አዲስ ሪፓርተር ዜና ፡- በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፣”በሃይማኖት ሽፋን በኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር እና የዓመፅና የተጫረሱ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው በሚል፣ “ሞዐ ተዋሕዶ” የተሰኘ ሕቡዕ ድርጅት መሪ በሆኑት መምህር ፋንታሁን ዋቄና ተባባሪዎቻቸው ላይ ምርመራ እንዲደረግ ለሚመለከታቸው አካላት ጥቆማ ማቅረባቸው ተሰማ። አመልካቾቹ ግለሰቡን ጨምሮ በስም ያልዘርዘሯቸውን ተባባሪዎቻቸውን በመጠቀስ ክስ ያቀረቡት በኢትዮጵያ እምነትን ተነተርሶ የተቀነባበረ የሽብር ቅስቀሳ እየተፈጸመ ነው ያሉትን በመዘርዘር ነው።
ክስ አቅራቢዎቹ ከሆነ በተለይ መምህር ፋንታሁን ዋቄ በቲክቶክ የማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የሃይማኖት እልቂት የሚያነሳሱና የርስ በርስ ትርምስ እንዲነሳና የሽብር ወንጀል እንዲፈፀም በግልፅ አስበውና አቅደው አደገኛ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ እንደ ነበር በዝርዝር አስረድተዋል። የቅስቀሳውንም የቪዲዮ ማስረጃዎች ከሌሎች አባሪ ናቸው ካሏቸው በርካታ ማስረጃዎች ጋር አያያዘዋል። የሚመሩት የሃይማኖት ክንፍ የፋኖ አደረጃጀት መስራች መሆኑንም በይፋ በቃለ ምልልስ መዐዛ መሃመድ በምትመራው የትግል ሚዲያ ገልጸዋል።
እንደ አመልካቾቹ ገለፃ፣ መምህር ፋንታሁን በተለይም በአዲስአበባ፣ በአዳማ እና በአርሲ አካባቢዎች የሚኖሩ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን ኢላማ በማድረግ “ተነሱ ለዕምነታችሁ ሙቱ” የሚሉ እና “እጃችሁ ላይ መድኃኒት አለ” የሚል ምስጢራዊ ኮድ በመጠቀም የዓመፅ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ ውስጥ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ላለው ብሔር እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ቀጥተኛ ቅስቀሳ እንደሆነ በአስተያየት ሰጪዎች እየተገለፀ ይገኛል። ቅስቀሳው ይዘቱ እጅግ አደገኛ እንደሆነና ወደፊት ሊቆም የማይችል ኃይማኖትን የለየ እልቂት እንዲነሳ የሚገፋፋው ቅስቀሳ በተለያዩ ሚዲያዎችና የቡድኑ ተባባሪዎች በቅንበር መሰራጨቱ ያሳደረባቸውን ስጋት በመግለጽ ለአዲስ ሪፖርተር የዋሽንፍቶን ተባባሪ እንዳስረዱት፣ ጥቆማውና ክሱ የሚቀጥል ነው።
የጥቆማ ማመልከቻ ክሱን ያስገቡት ወገኖች፣ መምህርፋንታሁን በስደት በጊዜያዊ መኖሪያ ቪዛ በአሜሪካ ግዛት ውስጥ ሆነው የውጭ አገርን ዜጎች ደህንነት አደጋላይ የሚጥል የሽብር ወንጀል እንዲፈፀም ቅስቀሳ ማድረጋቸው አሜሪካበ አለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ያወጣቻቸውን ህጎች እንደሚጥስ አመልክተዋል። እስካሁን ድረስ አስራ ስድስት የሚሆኑ ወገኖች ለአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር (DOJ)፣ ለፌዴራልየምርመራ ቢሮ (FBI) እና ለሀገር ውስጥ ደኅንነትና ኢሚግሬሽንአስከባሪ አካል (DHS/ICE) የክስ ማመልከቻቸውን በይፋ ያስገቡ ሲሆን፣ ሌሎችም ዜጎች ይህን የሽብር ድርጊት ለመከላከል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
አመልካቾቹ ግለሰቡ ለሚመሩት “ሞዐ ተዋሕዶ” ድርጅት በፋኖ የትጥቅ ዘመቻ ውስጥ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ፣ ሃይማኖትን እንደ የጦርነት ሽፋን በመጠቀም የሚደረገው ቅስቀሳ የሽብር ድጋፍ ወንጀል የሚያስጠይቅ እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህ የሕቡዕ አደረጃጀት በኢትዮጵያ ለዘመናት በአንድነት የኖረውን ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ በማድረግ ለቀጣይ የጅምላ ጭፍጨፋ እና የሃገር መፍረስ አደጋ እየዳረገ መሆኑንም በማመልከቻው ላይ በግልጽ አስፍረዋል።
የአዲስ ሪፓርተር ተባባሪ በዋሽንግተን ዲሲ የሕግ ቢሮ ከፍቶ በጥብቅና ሙያ የሚያገለግሉ የሕግ ባለሙያ በጉዳዩ ዙረያ አስተያየት እንዲሰጡ በጠየቀው መሰረት፣ በአሜሪካ ግዛት ውስጥ ሆኖ በሌላ ወዳጅ ሀገር ላይ ዓመፅን፣ ግድያን እና የመንግሥት ግልበጣን ማቀድ ከባድ የፌዴራል ወንጀል መሆኑን አመልክተዋል። በተለይም የአሜሪካ የፌዴራል ሕግ (18 U.S.C. § 956)፣ ከሀገር ውጭ የሚገኝ ሰውን ለመግደል ወይም ንብረት ለማውደም ሴራ መወጠን የሚከለክል በመሆኑ፣ መምህር ፋንታሁን ባስተላለፉት የዓመፅ ትዕዛዝ ይህንን ህግ መተላለፋቸው እንደማይካድ አመልክተዋል። እንዲሁም መምህር ፋንታሁን ከዚህ ቀደም በአሜሪካ መንግስት በምድብ ሶስት አሸባሪ ቡድን ስር በሽብርተኛነት የተፈረጀውን የፋኖ ታጣቂ ቡድን በማደራጀትና በመደገፍ ሞአ ተዋህዶ ትልቅድርሻ እንዳለው በይፋ በመግለፁ በቀጥታ ቪዛቸውን ተነጥቀው ከአሜሪካ ሊባረሩ እንደሚችሉም ገልፀዋል።
ይህ የጥቆማ ሂደት ግለሰቡ በአሜሪካ ህግ መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ተጨማሪ የሽብር ጥቃቶችን እና የጅምላ እልቂቶችን ለመግታት ያለመ መሆኑን ጥቆማውን የሰጡት ወገኖች ገልጸዋል። የአሜሪካ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ የሚከናወኑ የሽብር ቅስቀሳዎችን በጥብቅ እንደሚከላከል በማስታወስ፣ ጉዳዩ በህግ አካላት ተጣርቶ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ በጥብቅ እየጠየቁና እይወተወቱ መሆኑንንም አመልክተዋል።
በአርሲ በተደጋጋሚ የደረሰውን የተቀነባበር ግድያ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች እንደሚፈጽሙ፣ ይህንን ለመከላከል ሙስሊሞችን ጨምሮ ሚሊሻዎችና የፖሊስ ኃይሎች መገደላቸውን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችና ድርጊቱ በተፈጸመበት ስፋራ የነበሩና ከጥቃቱ ያመለጡ ለአዲስ ሪፖርተር፣ ለቢቢሲ፣ ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ እንዲሁም ለቤተክርስቲያን መዋቅር በግልጽ መናገራቸው ይታወሳል። በአርሲ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አካባቢዎች ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭትና ግድያ ሲፈጸም ተጎጂዎች በግልጽ ያጠቃቸውን፣ ንብረታቸውን ያወደመውንና የዘረፋቸውን ወገን እያስታወቁ አጥፊውን በመለየት በስም ጠርቶ ማውገዝ አልተለመደም። የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ራሳቸውን አክቲቪስት የሚሉ፣ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ሚዲያዎችና በሚዲያ ዙሪያ የሚሰሩ ትኩረታቸው የጉዳቱ መጠን ላይ እንጂ ጉዳቱን በተደጋጋሚ በሚያደርሱት ቡድኖች ላይ አለመሆኑ የንጹሃንን ጥቃት እንዳባባሰው ገለልተኛ ወገኖች በተደጋጋሚ የሚተቹበት ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል።
ዌብሳይት፡ https://addisreporter.com/
ኢሜል፡ info@addisreporter.com
ቴሌግራም፡ https://t.me/addisreporter2
X፡ https://x.com/amejuju?s=21
https://web.facebook.com/addm






