ህወሃት – የግዳጅ አፈሳ ፣ የታጣቂዎች ጥምረት፣ ከሻዕቢያ ፣ ከሱዳን አሸባሪና ግብጽ ጋር እየሰራ”ተጠቃሁ”

Date:

አዲስ ሪፖርተር ዜና – በኃይል የጊዜያዊ አስረዳደሩን በማፍረስ ስልጣን የያዘው ሕገወጡ የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ትህነግ) ሰሞኑን “በትግራይ ዲፕሎማሲ እና አድቮኬሲ ካውንስል” ስም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለአውሮፓ ኅብረት እና ለአፍሪካ ኅብረት የጻፈው ደብዳቤ የራሱን ሕገ-ወጥ ድርጊቶች ለመሸፈን እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማታለል የሞከረበት የተለመደ የሃሰት ፕሮፓጋንዳ መሆኑ ተመለከተ። የደብዳቤውን ይዘት እና ወቅታዊ እውነታዎችን መሠረት በማድረግ አስተያየት የሰጡ የቀድሞ የህወሃት ደጋፊዎች እንዳሉት ድርጅቱ የሚሰራውን የማያውቅበት ደረጃ ደርሷል።

ደብዳቤው “የኢትዮጵያ መንግሥት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ጥሷል” በድሮን ወታደራዊ ኮምቦይ ላይ የተወሰደውን ጥቃት እንተርሶ ከሷል። የትግራይ ተቃዋሚ ድርጅቶችና የቀድሞ ደጋፊዎቹ በተለያዩ የመረጃ አውታሮች እንዳሉት ህወሃት አስቀድሞ የፕሪቶሪያው ስምምነት መፍረሱን ደጋጋሞ አውጇል። ትህነግ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ በትግራይ ክልል የነበረውን ጊዜያዊ አስተዳደር በኃይል እና በሕገ-ወጥ መንገድ ማስወገዱን ያመለከቱት እነዚሁ ክፍሎች “ራሱ አስቀድሞ ፈርሷል ሲል ያወጀውን አዋጅ መልሶ መከራከሪያ ማድረጉ ይገርማል” ብለዋል። በጥቃቱ በምስኪን ወታደሮች ላይ የደረሰው ጥቃት እንደሚያሳዝን የጠቀሱ የህወሃት የቀድሞ ደጋፊዎች “ምንም ይሁን ምን በትግራይ ጦርነት እንዳይነሳ መስራት ያስፈልጋል” በሚል መሆን ስለሚገባው ጉዳይ አስታውቀዋል። ። “ህወሃት በራሱ ፍላጎት የሰላም ስምምነቱን ያፈረሰ፣ ሁሉንም የክልሉን እንቅስቃሴዎች የዘጋ እና የራሱን ሕገ-ወጥ የክልል መንግሥት ያዋቀረ ኃይል በመሆኑ፣ ስለ ሰላም ስምምነት መከበር የመናገር የሞራልም ሆነ የህግ መብት የለውም” ሲሉም ተከራክረዋል።

ደብዳቤው “በመደበኛ ሥራቸው ላይ በነበሩ የትግራይ ሠራዊት ላይ (በኢትዮጵያ መንግሥት) ድብደባ ተፈጸመ” በማለት የትግራይን ታጣቂዎች እንደ ሕጋዊ መከላከያ ሠራዊት ሊያቀርብ መሞከሩን የተቃወሙ የህግ ባለሙያዎች፣ ህወሃት ሰራዊት የሚያዘጋጀው፣ መሳሪያ የሚሸምተውና የሚያጋግዘው ጦርነት ለመከፈት እንደሆነ በገሃድ እያስታወቀ ለምን ቀድሞ ጥቃት ደረሰበኝ የማለት መብት አለው ብለው እንደማያስቡ አመልክተዋል። ጥቃቱ ሰላማዊ ሰዎችን እንዳልነካ ህወሃት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ጠቁመው በወታደራዊ ኦፕሬሽን ላይ ባሉ አካላት ወይም ቡድኖች ላይ ጥቃት ደረሰ በማለት መቃወም አግባብ ሊሆን አይችልም።

  • ህወሃት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰረዘ እና ምንም ዓይነት ሕጋዊ እውቅና የሌለው ስብስብ መሆኑ፣ በአንድ ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ ከተገቢው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ውጪ ሌላ ትይዩ ሠራዊት ማቋቋም ሙሉ በሙሉ ሕገ-ወጥ ነውና፣ ቁጥሩ 12 የሚሆን የጦር መሳሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወዴት ነው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ለሚረዱ? ህወሃት ከውጭ ኃይሎች፤ ከኤርትራና ሱዳን አካላት ጋር “ፅምዶ” የተባለ ሕገ-ወጥ ጥምረት በመፍጠሩ እየታወቀ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ እንደሆነ እያስታወቀ ባለበት፣ ይህንኑ ዝግጅቱን ከዘጠኝ በላይ ታጣቂ ኃይሎች ሰብስቦ አዲስ የጦር ህብረት ማቋቋሙን እያስታወቀ ባሎእበት ወቅት ላይ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በዝግጅት ላይ ባሉ ታጣቂዎች ላይ የወሰደው እርምጃ ሕጋዊ እና ሀገርን የማዳን ተግባር እንጂ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተደረገ ጥቃት ተደርጎ እንደማይወሰድ አመልክተዋል።

“ህወሃት ሰላማዊ መስሎ ለመታየት ቢሞክርም፣ ከበስተጀርባ ግን ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት እያደረገ እንደነበር ይፋ የሆኑ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። የትህነግ ከፍተኛ አመራሮች በደላሎች አማካኝነት ከምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ የድሮን ማክሸፊያ (Drone Jamming) ቴክኖሎጂ ገዝተው በኩሃ አካባቢ በሚገኘው የሰሜን አየር ዕዝ ላይ ሲገጣጥሙ ቆይተዋል” ያሉት የትግራይ አክቲቪስቶች፣ በህወሃት መግለጫ ተሳልቀዋል።

ይህ ተግባር ቡድኑ አሁንም ለጦርነት እንጂ ለሰላም እየሠራ እንዳልሆነ የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ የገዙት መሣሪያ ጊዜ ያለፈበት (Second-hand) በመሆኑ እና ዘመናዊ ድሮኖች የላቀ የፀረ-ጃሚንግ (Anti-Jamming) መከላከያ ስላላቸው ሳይሠራ ቀርቷል። ይህ የሚያሳየው የትህነግ አመራሮች የሕዝብን ሀብት ለጦርነት ደላሎች ሲሳይ እያደረጉ መሆኑን እና ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሚዋሹበትን የ“ተጠቂነት” ትረካ ለማድመቅ የጦርነት መዋቅር እየገነቡ እንደነበር ነው። የድሮን ማክሸፊያ መገዛቱን የተናገረው ዳዊት ከበደ (አውራምባ ታይምስ) ነው፤ ስለዚህ ከዚሁ ጋር አብሮ መነሳት ያለበት ጉዳይ 400 ሚሊዮን ዶላር ከየት ተገኘ? የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ዳዊት ከሌተናል ጄኔራል ታደሰ ጋር ቅርበት ያለውና መረጃ ከሳቸው ስለሚያገኝ መረጃው ውሎ አድሮ እንደሚያነጋግር መሆኑን ነው።

ደብዳቤው “የፌዴራል መንግሥቱ በጀት እና ደሞዝ በመክልከል የኢኮኖሚ ጦርነት ከፍቷል” ሲል ይከሳል። ይህን ክስ አስመልክቶ “የፌዴራል መንግሥት የበጀት እና የደሞዝ ድጎማ የሚያደርገው በሕግ እውቅና ላላቸው የክልል መዋቅሮች ነው። ትህነግ ሕጋዊውን መዋቅር በኃይል አፍርሶ፣ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘ ድርጅት ሆኖ ሳለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለጦር መሳሪያ መግዣ እያባከነ የሀገሪቱን ሀብት ለራሱ ታጣቂዎች ማጠናከሪያ እንዲሰጠው መጠየቁ ፍጹም ዘራፊነት እና ሕገ-ወጥነት ነው” ብለዋል። አክለውም “በጀት፣ መድሃኒት፣ ነዳጅ፣ ነጻ የባንክ እንቅስቃሴ ወዘተ እየጠየቀ መልሶ አገር ለመውጋት ዝግጅት ላይ መሆኑን ይገልጻል” ብለዋል።

ትህነግ በዚህ መልኩ በሕገወጥነት የሚንቀሳቀስ አሻባሪ ቡድን ቢሆንም እና ምንም ዓይነት ገንዘብ ከፌዴራል ሊላክ የማይገባ ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ እንዳይቸገር በሚል የፌዴራል መንግሥቱ አሁንም ድረስ ለሕዝቡ የበጀት፣ የነዳጅ፣ የመድኃኒት፣ ወዘተ ድጎማ አለማቋረጡን እንደሚያውቁ እነዚሁ ወገኖች አመልክተዋል።

ደብዳቤው በተደጋጋሚ “ዳግም ጄኖሳይድ” (ሁለተኛ ዙር የዘር ማጥፋት) የሚሉ ቃላትን በመጠቀም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ስሜት ለመግዛት ይሞክራል። ይህ የጥፋት ቡድን የትግራይን ሕዝብ እንደ መከላከያ ጋሻ በመጠቀም እና በውሸት ፕሮፓጋንዳ በማታለል የራሱን የሥልጣን ጥም ለማርካት የሚጥር መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊገነዘበው ይገባል። እውነተኛው ስጋት የኢትዮጵያ መንግሥት ሳይሆን፣ ሰላምን የማይፈልገው፣ ስምምነቶችን የሚያፈርሰው እና ሀገሪቱን ወደ ሌላ የእርስ በእርስ ጦርነት ለመክተት አዲስ የጦርነት ግንባር እየከፈተ ያለው ትህነግ ራሱ መሆኑን ሰሞኑን የሚካሄዱት አፈሳዎች በመቃወም መግለጫ ያወጡ ገልጸዋል።

ይህ የህወሃት አካሄድ በሀገር ውስጥ ካሉ ተፎካካሪ ፓርቲ ነን ከሚሉ ጋር በደንብ ተናብቦ የተሠራ ለመሆኑ ጠቋሚዎች አሉ። የትብብር አመራር የሆኑት ጌትነት ወርቁ በአርሲ ስም ለጠቅላይ ሚኒስቱ የጻፉትን ግልፅ ደብዳቤ አስመልክቶ “በሐዘንና ግልፅ ደብዳቤ ስም የተሸፈነ የድህረ ምርጫ ሀገር የማተራመስ ስትራቴጂ” በሚል ርዕስ አዲስ ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል። የአቶ ጌትነት ጽሑፍና የትህነግ ደብዳቤ በይዘትም በአቅጣጫም በጣም የተመሳሰሉ ናቸው። ትህነግ “ዘር ማጥፋት/ጄኖሳይድ” ይላል፤ ጌትነትም የጄኖሳይድ የመጨረሻው ደረጃ ላይ ነን ይላሉ። እየተናበቡ ለመሥራታቸው እንደ ማሳያ መቅረብ የሚችል መሆኑን ያመለከቱ እንደሚሉት፣ የህወሃትን አካሄድ የዲፕሎማሲው ማህበረሰብ በወጉ እንደሚያውቀው አስታውቀዋል።

“የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የፕሪቶሪያው ስምምነት ታዛቢዎች በተለይ ደግሞ የትግራይ ተወላጆች የዚህን ደብዳቤ የሐሰት ትርክት ውድቅ ። ትህነግ የሰላም ስምምነቱን የጣሰ፣ ሕጋዊ ተቋማትን ያፈረሰ፣ ለጦር መሣሪያ ዝግጅት ሚሊዮኖችን የሚያባክን፣ የትግራይ ልጆችን እንደገና ለማስጨፍጨፍ እያፈነ ወደ ጦር ካምፕ የሚወስድ እና አዲስ ጦርነት ለመጫር ከውጭ ኃይሎች ጋር የተሰለፈ የትርምስ ምንጭ ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያወግዘው የሚገባው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሳይሆን፣ ሕገ-ወጥነቱን ይዞ በየመድረኩ የሚጮኸውን የትህነግን የጥፋት ቡድን ነው። የትግራ ተወላጆች ደግሞ ቀዳሚ መሆን ይገባቸዋል” በማለት አስተያየት የሰጡ፣ የትግራይ የሰላም ኃይሎችና አዲስ የተቋቋመው የተቃዋሚዎች ምክር ቤት የትግራይን ሕዝብ ከጦርነት ስጋት እና ከሻዕቢያ መዳፍ እንዲላቀቅ ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm

Share and Enjoy !

Shares

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

Share post:

Subscribe

spot_imgspot_img

Popular

More like this
Related