል በሚል ተስፋ ነው” ሲል ጽምዶ ለተቋሙ ሳይቀር ሞዴል እንደሚሆን የጠቀሰው ደብዳቤ፣ በግብጽ ዕቅድ አቅራቢነትና ድጋፍ በኤርትራ ውስጥ ኢትዮጵያን እንዲወጉ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሽፋን የሚሰባሰቡት ቡድኖች ሚና አላስታወቀም።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ መንግሥት ቋሚ መልዕክተኛ መሥሪያ ቤት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ቢሮ የላከው ደብዳቤና የበዓል ቀን ቪዲዮ አስመልክቶ “ሻዕቢያና ወያኔ ተናበው የሚሰሩት ስራ ዓለም ሁሉ እንደ እነሱ ቆም የቀረና ምንም የማይገባው ይመስለዋል” በማለት ባነበቡት ደብዳቤ ማዘናቸውን የገለጹ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር “ሻዕቢያ ምን እያከናወነ እንደሆነ፣ እሱ ራሱን ከሚያውቀው በላይ ትልልቆቹ የተባበሩት መንግስታት አባል አገራት ይረዳሉ” ያሉት ምሁሩ “ችግሩ ሻዕቢያ ቆሞ በመቅረቱ በዚህ ደረጃ መረዳቱ ስለሌለው ነገሩ ሁሉ የዘመናችን አስደናቂ ተውኔት እየተባለ ያልፋል። ኮሚኮች ለመድረክ ፉገራ እንኳን በዚህ ደረጃ ቅሽም ድረሰት አይደርሱም” በማለት አስተያየት እንኳን ለመስጠት የማይመች ሲሉ ደብዳቤውን ገልጸውታል።
“በትግራይ እናቶችና ሴቶች ማህጸን ባዕድ ነገር፣ ብረታብረትና ደብዳቤ በመላክ፣ ሆን ብሎ በኤች አይቪ ቫይረስ በመበከል፣ በደንብ በጭካኔ ያልፈተሙትን ‘በታዘዝከው መሰረት አልተገበርክም’ በሚል ሲቀታ እንደነበር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በተለያዩ ተቋማትና ታዋቂ ሚዲያዎች የተረጋገጠበት ወንጀለኛ አገር መሪዎች በዚህ ደረጃ በትግራይ ህዝብ መሳለቅ የጀመሩት ገና ጽምዶ የሚባለውን ጉዳይ ሲጀመሩ ነበር” ያሉት ምሁሩ፣ “ካሁን በኋላ ስለጄኖሳይድ፣ ስለአስገድዶ መድፈርና ስለዘረፋ አታንሱ” በሚል ቅድመ ሁኔታ ጽምዶን ሲጀመሩ ይህ ደብዳቤ መረቀቅ መጀመሩን አውቅ ነበር” ያሉት ምሁሩ በዚህ ጉዳይ የህወሃትን ክህደትና በትግራይ ሕዝብ ስብዕና ላይ የፈጸማቸውን፣ የሚፈጽማቸውንና ሊፈጽም ይችላል የምለውን በመዘርዘር በስፋት በተከታታይ አቀርባለሁ” ብለዋል።
ግብጽ ኤርትራን፣ ሱዳን፣ ወያኔ፣ ፋኖና ወያኔ የሰበሰባቸው ስምንት የነጻ አውጪ ታጣቂዎችን በጽምዶ ስም በማደረጃት ኢትዮጵያን ለማወክ እንደምትሰራ የአሜሪካ ባለስልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች፣ እንዲሁም የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ አስመራና መቀለ በመገኘት በግልጽ ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያና ምክር መለገሳቸውን መዘገባችን ይታወሳል። አገራቱ የራሳቸው ብሄራዊ ፍላጎት ስላላቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲያሳስቡ ይህን በሚተላለፉት ላይ ማዕቀብ እንደሚጥሉና ከዚያም የዘለለ እርምጃ እንደሚወስዱ አሳስበዋል።
ኤርትራ ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ እንደሚነሳላት ቃለ የተገባላትም በቅድመ ሁኔታ ሲሆን ይህ ባለመሟላቱ ይህ እስከተጻፈ ድረስ ጆንባይደን የፈረሙት የማዕቀብ ደብዳቤ በዶናልድ ትራምፕ አልተሻረም።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






