አዲስ ሪፖርተር | የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአረብና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ፣ “አሜሪካ ከኤርትራ ጋር በመተባበር በአንድ የአፍሪካ ቀንድ አገር ላይ ምስጢራዊ ድርድር ወይም ስምምነት ለመፍጠር እየሰራች ነው” የሚለውን ግምቶች ላይ የተነተራሱ ዜናዎች ለሁለተኛ ጊዜ በግልጽ አስተባብለዋል። “አናሴርም” ሲሉ ነው በግልጽ አቋማቸውን የገለጹት።
ማሳድ ቡሎስ በኤክስ (X) ማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ሁለተኛው መልዕክታቸው፣ “አሜሪካ ከአንድ የቀጣናው አገር በተቃራኒ ከኤርትራ ጋር ድርድር እያደረገች ነው ወይም ምስጢራዊ ስምምነት ለመድረስ እየሞከረች ነው መባሉ ፍጹም ሐሰት ነው” በማለት የተሰራጩ ዘገባዎችን ውድቅ አድርገዋል።
ከፍተኛ አማካሪው በመግለጫቸው የተጠቀሰው የአፍሪካ ቀንድ አገር የትኛው እንደሆነ በስም ባይገልጹም፣ በቅርብ ወራት በአፍሪካ ቀንድ በተፈጠረው የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ፣ በኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት መነሻ፣ በግብፅ–ኤርትራ–ሶማሊያ ከፈጠሩት ህብረት ጋር ተያያዥነት እንዲኖረው ተደርጎ ለቀረበው ዜና ነው ማስተባበያ የሰጡት። ዜናውን ዲፕሎማቶችን ምንጭ አድረገው ቢቢሲን ጨመሮ ዜናውን ያሰራጭ አሜሪካና ኤርትራ በሚስጢር እያሴሩ መሆኑን ሲጠቅሱ የኢትዮጵያን ስም አላነሱም። ይሁን እንጂ ዘገባዎቹ ኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ።
በሁለት ሳምንታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መግለጫ ማስተባበያ ያሰራጩት ቡሎስ፣ ከዚህ በፊት በካይሮ ከግብፅ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በተናጠል ያደረጉት ውይይት ከኢትዮጵያ በተቃራኒ የተደረገ መሆኑን የሚጠቁሙ ዘገባዎች ከተሰራጩ በኋላም ተመሳሳይ ማስተባበያ ሰጥተው ነበር።
በዚያን ጊዜም “ውይይቱ ተገቢ ያልሆነ ገጽታ ተሰጥቶት ቀርቧል” በማለት፣ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ “ፀረ ኢትዮጵያ ትብብር” ለመገንባት እየሰራች ነው የሚሉ ግምቶችን አጣጥለው ነበር። እሳቸው ይህን ባሉ በቀናት ልዩነት ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያ ከአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ያዘጋጀችው የአፍሪካ ሎጂስቲክስ እና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚዬም (ALCS26) አዝጋጅተዋል። መድረኩ የሁለቱን ሀገራት የታደሰ የደኅንነት አጋርነት እና የቀጣናውን ሰላም የሚያጠናክር እንደሆነ ተመልክቷል።
«የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ዓላማ ተቀናቃኝ ቡድኖችን መፍጠር ወይም ልዩነቶችን ማስፋት ሳይሆን፣ ግጭቶችን በማስወገድ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት መፍጠር ነው። ከአንድ የቀጣናው አጋር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከሌላው አገር ጋር መቃረን ማለት አይደለም።» — ማሳድ ቡሎስ፣ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ
ይህ ሲምፖዚየም በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ስትራቴጂያዊ ምዕራፍ መሸጋገሩን የሚያሳይ ሲሆን፣ አሜሪካ አሁንም ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋትን ለማስከበር እንዲሁም አልሸባብን የመሰሉ የጸረ-ሽብር ስጋቶችን ለመከላከል እንደ ዋና እና የማይተካ የሎጂስቲክስ ማዕከል አድርጋ እንደምትመለከታት ያረጋገጠ መሆኑ ተዘግቧል።
የአፍሪካ ሎጂስቲክስ እና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚዬም (ALCS26) ቀደም ሲል ለብቻቸው ይካሄዱ የነበሩትን የሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን መድረኮች ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ላይ ያቀናጀ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የአፍሪካ ሀገራት በረጅም ጊዜ ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ (Self-sustaining) የሚያስችል አቅም መገንባት እና በቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የታገዘ የደኅንነት ትብብር መፍጠር ነው። የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ከኢትዮጵያ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት በቀጣናው የሚታዩትን እንደ አልሸባብ ያሉ የጸረ-ሽብር ስጋቶች በጋራ ለመከላከል ቁርጠኝነቱን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ይህም የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ወደ ላቀ ስትራቴጂያዊ ምዕራፍ ያሸጋግረዋል። የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር መሪዎች ይፋ ይህን ይፋ እያደረጉ ባለበት ወቅት “አሜሪካ ከኤርትራ ጋር በሚስጢር ኢትዮጵያ ላይ እያሴረች ነው” የሚለው ዜና ጎን ለጎን መሰማቱ በርካቶችን አስገርሞ ነበር።
ቡሎስ በካይሮ ምን ተወያዩ?
ቡሎስ በካይሮ ከኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ፣ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲሳላም አብዲ አሊ ጋር በተናጠል ተገናኝተዋል።
በእነዚህ ውይይቶች ዋና አጀንዳዎች የአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ የክልሉ ደኅንነት፣ የሁለትዮሽ ትብብር፣ የንግድ ግንኙነት፣ የኢኮኖሚ ልማት እና የክልሉ መረጋጋት እንደነበሩ ቡሎስ ገልጸዋል።
ከኤርትራ ጋር በተደረገው ውይይት በተለይ የክልሉ የፀጥታ ሁኔታ፣ የንግድ ግንኙነት እና የደኅንነት ትብብር ላይ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል። ከሶማሊያ ጋር ደግሞ የክልሉ ደኅንነት፣ የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ የሶማሊያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሂደት እና በቀጣናው መረጋጋት ላይ የጋራ መስራት መወያየታቸውን አስታውቀዋል።
ቡሎስ እነዚህን ውይይቶች “ፍሬያማ” ሲሉ የገለጹ ሲሆን፣ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ዓላማ በአፍሪካ ቀንድ ተቀናቃኝ ጎራዎችን መፍጠር ሳይሆን በሁሉም አገራት ጋር በመስራት ግጭቶችን መቀነስና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የግብፅ–ኤርትራ–ሶማሊያ ትብብር እና የቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ
የማሳድ ቡሎስ ተደጋጋሚ ማስተባበያ የመጣው በአፍሪካ ቀንድ የጂኦፖለቲካ ውድድር በፍጥነት እየተቀየረ ባለበት ወቅት ነው። በተለይም ግብፅ፣ ኤርትራና ሶማሊያ በቅርብ ዓመታት የገነቡት የፖለቲካና የደኅንነት ትብብር፣ ከኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት እና ከቀይ ባሕር ደኅንነት ጋር ተያይዞ በቀጣናው አዲስ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ፈጥሯል።
ሶስቱ አገራት ከሁለት ዓመታት በፊት በአስመራ የጋራ የፖለቲካና የደኅንነት ትብብር መስርተዋል። ይህ ትብብር በወቅቱ የተለያዩ የክልሉ ጉዳዮችን ቢያካትትም፣ ከኢትዮጵያ ጋር የነበሩ የፖለቲካና የደኅንነት ልዩነቶች የሚያገናኙዋቸው እንደነበሩ በስፋት ተነግሯል።
ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ (GERD) ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ አለመግባባት ውስጥ ትገኛለች። ኤርትራ ደግሞ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር የባሕር በር ማግኘትን በይፋ ካነሳች በኋላ በጉዳዩ ላይ ስጋቷን በተደጋጋሚ አንጸባርቃለች። ሶማሊያም ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ በመቃወም ለረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ ውጥረት ውስጥ ቆይታለች።
በዚህ ዳራ ውስጥ የግብፅ፣ የኤርትራና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በካይሮ ያደረጉት ስብሰባ በቀጣናው የትኩረት ማዕከል ሆኖ ነበር። ከስብሰባው በኋላ የቀይ ባሕር ደኅንነትና አስተዳደር የሚመለከተው “የቀይ ባሕር ጠረፍ አገራትን ብቻ” መሆኑን በጋራ ማስታወቃቸው በኢትዮጵያ የባሕር በር ውይይት አንፃር በስፋት ተተርጉሟል።
“አሜሪካ ጎራ እየመረጠች ነው?” የሚለው ጥያቄ
እነዚህ ክስተቶች በተከታታይ ሲከሰቱ፣ አሜሪካ ከኤርትራና ከሌሎች የክልሉ አገራት ጋር ያደረገችው ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል ወይ? የሚለው ጥያቄ በዲፕሎማሲ አግባብና እና በሚዲያዎች ተነስቷል።
ነገር ግን የቡሎስ ተደጋጋሚ መግለጫ የአሜሪካ አቋም የተለየ መሆኑን ያመለክታል። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ዋሽንግተን ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ፣ ከግብፅ፣ ከሶማሊያና ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባሕር አገራት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
“ከአንድ የቀጣናው አጋር ጋር የሚደረግ ግንኙነት ከሌላ አገር ጋር መቃረን ማለት አይደለም” የሚለው የቡሎስ አቋምም የአሜሪካ ዲፕሎማሲ በክልሉ ተቀናቃኝ ጎራዎችን ከመገንባት ይልቅ ሁሉንም ወገኖች በማነጋገር የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ እንደምትሞክር የሚያሳይ ነው።
ይህም ከቅርብ ቀናት በፊት በአዲስ አበባ በኢትዮጵያና በአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ (AFRICOM) ትብብር የተካሄደው የአፍሪካ ሎጂስቲክስና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም (ALCS26) ጋር ሲጣመር የዋሽንግተን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው የደኅንነትና የስትራቴጂ ግንኙነት እንደቀጠለ የሚያሳይ ሌላ አመላካች ሆኖ ታይቷል።
በዚህ መሠረት፣ አሜሪካ በአንድ በኩል ከኤርትራ ጋር የዲፕሎማሲ መስመሮቿን ክፍት እያደረገች ስትሆን፣ በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የደኅንነትና የወታደራዊ ትብብር እንደማታቋርጥ የሚጠቁሙ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸው የክልሉን የዲፕሎማሲ ስዕል የበለጠ ውስብስብ አድርጎታል።
ትንታኔ፦ የአሜሪካ ማስተባበያ ለምን አስፈለገ?
የማሳድ ቡሎስ ተደጋጋሚ ማስተባበያ የመጣው በአፍሪካ ቀንድ ያለው የፖለቲካና የደኅንነት ሁኔታ እጅግ ውስብስብ በሆነበት ወቅት ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን የውጭ ፖሊሲዋ ቀዳሚ አጀንዳ ካደረገች በኋላ፣ በቀይ ባሕር እና በአፍሪካ ቀንድ የኃይል ሚዛን ላይ አዲስ ውይይቶች ተከፍተዋል። በዚሁ ጊዜ ግብፅ፣ ኤርትራና ሶማሊያ ያጠናከሩት ትብብር የክልሉን የጂኦፖለቲካ ሁኔታ የበለጠ አወሳስቦታል።
ይህ እውነታ አሜሪካ ከእነዚህ አገራት ጋር የምታደርጋቸውን የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች በተለያየ መንገድ እንዲተረጎሙ አድርጓል። በተለይም የቡሎስ ከካይሮ ጉብኝት በኋላ በአንዳንድ ሚዲያዎችና በማኅበራዊ ሚዲያ የቀረቡ ዘገባዎች፣ ዋሽንግተን ከግብፅ፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ ጋር በመቀራረብ በኢትዮጵያ ላይ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ እየፈጠረች ነው የሚል ግምት እንዲስፋፋ አድርገው ነበር።
ነገር ግን የቡሎስ መግለጫ የአሜሪካ አቋም ከዚህ የተለየ መሆኑን በግልጽ አስቀምጧል። እሳቸው እንዳሉት፣ የአሜሪካ ዲፕሎማሲ ተቀናቃኝ ጎራዎችን ለመፍጠር ወይም የቀጣናውን አገራት ለመከፋፈል ሳይሆን፣ ግጭቶችን በመቀነስ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ነው።
በተመሳሳይ ጊዜ ዋሽንግተን ከኢትዮጵያ ጋር በደኅንነት፣ በፀረ-ሽብር ትብብር፣ በንግድ እና በቀጣናዊ መረጋጋት ጉዳዮች ያላትን ግንኙነት እንደምትቀጥል ሲገልጽ፣ ከኤርትራ፣ ከግብፅና ከሶማሊያ ጋርም ውይይት ማድረጓን እንደምትቀጥል አስታውቃለች። ይህም የአሜሪካ ፖሊሲ በአንድ ጎራ ከመሰለፍ ይልቅ ከሁሉም ተዋናዮች ጋር የመስራት አቀራረብ መሆኑን ያመለክታል።
መደምደሚያ
በአጠቃላይ፣ የማሳድ ቡሎስ ተደጋጋሚ መግለጫ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር በመተባበር በማንኛውም የአፍሪካ ቀንድ አገር ላይ ምሥጢራዊ ድርድር ወይም “ፀረ-አንድ አገር ስምምነት እየፈጸመች ነው” የሚለውን ወሬ በግልጽ ውድቅ ያደረገ ነው።
በሌላ በኩል ግን፣ የቀይ ባሕር ደኅንነት፣ የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎት፣ የግብፅ፣ኤርትራና ሶማሊያ ትብብር እና የአሜሪካ ቀጣናዊ ዲፕሎማሲ አሁንም በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ውስጥ በቅርብ የሚከታተሉ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል። በመሆኑም በቀጣዮቹ ወራት የሚካሄዱ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች የአፍሪካ ቀንድ የደኅንነት አቅጣጫን በመወሰን ረገድ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል።
ፌስቡክ፡ https://web.facebook.com/addisreporternews/
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter11
X፡ https://x.com/addisreporter
ስልክ ቁጥር፡ +251116393393






