በአሜሪካ የነጻ አውጪ ታጣቂ ወኪሎች ገበያ አሥር ሺህ ዶላር ደረሰ ፤ የተገንጣይ ቅርምት

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና – ራሳቸውን የአማራ ሕዝብ ወኪል እና ተከላካይ አድርገው የሚያቀርቡት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ከአምባሳደር ብርሃኑ ጋር የሚመሩት፣ የተለያዩ ተገንጣይ ኃይሎችን ያሰባሰበ፣ ሕወሃትና ኦነግን ያገለለ አዲስ የታጣቂዎች ቡድን እያቋቋሙ መሆኑ ተሰምቷል። ባለፈው ማክሰኞ በዙም (Zoom) በተካሄደ ስብሰባ ላይ የነጻ አውጪ ታጣቂ ወኪሎች እያንዳዳቸው አስር ሺህ ዶላር መከፈሉን ተመልክቷል። መረጃውን በተለይ ለአዲስ ሪፖርተር ያካፈሉ “በአሜሪካ የነጻ አውጪ ታጣቂ ወኪሎች ገበያ በአሥር ሺህ ዶላር ደረሰ” ብለዋል።

የአዲስ ሪፖርተር የዋሽንግቶን ተባባሪ እንደገለጸው፤ ሻለቃ ዳዊት ሕወሃትን ያገለለ አዲስ የታጣቂዎች ስብስብ ለማቋቋም ሲሰሩ የቆዩት፣ ከምርጫው በኋላ ይፋ የሆነውና “ይሰናከላል” ተብሎ ተጠብቆ የነበረው ምርጫ በመካሄዱ ምክንያት ነው።

ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንዳንዶቹ እንደተናገሩት፤ የአማራ ታጣቂዎች ከሕወሃት ጋር የፈጸሙት “ጽምዶ” (ጥምረት) ሕዝቡን ስላስቆጣ፣ ሕወሃት የሌለበት አዲስ የታጣቂዎች ሕብረት ለማቋቋም ምክንያት ሆኗል።

አርበኛ እስክንድር ነጋ በፋኖ እንቅስቃሴ ውስጥ (በተለይም የአማራ ፋኖ በጎጃም መሪ በነበረበት ወቅት) መዋቅራዊ ለውጦችን ለማድረግና ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ለመዘርጋት በፈጠረው ምክር ቤት ውስጥ፣ ለሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የዓለም አቀፍ ፖለቲካና ዲፕሎማሲ ዘርፍ ኃላፊ (የካውንስሉ የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ኮሚቴ ሰብሳቢ) አድርጎ ሹሞአቸው እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በውጭ አገር ከሚሰበሰበውና ለፋኖ ከሚላከው የገንዘብ ድጋፍ (Fundraising) አያያዝ፣ ግልጽነት እና ክፍፍል ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ውዝግብና የጋራ መተማመን ማጣት ውስጥ ገብተው፣ ወዲያውኑ በስም ማጥፋትና በሌብነት ስማቸው መነሳት ጀምሮ ነበር።

በተለይም ከተሰበሰበው የገንዘብ መጠን ከፍተኛነት ጋር በተያያዘ በውጭ አገር ባሉ የፋኖ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴዎች፣ በጎጃም ፋኖ የፖለቲካ ክንፍ መሪዎች እና በራሳቸው በሻለቃ ዳዊት መካከል በገንዘብ አመዳደብና በወጪ ግልጽነት ዙሪያ የተነሳው ተቃውሞ ከቃላት ጦርነት አልፎ በመግለጫ እስከ መዘላለፍ ደርሶ ነበር።

ሻለቃ ዳዊት በወቅቱ በስማቸውና በያዙት ኃላፊነት ዙሪያ የሚነሱት የገንዘብ ክሶችና አለመግባባቶች በትግሉ ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥሩ፣ እንዲሁም በመሬት ላይ ካለው አመራርና በውጭ ካለው አስተባባሪ ኃይል ጋር የተፈጠረው የአሠራርና የእምነት ክፍተት ሊጠገን ባለመቻሉ፣ ራሳቸውን ከማንኛውም የፖለቲካ ተሳትፎ ማግለላቸውን አስታውቀው ነበር።

ከእስክንድር ነጋ ጋር አብረው ከፈጠሩት የፖለቲካና ዲፕሎማሲ ኮሚቴ አመራርነት በፈቃዳቸው ገለል ማለታቸውን አስታውቀው የነበሩት ሻለቃ ዳዊት፣ ወደ ኤርትራ ተደጋጋሚ ጉዞ ካደረጉ በኋላ አዲስ ሕወሃትን ያገለለ የታጣቂዎች ስብስብ ማደራጀት መጀመራቸው በተመሳሳይ ሥራ ላይ በሚንቀሳቀሱ ሌሎች ወገኖች ዘንድ ስጋትና መደናገጥን ፈጥሯል።

በውጭና በውስጥ ያለው የፋኖ ደጋፊ ኃይል እና በየፊናቸው ያሉት የታጣቂ አመራሮች “የተሰበሰበው ገንዘብ አልደረሰንም” በሚል ያነሱት የፋይናንስ ቁጥጥር ድክመትና የክፍፍል ችግር፣ እርስ በርስ እስከ መታኮስና በድርጅት ደረጃ መሣሪያ እስከ መንጠቅ አድርሷቸው እንደነበር የሚያስታውሱት የዜናው ምንጮች፤ “በስብሰባው ላይ ሻለቃው የብሩን ምንጭ ይፋ ሳያደርጉ ለጋምቤላና ለቤኒሻንጉል ታጣቂ አስተባባሪዎች ለእያንዳንዳቸው አሥር ሺህ ዶላር ሰጥተዋል” ማለታቸውን አመልክተዋል።

የዘመነ ካሴን አደረጃጀትና ሕወሃትን በማግለል አዲስ የተጀመረው የሻለቃ ዳዊት ግንባር ከኤርትራ በኩል ድጋፍ ያለው መሆኑ፣ “ጽምዶ” በማለት የተደራጁትንና አደረጃጀቱን እያስተዋወቁ “ይህ መንግሥት አበቃለት” በሚሉት የእነ አቶ ነዓምን ክንፍ በኩል ድንጋጤና ስጋት አስነስቷል።

ሻዕቢያ እነ አቶ ነዓምን በርካታ ብር ወስደው ምርጫውን ማስተጓጎል ባለመቻላቸው ገምግሟቸው ነበር። አቶ ነዓምን የሰብሳቢነትና የአደራጅነት ሚና ለመጫወት የፖለቲካ ብቃትም ሆነ የአስተዳደር ጥበብ የሚጎድላቸው፣ በምግባርም በሌሎች የማይከበሩ መሆኑ ተጠቅሶ ከመገምገማቸው ጎን ለጎን፣ የሻለቃ ዳዊት ዳግም ብቅ ማለት ዜናውን ላካፈሉት ወገኖች ግልጽ ያልሆነ ጉዳይ ሆኖባቸዋል።

ሻለቃ ዳዊት ከሁለት ቀን በፊት በዙም ባካሄዱት ስብሰባ፦ “አሁን የቀረን የሶማሌና የአፋር ወገን ነው። ከአፋርና ከሶማሌ ክልል አስተባባሪዎችን ስናገኝ ተመሳሳይ የአሥር አሥር ሺህ ዶላር የሥራ ማስኬጃ እንሰጣለን። በዚህ በኩል ግንኙነት ፈጥረን እየሠራን ነው” ብለዋል።

ጉዳዩን የሚከታተሉ ሌሎች ወገኖች እንዳሉት ከሆነ፣ ሻለቃ ዳዊት እያስኮበለሉ ያሉት እነ አቶ ነዓምን ጋር የተሰባሰቡትንና ኢሕአዴግ “አነስተኛ ክልል” ወይም “አጋር ድርጅት” እያለ የሚጠራቸውን ክፍሎች ነው። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ/OLA) ወኪሎች ለዚህ ፈቃደኛ ይሁኑ አይሁኑ እንደማያውቁና ሻለቃ ዳዊትም ይህንን ግልጽ እንዳላደረጉ እነዚህኑ ወገኖች ጨምረው አስታውቀዋል።

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መሪዎችን በቅርብ የሚያውቁ ወገኖች ለዋሽንግቶኑ ተባባሪ እንደገለጹት ከሆነ፣ ሻለቃው እየሠሩ ያሉት ሕወሃትንና ኦነሠን ያገለለ ስብስብ ለመፍጠር ነው። ሻለቃ ዳዊት በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በተደጋጋሚ በሞባይል ስልካቸው ቢደወልላቸውም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም።

ሻለቃ ዳዊት ቀደም ሲል በደርግ ዘመን ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ከረሃብተኞች ጉሮሮ በመንጠቅ አገር የከዱ መኮንን እንደሆኑ የተለያዩ የውጭ አገር መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው አይዘነጋም።

ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ምስራቅ ጀርመን ለጉብኝት በሄዱበት ማግስት፣ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እና በአሥመራ በሚገኘው አብዮታዊ ጦር ዋና መሥሪያ ቤት በተመሳሳይ ሰዓት እንዲከሽፍ ተደርጎ በተጀመረው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እጃቸው እንዳለበትና ሱዳን ሆነው ይመሩት እንደነበር ራሳቸው ማመናቸው ይታወሳል።

በዚሁ ሻለቃው ከፊት በነበሩበት ሴራ ምክንያት፦ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሌተና ጄኔራል መርዕድ ንጉሤ፣ የባሕር ኃይል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አምኃ ደስታ፣ የቀድሞው የአየር ኃይል አዛዥና የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሜጀር ጄኔራል ፈንታ በላየነህ፣ በአሥመራ የነበረው የዳግማዊ አብዮታዊ ጦር አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ እና የአሥመራው ጦር የፖለቲካ መመሪያ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ሰለሞን ከበደ ከተገደሉት ወታደራዊ መኮንኖች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ከከሸፈ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለው በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው በግንቦት 1982 ዓ.ም የተረሸኑ 12 ከፍተኛ ጄኔራሎች ይገኙበታል። ከእነዚህም መካከል፦ ሌተና ጄኔራል ኃይሉ ገብረሚካኤል፣ ሜጀር ጄኔራል አበራ አበበ፣ የአየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ታደሰ ተሰማ እና ሌሎችም ስመ-ጥር መኮንኖች ነበሩበት።

ይህ እንዲከሽፍ ታስቦ የተቀነባበረው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መክሸፍ እና የጄኔራሎቹ ማለቅ የኢትዮጵያን የጦር ኃይል የጀርባ አጥንት ሰብሮታል። ጦሩን በብቃት መምራት የሚችሉ አንጋፋ ወታደራዊ መሪዎች በአንድ ጊዜ እንዲያልቁ መደረጉ፣ በሰሜን (በኤርትራና በትግራይ) የነበረው የአገር መከላከያ ጦር ለአማፂያኑ (ለሕወሃትና ለሻዕቢያ) በቀላሉ እንዲንበረከክና ከሁለት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ እንዲገቡ አስችሏቸዋል።

በዚህም ምክንያት ሻለቃ ዳዊት የሻዕቢያ ታማኝና ባለውለታ ተደርገው በመቆጠር፣ ተሸልመውና ተመስግነው አሁን ድረስ ግንኙነታቸውን ጠብቀው እንደሚገኙ በርካቶች በጽሑፍና በቃለ ምልልስ የገለጹት፣ ራሳቸውም በከፊል ያመኑት ጉዳይ እንደሆነ ማስታወስ አግባብ ይሆናል። እኚህ ሰው ናቸው ዛሬ አዲስ ጥምረት ለመፍጠር ብር እየከፈሉ፣ “ኢትዮጵያን ማዳን” በሚል ስም በ85 ዓመታቸው ሠራዊት ለመገንባት ደፋ ቀና እያሉ ያሉት። እሳቸው ከሌሉበት ወገን የሆኑት ፋኖዎች ግን እስካሁን ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጡት አስተያየት የለም፤ አርበኛ እስክንድር ነጋም የተነፈሰው ነገር የለም።

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related