የኦባሳንጆ አስቸኳይ የመቐለ ጉዞ፦ “ህወሃት ወደ ቀልቡ ይመለስ እንደሆነ የመጨረሻ እድሉን እንዲጠቅምና የፕሪቶሪያውን ስምምነት እንዲያከብር ለመምከር ነው” ሪፖርታዥ

Date:

ዶክተር ደብረጽዮን የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከሚፈቅደው ውጪ አስተዳደር ፈንቅለው ስልጣን ይዘዋል። በስምምነቱ መሰረት ህገወጥ እንደሆነ ያመኑትን ምርጫና በዚሁ ህግወጥ ምርጫ የተመረጡትን ይዘው ክልሉን እየመሩ ነው። ከዚህም በላይ ከሻዕቢያ፣ ከሱዳን እና አገር ውስጥ ካሉ ታጣቂዎች ጋር ህገመንግስቱ ከሚፈቅደው ውጪ ወታደራዊ ጥምረት መመስረታቸውን እያወጁ ነው። ለዓለም ዓቀፍ የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ ደግም ድርድር እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ እያስታወቁ ነው። በዚህ መካከል …. ራሳቸውን የሰላም ኃይል የሚለው ወታደራዊ ክንፍ ህወሃትን ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ነቅሎ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን እየገለጸ ባለበት…

አዲስ ሪፖርተር ዜና – መንግስት ለህወሃት “ቢሰማ” የመጨረሻ እድል ለመስጠት ቁርተኛነቱን እንዳለው መግለጹን ለማሳየት ብዙ ርቀት እንደሚጓዝ ተገለጸ። አቶ ጌታቸው ረዳ እና አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በአልጀዚራ ላይ ያወጡት የጋራ መጣጥፍ እና የኦሊሴጉን ኦባሳንጆ አስቸኳይ የመቐለ ጉዞ በተመሳሳይ ቀን ሰኔ 4 ቀን 2018 ዓ.ም መሆኑ ተራ አጋጣሚ እንዳልሆነም ተመልክቷል። “ፊኛው እጅግ በተወጠረበት ወቅት” ፈጥኖ ምላሽ የሰጠውና የአፍሪካ ህብረት ውክልና ያለው ቡድን ወደ ትግራይ ማቅናቱ፣ የተቀናጁ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃዎች መሆናቸውን ታዛቢዎች እየገለጹ ነው።

አዲስ ሪፖርተር ባገኘው ቀጥተኛ መረጃ፣ የአፍሪካ ህብረት ወደ ትግራይ የታወቁትን አካላት የላከው ህወሃት ለጦርነት እያደረገ ያለውን ዝግጅት ስለሚረዳና ጠንቅቆ ስለሚያውቅ፣ በመንግስት በኩል የመጨረሻ እድላቸውን እንዲሞክሩ ለማድረግ ነው። መንግስት የጦርነት ፍላጎት ስለሌለው ይህን አማራጭ ህወሃት እንዲጠቀምበት ፈቀደ እንጂ፣ በህወሃት በኩል አንዳችም ድብቅና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር የለም።

የአፍሪካ ህብረት ውክልና ያላቸው ኦባሳንጆ ወደ ትግራይ ሲያቀኑ በሙሉ የመንግስት እውቅና እና ፈቃድ እንደሆነ ያመለከቱት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ታማኝ ምንጮች፣ “ህወሃት ወደ ቀልቡ ይመለስ እንደሆነ እድል እንዲሰጠው ታስቦ ነው። በአሁኑ ወቅት ሁሉም የህወሃት ፖለቲካም ሆነ የታጣቂ አመራሮች መግቢያና መውጫ፣ መዋያና ማደሪያ በፌዴራል መንግስት ቁጥጥር እና ክትትል ስር ነው” ሲሉ በመንግስት በኩል ስጋት እንደሌለ አመልክተዋል።

“እውነታው ይህ ቢሆንም መንግስት ዛሬም በሆደሰፊነት ለትግራይ ህዝብ ሲባል ዳግም እድል እየሰጠ ነው። አሁን ከሚታወቀው፣ በክትትል ስር ካለውና በትዕግስት እየታለፈ ካለው ወጣ ያሉ እንቅስቃሴዎች ሲታዩና ሲታመንበት ግን የማያዳግም እርምጃ መወሰዱ አይቀሬ ነው” በማለት ለውሳኔውና ለጉዳዩ እጅግ ቅርብ የሆኑት ክፍሎች ለአዲስ ሪፖርተር አስታውቀዋል።

“በተደጋጋሚ ህወሃት ‘አደራድሩኝ’ እያለ እየተማጸነ ነው። የፌዴራል መንግስት ደግሞ ድርድሩን ፕሪቶሪያ ላይ ጨርሰናል፤ አሁን ትግበራ ነው እያለ ነው” ያሉት እነዚሁ የመረጃው ባለቤቶች፣ መንግስት በማንኛውም ጊዜ ለትግራይ ሕዝብ ሲል ጥንቃቄ፣ ትዕግስት፣ ብልሃትና እንደመንግስት ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚከተለውን የሰላም መንገድ እንደሚገፋበት አመልክተዋል።

ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና የፕሪቶሪያው የሰላም አማራጭ ተደራዳሪዎች በአልጀዚራ «ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ጦርነት መመለስ የለባትም» በሚል ርዕስ ካሰሙት “ኢትዮጵያን ዳግም ጎትታችሁ ወደ ጦርነት አታስገቡኝ” አስቸኳይ ጥሪ አንጻር፣ የኦባሳንጆ የመቐለ ጉዞ ሰፊ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኗል።

“መንግስት የመጀመሪያው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት አንስቶ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና የሚቀርቧቸውን አካላት በመላክ እንዲያማልዱት ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር በምስልም ሆነ በጽሁፍ ማስረጃ አለ። አሁንም ቢሆን መንግስት ትንኮሳን በመታገስና በማርገብ ጦርነት እንዳይነሳ ይሰራል። ይህ ቀደሞም ባህሪው ነው” ሲሉ አስተያየት የሰጡ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ፖለቲከኛ፣ በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ህወሃት በተደጋጋሚ “ተገልያለሁ፣ አደራድሩኝ” በማለት በራሱ ስምና ባቋቋማቸው የተለያዩ ማህበራት ሲወተውት መክረሙ ከግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበት ማመልከታቸው፣ ከላይ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑት አካላት ከተገኘው መረጃ ጋር የሚገጥም ሆኗል።

በሌላ ወገን “መንግስት አለቀለት” በማለት የፕሪቶሪያውን ስምምነት የመራው የአፍሪካ ህብረት ወኪሎች ስብስብ ወደ ትግራይ ያመራው መንግስት “ፍጠኑና አደራድሩኝ ብሎ ነው። መሸወድ የለም፤ ብልጽግና አብቅቶለታል” የሚል የድል ዜና እያሰሙ ያሉ፣ በአደረጃጀታቸውና ባላቸው የማህበራዊ ሚዲያ ይህንኑ ቅስቀሳ እያባዙት ይገኛሉ።

“ማንም ይጠይቅ ማንም፣ ሽምግልና ሊኮነን አይገባም” የሚሉ የሰከኑ ዜጎች፣ “መንግስት እንደመንግስት በመታገስ፣ በሆደሰፊነትና ቻይ ሆኖ የህወሃትን አጀንዳ ቢያረግብና ህወሃትን ከፊት አድርገው ኢትዮጵያን እሳት እንዲበላት ለቋመጡት መርዶ ቢሆንባቸው እንዴት ይነቀፋል?” በሚል ግርምታቸውን በመግለጽ፣ “የእነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያዊነት ሊገባን አይችልም” ባይ ናቸው።

የትግራይ የሰላም ኃይሎች የህዝብ ግንኙነት ለአዲስ ሪፖርተር እንዳለው ህወሃት እየተነፈሰ ነው። አክሎም “ህወሃት ከየአቅጣጫው ታጣቂ የተባሉትን እየሰበሰበ አቅም እንዳለው በማስመሰል ያስጠነቅቃል። የአፍሪካ ቀንድ እንደሚናጥም ይገልጻል። እኛም እንደምናውቀው፣ የፌደራል መንግስትም እንደሚረዳው ፊኛው [ህወሃት] አብጧል። የፊኛው አቅም ይታወቃል። ያበጠ ፊኛ ከመተንፈስ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም። እንደሚገባኝ ከሆነ መንግስት ፊኛውን ማስተንፈስ አቅቶት ሳይሆን፣ ለዓለምና ለኢትዮጵያ ሕዝብ መክሬያለሁ፣ አስመክሬያለሁ፣ ለምኛለሁ፣ አስጠንቅቄያለሁ፤ በኋላ ለሚመጣው ነገር እኔ የለሁበትም የሚለውን መልዕክት ለማስተላለፍና ብዙ ርቀት መሄዱን ለማሳየት ሲል ያደረገው ይመስለኛል” ብሏል።

ባለስልጣናቱ በጽሑፋቸው በህወሃት ውስጥ ያሉ የተወሰኑ አመራሮች “ጊዜያዊ የተኩስ አቁም አግኝተው ኃይላቸውን መልሰው በማደራጀት ጦርነቱን ለመቀጠል ይፈልጋሉ” በማለት የህወሃትን አካሄድ ለይተው ተችተዋል። የኦባሳንጆ ቀጥታ መቐለ በመሄድ “ነባሩን መንግስት መልሻለሁ” ከሚለው ከዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ቡድን ጋር መወያየታቸው፣ አቶ ጌታቸውና አምባሳደር ሬድዋን የጠቀሱት “የጦርነት ፍላጎት ያለው የውስጥ ኃይል” የትኛው እንደሆነ በትክክል ያሳያል።

በመጣጥፉ ላይ ሁለቱ ባለስልጣናት በትግራይ ያሉ አመራሮች “ወጣቶችን የጦርነት ማገዶ (cannon fodder) እያደረጉ ነው” ሲሉ ክስ ሰንዝረዋል። ይህ ክስ በትግራይ ክልል ውስጥ በመካሄድ ላይ ካለው እና ህዝቡን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ከጣለው የግዳጅ አፈሳ እና ወታደራዊ ምልመላ ጋር ቀጥታ ይገናኛል። እንደ ኤርትራ በገሃድ የውትድርና አገልግሎት ባያውጅም፣ ህወሃት በግዳጅ አፈሳ ሰራዊት ለመገንባት ደፋ ቀና እያለ መሆኑን አመላክተዋል።

ኦባሳንጆ የሚመሩትን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ቡድንን የማዘዝም ሆነ አቅጣጫ የመስጠት ስልጣን የሌለው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በየትኛውም መስፈርት ቡድኑን ወደ ትግራይ ሊልክ እንደማይችል የሚገልጹት ፖለቲከኛ፣ በዚህ ደረጃ የአስታራቂውን ጉዞ አጣሞ ማየት ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ አይሆንላቸውም። “እርግጥ መንግስት ለኦባሳንጆና ለአባሎቻቸው ወደ ትግራይ ለማቅናት ፈቃድ እንደሚሰጥ ይታወቃል። ይህ ደግሞ ቀውሱን በንግግር ለመጨረስ ካለው ፍላጎት የሚመነጭ እንጂ ሌላ ዓላማ ስላለ አይደለም። ‘የሰላም ያለህ’ ሲሉ የነበሩ የታወቁ ክፍሎች ምነው ንግግሩ አስደነገጣቸው?” ሲሉም ጠይቀዋል። “ነገሩ ሻዕቢያ በኢትዮጵያ ላይ ዳግም ጠላት የሆነው የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲደረግ ስለሆነ፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተንተርሶ የሚደረግ ማናቸውንም እንቅስቃሴ ‘የፕሪቶሪያውን ስምምነት አፍርሱ’ ላለው ሻዕቢያና ከስሩ ለሚከተሉት ሁሉ ዜናው ባያስደስታቸው ወይም ቢያስደነግጣቸው አይገርምም” የሚል አስተያየት አክለዋል።

“አንድ መታወቅ የሚገባው እውነት አለ፤ መንግስት ዛሬ ላይ ከቀድሞው እጅግ በላቀ ሁኔታ ትንኮሳን የመሸከምና በስልት የማስተንፈስ አቅም አለው። ይህን መረዳት አለመቻል ለተለያዩ የስህተት ግምገማዎች የዳረጋቸው ሲሆን፣ ከስህተታቸው የተቀዳ ትንተና ሲሰጡ ይደመጣሉ። በዚሁ የተሳሳተ ትንተና መነሻነት በፉከራ ለከፋ ጥፋት የተዳረጉትን አይተናል” በማለት ፖለቲከኛው እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በወጉ መመርመር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አቶ ጌታቸው እና አምባሳደር ሬድዋን “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በህወሃት (በደብረፅዮን ክንፍ) ላይ የበኩሉን ከፍተኛ ጫና እንዲያደርግ” በጋራ ጥሪ ማቅረባቸው በግልጽ የመንግስትን አቋም የሚያሳይ እንደሆነ የሚገልጹ ወገኖች፣ ይህ ጽሁፍ በወጣበት ተመሳሳይ ቀን የኦባሳንጆ መቐለ መገኘት፣ ይህ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና የአፍሪካ ህብረት ጫና በተግባር መጀመሩን የሚያሳይ እንደሆነ ያመለክታሉ። እነዚሁ ወገኖች ኦባሳንጆ ዝም ብለው ለመጎብኘት ሳይሆን፣ በአልጀዚራ ላይ በይፋ የወጣውን የፌደራል መንግስቱን እና የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጠንካራ አቋም (ቀይ መስመር) ለደብረፅዮን ቡድን ለማስረዳትና ጫና ለመፍጠር፣ ወይም ይህንን መስመር መተላለፍ ጣጣ እንዳለው በግልጽ ለማስገንዘብ እንደሆነ ያለ ጥርጥር ይናገራሉ።

“ጽምዶ የአኩራፊዎች እና የፖለቲካ ከሳሪዎች ስብስብ ነው!” ሲሉ የትግራይ ሰላም ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ገብረ እግዚአብሔር በየነ (ወዲ አንጥሩ) ወቅታዊውን የትግራይ እና የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ ከኢቲቪ ትግርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠንከር ያሉ መልዕክት ማተላለፋቸውና ከፌደራል መንግስት ጋር አብረው እየሰሩ መሆናቸውን ማስታወቃቸው “የፊኛውን መወጠር ያሳያል” ለሚሉት ወገኖች አሳብ ማጠናከሪያ ሆኗል።

“የፕሪቶሪያ ስምምነት የትግራይ ሕዝብ ጋሻ ነው፣ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከማንም በላይ የትግራይን ሕዝብ ከጥፋት የታደገ ታሪካዊ ክስተት ነው ያሉት ጄኔራሉ፤ ትናንት በክፉ ቀን ቂማቸውን ሊወጡ የነበሩ ኃይሎችን ሴራ ያከሸፈ እና ቀጠናውን ወደ ሰላም የመለሰ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል” ይህ ንግግራቸው መንግስት ህወሃት ወደ ፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲመለስ ያለውን አቋም የሚያጎላ ሆኖ ተገኝቷል።

“ከሕወሓት ጋር በማበር ላይ የሚገኘው “ጽምዶ” የተባለው ስብስብ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ፍላጎታቸው ያልተሳካላቸው የአኩራፊዎች እና በፖለቲካው ዓለም የከሰሩ እና የመጥፊያ ሰዓታቸው የደረሰ ኃይሎች ጥምረት ነው። ይህ ስብስብ የቀጠናውን ሰላም ለማወክ የተደራጀ የባንዳ ስብስብ ነው” ሲሉም አክለው ገልጸዋል። እኚህ ከትግራይ የለውጥ ኃይሎች ጋር ከሚሰሩትና በቅርቡ ምክር ቤት ካቋቋሙት የለውጥ ኃይሎች ወገን የሆኑት መኮንን፣ “ቡድኑ አሁን ካለው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ አሰላለፍና እውነታ ጋር አብሮ የማይራመድ፣ ቆሞ የቀረ ስብስብ ነው” ሲሉ ክፉኛ ተችተዋል።

“ሕወሓት የተባለውን መዥገር ከሕዝቡ የመነጠል ጊዜው አሁን ነው” ያሉት ጄኔራሉ፣ በትግራይ ላይ በድጋሚ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ እና የሕዝቡ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን፣ የትግራይ ሰላም ኃይል ከፌዴራል መንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።

በጥቅሉ፣ የችግሩን አስከፊነት እና የጦርነት አፋፍ ላይ መደረሱን ለአለም ያበሰረ “የማንቂያ ደውል” ሲሆን፣ የኦባሳንጆ ጉዞ ደግሞ ያንን አደጋ ለመቀልበስ የተላከ “የእሳት አደጋ ሰራተኛ” ተደርጎ እንደሚወሰድ የአዲስ ሪፖርተር ግምገማ ያሳያል። በትናንቱ ንግግር ላይ አምባሳደር አዲስዓለም ባሌማ “የዛሬው ግንኙነት ከጫፍ የደረሰውን ሌላኛውን ዙር ጦርነት የሚያቀዘቅዝ እንዲሆን ፍላጎት አለን” ማለታቸው፣ የአቶ ጌታቸው እና የአቶ ሬድዋን ፅሁፍ እንዲሁም የኦባሳንጆ መቐለ መግባት በደብረፅዮን ቡድን ላይ የፈለጉትን የስነ-ልቦና እና የፖለቲካ ጫና መፍጠር መቻላቸውን ያሳየ ይመስላል። አሁን በትግራይ ያለው ህዝብ ከአፈሳ እና ከዳግም እልቂት ሊድን የሚችለው፣ ይህ የኦባሳንጆ የዲፕሎማሲ መስመር በደብረፅዮን ቡድን ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ሲያገኝ ብቻ ነው። እሱም የፕሪቶሪያው ስምምነት እንጂ ሌላ እንዳልሆነ አዲስ ሪፖርተር አረጋግጣለች።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related