አዲስ ሪፖርተር ዜና – አዲስ ሪፖርተር በFBI (Federal Bureau of Investigation) የአሜሪካ የምርመራ ቢሮ በኩል ክስ እንዲቀርብበት መጠየቁ ተሰማ። ኮሚቴም ተቋቋመ “የድርጅታችንን ዝግ ስብሰባዎችና መረጃዎች እንዳለ ይፋ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ መመርመር አለበት” ተብሏል።
በቅርቡ “እውነትንና ኢትዮጲያን እናስቀድማለን” በሚል መርህ ወደ ህዝብ መድረስ የጀመረው አዲስ ሪፖርተር፣ የሚታወቅ አድራሻ፣ የሚታውቁ ስልኮችና የኢሜል መገናኛዎች፣ የማህበራዊ ሚዲያ አውዶችን፣ እንዲሁም የአገሪቱን የብሮድካስት ህግ አክብሮ የሚሰራ የድረ ገጽ ጋዜጣ እንደሆነ ስራውን ሲጀመር ማስታወቁ አይዘነጋም።
አዲስ ሪፖርተር በአሜሪካኑ ኤፍቢአይ በኩል ክስ እንዲቀርበበት የተጠየቀው ከትናንት በስቲያ ነው። በኢትዮጵያ “ሕዝባዊ አመጽ ለማስነሳት” በሚል ራሳቸውን ያደራጁ የተለያዩ ስብስቦች ይፋዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ከማሳወቃቸው በፊት ጀምሮ እያንዳንዱን ስብሰባቸውን እየተከታተለ ማቅረቡ ያላስደሰታቸው እነዚህ ወገኖች ናቸው ጥያቄውን ያነሱት። የክስ አሳቡ ቅኔ ወርቁ “ውጭ የምንለውና በሚወጣው የስብሰባችን ሚስጢር የሚቀርበው ዜና የሚጣረስ በመሆኑ ተአማኒነት አጣን” ነው።
ባለፈው ሳምንት ብቻ አራት ጊዜ ስብሰባ የተቀመጠውና የተለያዩ ኮሚቴዎችን ያቋቋመው ይህ ቡድን፣ ቅዳሜ ዕለት ባደረገው ስብሰባ “የጃልመሮ አማካሪና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ቃለ አቀባይ የሕዝባዊ እምቢተኛነት አመቻች ስራ አስፈጻሚ አባል ሆኑ”በሚል አዲስ ሪፖርተር ያተመውን ዜና መነጋገሪያ አድርገው እንደነበር የአሜሪካ የአዲስ ሪፖርተር ተባባሪ አመልክቷል። መረጃም አቅርቧል።
ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አንዱ “ይህ አዲስ ሪፖርተር የሚባል ሚዲያ ማን ነው መረጃ የሚሰጠው፤ ስብሰባችን እግር በእግር እየተከተለ ነው መረጃ የሚያወጣብን” በማለት ቁጣ የተሞላው ጥያቄና አስተያየት ይሰጣሉ። ይህን ጊዜ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተመደቡበት ኮሚቴው ሁሉ ሰብሳቢ የሚደረጉት አቶ ያሬድ “አቶ ጂሬኛ አይተኸዋል” ሲሉ ፎቷቸው መለጠፉን ገልጸው ያመላክቷቸዋል።
ሌላኛው ተሰብሳቢ በበኩላቸው “እንዲህ አይነት መረጃዎች ሊወጡ የሚችሉበት ፋክተሮች 1ኛ. የተጠለፈ ስልክ፣2ኛ. የተጠለፈ ዙም 3ኛ. ከመካከላችን በማወቅ ወይንም ባለማወቅ ለሌሎች መረጃዎችን በማቀበል፣ እነዚህ ፖሲቢሊቲስ ይመስሉኛል” በማለት መረጃቸው ሊያፈተልክ የሚችልበትን አግባብ አስታወቁ።
ሌላው ተነስተው “አዲስ ሪፓርተር” ተቀማጭነቱ አውሮፓ የሆነ የብልጽግና የመረጃ ጦርነት ልሳን ነው። ግባቸውም 1ኛ. ስለ እንቅስቃሴያችን ውዥንብር መፍጠር 2ኛ፣ በመካከላችን ጥርጣሬና መከፋፈል መፍጠር መሆኑ ግልጽ ነው። በቀጣይ የመገናኛ ደህንነታችን የተጠበቀ እንዲሆን ስራዎች መሰራት ያለባቸው ይመስለኛል” በማለት ሃሳባቸውን ሰጡ፤ የዋሽንግቶን ተባባሪያችን እንዳለው ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ግለሰብ ላይ በማነጣጠር ዛቻ፣ ማስፈራሪያና አገር ቤት ባላቸው ህዋስ እርምጃ ሊያስወስዱ እንደሚችሉም መክረዋል።
ሌላው የቡድኑ አባል “እኔ ጉዳዩን ለFBI ማሳወቁ ክፋት የለውም ባይ ነኝ። ትኩረት ቢሰጡትማ፣ ባይሰጡትም ቢያንስ ነገሩ ፋይል መደረጉ ጥሩ ነው፤ በእነሱ በኩል መክሰሰ አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ” በማለት ሃሳብ አቀረቡ።
የቡድኑ ዋና ራስ የሚባሉት አቶ ነዓምን “ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከእኛ ጉዳይ ይልቅ እጅግ በርካታ የሆኑ ትልልቅ ጉዳዮች ስላሏቸው ለዚህ ጉዳይ ትኩረትም ቅድሚያ አይሰጡትም። አሁን ካላቸው አቅም በላይ በስራ ተጨናንቀዋል፤ እንዲሁም ከ2025 ጀምሮ በDOG (የመንግስት ብቃት መመሪያ/Department of Government Efficiency) እና ከፖለቲካ ጋር በተያያዙ የብዙ ወኪሎች (agents) ስንብትና ቅነሳ ምክንያት አቅማቸው በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል። እዚያ የሚሰሩ ሰዎችን አውቃለሁ፤ አሁን እንደ ድሮ አይደሉም” የሚል ሃሳብ በመሰነዘር ሌላ አማራጭ መከተል እንደሚሻል አመላከቱ። መጨረሻ ላይ ኮሚቴ አቋቋሙ።
አሁን ኢትዮጵያን እየመራ ያለውን መንግስት “አገዛዝ” በማለት በዴሞክራሲና በሰው ልጆች መብት የሚከሱ የተለያዩ ድርጅቶች፣ ማህበራት፣ የምሁራን ጥምረትና ፖለቲከኞች ከሚወነጅሉት መንግስት የሚሻሉበትን ማንነታቸውን ማሳየት ሲገባቸው፣ ከዛ በባሰ “ስብሰባችን ይፋ ሆነ” በሚል ስጋት ፍረጃና ማስፈራራት መለያቸው መሆኑ ብዙ እንደሚናገር ከተሰብሳቢዎቹ መካከል የሆኑ ተናግረዋል። አዲስ ሪፖርተር ዝርዝሩን ትመለስበታለች።
የዋሽንግቶን ተባባሪያችን በዘገባዎቹ ሁሉ አቶ ልደቱንና አቶ ነዓምንን በተደጋጋሚ ለማነጋገር ሞክሮ እንዳልተሳካለት አስታውቋል። ይህንኑ በዘገባዎቹ አመልክቷል። የአውሮፓ ተባባሪያችንም አቶ ጅሬኛን እና አቶ ያሬድን አነጋግሮ ለተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ሙሉ ባለመሆኑ መረጃውን ከማተም መታቀቡን አመልክቷል። ሁለቱም ተባባሪዎች ያተሟቸው መረጃዎች በዝግ ስብሰባ የተደረጉ ከመሆናቸው በቀር አንድም ሃሰት የለባቸውም። አዲስ ሪፖርተር የተፈረጀውና ሌሎች ሴራዎችም የተጎነጎኑለት ሚስጢር በማውጣቱ እንጂ በሌላ አይደለም።
የአዲስ ሪፖርተር የህግ አማካሪ ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ “ሰዎቹ የት ነው የሚኖሩት?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል። ዘጠና ከመቶ አሜሪካ መሆናቸውን ሲያውቁ “ሞክሩ የሚል ኤዲቶሪያል መጻፍ ይሻላል” የሚል የግርምት አስተያየት ሰጥተዋል። አክለውም አሜሪካ የፕሬስ ሴክረታሪ መሆን ከላይና ከታች እሳት እንደሚነድበት ዳቦ ዓይነት መሆኑን አሜሪካን አገር ሆኖ አለመረዳት ሌላ አስገራሚ ጉዳይ እንደሆነም ጠቁመዋል። በቀን አንዴና ሁለቴም ሊሆን ይቻላል አጠቃላይ የአገርና የውጩን መረጃ ጨመቅ አድርጎ ማቅረብ፣ ከዛም በጋዜጠኞች መለብለብ የኃላፊነቱ ምህላ ነው።
“ስውሩ ዓላማ ያልገባቸውን ከፊት አድርገው ከግብጽ፣ ከኤርትራና ከሌሎች ድርጅቶች ጋር አብረው የሚሰሩ አካላት በዚህ ደረጃ ሞራል አግኝተው ለማስፈራራት መነሳታቸው ያስገርማል” በማለት ሙያዊ ሳይሆን ግርምት የተሞላውን አሳባቸውን አካፍለዋል።
የዋሽንግቶን ዘጋቢያችን፣ የመረጃ ምንጮች እንዳሉት “እናንተ ከግብጽ እና ከኤርተራ ገንዘብ ታገኛላችሁ፤ እኛ የምናገኘው ምንም ሃብት የለም። መጠቀሚያ ልታደርጉን አትሞክሩ” በሚል ተነስቶ የነበረው ጭቅጭቅ መታተሙ ዋናዎቹን ክፉኛ አበሳጭቶ ነበር። በቅርቡ ደግሞ ራሳቸው አቶ ነዓምን አውሮፓና እዚህ ዲሲ ህዝብ ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አይወጣልንም። ከመኖሪያ ፈቃድ ጋር በተያያዘና በሌሎች ግፊ ምክንያቶች የሚሆን አይመስለኝም” ማለታቸው በአዲስ ሪፖርተር ላይ ይፋ መሆኑ በኤርትራዊያን አለቆቻቸው ዘንዳ እንዳስተቻቸው መረጃ ሰብስቧል። በመሆኑም “ስብሰባው ከተጀመረ ጀምሮ ያለማቋረጥ በአዲስ ሪፖርተር የወጡት መረጃዎች ብዙ ጉዳዮችን ስላበላሹ “ሚዲያውን መፈርጅ፣ ሰዎቹን ማሸማቀቅና ማስፈርራራቱ ይሻላል” የሚል አቋም መያዙን አረጋግጧል።
አዲስ ሪፖርተር የሰዎችን ስም ላለማንሳት በመጠንቀቅ ሲዘግብ እንደነበር ይታወሳል። ይህም የሆነው በቀናነት አካሄዱ ሳይገባቸው የሚሳተፉ በመኖራቸው ነው። የዋሽንግቶን ተባባሪያችን እንደ መተዳደርሪያ ደንብ ዓይነት አዘጋጅተው ሲመጡ በተደረገ ውይይት መግቢያው ላይ “ይህ አምባገነን፣ ዘረኛ አገዛ” የሚል ሃረግ መቀመጡን በመጥቀስ ኢንጂነር ሙሉጌታ “ዘረኛ ስንል ማንን ነው? ኦሮሞን? ይህ ትክክል አይደለም” በማለት መናገራቸውን በአንድ ሪፖርት ላይ ማጉላቱን ያስታውሳል። በሌላ ሪፖርት ላይ “ከኤርትራና ሱዳን ጋር አብሮ መስራት ከብሄራዊ ጥቅም አንጻር እንዴት ይታያል” በሚል ጠንካራ ክርክር ያደረጉና “ስለ ኤርትራ እዚህ አታንሱ፤ ስለ ኤርትራ እዚህ አይነሳም” የሚል ግብረ መለስ ያቀረቡ እንደ አቶ ነዓምንና አቶ ገዱ ያሉትን በስም ሕዝብ እንዲያውቅ ይፋ ማድርጉን አመልክቷል። ይህ የሆነው እንደ ባለሙያ ሕዝብ እንዲመዝን መረጃ የመስጠት ኃላፊነት ስላለበት እንደሆነ አመልክቷል።
አዲስ ሪፖርተር የፋኖ ዜናዎችን በሌሎች ሚዲያዎች በሚዘገበው መጠን ሽፋን የማይሰጠው መረጃውን ለማመጣጠን የሚታወቁ፣ አድራሻ ያላቸው፣ በሚፈለጉ ጊዜ ማብራሪያ የሚሰጡ የህዝብ ግንኙነቶች ስለሌላቸው፣ በአንድ ጉዳይ ላይ ከተለያዩ የሚዲያ አበጋዞች የተለያዩ መረጃው ስለሚሰጡ ዘገባው ሰባራ ስለሚሆን ነው። ያም ሆኖ ወደ ሕዝብ የቀረቡ ጉዳዮች ሲኖሩ በጥንቃቄ ሽፋን እንደሚሰጥ አንባቢያን ሊመለከቱ እንደሚችሉ በዚህ አጋጣሚ ዝግጅት ክፍሉ ጠይቋል።
በመንግስት በኩልም ሚናውንና የተፈጠረበትን ዓላማውን ሲወጣ የማይታየው የኮሙኒኬሽን ቢሮም ቢሆን በተንጣለለ ቢሮ ውስጥ፣ በከፍተኛ ማዕረግና እንክብካቤ ከመቀመጡ በቀር መረጃን ለመስጠት ጫካ ካሉት የተሻለ ተነሳሽነት፣ ሲስተምም ሆን ግዴታ የሌለው ያለበት አይመስልም። ይባስ ብለው “እንዴት እንደምትሩ ተገምግማቹህ ነው መረጃ የምታገኙት” የሚል ማሳሰቢያ የሰጡበትም ቀን አለ።
እንደ ወታደር የሚያገለግል ትንታግ ቃል አቀባይ የሌለው ተቋም በመሆኑ የዜና ማመጣጠን ላይ እንቅፋት መሆኑን አዲስ ሪፖርተር በተለያዩ ጊዜያት አረጋግጣለች። ከላይ የህግ ባለሙያችን እንዳለው ልክ እንደ አሜሪካን ስቴት ሴክሬቴሪ በኢትዮጵያም የመረጃ ማጋራት ስራ ዕለት ተዕለት የሚተገበር የኃላፊነቱ ምህላ ነው። ይህን ምህላ መተግበር የማይችል የፕሬሰ ሴክሬታሪ በአሜሪካ “ተባረሃል” ሳይባል ራሱን ያባረራል። አለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያ ሁለቱም ርምጃዎች አይታዩም። ይዞ መውደቅ እንጂ “ይህን አልችም። ይህ ሙያዬ አይደለም። ለዚህ ኃላፊነት ልምድ የለኝም” አይባልም። መንግስትም ታላላቅ ሪፎርም አድርጎ በርካታ ስራዎችን ሲሰራ የቃል አቀባዮችን ጉዳይ መላ ሊል አለመቻሉ በስፋት የሚያነጋግር ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ሪፖርተር ከብዙ ትዝብት በኋላ ያለ አንዳች መሸማቀቅ ያስገነዝባል።
እንኳን ለዜናና ለሪፖርት፣ ለመንደር ወሬነት የሚበቃ ስራ በማይሰራባት ኤርትራ፣ ተዓምር እንደተሰራ በማስመሰል ዜና የሚረጩትን የፕሬዚዳንት ኢሳያስን አፍ ስንመለከት፣ ሞልቶ የሚፈስ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዜና የሚመረትባት ኢትዮጵያ “አፍ” ስለሌላት ደፋሮች ከኤርትራ ሊያወዳድሯት ሲዳዳቸው፣ አንዳንዴም ሲያወዳሩና “ኤርትራን ሞዴልችን” ሲያደርጉ ማየት ለአዲስ ሪፖርተርም ሆነ ለሚገባቸው ዜጎች አዲስ አይደለም። የአዲስ ሪፖርተር የዲሲ ተባባሪ ባለው የተጨበጠ መረጃ “ለምን ስብሰባችን ይፋ ሆነ” በሚል የሚያቅራሩት፣ ለኤፍቢአይ ክስ ይመስረት የሚሉት “ኤርትራና ኢሳያስ ሞዴላችን ናቸው” በሚል የአምልኮ መጋኛ የተመቱ የሚበዙበት ጥርቅም ነው። የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር ተማሪዎች ናቸው። የዛ ዘመን ምርቶች ናቸው። ዛሬም እንደዛ ሊረሳ እንደማይችለው ዘመን “እናቸንፋለኖች” ናቸው።
የማያሞግስን፣ የማያደንቅንና የሚተችን ሚዲያ መርጦ መፈረጅ፣ ሰዎቹን ለይቶ መስደብ፣ ማስፈራራት፣ መፈርጅ፣ ማሸማቀቅ ወዘተ “የተሻለ ስርዓት እናዋልዳለን” የሚሉት ቡድኖች ወግ ነው። መለያቸው ነው። አዲስ ሪፖርተርና ሰራተኞቹን ላይ የሆነውም ይህ ነው።
የሚያደንቃቸውን፣ የሚያሚያሞግሳቸውን፣ ማዕረግ በመስጠት ውዳሴ የሚያጎርፉላቸውን፣ ጥፋትን እንደ ከፍታ አግንነው ለሚያቀርቡ አድናቆትና ድጋፍ መስጠትም የነዚሁ ቡድኖች ሌላው መለያ ነው። አፈሩን ቀላል ያድርግላቸውና ፕሮፌሰር መስፍን ገና ድሮ ገብቷቸው “ከሽፈናል” ብለው የደመደሙበት ያለፉው የሰላሳ ዓመታት አስተምሮት ውጤት በመሆናቸው አዲስ ሪፖርተር በተሰነዘረበትና ሊሰነዘርበት በታሰበው ጥቃት ከማዘን ይልቅ የውድቀቱን ግዙፍነት የሚያይበት በመሆኑ እንደ ዜጋ “ሃሳብ እንዲከበር” አበክሮ ከመስራት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ያምናል፤ በዚህ አጋጣሚ የቡድኑ አለቃ አቶ ነዓምንም ሆኑ ሌሎች ልክ እንደ አቶ ጂሬኛ ተባባሪ ከሆኑ ለማስተናገድ አዲስ ሪፖርተር ዝግጁ ነው። አቶ ጂሬኛ ላደረጉት ቀና ትብብር አዲስ ሪፖርተር እያመሰገነ፣ ሌሎችም “መረጃችን ወጣ፣ ክስ ኤፍቢአይ ጋር እንሩጥ” ከሚል ተረት ተረት በመውጣት መረጃን በድፍረት በመስጠት ወደፊት መንግስት ሲሆኑ የሚዘረጉትን የሚዲያና የሃሳብ ነጻነት ጅምር ለማሳየት ቢጥሩ አዲስ ሪፖርተር መረጃን ከማብራሪያ ጋር በማጣመር ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ከወዲሁ ማሳሰብ ይወዳል። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር ተማሪና ደቀመዝሙርነትን ክብር አድርጎ ርቆ መራመድም እንደማይበጅ አዲስ ሪፖርተር ደግሞ ያሳስባል።
አሁን አሁን ታዋቂ ዩቲዩበሮችና ብሎገሮች ሳይቀሩ በነጩ ቤተመንግስት ቋሚ ቦታ ተስጥቷቸው በየቀኑ መረጃ እንደሚሰጣቸው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ መንግስትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲናገሩ፣ በግል ማህበራዊ አውዳቸው መረጃ ሲያጋሩ፣ ምስልና መረጃ ሲሰጡ፣ አንዳንድ ባለ ስልጣናት በግል ደረጃ ክንውኖችን ሲያጋሩ ከሚሰማው በስተቀር የመንግስት ኮሙኒኬሽንም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕለት ዕለት ሚዲያዎችን ሳይለይ ጠርቶ መረጃ እንዳይሰጥ ማዕቀብ የተጣለበት ነው የሚመስለው። ይህ አካሄድ የመንግስት አፍ ለሆነ ተቋም አይመጥነውም። ሰለዚህ መረጃ ይስጥ፣ ይጠየቅ፣ ይመልስ “ሕዝብ የማወቅ መብት አለው” ሲባል ያለማቋረጥ መረጃ በመስጠት የሚተገበር መሆኑን መገንዘብ ግድ ይላልና መንግስት በአፉ ይናገርበት፣ ዕለት ዕለት መረጃ ይስጥበት ሲል አዲስ ሪፖርተር ይማጸናል። አለያ እንደ አመጽ አመቻቾቹ ቡድን መሪዎች “የት ክስ እንመስርት” የሚለውን የሚያጠና ኮሚቴ ወይም ኮማንዶ ወደ ማቋቋም መኬዱ አይቀርም። ምክንያቱም አዲስ ሪፖርተርም ከመጠየቅ ሌሎችም ዝም ከማለት የሚቦዝኑ አይመስልምና!!
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






