አዲስ ሪፖርተር ዜና – በተሳሳተ መረጃ ተደልለው ለሽብር ስልጠና ወደ ኤርትራ ሊጓጓዙ የነበሩ በርካታ የሶማሌ ክልል ተወላጆች መያዛቸው ተሰማ። ምልመላው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎች ክትትል ሲያደርጉበት የነበረው ይህ እንቅስቃሴ፣ ከግብፅ በተሰጠ የበጀት ድጎማ ይከናወን እንደነበር ተመላሾቹ (ምልምሎቹ) አስታውቀዋል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኤርትራ ኤምባሲ አማካይነት መጋበዛቸውን አስታውቀው በተገኙበት የፖርት ሱዳኑ “ጽምዶ” ስብሰባ ላይ፣ ከነበሩት የመገንጠል ዓላማ ከሚያራምዱ ድርጅቶች መካከል ያፈነገጠው የኦብነግ (ONLF) መሪ አብዲራህማን መሀዲ ይገኙበታል።
አብዲራህማን መሀዲ በፖርት ሱዳን “ኢትዮጵያን ተባብሮ ለመውጋት” ተደረገ በተባለው ስብሰባ ላይ ከተሳተፉ በኋላ፣ ወደ ኤርትራ በመሄድ ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ክልሉን በሽብር ላይ ለመጣል ስልጠና ስለሚሰጥበት አግባብ ተወያይተው ከስምምነት መድረሳቸው በአንዳንድ ሚዲያዎች ይፋ ሆኖ ነበር።
በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል አልሸባብ እየሆነ እያስቸገረ ያለው ታጣቂ ኃይል በኤርትራ ሰልጥኖ የወጣ እንደሆነ የሚናገሩት የዜናው ምንጮች፣ የኤርትራ መንግሥት ለኦብነግ ምልምሎች ወደ ኤርትራ የሚጓዙበትን አቅጣጫ ጭምር መክሮ እንደነበር ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ጀምሮ በኤርትራ ውስጥ መጠለያና ስልጠና በማግኘት፣ እንዲሁም ከሌሎች አገራት ፋይናንስ በማሰባሰብ ኢትዮጵያን እንዲወጉ ድጋፍ ሲደረገላቸው ከነበሩት እንደ ኦነግ፣ የአርበኞች ግንባር፣ ደሚት ወዘተ መካከል ኦብነግም አንዱ ነበር።
ለውጡን ተከትሎ ከአስመራ ወደ ኢትዮጵያ በሰላም ስምምነት ከገቡት “ነጻ አውጪ” ነን ባይ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ኦብነግ፣ ብዙም ሳይቆይ ሊቀመንበሩን አሰናብቶ ነበር።
በሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም. “የቀድሞው ሊቀመንበር አብዲራህማን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸውና የተገኘውን የሰላም አየር ወደ ጎን በመተው፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ባልተገኘበትና ውሳኔ ባልሰጠበት፣ በራሳቸው ተነሳሽነት የፓርቲው አቋም ያልሆኑ ግጭት ቀስቃሽ መግለጫዎችን በማውጣታቸው እና የተለያዩ አስተዳደራዊ ክፍተቶችን በመፍጠራቸው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተወስኗል” በሚል ምክትላቸው አቶ ሙሁመድ አሳድ ሼክ በክሪ ተክተዋቸው ነበር።
ይህ ከሆነ በኋላ ዳግም ወደ ትጥቅ ትግል ለመመለስና ኦጋዴንን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል እንቅስቃሴ የጀመሩት አብዲራህማን መሀዲ፣ በቅርቡ “የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው” በሚለው መርህ መሠረት በሐሳብ፣ በርዕዮተ ዓለምና በራሷ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ፍጹም የማይገናኝ አቋም ካላቸው ጠብመንጃ ካነሱ ድርጅቶች ጋር ግብፅ በሻዕቢያ በኩል ባዘጋጀችው የጥምረት ዕቅድ መሠረት ሲሰባሰቡ እርሳቸውም ተጋብዘዋል።
በሶማሊኛ ቋንቋ የሚሰሩ ሚዲያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት፣ አብዲራህማን መሀዲ ስለ ትጥቅ ትግል ያወራሉ እንጂ መሬት ላይ ምንም ዓይነት ኃይል የላቸውም። በአሁኑ ሰዓት በክልሉ በከፍተኛ ደረጃ አገራዊ ታላላቅ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ መሆኑን በተደጋጋሚ እየተገለጸ ይገኛል። ቢሊዮን ዶላር በጀት እየፈሰሰበት ለቀጠናውና ለአፍሪካ የሚሆኑ ፋብሪካዎችና የነዳጅ ማጣሪያዎች እየተገነቡበት ያለውን የሶማሌ ክልል፣ ጠብመንጃ አንስቶ የተጀመረውን ልማት የሚያወድምበት ምድራዊ ምክንያት እንደሌለው የሚናገሩት እነዚህኑ ሚዲያዎች፣ የአብዲራህማን መሀዲን አቋም አጥብቀው እየተቹት ነው። ከዚያም ባለፈ “ማንንም አትወክልም” በሚል መከራከሪያ ድርጊታቸውን እያጋለጡት ይገኛል።
አብዲራህማን መሀዲ በፖርት ሱዳን የጽምዶ ስብሰባ ላይ ከተገኙ በኋላ ወደ ግብፅና ኤርትራ ደርሰው ተመልሰዋል። በመቀጠልም ለምልመላ በተሰጣቸው ሀብት ተሳስተው ወደ ኤርትራ ለማቅናት ፑንትላንድ የገቡ የሶማሌ ክልል ተወላጆች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል።
በሶማሊላንድ አድርገው በጀልባ ወደ ኤርትራ ለማቅናት የተሰባሰቡት ምልምሎች፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ወዳጅ ከሆነው የፑንትላንድ አስተዳደር ጋር በተደረገ ትብብር የተያዙ ሲሆን፣ ወጣቶቹ ተደልለውና የሐሰት መረጃ ተሰጥቷቸው ወደ ፑንትላንድ መግባታቸውን አስታውቀዋል። የፑንትላንድ አስተዳደርም ወጣቶቹን ለኢትዮጵያ መንግሥት አሳልፎ ሰጥቷቸዋል።
ፎቶ ፑንትላንድ የጸጥታ ኃይል
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






